የባሕር በር ጥያቄ ሁለንተናዊ ፋይዳዎች

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገቷን ለማፋጠን በአደባባይ የማይነሳ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ ባለፉት አራት ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ እያነሳች ትገኛለች:: የባሕር በር እና የወደብ አስፈላጊነት እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሰፊ የቆዳ ስፋትና ብዙ ሕዝብ ላላት ሀገር ቁልፍ ጥያቄ ነው::

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ወገኔ ማርቆስ (ዶ/ር)፣ የባሕር በር ከፍተኛ የወጪና ገቢ ንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር የንግድ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችል ወሳኝ መተላለፊያ መንገድ መሆኑን ይናገራሉ:: ወገኔ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ከዚህ አንጻር የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚዎች ናቸው:: የባሕር በር ያላቸው ሀገራት የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት ይልቅ የምርቶቻቸው ዋጋ አነስተኛ ስለሚሆን ምርታቸው በዓለም ገበያ ተመራጭ ይሆንላቸዋል::

የባሕር በር ያላቸው ሀገራት በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና በሌሎችም ዘርፎችም ያደጉ ይሆናሉ:: ከዚህም ባሻገር ወደ ውጭ የሚልኩትንም ሆነ ወደ ሀገር የሚያስገቧቸውን ምርቶች፣ መሣሪያዎች እና የተለያዩ ግብዓቶች ሚስጥራዊነታቸውን ከሶስተኛ ወገን በተጠበቀ ሁኔታ መላክና ማስገባት ያስችላቸዋል ነው ያሉት::

የባሕር በር አለመኖር ብሎም ወደብን በከፍተኛ ወጪ መከራየት የሀገር ውስጥ ምርት መጠንን፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጫን መሆኑ ላይ የሚያሰምሩበት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፣ ጫናው በሀገር ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች ሁሉ ላይ የሚያርፍ ነው ይላሉ::

በ2003 ዓ.ም በያዕቆብ ኃይለማርያም የተጻፈው አሰብ የማናት (የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ) መጽሐፍም እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆኑ ሀገሮች ከዋና ዋና የገበያ ማዕከሎች የተገለሉና ከገበያ የራቁ መሆናቸውን አንስቶ፣ ወደብ አልባነት ለኢኮኖሚያዊ እድገታቸው ማነቆ እንደሆነባቸው ይገልጻል:: ወደብ አልባ በመሆን ብቻ የአንድ ሀገር የወጪ ንግድ መጠን ከ33 ከመቶ እስከ 43 ከመቶ ሊቀንስ እንደሚችልም ያስረዳል::

ለአንድ ሀገር ልማት አስፈላጊ ከሆኑ ዋነኞቹ ግብዓች መካከል አንዱ ከውጭ ወደ ሀገር የሚገባውና በሥራ ላይ የሚውለው ገንዘብ የውጭ ምንዛሪ መሆኑን የሚጠቅሰው መጸሐፉ፤ አንዲት ሀገር ይህን አስፈላጊ ግብዓት ማግኘት የምትችለው የምታመርተውን ምርት ወደ ዓለም ገበያ ማዝለቅ ስትችል መሆኑን ያነሳል:: ወደብ ደግሞ ለዚህ ወሳኙ ድልድይ መሆኑን በማስረዳት፣ ወደብ አልባነትም ሆነ ከወደብ የራቀ ሀገር መሆን የሀገር ምርትን በቀላሉ ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብና አስፈላጊውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አሉታዊ ተጽዕኖን የሚያሳድር መሆኑን ያብራራል::

