በዞኑ 322 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው

ዲላ፦ በጌዴኦ ዞን 322 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት ላይ መዋላቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በታችኛው የትምህርት እርከን ላይ ትኩረት ተደርጓል። በዚህም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ አንደኛ መማሪያ ክፍሎችን ተገብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በጌዴኦ ዞን ባለፉት ሁለት ዓመታት ለቅድመ አንደኛ ትምህርት በተሰጠው ትኩረት 322 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል ያሉት አቶ ዘማች፤ የተገነቡት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ገልጸዋል።

አሁን ላይ በጌዴኦ ልማት ማህበር እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከአሥራ አራት በላይ ሞዴል የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘማች፤ እነዚህን እያሰፋን በሁሉም አካባቢ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን በስፋት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ቢጀምሩም ውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ዘማች፤ የህፃናት መጫወቻዎች እና መሰል የቅድመ አንደኛ የትምህርትን ቁሳቁሶች እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።

ማህበረሰቡም ልጁን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ ትምህርት ቤቱን ተንከባክቦ በመያዝ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አለበት ያሉት አቶ ዘማች፤ የትምህርት ዘርፉን የማሻሻል ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሕዝቡን ያሳተፉ የተለያዩ ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

ትምህርት ቤቶችን ምቹና ሳቢ ለማድረግ በተጀመረው በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ላይ አበረታች አፈፃጸም መመዝገቡን ገልጸው፤ የትምህርት ቤቱ መገንባት የነዋሪዎችን የዘመናት ጥያቄ መልስ የሰጠ ነው። በተለይ ከትምህርት ቤቶቹ በዕውቀታቸው የተሻሉ ልጆች እንዲወጡ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You