ገበታ ሥርዓት አለው፡፡ በሀገራችን ገበታ ሳይነሳ መነሳት ክልክል ነው፡፡ አንድ ሰው አስቀድሞ ቢጠግብ እንኳ ሌላው እስከሚጨርስ ጠብቆ ገበታ ከተነሳ በኋላ ነው መነሳት ያለበት፡፡
ገበታ በጣም ይከበራልናም እንጀራ ከአጠገብ ቢያልቅ ገበታው/ትሪው/ እንዲዞር አይደረግም፡፡እናቶች እንጀራ በብዛት ካለበት ቦታ እየቆረሱ ወደየበላተኛው ፊት ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህ በኩል የፊተኞቹ እናቶች ይታወሳሉ፡፡ ሰው በልቶ የሚጠግብ አይመስላቸውም፡፡
ከዚህ ውጪ ገበታ ወይም ትሪ ወደ እሱ አቅጣጫ ሲያሽከርክር የተገኘ ይቀጣል፤ በትራፊኮች በገበታ ስነ ስርአት አዋቂዎች፡፡ ይህን ሥርዓት ያጎደለው ትልቅ ሰው ከሆነ በትዝብት ይታለፋል፡፡ ልጅ ከሆነ ግን እኔን አያርገኝ፡፡ እጁን ሊመታ ይችላል፤ ተግሳጹ የዱላ ያህል ይሆናል፡፡
የእዚህ ዘመን ወጣቶች ለብቻቸው ሲገናኙ ታዲያ ከፊታቸው ምግቡ ሲያልቅ ምግቡን ቆርሰው ከማዞር ይልቅ አለም እንደምትዞር በመግለጽ ትሪውን/ገበታውን/ ያዞሩታል፡፡
ይህ የገበታ ሥነ ሥርዓት አሁን አሁን ብዙም አይታይም፡፡ ሁሉም የድርሻውን በየእጁ ይዞ ነው የሚመገበው፡፡ በእርግጥ በገጠር እና በአንዳንድ የከተማ አካባቢዎች አሁንም አለ፡፡
በገበታ ጉዳይ ይህን ያህል ያልኩት ጨዋታን ጨዋታ ቢያመጣብኝ ነው፡፡ በቅርቡ በህዝብ ብዛቷ የሚስተካከል ባልተገኘላት፣ በታሪክም በጥበብም፣ በቴክኖሎጂም፣ በሀብትም ባለጸጋ በሆነችው ሀገር የአንድ ሰባት ቆይታ ባደረግሁበት ወቅት ያስተዋልኩት ገበታ ትዝ ብሎኝ ነው፡፡
የቻይና ገበታ ባለሁለት መም ሲሆን የመሀለኛው የሚሽከረከር ነው፡፡ በሆቴል ቤቶች እንደማንኛውም ሰው እያነሱ የሚወስዱት ምግብ እያለም በልዩ ትእዛዝ ይመሰለኛል በአንድ ክፍል ውስጥ ይህ ገበታ ይዘጋጃል፡፡ ወደ ክፍሉ ሲገቡ አንድም ምግብ አያዩም ፤ ቾፕስቲክ /እንደ ማንኪያና ሹካ የሚያገለግሉት የቻይና መመገቢያ እንጨቶች/፣ የሻይ ስኒ፣ ሹካ፣ማንኪያ፣ ሳህን፣ የሾርባ ሳህን ቀርበው ያገኛሉ፡፡
በክብ ጠረጴዛው ዙሪያ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ በቅድሚያ ግሪን ቲ /አረንጓዴ ሻይ/ ይቀርባል፡፡ ሻዩ ስኳር አያውቅም፡፡ እንዲያም ሆኖ ታዲያ ቻይናዎቹ ለጉድ ይጠጡታል፡፡ እኔም ያልጎመዘዘኝን ያህል እንደ አገሬውም ባይሆን እያደር ወደ መጠጣቱ ገብቻለሁ፡፡ ስኳር መጠየቅ ይቻላል፡፡ ቆይቶም ቢሆን ይመጣል፤ ማንኪያ ደግሞ ይቸግራል፤ ስኳሩ ከተገኘ እሱ እዳው ገብስ ነው፡፡እንደሚማሰል ይማሰላል፡፡
በተዘዋወርንባቸው ወደ አራት እና አምስት ከተሞች ያስተዋልነው ይህንኑ ነው፤ ቡና ማግኘት ከባድ ቢሆንም ያለስኳር አንድ ጣሳ/ካፕ/ ቡና ይቀርብሎታል፡፡ በስኒ የለመደ በጣሳ ሲሆን ምን ሊሆን እንደሚችል ገምቱ፡፡ ለዚያውም ቡና ቡና አይልም፡፡ ቡና አጥተው ነው ወይስ ለምን ይሆን? አጥተው ከሆነ በቻይና ያለው ሚሲዮናችን ይህን ያህል ዘመን የማንን ጎፈሬ ሲያበጥር ነው የኖረው ?
ለቡናውም ስኳር ጠይቀው ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ሁሌም ተጠይቆ የሚሉ ከሆነ ደግሞ ደረቁን ይጠጡታል፡፡ ያለስኳር፡፡ ከቡና ጋር ጥብቅ ዝምድና ላለው ቡናው መገኘቱም አንድ ነገር ነውና የሚችሉትን ያህል ይጠጡታል፡፡
እንዳልኩት ምንም የምግብ አይነት ባልቀረበበት ሁኔታ አረንጓዴ ሻይ ይቀርብና ጨዋታ ይጀመራል፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሾርባ ይቀርባል፡፡ ከዚያም ምግብ መቅረብ ይጀምራል፡፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ ጥያቄ መቅረብ የሚጀምረው፡፡ በእያንዳንዱ ገበታ ጥያቄ አለ፡፡
ቡናና ሻይ ያለ ስኳር መጠጣት ለሚፈልግ መንገዱ ጥርጊያ ሆነለት ማለት ነው፡፡ ሁለቱንም ጨርሶ ላለመጣጠትም እንዲሁ፡፡ በተለይ የቡና ሱሰኛ የሆነ ቡናን ለመሰናበት ጥርጊያ ይሆንለታል፡፡ ይህ አባባሌ ግን አንድ ሰው አስታወሰኝ፡፡ በሆነ አጋጣሚ ከህክምና ጋር በተያያዘ ነው መሰለኝ ቡና ይተዋል፤ ወራትም ይዘልቃል፡፡ ይሁንና ቄስ አልገዘተኝ እያለ አንዳንድ ሲል ተመልሶ ወደ ቀድሞ ሱሱ ይገባል፡፡ለሳምንት ከቡናና እና ከሻይ የተለያየ ለማናቸውም ለመተው ቢሞክር አጋጣሚው ጥሩ ነው፤ ትንሽ ጊዜ ማረፉንስ ማን አየው፡፡
በቻይና የምግብ ነገር ያነጋግራል፡፡ የቻይና የምግብ አይነቶች ጉዳይ አነጋጋሪ በመሆኑ አንዳንዶቻችን ቀደም ብለው ሀገሪቱን ከጎበኙ ባልደረቦቻችንና ጓደኞቻችን ባገኘነው መረጃ መሰረት በሶ፣ ጭኮ፣ ቆሎ እና ኩኪስ ይዘናል፡፡ በተለይ አውሮፕላን ለመቀየር በሚደረግ ጥበቃ ወቅት፣ ምግብ ማግኘት እንደሚቸግር መረጃው ስለነበረኝ እኔ እነዚሀን ምግቦች ይዣለሁ፡፡
በዚህ ላይ ደግሞ የባህል ልዩነቱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የማይመገቧቸው የቻይናውያን ምግቦች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉም መረጃው አለንና ስለእያንዳንዱ የምግብ አይነት ሳንጠይቅ ወደ መመገብ አንገባም፡፡
የቻይና ገበታ ተሽከርካሪ ክፍል አንዳንድ እያለ በምግብ መሞላት ይጀምራል፡፡ የፈልጉትን ምግብ ለማንሳት ተዘዋዋሪውን የገበታ ክፍል ወደ አቅጣጫዎ እያሽከረከሩ ያመጡታል፡፡ ያነሱትን ምግብ ወይም መጠጥ ግን ባለተሽከርካሪው ጠረጴዛ ላይ ማድረግ የለቦትም፡፡ ካደረጉ ሲዞር ውሎ ነው የሚመጣው፡፡
