የደብተር ሽፋን

ትምህርት በተጀመረበት ሳምንት ከአንድ የቤተሰብ አባል ጋር ሆነን ለዘመድ ልጆች ደብተር ለመግዛት በየሱቆች ዞር ዞር እያልን ነበር። ከአንደኛው ሱቅ ገዝቶ መጣ። የደብተሮችን ሽፋን እያየን እኛ ስንማር ከነበሩት ጋር እያነፃፀርን ነበር። እሱ የሒሳብ መምህር ስለሆነ ለምዶበት ነው መሰለኝ ደብተር በትኩረት ያያል።

የዋጋው ውድነት የገበያ ሁኔታ ነውና ለመውቀስም አያስኬድም። ሲያነጋግረን የነበረው የደብተሮቹ ሽፋን ትምህርታዊ መረጃዎችን አለመያዙ ነው። ምናልባት በዚህ ዘመን የሚመረቱት ደብተሮች ሁሉ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን እኛ ካየናቸው ቢያንስ ከአራት በላይ ሱቆች የበፊቱን አይነት ሽፋን ያለው ማግኘት ነበረብን። ምናልባት በጣም አልፎ አልፎ ከሆነ የሚገኝ ልክ አይደለም ማለት ነው።

በነገራችን ላይ ትምህርት የሚጀመረው በመስከረም ወር መጀመሪያ ቢሆንም፤ በተለይም በገጠር አካባቢ መምህርና ተማሪ ተሟልቶ መደበኛው መማር ማስተማር የሚጀመረው ግን በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ ወይም በጥቅምት የመጀመሪያ ሳምንት ነው። ዋና ጉዳያችን እሱ ስላልሆነ፤ በዚሁ እግረ መንገድ ግን ስለደብተር ጀርባም እናውራ።

ተማሪነቴን ሳስታውሰው፤ መምህሩ ጠቃሚ ነገር (ሁሉም ጠቃሚ ቢሆንም የተለየ ያልኩትን) ሲናገር መሐል ላይ ካለው ዋናው ገጽ ይልቅ ከጀርባ ባለው ገጽ ላይ ነበር የምጽፈው። እንዲያውም ፈተና ላይ እንኳን የሚመጡት ከጀርባ የጻፍኳቸው ናቸው።

ቀድሞ የተማርኩባቸውን ደብተሮች እያገላበጥኩ ሳይ አሁን ካሉት ደብተሮች ጋር ብዙ ልዩነት አየሁባቸው። እንዳይገርማችሁ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የተማርኩበት ደብተሬ አሁን ድረስ አለ።

ደብተር በዋናነት የሚመረተው ተማሪን ታሳቢ አድርጎ ነው። ስለዚህ በደብተሩ ሽፋን ላይ የሚኖሩ ነገሮች ትልቅ ድርሻ አላቸው። ለምሳሌ ቀደም ሲል በነበሩ ደብተሮች ላይ ከፊት ለፊት ባለው ሽፋን ላይ በ2009 ዓ.ም በሞት ያጣናቸው የተረት አባት አባባ ተስፋዬ ነበሩ። አባባ ተስፋዬ ልጆች ሁሉ ሊያውቋቸው የሚገባ አባት ናቸው። ልጆችን በተረት እያስተማሩ አንጸው ያሳደጉ። እንደ እርሳቸው አይነት ታላላቅ ሰዎች መኖር ነበረባቸው።

የሚገርመው ግን በዚያው ዓመት አካባቢ ቃና ቴሌቪዥን ገና አዲስ በነበረበት በቃና ቲቪ ላይ የሚታወቁት ዛራና ቻንድራን የደብተር ሽፋን ላይ ማድረግ ተጀምሮ እንደነበር ሰምቻለሁ። የድራማውን ተወዳጅነት ማድነቅ ይቻል ይሆናል፤ ዳሩ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የደብተር ሽፋን የሚሆን ሰው ጠፍቶ ነው የውጭ ዝነኞች የምናደርግ? በእርግጥ በፊትም የውጭ ተጫዋቾች ፎቶ ያለበት ደብተር ነበር። የታዋቂ ሰዎችን ፎቶ እንተወውና ወደ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንሂድ።

በመማሪያ በደብተር ላይ ሳይንስን የሚያስተምር ምልክት መኖር አለበት። ምንም እንኳን አሁን ዘመኑ የቴክኖሎጂ ስለሆነ ማንም ሰው በቀላሉ የሚያገኛቸው ቢሆኑም፤ ታሳቢ መደረግ ያለበት ግን ልጆች የስማርት ስልኮች ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ነው።

እኔ በማስታውሰው ደብተር የፊት ሽፋን ላይ አበባ ይኖራል። የአበባ ክፍሎች ቁልጭ ብለው ይታያሉ። ተማሪዎች ደግሞ የተክሎችን አረባብ የሚማሩት በአበባ ክፍሎች ነው። ስለዚህ በቀላሉ ሁሌም በሚያዩት በደብተራቸው ላይ ሊኖር ይገባል።

በደብተሮች ላይ በዋናነት ወደታዘብኩት ነገር ስሄድ ደግሞ የደብተሩ ሽፋን ላይ ያሉ መረጃዎችን ማጣቴ ነው። አሁን ተማሪዎች የሚማሩባቸውን ብዙ ደብተሮች አየሁ። የደብተሩ ሽፋን ላይ ምንም መረጃ የለም። ልሙጥ ወረቀት ነው። ለዚያውም በጣም ስስ የሆነና በቀላሉ የሚቀደድ። የስስነቱ ነገር ዋና ትኩረቴ ባይሆን እንኳን በተማሪ ደብተር ላይ ያሉ ሳይንሳዊ መረጃዎች ለምን ቀሩ? ምናልባት ዋናው ትምህርት እንጂ በደብተሩ ላይ ያሉ መረጃዎች ተራ ነገር ይመስሉን ይሆናል፤ ግን ተራ ነገር አይደሉም። እዚያ ላይ የሚወጡ መረጃዎች ታስቦባቸው የተዘጋጁና ጠቃሚዎች ናቸው።

