በከተማዋ ከ690 ሺህ በላይ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት ተሠጥቷል

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የልጅነት ልምሻ ወይም የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ ከ690 ሺህ በላይ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት መስጠት መቻሉን ከተማው አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ምርምር እና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ዳምጠው ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የልጅነት ልምሻ ወይም የፖሊዮ ቫይረስ በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝት የሚመጣ ሲሆን ሕፃናትን ለዘላቂ አካል ጉዳት ብሎም ለሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ ነው፡፡

ይህንን ለመከላከልም እንደከተማ ከመስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 02 ቀን 2017 ዓ.ም ለስድስት ቀናት የልጅነት ልምሻ ወይም የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የተካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ በዘመቻውም ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ 628 ሺህ 714 ህጻናት ለመከተብ ታቅዶ 691 ሺህ 206 ያህል ህጻናት ክትባት መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

የክትባት ዘመቻው ቤት ለቤት ጨምሮ በትምህርት ቤት፣ በሕጻናት ማቆያ፣ በማሳደጊያ እና በሌሎች ሕጻናት በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘመቻው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁሉንም ህጻናት ከመከተብ በተጨማሪ ክትባት ያልጀመሩ ወይም ያቋረጡ ካሉ ወደ መደበኛ ሥርዓት ውስጥ የማስገባት እና ፖሊዮ መሰል ምልክቶች የሚታዩባቸው ህጻናቶች ካሉ የመለየት እቅድ በመያዝ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተደረገ አሰሳ 412 ክትባት ያልጀመሩ ወይም ያቋረጡ በጎዳና እና በማቆያ የሚገኙ ህጻናት መደበኛ ክትባትን እንዲጀምሩ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳም ምንም አይነት በፖሊዮ የተጠቃ ወይም የሚያጠራጥር ህጻን አለመኖሩን ማየት የተቻለ ሲሆን ይህም መደበኛ የክትባት ፕሮግራም ምን ያህል አዋጭ መሆኑን የታየበት ነው ብለዋል፡፡

አቶ ዳንኤል እንደገለጹት፤ ክትባቱ ወረርሽን ከመከሰቱ በፊት የመከላከል አቅምን ለማሳደግ ይረዳል፡፡95 በመቶ ህጻናቶች የክትባት አገልግሎትን ካገኙ የከተማው የመከላከል አቅም ከፍተኛ የሚባል ሲሆን ከታቀደው በላይ ማሳካት በመቻሉም በከተማው ወረርሽኝ ቢከሰት እንኳን ህጻናቱ እንዳይጠቁ ለማድረግ ያስችላል፡፡

የፖሊዮ በሽታ በዋናነት ህጻናትን የሚያጠቃ በፖሊዮ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት የእግር፣ የእጅ እንዲሁም የውጭ ክፍልን የሚያልፈሰፍስ በሽታ ሲሆን የሚተላለፍ መንገዱም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ባለ ንክኪ፣ በተበከለ ምግብ እና በተበከለ ውሃ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ንጽህናን ከመጠበቅ ባለፈ በዋነኝነት ክትባቱን በአግባቡ በመውሰድ ህጻናት ከበሽታ የመከላከል አቅማቸውን በማሳደግ የፖሊዮ በሽታን መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡

በከተማዋ ለሚገኙ ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት በሙሉ ክትባት በመስጠት ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለማድረግ የተካሄደው የክትባት ዘመቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊዮ ቫይረስን ለመከላከል የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You