ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማስፈጸም 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ያስፈልጋል፤ የዚህ 75 በመቶ የሚገኘው ደግሞ ከግብር ነው።
በ 2007 ዓ.ም ከአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት 13 ነጥብ 4 በመቶው የግብር ድርሻ ነበር፡፡ በ 2009 ዓ.ም 186 ቢሊየን ብር ከታክስ ለማግኘት ታቅዶ ሊሰበሰብ የቻለው ግን 160 ቢሊየን ብሩ ብቻ ነው። በተመሳሳይ በ 2010 በጀት ዓመት 230 ቢሊየን ብር ይሰበሰባል ተብሎ ቢታቀድም፣ ማሳካት የተቻለው ግን 176 ቢሊየን ብሩን ብቻ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል ።
ይህ ሁኔታ ደግሞ አገሪቱ በ2012 ትደርስበታለች የተባለውን 17 ነጥብ 2 በመቶ አጠቃላይ የግብር ገቢ በእጅጉ እንዳይጎዳው ተሰግቷል።
ግብር ካለመክፈል ከድህነት አምባ፤
በፍቅር እንሻገር ኢትዮጵያን እንገንባ፤
እድገት መተሳሰብ ፍቅር የሞላባት፤
በአገር መውደድ ስሜት እኛው የመንገነባት፤
ኃላፊነት ወስደን ግብራችንን ከከፈልን ፤
ሰላም የሞላባት ኢትዮጵያ እናያለን…….፤ ይህ ግጥም የተነበበው የገቢዎች ሚኒስቴር ሀገሪቱ የገጠማትን አሳሳቢ የግብር አከፋፈል ችግር ይቀይርልኛል፤ ህብረተሰቡም ግብር በመክፈሉ የሚያገኘውን ጥቅም ያሳይልኛል በማለት «ግዴታዬን እወጣለሁ ፤መብቴንም እጠይቃለሁ» በሚል መሪ ሀሳብ ሰሞኑን ባስጀመረው የታክስ ንቅናቄ ማብሰሪያ ፕሮግራም ላይ ነው።
አዎ! ንቅናቄው ከ 1 ሺ በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት መበሰሩም ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል። በፕሮግራሙ ላይ ወጣቶች ፣ተማሪዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ ከመሆኑ በላይ የራሳቸውን ኃላፊነት በታማኝነት ተወጥተው ባላቸው ተሰሚነት ሌሎችም ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራርመዋል።
የህክምናና የስነልቦና ባለሙያው ዶክተር ምህረት ደበበ ፤‹‹ሰዎች ወደ ስራው አለም ሲሰማሩ ግብር ለመክፈል የሚያቅማሙት ከልጅነታቸው ጀምሮ በግብር አስፈላጊነት ላይ የቀረጻቸው ስላላገኙ ነው፤ ሌላው ደግሞ በግብር መልክ ለመንግሰት የሰጡት ገንዘብ ምን ላይ እንደሚውል ማየት ስለሚፈልጉ ነው፤ በታማኘነት ግዴታቸውን በሚወጡና በሚያጭበረብሩ ሰዎች መካከል ልዩነት ሊታይ ስላልቻለ ነው ይላሉ።
‹‹በመሆኑም ልጆችን ከህጻንነታቸው ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው፣ መምህሮቻቸው ስለ አገር ፍቅር እያስተማሩ አገራቸውን ስለሚወዱ ደግሞ ከሚያገኙት ገቢ ላይ በታማኝነት ግብር እንደሚከፍሉ እያሳዩ ማሳደግ ይገባል‹‹ ያሉት ዶክተር ምህረት፣ እነርሱም ይህንን ባህላቸው በማድረግ፣ አለመክፈል አሳፋሪ መሆኑን እየተረዱ እንደሚያድጉ ይገልጻሉ። ስለዚህ ልጆች ላይ በመስራት ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት መጀመር አለብን ሲሉ ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር ምህረት ገለጻ ፤መንግስትም በተለይም በታማኝነት ግብር የሚከፍሉ ወገኖችን በይፋ ማመስገን ከተቻለም መሸለም ይገባዋል። ይህንን ባልሆነበት ሁኔታ ደግሞ አጥፊዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት ማሳረፍም አለበት ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱም በሰጡት አስተያየት ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በግብር ጉዳይ ላይ በተካሄዱ በርካታ መድረኮች ላይ በመገኘት ሀሳብ መለዋወጥ መቻሉን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹አሁን ማስገንዘብ የሚያስፈልገው ግብር ከፋዩና መንግስት ሁለት አካል አለመሆናቸውን ነው፤ እንደ አጋር መተያየት መጀመር አለባቸው፤ ይህ ንቅናቄም ምናልባት ይህንን ይፈጥር ይሆናል።