ብሪታንያና የአውሮፓ ህብረት ሊፋቱ (ብሬግዚት) ሦስት ወራት ብቻ ቀርቷቸዋል። ይሁንና በውሉ መሠረት ብሪታንያን ከአውሮፓ ህብረት አባልነት የማፋታቱ ተግባር ፍጥነት ሲለካ በተፈለገው መጠን እየሄደ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይም ፍላጎታቸውን ተፈፃሚ ለማድረግ የአገሬውን ፓርላማ ድጋፍ በሚፈለገው ልክ ማግኘት አልቻሉም።
የጠቅላይ ሚኒስትሯ ዕቅድ በተቃዋሚዎቻቸው ብቻም ሳይሆን በፓርቲያቸው አባላት ሳይቀር ማጉረምረምና ቁጣን መቀስቀስ ከጀመረ ቆየት ብሏል።በተለይ የብሪታንያው ዋነኛው የፖለቲካ ድርጅት ሌበር ፓርቲ ሀገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የምታደርገውን ፍቺ እንደማይቀበለው ከወራት በፊት በሙሉ ድምጽ ወስኗል።ከዚህም ተሻግሮ በሊቀመንበር ጀርሚይ ኮርበን አማካኝነት አገሪቱ በአውሮፓ ህብረት አባልነት ቆይታዋ ላይ ዳግም ጠቅላላ ምርጫ እንድታካሂድ ጥሪ እስከማቅረብም ደርሷል።
ብሪታንያ በዚህ አያያዟ ከቀጠለች 2016 ያደረገችውን ሪፈረንደም እንደገና ልታየው እንደምትችል የፖለቲካ ተንታኞችና የመገናኛ ብዙሃን አስተያየትና ዘገባዎች ማመላከት ጀምረዋል።
ካርላ አዳም እና ዊሊያም ቡዝ ዋሽንግተን ፖስት ላይ ባሳፈሩት ትንታኔም፤ ቅዠት ይመስል የነበረው የዳግም ህዝብ ድምጽ ውሳኔው ጉዳይ አሁን እውን ሊሆን ዳድቶታል፤ በርካታ ወገኖችም ከወቅታዊው ቀውስ የማምለጫው ብቸኛው መንገድ ይሄው ዳግም ምርጫ ነው ማለት ጀምረዋል።
ከአውሮፓ ህብረት መለያየቱ የከበዳቸውና የቤት ሥራውም እንዳሰቡት ቀላል አለመሆኑ የገባቸው ብሪታኒያውያንም እውን ከህብረቱ የመውጣት ፍላጎት አለን? ሲሉ ራሳቸውን በመጠየቅ ለራሳቸው መልስ ሊሰጡ መንደርደራቸውን አብራርተዋል።
እ.ኤ.አ 2016 ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ አገራቸውን ከአውሮፓ ህብረት ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሯም ሆኑ ካቢኔያቸው ፍቺውን እውን በማድረጉ ላይ ፓርላማውን ማሳመን መቸገራቸው በርካታ ወገኖች ዳግም ህዝብ ውሳኔ በመካሄዱ ላይ መነጋገርን ምርጫቸው እንዲያደርጉ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
«ከወራት በፊት ማፈግፈግ የሚባል ነገር አልነበረም። ይሁንና ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዳግም ምርጫ ይካሄድ የሚሉ ድምፆች ተሰምተዋል፤ ድምፆቹም ከፍ ብለው የሚሰሙ ናቸው፤ ይህም በድጋሚ የህዝብ ድምፅ ማካሄድ የማይታሰብ ነው የተባለው በስህተት ስለመሆኑ ማረጋገጭ ሰጥቷል» ሲል ፍራንክ ላንግፊት በኤንፒ አር ላይ ባሰፈረው ዘገባው አስነብቧል።
