“የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻው ዲያስፖራው በኢንቨስትመንት እንዲሠማራ ማነቃቂያ ተፈጥሯል”  – ዲያስፖራዎች

አዲስ አበባ፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻው ዲያስፖራ በብዛት በኢንቨስትመንት እንዲሠማራ ማነቃቂያ መፍጠሩን የተለያዩ ዲያስፖራዎች ገለጹ፡፡

ከካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ የመጡት አቶ ኃይለኢየሱስ መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጭ ሀገር ለሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሠማርተው ሀገራቸውንና ራሳቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ከፍተኛ ማነቃቂያ ፈጥሯል፡፡

የኢኮኖሚ ማሻሻው ውጭ ለሚኖረው ዲያስፖራ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ ከፍተኛ ማነቃቂያ ነው ያሉት አቶ ኃይለኢየሱስ፣ መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚያበረታታ የውጭ የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን የሚያስችል ማስተካከያ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ማሻሻያውን ተከትሎም እሳቸው በሆቴል ኢንዱስትሪው ወደ ሥራ ለመግባት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ማሻሻያው የተወሰነ የኑሮ ውድነትን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ገልጸው፣ የውጭ ንግድን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽልና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ፣ ከሀገር በሚወጡ እቃዎች ላይ አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ያደርጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዲያስፖራውም ማሻሻያውን ተከትሎ ወደ እንቅስቃሴ እንዲገቡ የሚያስችል መሆኑን በመግለጽ፣ አባላቱ ወደ ሀገር ቤት የሚልከውን የውጭ ምንዛሬ ከፍ እንዲል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የተሠሩት የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ መቀየሩን የገለጹት አቶ ኃይለኢየሱስ፣ በሌሎች ዓለም ሀገራት ከተሞች ላይ የሚታዩ መንገዶች፣ መብራቶች፣ እግረኛ፣ የሳይክል መንገዶችን ጨምሮ የመዝናኛና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዱባይ የመጡት አቶ ኤሊያስ ከበደ በበኩላቸው፣ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻው ለዲያስፖራው አባላትን ወደ ኢንቨስትመንት ለማምጣት የሚያስችል ማበረታቻ ነው፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ማቀዳቸውን ጠቅሰው፣ መንግሥት በሚያስቀምጠው አሠራርና መመሪያ መሠረት በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የተሠራው የኮሪደር ልማት ከተማዋን እንደስሟ አበባ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለእንግዶች ምቹ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ መግባቷ የሚታወስ ሲሆን የማሻሻያው ዓላማም የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You