›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ የግብር አሰባሰብ ከዓለም አገራት ሁሉ ዝቅተኛው ነው፤ ምናልባት አንድ አገር ትከተለን ይሆናል፤ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የማሽቆልቆል አዝማሚያ እያሳየ ነው›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ ፣መጀመሪያ ይህ ሁኔታ መቀየር እንደሚኖርበት፣ ሲቀየር ደግሞ የሚጠይቃቸው ስራዎች እንደሚኖሩም ያመለክታሉ።
ሁኔታውን ለመቀየር ፖሊሲ እና የግብር አስተዳደር አመለካከትን መቀየር እንደሚያስፈልግ፣ ለእዚህም በጥሞናና በተረጋጋ መንፈስ በጥናት ላይ በመመስረት መስራት ጥሩው መንገድ መሆኑን ይገልጻሉ፤
አሁን ያለውን የዘርፉን ችግር ለመፍታት በግብር አሰባሰብ ላይ ያልተቋረጠ የግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርት መስጠት የስራው ሁሉ መጀመሪያ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመው፣ ይህን አካሄድ ግብር መክፈል ባህላቸው የሆኑት አሜሪካውያንንም ይከተሉታል ይላሉ፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝደንት ደራሲ ጌታቸው በለጠ ፤ ‹‹ግብር የአገር፣ የመንግስት ፣ የህዝብ እስትንፋስ ነው፤ ግብር ከሌለ የአገር ልዋላዊነትና ነጻነት ሊከበር አይችልም።›› ሲሉ ገልጸው፣ ‹‹ዜጎች በሰላም ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን መሰረታዊ ነገሮች ለማግኘት አስትንፋስ የሆነውን ይህን ገንዘብ መስረቅ፣ ማጭበርበርና መሰወር ነውር መሆኑን ሊረዱ ይገባል›› ይላሉ ።
የሀገራችን የግብር አሰባሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ለመምጣቱ ውጫዊና ወስጣዊ ምክንያቶች እንዳሉም ደራሲ ጌታቸው ጠቅሰው፣ ‹‹ውጫዊ ምክንያቱ ድህነታችን ነው፡፡ ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ነጋዴው ወይም ግብር ከፋዩ የሚያገኘው ሀብት ለኑሮውም ላይበቃው እንደሚችል ተናግረው፣ መንግስት ለንግድ ዘርፉ ድጋፍ ማድረግ ሲገባው ብዙ ጊዜ ጠያቂ መሆኑንም ያመለክታሉ።
ደራሲ ጌታቸው የግሉ ዘርፍ ብዙ የስራ እድሎችን እንደሚፈጥር ጠቅሰው፣በመሆኑም አምጣ ብሎ እጅ ከመዘርጋት በፊት በምን ላግዝህ ብሎ ሁኔታዎችን ማጤን የመንግሰት ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ነጋዴውም የሚከፍለው ግብር መልሶ እሱን እንደሚጠቅም ተረድቶ በጊዜውና በአግባቡ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ያሳስባሉ።
