ለበርካታ አሥርት ዓመታት በአገራችን በተለያዩ የርዕዮተ ዓለምና ምናባዊ ቅርፆች ሲንገታገት የቆየው የዴሞክራሲ የፍትህ የእኩልነትና የነፃነት ትግል አሁን ካለበት ተስፋን ከሰነቀና ስጋትን ከቋጠረ እርከን ላይ ደርሷል። ይህንን ትግል እዚህ ደረጃ ላይ ለማድረስ ደግሞ በተለያዩ ወቅቶችና የትግል ሜዳዎች ወጣቶች፣ አዛውንት፣ ገበሬዎች፤ ሰራተኞች በጥቅሉ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ወገኖቻችን ከህይወት እስከ አካል መጉደል ከግርፋት እስከ ስደት የሚደርስ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለዋል።
የተከፈለው መስዋዕትነትና በዚህም ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ፈተናዎች ተደምረውና በትውልድ ድምፅ ታጅበው ከግብ እናደርሰው ዘንድ ይጣራሉ፤ ይሞግቱናልም። ይህ ጥሪ ሁላችንም የዚህች አገር ጉዳይ ያገባናል የምንል ሁሉ ቀበቶአችንንና መቀነቶቻችንን አጥብቀን እንድንነሳ የሚጋብዝ ሲሆን ትግሉን ከግብ ለማድረስ ደግሞ የትግሉን ውስብስብነትና የተጋረጡብንን ፈተናዎች በሚገባ ነቅሶ ማውጣትና ተገቢ ስልት መቀየስ በእጅጉ ጠቃሚ ይመስላል።
በደስታ እና በተስፋ የተቀበልነው ለውጥ እየተውገረገረም ቢሆን የዓመት ከመንፈቅ እድሜ አስቆጥሯል። ዛሬ ያ ደስታችን በበርካታ አስደንጋጭ ክስተቶች ተውጧል። ተስፋችንን የሚያጨልሙ በርካታ ህገወጥ ክስተቶች ሲከናወኑ ማየታችን የነበረንን ደስታ እንድንረሳ አድርጎናል። ከመጀመሪያውም በለውጡ ላይ ደስተኛ ያልነበሩም ሆነ ተስፋ ያላደረጉ ሰዎች የተመኙት ወይም የፈሩት የደረሰ መሆኑን ለማሳየት ንግግራቸውም ሆነ ምልከታቸው ‘እንደተመኘኋት አገኘኋት’ የሚለውን ዘፈን የሚያቀነቀኑ አስመስሏቸዋል። በጎ ተመኝተው፣ ተስፋ አድርገው እና ለውጡን በሚችሉት መንገድ ሁሉ ደግፈው አመድ አፋሽ የሆኑ የመሰላቸው ደግሞ የተጎጂነት ስሜት ተሰምቷቸው እዮዮውን ተያይዘውታል። አሁንም በለውጡ ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ያልቆረጡ ብዙዎች ቢጨልምም ይነጋል በሚል እምነት መንግሥትን መወትወት እና ችግሮቹን እንዲያስተካክል ማሳሰባቸውን ቀጥለዋል።
በተለይ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት በክልልና በፌዴራል ደረጃ ህዝብና መንግሥትን ሲያገለግሉ የነበሩ የህዝብ ልጆች የተሰውበት፣መላው ኢትዮጵያውያንን ሀዘንና ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ጥቁር ቀን ሆኖ ሲታወስ ይኖራል። ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በአንፃራዊነት ባገኙት ነፃነትና አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ወደ ቀጣዩ ምእራፍ ለመሻገር ደፋ ቀና እያሉ ያሉበት፣በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችም ለውጡን ለማሻገር በየዘርፋቸው እየደከሙ ባሉበት አጋጣሚ የተፈጠረ መጥፎ የታሪክ እውነት ሆኖ ተመዝግቧል።