ምግቡን የያዘው ተሽከርካሪው ጠረጴዛ አጠገቦ ሲመጣ ምግብ መምረጥ ይጀምራሉ፡፡ ይህ ምንድን ነው ሲሉ አስጎብኚዎችን ይጠይቃሉ፤ ችክን/ዶሮ/ ነው ይባላሉ፤ ከፈለጉ ያነሳሉ፤ አሁንም ሌላ አይነት ይመጣል፤ ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ ቢፍ/የበሬ ስጋ /ነው ይባላሉ፤ ከተስማማዎት ያነሳሉ፡፡እንዲህ እንዲህ እያሉ እያንዳንዱን የምግብ አይነት እየጠየቁ መርጠው ይመገባሉ፡፡ ጥያቄው የማያውቁትን የሚሰጉበትን የምግብ አይነት ላለመመገብ ነው፡፡
አለዚያም ጥያቄ የማያነሱባቸውን የበቆሎ ቅቅል፣ ሩዝ፣ ካገኙ እነሱን ያነሳሉ፡፡ የበቆሎ ነገር ግን ብዙ አስገርሞኛል፡፡ በቆሎ እሸት ከእነ ቆሮቆንዳው በወተት ተቀቅሎ ፣ ወይም በሀገራችን እንደሚደረገው ብቻውን ተቀቅሎ ከምግብ አይነቶቹ መካከል ይሰለፋል፤ በቆሎ እሸትን ሌላም ሆኖ አየሁት፡፡ ይሄ ደግሞ የተፈለፈለ በቆሎ ከሌላ የምግብ አይነት ጋር ተደርጎ እንደ እንጀራ የተጋገረ ነው፡፡ በላሁት፤ ይጥማል፡፡በቆሎን የፆም ቀኑን፣ አንዳንድ ምግቦችን ለመሸሽ በሚገባ ተጠቀምኩበት፡፡
ሁኔታው በቆሎ በሀገራችን ተጎድቷል፤ እኛም ተጎድተናል ለካ ብዬ እንዳስብ አረገኝ፡፡ በቆሎ በሀገራችን በተለይ በእሸት ወቅት ቅቅሉ፣ ጥብሱ፣ ቆሎው በጣም ይበላል፡፡ በዚህ አይነት መልኩ ግን በትላልቅ ሆቴሎች ስለመገኘቱ እጠራጠራለሁ፡፡ በቻይና ግን በትላልቅ ሆቴሎች እየሆነ ያለውን ነው የምነግራችሁ፡፡
በሀገራችን በቆሎ በተለያየ አይነት መንገድ ተሰርቶ እንደሚበላ የሚታወቀው ምርቱ የበዛ ዘመን በሚቀርቡ የተለያዩ ዘገባዎች ነው፡፡ የስነ ምግብ ባለሙያዎች በቆሎ ምን ምን አይነት ምግብ ሊሰራበት እንደሚችል ያስገነዝቡ የነበሩባቸው በቆሎ በስፋት ተመርቶ አርሶ አደሮች ዋጋ ወድቆባቸው የተቸገሩባቸው አመታትን አስታውሳለሁ፡፡ በቆሎን ምርቱ ብዙ ካልሆነ የሚያስታውሰው የለም፡፡እናም በቆሎ እንዲህ እንደ ቻይና ተወዳጅ እንዲሆን ቢደረግ በላተኛም አርሶ አደርም ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡ ለማናቸውም ከበቆሎ ጋር የከረምን ከርመናል፡፤ የክፉ ቀን ብለነዋል፡፡
ዳክዬ ዋና ምግብ ናት፡፡የዶሮ አበላለቷ ላይ ሰፊ ልዩነት ቢኖርም ሌላ ዋና ምግብ ናት፤ ችክን፣ አሳም በተለያየ አይነት ይቀርባል፡፡ በሀገራችን የምናውቀው አሳ እንዳለ ሆኖ እኛ ናይል ፣አርባምንጭ ወዘተ እንደምንጠራው አይነት አሳው የወንዝ፣የሀይቅ ወዘተ እየተባለ ይጠራል፡፡
