ኢትዮጵያ እያስተናገደች በምትገኘው የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በቡድን ውድድር ከ24 ዓመታት በኋላ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች። ከጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጅምናዚየም የሚካሄደው የአፍሪካ አዋቂዎች ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በጠንካራ ፉክክሮች ታጅቦ አምስተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል።
በጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑ ሀገራት እየተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያ በሴቶች ድል አልቀናትም። በወንዶች መካከል በሚደረገው ፉክክር ግን በቡድን አራተኛ ደረጃን በመያዝ ከረጅም ዓመት በኋላ የነሐስ ሜዳሊያ ተመዝግቧል።
በሁለቱም ፆታ በተለያዩ ምድቦች ሀገራት የሚያደርጉት ፉክክር ጠንካራና በብዙ ተሰጥዖዎች የተሟላ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በሜዳዋና ደጋፊዋ ፊት እንደመጫወቷ ጥሩ ተፎካካሪ ሆና ከነሐስ ሜዳሊያ በላይ ማስመዝገብ አልቻለችም። ከትናንት በስቲያ በወንዶችና ሴቶች የቡድን ምድብ የግማሽ ፍጻሜና የፍጻሜ ጨዋታዎች ሲካሄዱ፣ ሻምፒዮኑ እንዲሁም ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቁ ሀገራት ተለይተዋል።
ይህን ታላቅ አሕጉራዊ ውድድር የምታስተናግደው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኗን ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን አሠልጣኝ በመጋበዝ እና በራሷ አሠልጣኞች ታግዛ ጠንካራ ዝግጅቶችን ስታደርግ ቆይታለች። ለአዘጋጅ ሀገር የሚሰጠውንም ዕድል በመጠቀምም ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማሰለፍ ዋናውን ጨምሮ 8 ወንዶችን እና 8 ሴት የጠረጴዛ ቴኒስ ተጫዋቾችን በማሳተፍ ላይ ትገኛለች።
በኢትዮጵያ የክለቦች ሻምፒዮና እንዲሁም ከሌሎች ሀገር አቀፍ ውድድሮች የተመረጡት ተጫዋቾችም ለዚህ
ውድድር ባደረጉት ልዩና ጠንካራ ዝግጅት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነዋል። ውድድሮቹ በቡድን፣ በድብልቅ ፆታ፣ በጥንድና በነጠላ እየተካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡድንም በቡድን ውድድር በምድብ ጨዋታዎቹ ጠንካራ ሀገራትን ገጥሞ ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን አራተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ነው የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት የቻለችው።
በወንዶች የቡድን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከሱዳን እና ቱኒዚያ ጋር የተደለደለችው በሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ከቤኒን ተጫውታ 3 ለ 2 በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ መድረስ ችላለች። ከምድብ ማጣሪያ ጀምሮ በቡድን ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየትም ለዋንጫ ለማለፍ በተካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ በናይጄሪያ 3 ለ 0 ተሸንፋ ለዋንጫ ሳታልፍ ቀርታለች። የውድድሩ ከባድ ተፎካካሪ የሆነችው ናይጄሪያ ከኢትዮጵያ በፊት በሩብ ፍጻሜው ፍልሚያ ሌላኛዋን ጠንካራ ተፎካካሪ ሀገር ቶጎን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፋለች። በዚህም መሠረት ናይጄሪያ በቡድን ውድድር ዋንጫውን እስከማንሳት ተጉዛለች።
ናይጄሪያ በፍጻሜው ጨዋታ የሰሜን አፍሪካዋን ጠንካራ ተፎካካሪ ሀገር አልጄሪያን ገጥማም 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነበር በሰባት ዓመት የመጀመሪያውን የቡድን ዋንጫ ያሳካችው። በዚህ የቡድን ውድድር አልጄሪያ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ቱኒዚያ ሦስተኛ፣ ኢትዮጵያ አራተኛ ሆና የነሐስ ሜዳሊያን ማስመዝገብ ችለዋል።
በሴቶች የቡድን ውድድር በምድብ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ውጤት ያልቀናት ሲሆን ግብፅ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችላለች። በወንዶቹ የቡድን ዋንጫ ያነሳችው ናይጄሪያ በሴቶችም የቡድን ፍልሚያ ለፍፃሜ የበቃች ቢሆንም በግብፅ 3 ለ 0 ተሸንፋለች። ግብፅ በበኩላ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን ወስዳለች።
በአሕጉራዊው መድረክ ናይጄሪያና ግብፅ በውጤት ረገድ የበላይነትን የሚይዙ ሲሆን ኢትዮጵያ እአአ በ2000 እራሷ ባስተናገደችው ውድድር ሜዳሊያ ውስጥ ከገባች በኋላ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ የአሁኑ ሁለተኛዋ ነው። ከዚህ በፊት የአዋቂዎች ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮናን ጨምሮ በ1993 አስራ አራተኛው የመላ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድርን እና በቅርብ ጊዜ ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮናን በተሳካ ሁኔታ አስተናግዳለች። ውድድሩ በቀጣይ ቀናት በተለያዩ ምድቦች የማጣሪያና የፍጻሜ ፍልሚያዎችን እያስተናገደ የሚቀጥል ሲሆን፣ በመጪው ቅዳሜ አጠቃላይ አሸናፊ የሚሆነውን ሀገር በመለየት ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል።
አልጄሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን፣ ካሜሮን፣ ጋና፣ ሩዋንዳ፣ ቱኒዚያ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቶጎ፣ ዩጋንዳ፣ አስተናጋጇ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ውድድራቸውን በተለያዩ ምድቦች እያደረጉ ይገኛሉ።
ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ የውድድር አመራር ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን በተጨማሪም በትናንትናው እለት የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ጠቅላላ ጉባኤም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተካሄዷል። በመድረኩ የዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፔትራ ሶርሊንግን ጨምሮ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፕሬዚዳንት፣ የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ ተብሎ ተገኝተዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም