ውብ ጸጉር ያለው ታዳጊ ነው። ለጸጉሩ ያለው ፍቅር ከሴቶችም በላይ ነው። በእንክብካቤ ይይዘዋል። ቢነካካው፣ ቢታጠበው፣ ቢያበጥረው፣ ቢዳስሰው አይጠግብም ።በክረምት ደግሞ አሳድጎ እሱ የሚጨምርበት ንቅናቄ እንዳለ ሆኖ ነፋስ ሽው ሲያደርገው እንደደረሰ የጤፍ ቡቃያ ይዘናፈላል። ሀርነቱ፣ ዞማነቱ ብቻ እንደ እኔ ጸጉር የሚወድን ሰው ብቻ ሳይሆን ጸጉር ለሴት እንጂ እስከሚለው ሰው ድረስ አይን ይስባል። ያማልላል።
ይሄ የምላችሁ ልጅ ጸጉር ታዲያ መስከረም ሲጠባ ያው እንደተለመደው የትምህርት ቤት ህግ አለና ይቆረጣል። ባይወድም ግድ ነውና መቼ ይሆን ዩኒቨርሲቲ ገብቼ እንደፍላጎቴ የማደርገው ብሎ እየተነጫነጨም ቢሆን ብቻ የትምህርት ቤቱ ህግ ነው ይታጨዳል ።ለአስር ወራት የትምህርት ጊዜውን ተስተካክሎ ወጣት ወንድ ተማሪ የሚያስመስለውን ጸጉሩን ታጥቦ ከመውጣት በስተቀር ሌላ ምርጫ የለውም ።
እንዳው ይሄንን ስል መመስገን የሚገባቸውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ላመስግን። ሁሉም ባይሆኑም ብዙዎች የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪዎቻቸውን ጸጉር ፣ ዩኒፎርም እና የሚያደርጉትን ጫማ ጭምር ከስርዓት የወጣ እንዳይሆን ይቆጣጠራሉ።ወንዶቹ ሱሪያቸውን በስርዓት እንዲታጠቁ ያስገድዳሉ።እንዳውም አንድ የትምህርት ቤት ባለቤት በትምህርት ዘመኑ መጀመሪያ ቀን ተማሪዎችን አሰልፎ “እያንዳንዳችሁ ወንዶች ቀበቶ መታጠቅ አለባችሁ ። ሱሪዬን ዝቅ አደርጋለሁ ብትሉ አትገቡም። ወላጆቼ ቀበቶ አልገዙልኝም፣ የለኝም የምትሉ ካላችሁ ሱሪያችሁን በቃጫ ድብን አድርጋችሁ ታስራላችሁ” እንዳላቸው የነገሩኝን አልረሳውም። በእነሱ አባባል ሙድ ቢጤ ቢይዙበትም ለእኔ ግን ትልቅ መልዕክት ትቷል። እንዲህ አይነት ልጆችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ስነስርዓት ይዘው እንዲያድጉ የሚያደርጉትን ታዲያ ማመስገን አለብን በሚለው ሁሉም ይስማማል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ሱሪያቸውን እንደ እጀጠባብ አጣብቀው ከወገባቸው ዝቅ አድርገው ጸጉራቸውን አንጨባረው፣ አንጨፋረውና ቆጣጥረው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱትን ደግሞ ዝም ብለው የሚቀበሉ ትምህርት ቤቶች እና መምህራን መኖራቸው አይዘንጋ። በቀለም አባትነት የሚቀርፁትን ተማሪ በምንቸገረኝነት የሚመለከቱ ታዲያ መምህራን ናቸው ብሎ መናገር መዳፈር አይሆን ይሆን? እንደ እኔ መምህራን ናቸው ። ተማሪ እየቀረፁ ነው ማለቱ ከበድ አለኝ።