በመላው ህብረተሰብ የተወገዘው ድርጊቱ በአገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ አሰላለፍ ያደረሰው ጉዳትም ቀላል የሚባል አይደለም። ይህ ድርጊት ሀሳብን ወደ ጠረጴዛ አምጥቶ ለመወያየት በማይቸግርበት ስለፖለቲካና ስለአገራዊ ሁኔታ ከወትሮው በተለየ ህዝቡ የራሱን አማራጭ ለመውሰድ የሚያስችል ንቃተ ህሊና ባዳበረበት ጊዜ መፈፀሙ እጅግ አሳዛኝ ያደርገዋል።
አንፃራዊ በሆነ መልኩ የፖለቲካ ምህዳሩ በሰፋበት በአሁኑ ወቅት ጉዳዮቻችንን ለምን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን መወያየት አቃተን ? ከውይይት ይልቅ ለምን ጉልበት መጠቀምን የመጀመሪያ ምርጫችን አደረግን? የፖለቲካ ትግላችን ከጉልበት ወጥቶ በውይይትና በሃሳብ የበላይነት ማመን ለምን አቃተው? የሚሉትን አንኳር ጥያቄዎች በማንሳት እየታዩ ያሉ ችግሮች መንስኤና መፍትሄ ለመጠቆም ውይይት ማድረግ ይመለከተናል ከሚሉ ዜጎች በተለይም ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው።
እኛም የውይይቱ ውጤት በለውጡ ሂደት ላይ የሚያስከትለውን ጫና በመቀነስ ለአገራዊ ለውጡ ስኬታማነት ይረዳ ዘንድ የፖለቲካ ሳይንስ፣የህግና የታሪክ ምሁራንን፣ የሃይማኖት መምህራንና ሰባኪያን ጋር ውይይት አድርገናል።
መወያየትና በሰከነ መንፈስ መነጋገር በሂደቱም የሀሳብ የበላይነትን ማክበር የሰለጠነ ማህበረሰብ አንዱ መገለጫ ከመሆኑ ባሻገር ህዝቦች የተለያየ ሀሳብ፣እምነት እና አቋም ቢኖራቸውም እንኳ ተከባብረው በሰላም እንዲኖሩ አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ያወሳሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖታዊ፣ፖለቲካዊ፣ክልላዊ እና ሌሎች ማንነቶችን ተሻግሮ አብሮ የሚኖር ህዝብ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም ታምራት ሀዘን ደስታውን እየተጋራ አብሮ መኖር የሚችል ህዝብ መሆኑን ይመሰክራሉ።
እንደባለሙያው ገለፃ ችግሩ በውስን ፖለቲከኞቻችን የሚመጣ በመሆኑ ነገሮችን መሻገር ካለብን ትላንት ጥቁር ነገር ያመጡብንን ምርጫዎችና ውሳኔዎች፣ተደጋግመው የተነገሩ አሳሳች ትርክቶችን በግልፅ ማውገዝ አለብን። ትርክቶቹ ሰዎች ለሚፈልጉት የፖለቲካ ግብ ብዙሀኑን ማነሳሻ ተጠቅመውበታል። ከወንድማማችነትና ከአብሮነት ይልቅ ጥላቻ ተሰብኳል፤ጥላቻው ሲሰበክ በሌሎች ተጨባጭ ማስረጃዎች ሳይደገፍ ነው። የፌዴራል የመንግሥት አስተዳደር ስርዓት ልዩነቶችን አቻችሎ ለመኖር የተቀረፀ ስርዓት ነው። ልዩነት ማለት በአንድ ቀጭን ክር ውስጥ በርካቶች አብረው የሚገኙበት መስመር በመሆኑ ክሩ እንዳይበጠስ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም መሆን አለበት። ክሩ እንዲበጠስ የሚያደርገው የጥላቻ ትርክት ነው።
የጥላቻ ትርክት መዘዙ ብዙ በመሆኑ ሰዎች በውይይት እንዳያምኑ የማስገደድ ባህሪ አለው የሚሉት አቶ ኤፍሬም ሰኔ 15 በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ግድያ ከመፈፀሙ በፊት ግለሰቦች ተነጥለው የጥላቻ ንግግር በማህበራዊ ሚዲያዎች ይካሄድባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የጥላቻ ንግግር በሩዋንዳ እና በዩጎዝላቪያ ያደረሰው እልቂት ትልቁ ማሳያ መሆን ይችላል። በሩዋንዳ ግጭት ጊዜ ሁቱዎቹ ቱትሲዎቹን በረሮዎች ‹‹ኮክሮች›› ይሏቸው ነበር። ልክ በረሮን በቀላሉ በነጠላጫማ እንደምትገድለው ሁሉ ሰውን መግደል ቀላል ሆኖ ነበር።