በእርግጥም በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ታዋቂ የፖለቲካ ምሁራንና የቀድሞ መሪዎች ጭምር ዳግም ህዝበ ውሳኔውን ምርጫቸው ማድረግ ጅምረዋል ። ባሳለፍነው ሳምንት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ከወቅቱ የፖለቲካ ጡዘት እና ከቀጣዩ የኢኮኖሚ ድቀት ስጋት ጋር በተዛመደ ብሪታኒያ በህብረቱ ለመቆየት ወይም ላለመቆየት ፍላጎቷን ማረጋገጥ የሚያስችላት ሌላ አማራጭ መመልከት እንዳለባት ሲገልፁ ተሰምተዋል።የዳግም ምርጫው መካሄድ እየታየ ላለው የፍቺ ቀውስ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በአንፃሩ የብሪታኒያን ዜጎች ከህብረቱ የመገንጠል ፍላጎት ወደ ኋላ ለመመለስ ወደ ድምፅ መስጫ ኮሮጆ ማማተር የአገሪቱን ህገ መንግሥት እንደመክዳት ነው ይላሉ። «ህዝቡ ፍላጎቱን በምርጫው አረጋግጧል፤ድጋሚ ምርጫ የሚባል ነገር አይሰራም፤ ሌላ ምርጫ ማካሄድ በአገራችን የፖለቲካ ታማኝነትና ምሉዕነት ላይ መቼም የማይሽር ጠባሳ ያሳርፋል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ ይህን ማድረግ በብሪታኒያ ዴሞክራሲ ምሉዕነት ላይ የሚተማመኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማሳሳት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ብሪታኒያ ከህብረቱ ልትለያይ ወራት በቀሩበት በዚህ ወቅት በቴሪሳ ሜይ ላይ ጫናዎች ተበራክተዋል። ዳግም ህዝበ ውሳኔ መካሄድ እንዳለበት የሚያሳስቡ ድምፆችም ከየአቅጣጫው መሰማት ጀምረዋል። ይሁንና ህዝብ ውሳኔው ይካሄድ ቢባል አብረው የሚነሱ ፈተናዎች እንዳሉም አንዳንድ ወገኖች ይጠቁማሉ።
ይህ ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን የሚያስረዳው የኢቭኒንግ ስታንዳርድ ኢላ ዊላስ ጆርጂያ ቻምበርስ ዘገባ፣በመጀመሪያው ዙር ብቻ ፓርላማው ህገ ደንቡን እስኪፈርም ሰባት ወራትን መጠበቅ ግድ እንደሚል ያመለክታል፡፡ህዝበ ውሳኔው ህገ ደንብ ያስፈልገዋልና ይህን ለማጠናቀቅ በራሱ ወራትን እንደሚወስድ፣ በተለይ ሁለት ዓይነት ፍላጎትና አቋሞች መኖራቸው ይህን ሂደት የተንዛዛና ረጅም ጊዜ የሚፈልግ እንደሚያደርገው ያብራራል።
አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራንም ሆኑ የህግ አርቃቂዎች ሁለተኛውን የህዝበ ውሳኔ ሁነት ይደግፉታል፡፡ ተግባራዊነቱ የሚወስደው ጊዜ ግን የብዙዎች ስጋት መሆኑን የሚስማሙበት የዋሽንግተን ፖስት ጸሐፍቶቹ ካርላ አዳም እና ዊሊያም ቡዝ ፤አሁን ባለው ሁኔታ ብሪታኒያ ጊዜ እንደማይኖራት ይገልጻሉ።‹‹ህብረቱን ለመልቀቅ ሦስት ወራት ብቻ ነው የሚቀራት።ይህ በሆነበት ፍላጎቷን ለመገምገም ደግሞ ወደ ብራሰልስ በማቅናት የብሪክስ የፍቺ ቀጠሮ እንዲራዘምላት መጠየቅን ግድ ይላታል» ብለዋል።
የግሪን ፓርቲ ህግ አርቃቂ ካሮሊን ሉካስ ካርሎስ ለዋሽንግተን ፖስት፣ ‹‹ህዝቡ በፍቺው ላይ የተስማማበትን ድምፅ ሲሰጥ፤ ይህ ነው የሚባል መረጃና እውቀቱ አልነበረውም። እናም ይህን አሁን መፈተሽ አለበት›› ሲሉ ገልጸዋል።
የሲቢሲ ዘገባም ባለፉት አራት ወራት ይህ ነው የሚባል የብሪክስ ውል እንዳልታሰረ ጠቅሶ፣በተለይ የንግድ አንቀሳቃሾች ለዓለማችን አምስተኛዋ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ አገር መጪው ጊዜ አስጊ እንደሚሆንባት ገልጸዋል፡፡ የሌበር ፓርቲው መሪ ጄርሚ ኮርቤይንም ይህን ሃሳብ ከሚጋሩት መካከል መሆናቸውን አመላክቷል።