የውስጥ ችግሩ ደግሞ የገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ አደረጃጀት መሆኑን ይገልጻሉ። «ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም» ያሉት ደራሲ ጌታቸው፣ ከዚህ በኋላ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትሯ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የግብር አምባሳደር ሆነው የተሾሙትና ተሳታፊዎች ሁሉ ቃል መግባታቸውን ጠቅሰው፣ ቃላቸውን ወደ ተግባር እንደሚቀይሩትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የባህርዳር ሀገረ ሰብከት ዋና ስራ አስኪያጅና የአማራ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ መላዕከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉአለም ቅዱሱ መጽሀፍ «የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር፤ የቄሳርን ለቄሳር ክፈሉ» እንደሚል ጠቅሰው፣ ግብር ሀይማኖታዊ ድጋፍ እንዳለውም ይገልጻሉ፡፤
‹‹አገሬን እወዳለሁ፤ እንድታድግ እፈልጋለሁ፤ ህዝብና መንግስትን አከብራለሁ›› የሚል ዜጋ ለግብር ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ያስገነዝባሉ። እኛም በየአውደ ምህረቱ ለተከታዮቻችን በማስተማር ኃላፊነታችንን እንወጣለን›› ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ ሰላምንም ሆነ ፍትህን በአገር ላይ ለማስፈን ደግሞ መንግስት እጅና እግር የሚያገኘው ግብር መሰብሰብ ሲችል ነው። ግብር ሲባል ቢቀልም ለመንግሰት ግን እንደ እስትንፋስ (ኦክሲጅን) አስፈላጊ ነው ፡፡
ግብር የብዙዎቻችን ህይወት ለመታደግ የሚያስችል አገራዊ አቅምን እንደሚፈጥር ጠቅሰው፣ ‹‹ግብር ባለመክፈል በአገር ላይ ከሚደርሰው ኪሳራ በመክፈሉ የሚገኘው ስልጣኔ ለሁላችንም ሊበለጥበን ይገባል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ለግብር ያለው ደካማ አመለካከት መቀየር እንደሚኖርበት ተናግረው፣ ግብር የሚያጭበረብር ሰው እንደ አራዳ መታየቱ ቀርቶ አገሩንና መንግስቱን የሚጠላ፤ ስለ ራሱ ልጆች የዛሬና የወደፊት ህልውና ምንም የማይጨነቅ ሞኝ ተደርጎ ሊቆጠርም ይገባል ብለዋል።
«የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም» የሚለውን አባባል በመጥቀስም፣ ያለፈው በዚሁ እንዲበቃ ለወደፊቱ የተሻለ ለመስራት አስቻይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ የማድረጉ ስራ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ግብር ክፈሉ ከማለት ባለፈ ገንዘብ ይዞ ለሚመጣ ግብር ከፋይ የሚመጠን ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራር አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎችን ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እየዳረገ ግብር ከፋዩን ሲያሸሽ ቆይቷል። በመሆኑም የግብር አሰባሰብ ሂደቱም ዘመናዊነትን የተላበሰ እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪም የግብር ስርዓታችን ፍትሀዊ ተገማች እና ቀላል እንዲሆን ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡
ግብር ከፋዩ ግዴታውን ለመወጣት ለቀናት ደጅ የሚጠናበትና አላስፈላጊ ወጪና እንግልት የሚዳረግበት አስራር ከምንገኝበት የቴክኖሎጂ ዘመን የማይጠበቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጀምሮ ሌሎች ፈጣን የክፍያ ስርዓቶችን መጠቀም የሚያስችል ማዕቀፍ ተግባራዊ እንደሚደረግ፣ ያመለክታሉ፡፡
ግብር ከፋዮችን በቢሮክራሲ፣ በጉቦ፣ በአልተገባ አሰራር የሚቀጣውን የመንግስት የስራ ኃላፊም ሆነ ሰራተኛ ግብር ከሚያጭበረብሩ ተለይቶ እንደማይታይ ያስታውቃሉ፡፡ ‹‹ገንዘብ ለአገሩ ሊከፍል የመጣን ሰው አክብሮና ጋብዞ ከመቀበል ይልቅ ያልተገባ ቢሮክራሲን የሚፈጥር ሰውንም ሆነ አሰራርን ከእንግዲህ አንታገስም›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
«ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት እንጂ አንዱ ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ አይደለም፤ አንዱ በሚከፍለው ግብር ሌላው የሚንደላቀቅበት ምክንያትም አይኖርም፤ በመሆኑም የተሳሳተ መስመር ውስጥ ያላችሁ በሙሉ ቀኑ ከመጨለሙ በፊት ወደ ትክክለኛው አሰራር እንድትደመሩ›› ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
‹‹እስከ አሁን አጭበርባሪዎችን ከመቅጣት በዘለለ በታማኝነት ግዴታቸውን የሚወጡትን አበረታተን አናውቅም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ በኋላ ግዴታቸውን በታማኝነት የሚወጡትን የሚያበረታታ አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ ግብር ለየትኛውም አገር ህልውና ማረጋገጫ እና መንግስታት የመረጣቸውን ህዝብ ጥያቄ የሚመልሱበት ነው ይላሉ፡፡ ግብር ለታለመለት አላማ በውጤታማነትና በብቃት ሲውል የህዝብ ጥያቄ እንደሚመለስ፣ መተማመንም እንደሚፈጠር ይገልጻሉ።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ደረጃው ይለያይ እንጂ በየትኛውም ዓለም መንግስት የታክስ ህግ ተገዢነትን ለማምጣት፣ የታክስ አስተዳደሩን ፍትሀዊ ለማድረግ ሲጥር ግብር ከፋዩ በበኩሉ ላለመክፈል ዳተኝነትን ሲያሳይ ይስተዋላል፡፡ አገራት ይህንን ችግር ለመፍታትና የታክስ አሰባሰባቸውን ለማሳደግ የተደራጁ የማህበረሰብ ንቅናቄዎችን ወይም ዘመቻዎችን በማድረግ ግብር የግል ገንዘብ ሳይሆን የአገርና የህዝብ እዳ መሆኑን ያስተምራሉ፤ በዚህም መንገድ የተጓዙ አገሮች ህዝባቸው ግብርን መክፈል ባህል ስልጣኔና ኩራት አድርጎ እንዲወስድ ማድረግ ችለዋል፡፡
‹‹እኛም ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል አገሪቱ ውስጥ ለሚካሄዱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ስራዎች መፋጠን የበኩላችንን መወጣትና ለውጡን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ማድረግ አለብን›› ያሉት ወይዘሮ አዳነች ፣‹‹ይህንን ማድረጋችን ህዝቡ ለሚያነሳቸው የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ እንዲሰጥ እንዲሁም የሀብት ክፍፍሉ ፍትሀዊ እንዲሆን ያስችላል›› ሲሉ ያብራራሉ።
ግብር የመንግስት እስትንፋስ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ያለ እስትንፋስ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ መሰረተ ልማት የሚገነባው፣ ሰላምና ደህንነት የሚጠበቀው፣ ትምህርት የሚስፋፋው፣ ጤና የሚጠበቀው፣ ወዘተ ግብር ሲኖር ብቻ ነው፡፡
ስለግብር አስፈላጊነት ሲነሳ በቅድሚያ እንደተባለው ግንዛቤ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሌም ሊሰራ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ የግብር አሰባሰቡን ማዘመን፣ ግብራቸውን በተገቢው መንገድና በወቅቱ የሚከፍሉትን ማበረታት፣ የማይከፍሉትን መቅጣት ይገባል፡፡ ለሁሉም ግን የመንግስት እስትንፋስ የሆነው ግብር የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም ግብር ለመንግስት የእስትንፋስ ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
እፀገነት አክሊሉ