ታዲያ ይሄ የስነምግባር ችግር የሚታየው በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ብቻ እንዳይመስላችሁ። ምንቸገረኝነቱ በመንግስት ትምህርት ቤቶችም ጎልህ ነው። በነገራችን ላይ የትምህርት ቤት ስነምግባር ተጓደለ ስል ይሄ በተማሪው ብቻ እንዳልሆነ ይያዝልኝ።”ስርዓት አልበኛ” ከምንላቸው ተማሪዎች ባልተናነሰም ስርዓት አልበኛ መምህራንም ብዙ ናቸውና። ተማሪ ከትምህርት እንጂ ከእኔ ስነምግባር ምንአለው እስከሚሉት ድረስ ማለቴ ነው። ከሚያስተምሩት ተማሪ ጋር በጫት ቤት፣ በመጠጥ ቤት የሚጎዳኙ መምህራን መኖራቸው አይዘንጋ። አሁንም እላለሁ ሁሉም መምህራን አይደሉም። በሙያቸው በምግባራቸው አንቱ የተሰኙ፣ የእውነቱ የቀለም አባቶች አሉን። የማንረሳቸው ክፉ አይንካችሁ የምንላቸው፣ ከወላጅ አባት የማይለዩ ብዙ ምስጉን መምህራን አሉን። መቼም የማይረሱ ውለታቸውን እንዴት ልመልስ የሚያሰኙትን መምህራን ኢትዮጵያ አፍርታለችና።
አሁንም መምህርነትን እያከበሩና እያስከበሩ ያሉት እነሱ ናቸው። አሁንም እላለሁ እናንተም በራሳችሁ ለራሳችሁ ብቻም ሳይሆን ሌላውንም ከመስመር ወጣ የሚለውን መምህር ጭምር ሃይ በሉ። አበው በአንድ እጅ አይጨበጨብም እንዲሉ በጥቂት ብቁና ሙሉ መምህራን ብቻ ብልሹ መምህራንንና ተማሪን ማረቅ ከበድ ይላል።እዚህ ላይ መምህራኖች ተዳፍሬና ቀዩን መስመር አልፌ ከሆነ ሁሌም ስሳሳትና ሳጠፋ እንደምለው ይቅርታ ይደረግልኝ። ይሁንና ያየሁትን አይቼና የሰማሁትን ሰምቼ እንጂ ልቦለድ እያወራሁ እንዳልሆነ ግን እናንተንም ምስክሮቼ ብዬ እቆጥራለሁ።
አነጋጋሪው የስነምግባር ጉዳይ ከተማሪ ወደ መምህራን ሙልጭ አድርጎ ወሰደኝ አይደል፣ ልመለስ ስለተነሳሁበት ወጣት ሀሳብ ።ይሄ ጸጉራማ ወጣት ታዲያ ዘንድሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሊገባ ነውና ጸጉሩን እንደ ጉድ አሳድጓል።ዘንድሮ ክረምቱም ያማረ እንደነበረው ዝናብ የጠገበ ለምለም ቡቃያ መስሏል የእሱም ጸጉር ። ክረምቱ ጸጉርም ያሳምራል ልበል? አይቼ በውስጤ ያሰበኩት ነው።
አሁንም እንደለመድኩት ጥያቄ ማንሳቴን ግን አልተውኩም። ” ይሄ ጸጉር መፍትሄ የለውም እንዴ?” ስል አነሳሁ ። በሳቅ የታጀበ መልስ ነበር አጸፋው።” ዘንድሮ ጉዞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ነው። ተስተካከል ፣ ይሄን ልበስ ፣ያን አትልበስ፣ ደህና እደሪ” ነበር መልሱ። በልጁ አላዘንኩም መለስ ብዬ ያስታወስኳቸው ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ነበር። ልጁ ያለው እውነት እኮ ነው አልኩ። የት ነህ? ማንነህ? ምንድነህ?… የሚል ከሌለ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እውቀት መገብያ መሆናቸው ይቀርና ልክ የሰማነውን የምናየውን ይሆናሉ። እዚህ ላይ አንድ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ከፍተኛ ባለስልጣን ያሉኝን ላስታውስ። “ዩኒቨርሲቲዎቻችን ቡና የማይጠጡ ልጆችን ተቀብለው ጫት ቃሚ አድርገው ነው የሚያስረክቡት “ብለዋል ። ታዲያ ይሄንን እየሰማና እያየ ያደገ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ እንደፈለግኩ የምሆንበት ቦታ ነው ብሎ ቢያስብ ይፈረድበታልን?