የብሪክስ ጉዳይ በጦዘበት በዚህ ወቅት ከየአቅጣጫው ጫናዎች መበራከታቸውን ዘገባው ጠቁሞ፣በርካታ ወገኖችም አስፈላጊውና ወሳኙ ተግባር በቶሎ እንዲጠናቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው አስረድቷል፡፡ የብሪታኒያ ፖለቲከኞችም በተለይም ሁለተኛ ህዝበ ውሳኔ የሚባል ፍፀሞ መታሰብ የለበትም በሚለው አቋማቸው ፀንተው መቆማቸውን አመልክቷል።
እንደ ሜል ኦንላይኑ ቲም ስኩትሮፕ ዘገባ፤ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችና የብሪታኒያ ሚኒስትሮች በሁለተኛው ህዝበ ድምፅ ፈፅሞ እንዳይስማሙ ከሚያደርጋቸው ምክንያት ቀዳሚው አርቲክል ሃምሳ ነው።
ጠበቃዎች አርቲክል ሃምሳ ከመጪው ሐምሌ ወር በተጨማሪ መራመዝ አለመቻሉ ይህ እንዳይሆን ያደርገዋል ማለታቸውን አመልክቷል፡፡
ለፍችው ከተቀመጠው ይፋ የጊዜ ሰሌዳ አንጻር ጊዜው በጣም መቃረቡ የምርጫውን በድጋሚ ማካሄድ የማይታሰብ እንደሚያደርገው ጠቅሰው፣ ህዝብ ውሳኔውን ለማካሄድም ውስብስብና ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ፣አዲስ የህግ ማዕቀፍና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን የሚያስከትል መሆኑንም ያስገነዝባሉ፡፡አዲስ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ቢያንስ አስፈላጊ ህገ ደንቦችን ለማዋቀር ስድስት ወራትን እንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡
የሠራተኛና የጡረታ ሚኒስትሯ አምበር ሩድ ምንም እንኳን እርሳቸውን ጭምሮ ሌሎች የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ የበላይ አመራሮች የዳግም ህዝበ ውሳኔውን መካሄድ ቢቃውሙም የሁነቱ መካሄድ አይቀሬነትን የሚመሰክር አስተያየት እየሰነዘሩ ናቸው፡፡ ‹‹እኔ ህዝቡ ለዳግም ድምጸ ውሳኔው እንዲጠራ ፍላጎት የለኝም፤ የአገሬው ፓርላማም በአንድ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ለመድረስ አቋም መያዝ ካቃተው ግን ሌሎች አማራጮች ይታያሉ፤ ጉዳዩ ዳግም ለህዝቡ የሚቀርብበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ሲሉ ለ አይ ቲቪ መናገራቸውን ኤ ኤፍ ፒ አስነብቧል።
በአጠቃላይ አሁን ባለው ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ አስተዳደር ብቃት ላይም ሆነ በፍቺው ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችና የዳግም ድምፀ ውሳኔው መካሄድ አለበት ደጋፊዎች ተበራክተዋል። ብሪታኒያም በፍቺ ምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ መዳከር ውስጥ ገብታለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
ታምራት ተስፋዬ