ዩጎዝላቪያ ውስጥ ሰርቮች ‹‹ እኛ ለዚች አገር እንደዚህ ሆነን፣ እንደዚህ አድርገን ነገር ግን ሌሎቹ በለጡን›› በሚል የጥላቻ ስሜት መሳሪያ በእጃችው ስለነበር ሌሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ፈፀሙ። ዩጎዝላቪያ አስቀድማ በሰው ልብ ውስጥ ፈርሳ ስለነበር በእውን ለመፍረስ ጊዜ አልወሰደባትም። አንዱ ሰርቭ ጎረቤቱን ክሮዋት መግደል ጉንዳን እንደመግደል ቆጥሮ በቀላሉ ይገል ነበር። እነዚህ ሁለት ክስተቶች በጥላቻ ትርክት ምክንያት ከጂውሽ እልቂት በኋላ ዓለም በታሪኳ አይታ የማታውቀው እልቂት ሆኖ ተመዘገበ።
በአገራችንም በማህበራዊ ሚዲያ የሚተረከው የጥላቻ ትርክት ተገቢ አካሄድ እንዳይደለ በርካቶች ያምናሉ። እንደ አገራችን ሁሉ በዓለማችን በርካታ አገሮች የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተከታይ ናቸው። በሁሉም አገራት ያሉ ህዝቦች ተከባብረው ሲኖሩ የሚያስተሳስራቸው ደግሞ ህግ ነው። ህግን እንደመሸጋገሪያ ድልድይ ይጠቀሙበታል። በሺህ የሚቆጠር ሰራዊትን የሚያዘውም፣ሚሳኤል የሚያስተኩሰውም፣የአገራቱን የመጨረሻ የስልጣን እርከን የያዘውም ከህግ በታች ነው።
ሌሎች አገሮች መሳሪያን ለእኩይ ነገር በፍፁም አይጠቀምበትም። አቶ ኤፍሬም እንዳሉት በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ውስን ፖለቲከኞቻችን ተከታዮቻቸውን ሲቀሰቅሱ ጥላቻን መሰረት አድርገው በመሆኑ ጥፋት እንዲወለድ ተደርጓል። ነገር ግን የተገደሉትን ባለስልጣኖች የመግደል መነሻ ምክንያት ባይገኝለትም ሞታቸው ይበልጥ ያሳዘነን ነገ ወደ ሁላችንም ቤት የሚዘልቅ እንደሆነ ስናስብ ነው። ነገ በሌሎች ላይ መሰል ጥቃት ቢደርስ ‹‹መንግስት የለም›› የሚል መንፈስ እያደገ ስለሚመጣ አደጋውን ያከብደዋል።
በመሆኑም ሰዎች በሃይማኖታዊ እሴት እንደሚተሳሰሩ ሁሉ በፍትህ የሚያምን ፍትሀዊ ማህበረሰብን መገንባት ያስፈልጋል። በቋሚነት ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ገንብተው የሚኖሩ አገሮች አሁን ለደረሱበት ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት ፍትህን በማስፈን እና በህግ የበላይነት በማመን ነው። የህግ የበላይነት ስልጣን የመያዣ መንገድንም ይጨምራል። ተከባብረን እንድንኖር፣ የየእለት ተግባራችንን ለመከወን፣ በባለቤትነት በምናስተዳድረው የንግድ ድርጅት ወይም በመኖሪያ ቤታችን አካባቢ ሰላም የሚሰፍነው በህግ ነው። የጥላቻ ትርክቶችን በማስወገድ ጥፋት የሚያጠፋው ህግ መኖሩን አውቆ እጁን እንዲሰበስብ ህግን ማስከበር ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ የህግ ባለሙያው ያስረዳሉ።
