በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደራጀት የጀመሩት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ነበር። በዘመናዊ ትምህርት ቤት ያለፉ የጊዜው ወጣት የአሁኑ ዘመን አዛውንቶች ለፓርቲዎች መደራጀት በር ከፍተዋል። በተለይ በንጉሡ ዘመን በነበረው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ወጣቶች ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። በጊዜው በኅቡዕ ለተደራጁት ፓርቲዎች አመራርና መሥራቾች በፊውዳላዊው፣ በወታደራዊውና በፌዴራላዊው ሥርዓት ውስጥ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢያጋጥማቸውም እስካለንበት ዘመን መዝለቅ ችለዋል።
እየዳሁና እየተንገዳጉ እስካሁን ዘመን መዝለቅ የቻሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በተወሰኑ ግለሰቦች አመራር ላይ የተንጠለጠሉ ይመስላሉ። የአመራር ዘመናቸው እንደ ዘውዳዊ ሥርዓት እሰከ ዕለተ ሞት ነው ማለት ይቻላል። በብላቴና ዕድሜያችን የምናቃቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የቆዩና ወጣት አመራሮችን ማፍራት ያልቻሉ ናቸው። አንጋፋዎቹ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ወጣት አመራሮችን በማፍራት ረገድ ቀርፋፋዎች ነበሩ ማለት ይቻላል። በገዥው ፓርቲም በኩል ለወጣቶች ዕድል መስጠት የሞት ያህል የሚሰማቸውና አሮጌ ሀሳብ ይዘው ከአዲሱ ለውጥ ጋር መራመድ ተስኗቸው የሚንገታገቱ አዛውንቶችን እየተመለከትን ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ወጣቱን ለጦርነት እየፈለጉት ለአመራርነት ሲሆን ግን እየዘነጉት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል።
በኢፌዴሪ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቶች በዓባልነት የተስፋፉትና ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት በ1997 ዓ.ም በተካሄደ ምርጫ ነበር። በወቅቱ በተካሄደው የምርጫ ውድድር ላይ በወጣት አመራሮች የተደራጁት ፓርቲዎች ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተዋል። በአዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በምርጫው አሸናፊነት ተቀዳጀ ።
ነገር ግን ኢህአዴግ ልዩ ልዩ መሰናክሎችን ማጠንጠን ጀመረ። የመዲናዋን ዋና ዋና የገቢ ምንጮች የሆኑ እንደ ገቢዎችና ጉምሩክ ፣አንበሳ አውቶቡስ የመሳሰሉ ተቋማት ከአዲስ አበባ መስተዳድር ተቀምተው በፌዴራሉ መንግሥት ሥር እንዲሆኑ ተደረገ ። ዓላማው አሸናፊው ፓርቲ ሥልጣኑን እንዳይረከብ ከተረከበም ተግዳሮቶችን ለመፍጠር የታሰበ ነበር። ለዚሁ ውሳኔ ድጋፍ የሚሰጥ ሕግ ባልታሰበ ፍጥነት በተወካዮች ምክር ቤት እንዲወጣ ተደርጎ እንደነበርም አንዘነጋውም።
ይህን ተከትሎና በራሱ የውስጥ ችግሮች አሸናፊው ፓርቲ አዲስ አበባን ለመረከብ በሕግ ሽፋን የተሸረበበትን ሴራ በመቃወም መዲናዋን ለማስተዳደር እንደሚቸገር ኃላፊነቱንም እንደማይረከብ ገለፀ። ይህን ተከትሎ በከተማዋም ሆነ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በወጣቶች የታጀቡ ተቃውሞዎች ተበራከቱ። የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የሥራ ማቆም ዓድማ መቱ። ነጋዴዎችም ይህንኑ ተከትለው ከፊሎቹም ትራንስፖርት አጣን በሚል ምክንያት ሱቆቻቸውን በመዝጋት የዓድማው ተባባሪ ሆኑ። በጊዜው በወጣ መግለጫም ነጋዴዎችና ባለታክሲዎች ሁሉም ወደ ሥራው እንዲወጣ ቢነገርም ታክሲዎች ግን ወይ ፍንክች ብለው በውሳኔያቸው ጸኑ።