አቶ አያል ሰው ደሴ ከዛሬ 14 ዓመታት በፊት “የባሕር በር ጥያቄ ከኢትዮጵያ አንድነት፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ ከፀጥታ፣ ከልማትና እድገት ዋስትናነት አኳያ” በሚል ርዕስ ባስነበቡት መጣጥፋቸው፣ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የባሕር በር አስፈላጊነትን የሚያዩት ከንግድ እንቅስቃሴ መተላለፊያት ባለፈ የቆየ ታካቸውን፣ ያሉብን አስቸጋሪና ፈታኝ አካባቢያዊ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ከውጭ ለሚሰነዘር ጥቃትና ቀጥተኛ የእጅ አዙር የባዕዳን ጫና መጋለጥን፣ ከሀገራቸው አንድነት፣ ከአስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት፣ ከምጣኔ ሀብት እድገትና ብልጽግና እንዲሁም ከወደፊት ትውልዶች ዘለቄታዊ ጥቅም አኳያ በማየትና በማገናዘብ መሆኑን አስረድተዋል::

ከዘርፈ ብዙ ጠቀሜታው አኳያ የባሕር በር ጥያቄን አጠናክሮ መቀጠል ለነገ የማይባል መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑ ላይ አጽንዖት ሰጥተው የሚናገሩት ወገኔ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ እያነሳች ያለችው የባሕር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሠረት ያደረገ መሆኑ ላይ ያሰምሩበታል:: በተጨባጭም ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ ባለው የባሕር በር ተጠቃሚ ብትሆን ለጎረቤት ሀገራት መልካም እድልን የሚፈጥር ነው ያሉት ዶ/ሩ::

አንዲት ሀገር የባሕር በር ተጠቃሚ ስትሆን እንደ መንገድ፣ የኃይል አቅርቦትና መሠል የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ታካሂዳለች፣ የንግድ ልውውጥ እንቅስቃሴም ይጨምራል፤ የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅም መልካም እድልን እንደሚፈጥር ይናገራሉ::

እርሳቸው እንዳብራሩት፣ በሀገራት ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ላይ የተደረጉ ጥናቶች የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ለጎረቤት ሀገራት ማደግ ድርሻ እንዳለው ያነሳሉ:: የአንዲት ሀገር ሠላም ማጣት በጎረቤት ሀገራት የሠላም ሁኔታ ላይ አሉታዊ ጫናን እንደሚያሳርፈው ሁሉ አንዲት ሀገር የባሕር በር ተጠቃሚ በመሆኗ የሚኖራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በጎረቤቿ እድገት ላይ በጎ ሚና ይኖረዋል::

ወገኔ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በሀገራችን ማደግና መበልጸግ ላይ መልካም አመለካከት የሌላቸውና ሕዝባቸውን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምራት የተሳናቸው ሀገራት የሌለው እድገት ስጋት ውስጥ ይከታቸዋል ያሉት ምሁሩ፣ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን በመሥራት እንዲህ ያሉ ሀገራት ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግር አስቀድሞ መከላከል ያሻል::

በተለይም መንግሥት ውጤታማ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን መሥራት፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ታሪካዊ ዳራዎችን ማስረዳት ከቻለ፣ ፀጥታን ማጠናከር ከሚችል ጠንካራ ኃይል ጋር በመሆን ሀገራችን እንዳትለማና የባሕር በር ተጠቃሚ እንዳትሆን እንቅፋት ሊሆኑ የሚጥሩ ኃይሎችን ወደ ኋላ መመለስ ይቻላል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ::

የባሕር በር ጥያቄ ስኬት እስኪያገኝ ድረስ በጋራ የምንታገልለት ፍሬውንም ለትውልድ የሚሆን ጥያቄ እንጂ የመንግሥት ጉዳይ ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ያሉት ምሁሩ፣ የባሕር በር ተጠቃሚነት የሚያተርፍልን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በአጭር ጊዜም ይሁን በረጅም ጊዜ እያንዳንዱ ዜጋ ላይ ለውጥ የሚመጣ መሆኑን እንደ ሕዝብ ግንዛቤው ሊኖረን፤ ለስኬቱም በባለቤትነት ልንታገል ይገባልም ሲሉ መልዕክታቸው አስተላልፈዋል::

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You