የአሳ ጫጩት ሌላው የምግብ አይነት ነው፡፡ በሀገራችን የጥጃ ስጋ የሚባለው በእርግጥም ከጥጃ ስጋ ስለሚዘጋጅ ነው፡፡ የፈረንጅ ላሞች ወንድ ሲወልዱ ብዙም ሳይቆይ ለእርድ ይሸጣል ሲባል እሰማ ነበር፡፡እሱን አስቀምጦ ከመቀለብ እምቦሳ እያለ መሸጥ ይመረጣል፡፡ ፈላጊውም ብዙ ነው፡፡ እንዳው አንድ ቀን ሁለት እምቦሳ የፈረንጅ ጥጆች በታክሲ ኪስ ውስጥ ተጭነው ሲወሰዱ አይቼ ብጠይቅ ለእርድ እየተወሰዱ መሆናቸው ተነገረኝ፡፡ በሀገራችን ከብቶች እምቦሳ ምን ሲል ለእርድ ታስቦ!!
የአበሻ ወንድ ጥጃ የሴቷን ያህል ነው እንክብካቤ የሚደረግለት፡፡ለነገሩ ኮርማም የእርሻ በሬውም ፣ ሰንጋውም የሚወጣው ከዚሁ ከእምቦሳ ነው ለካ፡፡ በየልካንዳው የሚቀርበው ስጋም ጥጃውን ካላሳደጉት ፣ ካላደለቡት ፣ ሰንጋ ካላደረጉት አይሆንም፡፡
ወደ አፋር አካባቢም በከል የሚባል ነገር አለ አሉ፡፡ በወሬ በወሬ ነው የማውቀው፡፡በጣም እንደሚጣፍጥም ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ ከግልገል ፍየል የሚሰራ ምግብ መሰለኝ፡፡የአሳ ጫጩት ገበታው ላይ ስመለከትም እነዚህ የሀገራችን እውነታዎች ትዝ አሉኝ፡፡ የአሳ ጫጩቱም በጣም ይጣፍጣል፡፡
ለነገሩ ቻይናን ዞር ዞር ብሎ ለተመለከተ እዚህም እዚያም ከትንሽ እስከ ትልቅ የሚታየው የውሃ አካል ለአሳ እርባታ ምቹ መሆኑን በቀላሉ ይረዳሉ፡፡ የአሳ ጫጩቱም ከዚህ በቀላሉ ሊገኝ ይችላል፡፡አሳው እስኪያድግ ሳይጠበቅ እያረቡ ለምግብ ማዋል አንድ ብልሃት ነው፡፡ ዋናው ነገር ለአሳ ሀብት አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረጉ ላይ ነው፡፡
ምግብ ቀርቦ አያበቃም፡፡ ምን ያህል የምግብ አይነት እንደሚቀርብ ቢታወቅ ኖሮ ሁሉም ከቀረበ በኋላ ልክ እንደ ቡፌ መብላት ቢጀመር ለምርጫ ጥሩ በሆነ ነበር፡፡ያን አይነቱ እድል የለም፡፡አስቀድሞ ከቀረቡት ምግቦች ተመግበው ከጠገቡ በኋላ ሁሉ ምግብ ይቀርባል፡፡
ጨዋታው ይቀጥላል፡፡ ቀስ እያለ የሚበላም ይበላል፡፡አረንጓዴ ሻይ አሁንም አሁንም ልክ እንደ ጠላ፣ ጠጅ፣ ወዘተ ይቀዳል፡፡ ሻይ ለምን ይህን ያህል ስንል አስጎብኚያችንን ፍሌክስ ሊን የጠየቅነው ትዝ አለኝ፡፡ ይህ ከቤጂንግ ጉንዡ እንደ ገባን የተቀበለን አስጎብኚያችን ነው፡፡ ቀልጠፍ ያለ፣ እንግሊዝኛውም ጥሩ የሆነ አስጎብኚ ነው፡፤ታሪክም በሚገባ ያውቃል፡፡ በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ አለው፤በተለይ እንግሊዝኛ ማወቅ ቻይና ውስጥ ጥሩ እንጀራ እንደሚያበላ ነገሮናል፡፡