ነጋዴዎች ውሳኔውን በመፍራት ጭምር በአብዛኛው ወደ ሱቆቻቸው ሄዱ በወቅቱ በተወሰደው ‘ከፋፍለህ ቅጣ’ ትዕዛዝ ካልከፈቱ ሱቆች መካከል አንድ ሱቅ እየታሸገ አጠገቡ ያለሱቅ ደግሞ ሳይታይ እንደታለፈ በሚመስል እየተተወ ሌላ ሱቅ ደግሞ እየታሸገ ርምጃው ተወሰደ። ዓላማው ነጋዴውን ለመከፋፈል ታስቦ የተደረገ ስለነበር ሱቁ ያልታሸገበት ነጋዴ በፍጥነት ሱቁን ከፈተ። ሱቃቸው የታሸገባቸው ነጋዴዎች ከአንድ ዓመት በላይ ሱቃቸው ታሽጎ እንዲጉላሉና እንዲንገላቱ ተደረገ።ይህም ለታሸገባቸው ነጋዴዎች መቀጫና ለሌላው ደግሞ ማስፈራሪያ እንዲሆን የተደረገ ነበር ።
በወቅቱ ዋና ዋና የተባሉ የፓርቲ አመራሮች፣ ደጋፊዎችና ወጣቶች ከየቦታው እየተሰበሰቡ፣ እየታደኑ እና እየተደበደቡ ለእሥር ተዳረጉ። የአካል ጉዳት፣ የስነልቦና ስብራት የደረሰባቸውን የወቅቱን ወጣቶች ቤት ይቁጠራቸው ማለት ይሻላል።
ይህ መከረኛ የ1997 ዓ.ም ምርጫ በኢህአዴግ ላይ ብዙ ጣጣን አመጣ። የመጣውን ጣጣ ለመወጣት ከላይ እንደጠቀስነው አውራው ፓርቲ አሳሪ ሕጎችን አወጣ። ከምርጫው ውጤት መሰረዝ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ለተቃውሞ ወጡ በዚህም ምክንያት የፖሊሶች በትር አረፈባቸው። ከፊሎቹ ሲያዙ የተወሰኑት ሸሽተው አመለጡ። በእምነት ቦታዎች ግን ሽማግሌ ሆነው መገላገል በተሳናቸው አባቶች ምክንያት ወጣቶች ከተሸሸጉበት ተይዘው የፖሊስ ዱላና በትር እንዲሁም የእሥር ሰለባ ሆኑ ።
ከንጉሡ አገዛዝ ጀምሮ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል መሥራችና አመራር የሆኑት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ወጣት አመራሮችን ሲፈሩ እንጂ ሲያፈሩ ያልታዩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የተሻለ ለመሆን ወጣት አመራርን ለማብቃትና ለመተካካት ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው። ወጣት አመራሮች የወጣቱን ስሜትና ፍላጎት ያውቃሉ ይረዳሉ ስለዚህ ጥንታዊ አመራሮች ገለል ይበሉ ለወጣቶች በማማከር ያገልግሉ የሚል ሃሳብ አለ። በዚህ ላይ ልምድን በማካፈል በማማከር በመደገፍ ለማገልገል እንደሚቻል ማሰብ ተገቢ ነው።
የፖለቲካ ሥልጣን እንደ ንጉሣዊ ሥልጣን እስከ ዕለተ ሞት መሆን ያለበት አይመስለኝም። የፓርቲ ኃላፊነት እንደ ንግድ ቤት ግለሰቦች የሚያሽከረክሩት መሆን የለበትም ገደብ ሊበጅለት ይገባልም ብዬ አስባለሁ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለይም በየጫካውና ጉራንጉሩ ሲታገሉ ወጣቱን ለጦር በመማገድ ረገድ አይታሙም ። ወጣቱን ለመንበር ወይም ለአመራር በማብቃት ረገድ አንድ ርምጃ ፈቅ ያላሉ ናቸው። ፓርቲዎቻችን ለዜጎች ዴሞክራሲ መዳበር እየጣሩ መሆኑን ቢናገሩም ቅሉ እንደጠቀስነው ውስጠ ዴሞክራሲን አጎልብተው አመራር ሲቀይሩ አይታዩም ።
በኦሮሞ ህዝብ ብቻ የተደራጁ ከ 15 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ።አንጋፋ ከሆኑት ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሚታገሉት የብሔሩን መብት ለማስከበር ባህሉን ለማጠናከር እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም ግን “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ እንኳን የኦሮሞን መብት ሊያስከብሩና ባህሉን ሲያጠናክሩ የታዩበት ዘመን ግን አልነበረም።