የልጁን ፍላጎት አስቤ በተለይ ደግሞ የትምህርት ዘመኑ አልቆ ስንገናኝ ይሄ ጸጉር የት ሊደርስ እንደሚችል ዝም ብዬ ስስለው እንደሴቶቹ ወደኋላ ተኝቶ በፖኒተል አስሮ እንደምንገናኘ ሳላሸልብ አለምኩ። ደግሞም ይሆናል ምክንያቱም ሀይባይ የለማ። ይሄ የሚሆነው እስከ አለፈው ዓመት ብቻ ይመስለኛል። ምክንያቱም ቢዘገይም እንኳን ዘንድሮ ላይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ኮስተር ለማለት ማቀዳቸውን ሰምተናልና። ስርዓት አልበኛ ተማሪ አናፈራም፣ ሱሪ ዝቅ፣ ቡጭቅጭቅ …ለተማሪዎቻችን አይመጥንም እያሉ መሆናቸውን ጭምጭምታው ደርሶናል። እኛም ያድርገው እንላለን።ኧረ እንዳውም ደህና ነገር ሲሰማ አይቀይርብን ተብሎ ጸሎትና ዱአ ሁሉ ይደረጋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆነው እንዲገኙ እኛም ይሄንኑ እናደርጋለን ።
ይሄንን መነሻዬ አደረግኩት እንጂ ብዙ ኧረ በጣም ብዙ ዩኒቨርሲቲ ገብተን ፀጉራችንን ቆጣጥረን፣ አሳድገን፣ አፍሮ አበጥረን… ብለው የሚያልሙ እንዳሉ አንዘንጋ ። ሁሉም ይሄንን የሚያልሙት ታዲያ ከምን ተነስተው ነው ብለን ብናስብ መልሱ ቀላል ነው። ቀደም ሲል ከገቡ ተማሪዎች ያዩትን ለመድገም ፣ የዕድገት ወይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የመሆን መለያ አድርገው በማሰብ ይመስለኛል ብል ተሳሳትኩ እንዴ? ከሆነም ይቅርታ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሪዛቸውና ጸጉራቸው የሚያድገው ለመስተካከል ጊዜ እያጡ የጥናት ሰዓት ይሻማብናል ብለው ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በዚህ ሀሳቤ ዙሪያ አንድ የጤና ተማሪ ግን ምን አለኝ” ጸጉር መስተካከል እንዳውም የጥናት ጊዜ ያስገኛል ። ጸጉር መንከባከብ ነው ጊዜ የሚወስደው” አለኝ ።እንዴት? የእኔ ጥያቄ ነበር። በቃ አንድ ልጅ ጸጉሩን ካሳጠረ ጠዋት ፊቱን ሲታጠብ ጸጉሩንም ታጥቦ ንጹህ ይሆናል። ጸጉር ያለው ተማሪ ግን ያንን ጸጉሩን መንከባከብ ይጠበቅበታል ።መስታወት እያየ ማበጠርና ማስተካከል ሁሉ ይኖራል። ይሄ ደግሞ ጊዜውን ይሻማል ። ነገር ግን የጤና ተማሪዎች ከሶስተኛ ዓመት በላይ ሲሆኑ ፀጉር ማሳደግ አይፈቀድላቸውም። አለባበሳቸውም ሆነ ጸጉር አቆራረጣቸው ስርዓት ያለው መሆን አለበት ። ይሄ ግዴታ ነው። የሚያክሙትን ህመምተኛና የሚጎበኙት ታካሚ እምነት ሊጥልበት የሚችል ስርዓት የተከተሉ መሆን አለባቸው ተብሎ ይታመናል” ሲል አስረዳኝ። ይሄ በጣም ጠቃሚና ይበል የሚያሰኝ ሀሳብ ነው። ታዲያ ሌላው ሙያ ላይ እምነት የሚጣልበትና ለሚሰማራበት ሙያ አስፈላጊውን ስነምግባር የተላበሰ ማድረጉ ምነው ከፋን። ስለዚህ ሁሉም ተማሪ ስነስርዓት ያለው አለባበስና የጸጉር አቆራረጥ ይኑረው ነው ሀሳቤ። ይሄ በጣም ጥሩ ነገር ነው በሌላው ዘርፍስ በህብረተሰቡ ዘንድ ተመራጭ ተመስጋኝ ቢሆን የሚያገለግለው ደንበኛ የሚደሰትበት ቢሆን ኧረ እንዳውም ሱሪውን ከፍ አድርጎ ወገቡ ላይ የታጠቀ ወላጆቻችን እንደሚሉት ቆፍጣና ወንድ ቢሆን ምን አለ ። እንዳው ምነው ወንዶቹ ላይ በረታሽ አትበሉኝ። የሴቱም ለዛሬም ባይሆን ብዙ ይባልበታልና በዚሁ ይያዝ።
ዘንድሮ ግን ዩኒቨርሲቲዎቻችን የመጥፎ ምሳሌ አንሆንም! እምቢ አሻፈረኝ! ለማለት መዘጋጀታቸውን ወሬ አይደበቅ አይደል ሀሜቱ ሽው ብሎኛል። ቀድሜ ካመሰገንኩ በኋላ ለመውቀስ አይሁን ብዬ እንጂ እውነት ያሰቡትን ከተገበሩት ቀደም ብለን ምስጋና ይድረሳችሁ ማለት ይገባል።
ዩኒቨርሲቲዎች ሌላው አሳዳጊዎች ናቸው። ተማሪዎችን በእውቀት አጎልብተው፣ በአእምሮ አደርጅተው፣ ለሀገር ለወገን አሳቢ፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ አድርገው ማውጫ ቦታ ናቸው። ታዲያ በተማሪ አያያዛቸው እንደስማቸው ቢሆኑስ? ሰላም!
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2012
አልማዝ አያሌው