ወደ ጉዳዬ ልመለስ ፡፡አረንጓዴ ሻይ በብዛትና በፍቅር የሚጠጣው ስለሚያጫውት ነው አለን፡፡ በኛ ሀገር ቡና እንደሚያጫውተው ማለት ነው ፡፡ከዚያም ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ ማወራረጃም ነው ቢባል አይጋነንም፤ምግብ ሲበላ አሁንም አሁንም ከመቀዳቱ አንጻር ሲታይ ማወራረጃ ያስብለዋል፡፡ ሾርባ ምግብ ከመበላቱ በፊት ይቀርባል፤የበሬ ስጋ ሾርባው/ቢፍ/ ይጥማል፤ ሾርባው የሚደገምም ከሆነ ያኔውኑ ይደገማል በቃ፡፡ሻይ ግን ማቆሚያ የለውም፡፡
የክብ ጠረጴዛው ገበታ ረጅም ጊዜ ተቀምጠው የሚመገቡበት ነው፡፡ለክብር የሚዘጋጅም መሰለኝ፡፡ እራታችንን በሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ እየተጋበዝን የበላነው በዚህ ገበታ ነው፡፡ ጨዋታ አለው፡፤
ምንም እንኳ ከቻይናውያኑ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በአስተርጓሚ ቢሆንም እኛም እርስ በእርሳችን ስለምንጫወት ዘለግ ላለ ጊዜ ገበታ ላይ ቆይተን አይተነዋል፡፡ በእርግጥ አቀራረቡም ለእዚህ የሚጋብዝ ነው፡፡ በተለይ እራት ላይ ከሆነ ብዙ መጫወት ይቻላል፡፡ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንደሚባለው ስለውሏችን፣ ስለምንውልበት የምንነጋገርበትም ሆኖ አገልግሏል፡፡
እኛ ግን እንደተንከወከውን ነው አንድ ሰባቱን የጨረስነው፡፡የሚጎበኙትን ሁሉ ለማዳረስ በጉዞ ወቅት የተከሰቱ መጓተቶችን ለማካካስ በምሽት ጭምር ተጉዘናል፤ማለዳ መነሳት የግድም ነበር፡፡እራት በልተን አንድ ቀን ምን አልባት ሁለት ቀን ወጣ ብለን ዎክ አርገን ይሆናል፡፡በተረፈ ግን ማልዶ ለመነሳት ሲባል ቶሎ ወደ መኝታ መሄድ የግድ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ቻይናን በወፍ በረር ነው ያየናት፡፡በወፍ በረር እንዳየናት ሁሉ የጉዞ ማስታወሻውም የወፍ በረር ነው፡፡
በቻይና ቆይታዬ የማረሳቸው ‹‹ቼክ ኢን›› ‹‹ቼክ አውትን››አልረሳውም፡፡ ሆቴል አልጋ ሲያዝ ፣‹‹ቼክ አውት›› ሆቴል አልጋ ሲለቀቅ የሚካሄዱ ስነስርአቶች ናቸው፡፡ እኔም የጉዞ ማስታወሻዬን እዚህ ላይ አብቅቻለሁና‹‹ቼክ አውት›› ብያለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
ኃይሉ ሳህለድንግል