ኢትዮጵያ ከማይዳሰሱ ዓለም አቀፍ ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና የሳይንስ ድርጅት ያስመዘገበችው የገዳ ሥርዓትን ቃኝተው በፓርቲያቸው ውስጥ ሲተገብሩ አልታየም። ዘመናዊ ትምህርቱን ያልተማሩት አባገዳዎቻችን በየስምንት ዓመት ይመረጣሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ይህን ፅኑ የሆነ የአመራር ሥርዓት አይተው በየጊዜው አመራር እየተኩ ቢመጡ የተሻለ ነበር። በተለይ ደግሞ የኦሮሞን ባህል እናከብራለን እናስከብራለን ለሚሉት ፓርቲዎች ባህላዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነውን የገዳ ሥርዓትን አይተው ተግብረው መታየት ነበረባቸው። ለአርባ እና ሃምሳ ዓመት በፖለቲካ ፓርቲ አመራርነት መቆየት ሥልጣንን ዘውዳዊ አገዛዝ ፣የግል ርስት ጉልት አልያም የግል ሀብት ንብረት ያስመስላል ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን ይተቻሉ።
የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ፣ በሀገሪቱ ዴሞክራሲ የለም፣ አውራው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊነትን አያቀውም ይናገረዋል እንጂ አይተገብረውም የሚሉ ስሞታዎችን በስደት ሆነ በአገር ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲያሰሙ ነበር። ሲያቀርቡ የነበረውን ቅሬታ ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች በራሳቸው ፓርቲ ውስጥ ውስጠ ዴሞክራሲን ተግብረው ወጣቶችን ለአመራርነት አካተው ቢሆን ጩኸታቸውን ተሰሚነት ይኖረዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአውራው ፓርቲ ላይ በየጊዜው የሚያሰሙት ቅሬታ የራሳችውን ውስጠ ዴሞክራሲ ሳያጠናክሩ ወጣቱን ለአመራሩ ሳያበቁ ከሆነ ድምፃቸው “የቁራ ጩኸት” የሚሆን ነው። ስለ ዴሞክራሲ የሚያወሩን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወጣቶችን እያቀፉና እየደገፉ በኃላፊነት እያስቀመጡ መሆን አለበት ሲሉ ምሁራን ይናገራሉ።
በአገር ውስጥ የቆዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወጣት ተተኪዎችን ለማፍራትና ለአመራርነት ለማብቃት በፖለቲካ ፓርቲዎች ፍርሀትና ተግዳሮት እንደነበር ይገልፃሉ ። በውጪ ያሉ ፓርቲዎች ደግሞ ዴሞክራሲ በዳበረበት አገር እየኖሩ ልምዳቸውን በማጋራት ወጣት አመራሮችን ሲያፈሩና ሲደግፉ ያልታዩ ናቸው በዚህም ወጣት አመራሮችን ሲፈሩና ሲገፉ የታዩ ናቸው ማለት ይቻላል ።
ፓርቲዎቻችን ወጣቶችን በአባልነት ቢመለምሉ ተተኪ እያፈሩ ይለመልማሉ።ፓርቲዎቻችን እንዳይንጫጩ፣ እንዳይቀጭጩና እንዳይቀጩ አማራጩ ወጣት አመራሮችን ለኃላፊነት በማብቃት መተካካትን መርህ አድርጎ መሥራት ነው። ከላይ እንደጠቀስነው ፓርቲዎቻችን ዘመን ተሻጋሪ የሚሆኑት በጣት ከሚቆጠሩ አመራሮች ተላቀው ወጣቶችን ሲያካትቱ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን ይህን ከግምት አስገብተው ለመጪው ምርጫ ወጣቶችን እየመለመሉ መዘጋጀቱ የተሻለ ነው፡፡ በተለይ ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ፓርቲዎች ወጣቱን ለኃላፊነት ማብቃት ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ እንዳይሆን ከሁከትና ግርግርም እንዲታቀብ መጣር ይገባቸዋል
ኢህአዴግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥ ባሉ ዜጎችና በዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብሎም በዓለም ሀገራትና መንግሥታት ሠፊ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ሕዝብን የሚያዳምጥ የአመራር ለውጥ በማምጣቱ ነው። በአመራር ለውጡ ውስጥ ዐቢይ ሚና የተጫወቱ ወጣትና ጎልማሳ አመራሮች በመካተታቸው ነው። ለውጡ ከሀገሪቱ ዜጎች አልፎ በውጪና በአገር ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚበጅ መሆኑ ተመስክሮለታል ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች “ቅቤ በረደኝ ብሎ እሳት አይሞቅም” እንደሚባለው የሀገራችን ብሂል እንዳይሆኑ ከወዲሁ ተተኪ ወጣቶችን በማፍራት ህልውናቸውን ለማስቀጠል አንድ ርምጃ ወደፊት መራመድ አለባቸው። ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት ያልቻሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊቀመንበርነት ደመቀኝ ሞቀኝ ብለው ለወጣቱ ኃላፊነቱን ማስረከብ ካልቻሉ ኃላፊዎቹ ያለፉ ቀን የፓርቲዎቹ ህልውና ይኮሰምናል ብቻ ሳይሆን እንደ ቅቤ ቀልጦ ይቀራል።ለረጅም ዘመናት በኃላፊነት የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወጣቶችን ለኃላፊነት በማብቃት እና በመተካት አመራርነት በቃኝ ማለትን መለማመዱን ያዙ። ከወዲሁ ፓርቲዎች ለውስጠ ዴሞክራሲያዊ አመራር አንድ መሠረት መጣልን ባህላቸው አድርገው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ።
ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን በርግጥም ተፎካካሪ ፓርቲ ሆነው መታየት አለባቸው። ተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን ወጣት አመራሮችን ለማብቃትና ለመተካት ጥረት አድርጉ። ሀገራችን የወጣቶች አገር ነች ወጣት አመራሮችን ለተፎካካሪ ፓርቲ አመራርነት ቢበቁ የወጣቱን ስሜት ያውቃሉ ይረዳሉ። ‘ጥንታዊ’ የፓርቲ አመራሮች ከአመራርነት ገለል በሉ እና ልምድን በማካፈል፣ በማማከር ፣ወጣቶችን አገልግሉ። ተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን ይህን አካሄድ ካልተከላችሁና ካልዘረጋችሁ መሪነቱ ቀርቶ ጭራ ፓርቲ ሆናችሁ ትቀራላችሁ።
የብሔራዊ ምርጫ ጊዜ እየተቃረበ ከመሆኑ አንፃር የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ትጥቃቸውን ፈተው ሲሰለፉ ወጣቱንም እየመለመሉና እያሳተፉ ለኃላፊነት ለተተኪነት ማብቃት ይገባቸዋል። ወጣቶችን ለማፍራት ለኃላፊነት ለማብቃት ፍርሃት ሊይዛቸው አይገባም።
የፓርቲያቸውን ህልውና ማስቀጠል የሚችሉት እንደ ርስት ጉልት ለረጅም ዘመን የያዙትን አመራር ወጣቱን ሲያካትቱ ብቻ ነው። የረጅም ዘመን አገልግሎት ለአዛውንቶች ይበልጥ ተቀባይነት ያለው በእምነት ቦታዎች መሆኑ ይታወቃል። አንጋፋ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወጣቶችን በማብቃት ብቻ ሳይሆን በመተካት የፓርቲያችሁን ህልውና አስቀጥሉ ይህን ስታደርጉ በማማከር ልምድ በማካፈል ለፓርቲያችሁ እያገለገላችሁ በርግጥም አንጋፋ ትሆናላችሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011
ይቤ ከደጃች ውቤ