አዲስ አበባ፦ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የውጭ ምንዛሬ በአስቸኳይ ካልለቀቀለት ጋዜጦችን፣ፈተናዎችንና ሌሎች ህትመቶችን ከሁለት ወራት በኋላ ማተም ሊያቆም እንደሚችል ገለጸ።
የድርጅቱ የኮርፖሬት ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ነጋሽ ‹‹ለህትመት መሰረታዊ የሆኑት ወረቀት፣ ቀለም፣ ፕሌት፣ ኬሚካልና ሌሎች 90 በመቶ የሚሆኑት ግብዓቶች ከውጭ አገር ስለሚገቡ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል።
ከግብዓት በተጨማሪም መለዋ ወጫና አዳዲስ ማሽኖችን ለመግዣ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል። ለድርጅቱ ከአንድ ዓመት በላይ የውጭ ምንዛሬ እንዲፈቀድልን ጥያቄ ብናቀርብም እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ አልተፈቀደልንም። በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት ለብሄራዊ ባንክ ሊያጋጥመን የሚችለውን ችግር በስፋት አስረድተናል፤ ነገር ግን መፍትሄ አልተሰጠንም›› ብለዋል።
‹‹ጋዜጦችንና ሌሎች ህትመቶችን እያተምን ያለነው በህትመት ወረቀት አይደለም። አሁን ያለን ወረቀት ከሁለት እስከ ሶስት ወር ቢያደርሰን ነው›› ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ብሄራዊ ባንክና ንግድ ባንክ በአጭር ጊዜ ፈቅደው የህትመት ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ካልቻሉ የህዝብ ልሳን የሆኑ ጋዜጦችና ብሄራዊ ፈተናን ማተም እንደማይቻል፤ ይህም በመንግስትና በአገር ላይ ችግር እንደሚፈጥር አስጠንቅቀዋል።
‹‹የውጭ ምንዛሬ የሚፈቅዱት አካላት ችግራችንን እንዲገነዘቡ ስንል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዲሁም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲና ፈተናዎች ድርጅት እየገጠመን ያለውን ችግር አሳውቀናቸው የድጋፍ ደብዳቤ ለብሄራዊ ባንክ ጽፈዋል። በቅርብ ጊዜ ምንዛሬውን ልናገኝ እንደምንችል ተስፋ ቢሰጡንም ቶሎ ተፈቅዶ አቅራቢዎቻችን ግብዓቶቹን አምርተው በመርከብ ለማጓጓዝ ጊዜ ስለሚወስድ ህትመት ለማቆም ሊያስገድደን ይችላል›› ብለዋል።
የውጭ ምንዛሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተፈቀደ ግብዓቶቹን የሚያቀርቡ አሸናፊ ተጫራቾች ስለተለዩ ህትመቱ ሳይቋረጥ ሊቀጥል እንደሚችል የተናገሩት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ችግሩ ሳይብስ ለህትመት ግብዓት የተጠየቀው አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር በአራት ተከፋፍሎ በአስቸኳይ ሊለቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
‹‹በአገሪቱ ያለውን የህትመት ግብዓት ፍላጎት በውጭ ምንዛሬ እየጠየቁ መፍታት እሳትን የማጥፋት ያህል ነው›› ያሉት አቶ ጌታሁን፤ ‹‹ችግሩን በወጥነት ለመፍታት የህትመት ግብዓትን በአገሪቱ ማምረት ይገባል። በአገሪቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች አሉ።
እነዚህ ዜጎች የወረቀትና የህትመት ግብዓት ይፈልጋሉ። ከዕለት ወደ ዕለትም ፍላጎቱ እየጨመረ ነው። የብርሃንና ሰላም እድገት እንኳ በየዓመቱ ሃያ በመቶ ነው። ከዚህ ባለፈም በየዓመቱ በቢሊዮን በውጭ አገር ህትመት ይካሄዳል›› ብለዋል።
ድርጅቱ ባነሳው ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ለብሄራዊ ባንክ በስልክ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡት በደብዳቤ ሲቀርብላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በተመሣሣይም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥያቄውን ይመልሳል ላልነው አካል ደውለን ምላሽ እንዲሰጡ ለማድረግ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሪሳ እና ዓልዓለም ጋዜጦችን በብርሃንና ሰላም የሚያሳትመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድም ተክሉ‹‹የህትመት መገናኛ ብዙሃን ችግሩ ገፍቶ መቋረጥ ድረስ እየሄደ ነው።የህትመቱ መኖር ለትውልድ ቀረፃና ታሪክ ለማስተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ድርጅታችን 79 ዓመቱ ነው።
ለስነ ጽሁፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተና አንቱ የተባሉ ደራሲያንን ያፈራ ነው። ባለፈው ዓመት በወረቀት ዋጋ መጨመር በህትመት ላይ 30 በመቶ ዋጋ ተጨምሮብናል። ይህ ተቋም በህትመት ግብዓት ችግር አቋረጠ ሲባል የሚፈጥረው ፖለቲካዊ ጫና ቀላል አይሆንም። ይህን ከግምት በማስገባት የህትመት መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ትኩረት አልተሰጠውም። ግብዓቶች ከታክስ ነፃ መፈቀድ ነበረበት››ብለዋል።
ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የህትመት ጥራትን ለማሻሻል፣ ተደራሽ ለማድረግ የራሱ ማተሚያ ቤት ለመክፈት የአዋጅ ማሻሻያ ተደርጎ በዘንድሮው ዓመት ዝግጅት በማድረግ በ2013 ሥራ ለመጀመርና ሌሎች የህትመት መገናኛ ብዙሃንን አብሮ ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፤ ብርሃንና ሰላም ጨረታውን ተወዳድሮ ፈተናዎችን እንዲያትም ተቋማቸው ውል ባለመግባቱ ችግር እንደማይገጥማቸው ተናግረዋል።
ብርሃንና ሰላም ድርጅት የህትመት ሥራ ከጀመረ 98 ዓመቱ ሲሆን፤ ዓመታዊ ሽያጩ ከ550 እስከ 600 ሚሊዮን ብር ፤ ዓመታዊ ትርፉም እስከ 200 ሚሊዮን ብር ይደርሳል።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