በተለይም ሒሳባዊ ለሆኑ ትምህርቶች ደግሞ በጣም ወሳኝ ነው። ብዙ ጊዜ የመለኪያ አሐዶች ያስፈልጋሉ። የክብደት፣ የርዝመት፣ የፈሳሽ፣ የጊዜ፣ መለኪያዎችን ከደብተር ላይ ማግኘት ለተማሪዎች ዕውቀትን ያስይዛል። ከአንዱ የመለኪያ አሃድ ወደ አንዱ ለመቀየር የግድ መታወቅ አለበት። ለምሳሌ ከኪሎሜትር ወደ ሜትር ወይም ከሜትር ወደ ኪሎ ሜትር መቀየር የሚያስፈልገው ቀመር ይኖራል። ይህን ለማወቅ አንድ ኪሎ ሜትር ስንት ሜትር እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። ይህ ቀላል ምሳሌ ነው ያነሳሁት። በደብተር ጀርባ ላይ ከባድ ስሌት የሚጠይቁ ክፍልፋዮችም ስለሚቀመጡ በቀላሉ ለማወቅ ያግዛል።

የኬሚስትሪ ትምህርት ላይ አንድ የንጥረ ነገሮች ሰንጠረዥ አለ። ሰንጠረዡ በእያንዳንዱ ዓምድ ላይ የየራሳቸው ባሕሪ ያላቸው ንጥረ ነገሮችን ነው የያዘው። በዚህ ውስጥ የንጥረ ነገሮች ክብደት፣ የስማቸው ውክል፣ አቶማዊ ቁጥራቸው መታወቅ አለበት። ይህን የያዘ ሰንጠረዥ በቀላሉ ደብተር ላይ መገኘት አለበት። ምንም እንኳን የመማሪያ መጽሐፍ ላይ ቢኖርም ደብተር ደግሞ ከመጽሐፍ ይቀላል፤ ሁልግዜም ከተማሪው እጅ ላይ ይገኛል።

ከደብተር ጀርባ ላይ ያሉ መረጃዎች ሒሳባዊ ቀመሮች ብቻ አይደሉም። የባዮሎጂ (ሥነ ሕይወት) ትምህርትን የሚያሳዩም አሉ። ለምሳሌ የደም ዝውውር ሥርዓትን ለማሳየት፤ የደም ቧንቧዎችን ስም፣ የልብ ክፍሎችን ስም፣ ሳንባን የያዘ ምስል ከደብተር ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ። ተማሪዎች የእያንዳንዱን የአካል ክፍል ከነስማቸው በቀላሉ ደብተር ላይ ሲያገኙት ለማስታወስ ያግዛቸዋል።

ለመሆኑ ግን እነዚህን ነገሮች በደብተር ሽፋን ላይ ማድረግ ምኑ አስቸግሮ ይሆን የተተውት? የደብተሩ ስስ መሆን ምናልባትም ለቢዝነስ ይሆናል። ምናልባት ግን የማላውቅው ሆኖ እንጂ እነዚያን ሳይንሳዊ መረጃዎች ለማስቀመጥ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሆኖም ይሆናል። መቼም የደብተሩ አምራች ከዕውቀት ገንዘብ ይበልጥበታል። ግን ገዢዎች ለምን ይህን ይገዛሉ? ታዲያ ያልተመረተውን ከየት ያመጡታል? ዋናው ጥያቄ ይህ ነው! ጉዳዩን ለወላጅም ይሁን ለአምራቹ ለሚመለከተው አካል ልተወውና በራሴ ትዝታ ነው የምሰናበታችሁ።

ያቺን ባለ 16 ቅጠል ደብተር ታውቋታላችሁ አይደል? የዛሬ ዋጋዋን ባላውቅም ‹‹የ50 ሳንቲም ደብተር›› እያልን ነበር የምንጠራት። ዛሬ እኮ 20 ብር ሆና ይሆናል (ሲጀመር አለች እንዴ ግን?) ይቺን ደብተር የማስታውሳት በተለይም ከ4ኛ ክፍል በታች ነው። ደብተሯም የአንድ የትምህርት አይነት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ይጻፍባት ነበር። ለማባዛት የሂሳብ ስሌት ግልግል ነበረች። ከጀርባ በኩል ከ1 እስከ 12 ያሉ ቁጥሮችን ብዜትን የያዘች ነበረች። ሲጀመር ያኔ ራሴ ማባዛት ሁሉ እችል ነበር። ዛሬ ግን ሻይ ጠጥቼ እንኳን ለማስላት ስልኬን ነው የማወጣ።

ምናልባት ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ተማሪዎች እነዚያን መረጃዎች በቀላሉ ከስልካቸው ላይ ያገኙ ይሆናል። ዳሩ ግን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በታች ያሉ ተማሪዎች ስማርት ስልክ ከሚጠቀሙ በወረቀት የተሻለ ይሆናል። በዚያ ላይ ምን ያህል ወላጅ ለልጆቹ ስማርት ስልክ መግዛት ይችላል? በሌላ በኩል ከቴክሎኖጂ ጋር እንዲተዋወቁ ቢያግዝም በልጅነት አዕምሮ ሊያቦዝናቸውም ይችላል። በደብተር እስከተማሩ ድረስ ሳይንሳዊ መረጃዎች ቢኖሩ ግን የተሻለ ነው።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You