መምህር መስፍን ሰለሞንም በአቶ ኤፍሬም ሀሳብ ይስማማሉ። እሳቸው እንደሚሉት የመጣንበትን መንገድን ‹‹ሁሉን ነገር በጉልበት መፈፀምን አንደግምም›› እያልን ፍትህ ሲጓደል መንግሥት ጣልቃ ካልገባ መተማመን አይችልም። ለዚህ አቋማቸውም ማጠናከሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹ንጉስን ተማምኖ ሰው እንቅልፉን ይተኛል›› ብሎ የተናገረውን ሀሳብ ያነሳሉ። ከቦታ ቦታ የምንንቀሳቀሰው፤ገንዘባችንን ባንክ የምናስቀምጠው፣የምንተኛውም ጭምር መንግሥትን አምነን በመሆኑ መንግሥት ፍትህን በአግባቡ ማስከበር ካልቻለ መተማመን እየጠፋ ይመጣል።
መተማመን ሲጠፋ ደግሞ ሥርዓት አልበኝነት ይወለዳል። መንግሥትም ፍትህን ሲያጓድል ከታየ ፍርድ በራስ ወደ መስጠት ይገባል። ይህም ማለት መንግሥት በሚሰጠው ፍትህ አላረካም ማለት ነው። እንቅፋት ወደፊት እንጂ ወደኋላ ጥሎ አያቅም የሚሉት መምህር መስፍን ፍትህ አስፈላጊ ነገር በመሆኑ እንቅፋቶቻችንን ማጥፋት አለብን ይላሉ። ህጎቻችን በጣም ይታዩ፣ በደንብ ይታደሱ፣ እንፍራቸው፣ህግ የሚፈራ ማህበረሰብ መፍጠር ግድ የሚል ጉዳይ እንደሆነ ያወሳሉ።
የእንግሊዞች ትልቁ ሀብታቸው በህግ የታነፀ ማህበረሰብ ነው። ሁሉንም ነገር ለህግ አሳልፎ የሚሰጥ ማህበረሰብ አላቸው። እንደዚህ አይነቱን መልካም ነገር ኢትዮጵያውያን መማር አለብን። ፍትህ ከሌለ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍቅር፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ ነገር ሁሉ አይኖርም ብቻ ሳይሆን ገደል ይገባሉ። ምክንያቱም ፍትህ እየተጓደለ ሲመጣ ‹‹እኔ ግዙፍ፣ ሀይለኛ ነኝ›› ብሎ የምናመልክበት ቦታ ሊያሳጣንም ሆነ በህይወት ሊያጠፋን የሚመጣ አካል ሊኖር ይችላል።
አሁን ያለው መንግሥት ለመምህር መስፍን እንደደመራ ሆኖ ታይቷቸዋል። ከተለያዩ ቦታዎች ደመራውን የሚበሉ ችቦዎች እየመጡበት ነው። አባቶቻችን «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ከመጣ መጥፎ ነው» እንዲሉ አንዱ ችግር ሳይፈታ ሌላ ችግር ሲፈጠር አደገኛ ነው። መንግሥት ችቦዎቹ በልተውት ሳይወድቅ እና ወደባሰ ቀውስ ሳንገባ መፍትሄ ማፈላለግ ግድ ይላል። ባለፈው አንድ ዓመት ከምናምን ነገሮች ሁሉ እያደጉ ነው የመጡት። ነገ መንግሥት አልባ እንዳንሆን ፖለቲከኞችም በሰከነ መንፈስ፣ ወደ ልባቸው ተመልሰው ፍትህ ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ፍትህ በሁሉም ዘንድ የሚከበርና ለሁሉም እኩል የሚያገለግል ሲሆን ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህላችንን ያሳድጋል። አገልጋይ ዮናታን አክሊሉም በአገራችን እየታዩ ያሉትን ነገሮችን በጉልበትና በኃይል የማስፈፀም ችግሮችን ለመሻገር መንግሥት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ ፍትህን ማስጠበቅ መቻል አለበት ብለው ያምናሉ። በእርግጥ መንግሥት ለሁሉም ቀና ሆኖ ሁሉንም ማስደሰት ሁሉንም ማስከፋት አይችልም። አይደለም ጭቃ ሹም በሆነው በሰው ሥርዓት ዓለም ውስጥ ቀርቶ በፈጣሪ እንኳ እግዚአብሄር ከቅኖች ጋር ቅን ከጠማሞች ጋር ጠማማ ነው።
ሰማይ ላይ አንድ ፀሐይ ሆኖ በጭቃው ላይ መድረቅን፤ በቅቤው ላይ መቅለጥን ያሳያል ያደርጋልም። አሁን ያለው አንድ መንግሥት አንድ ሥርዓት ነው። ከዚህ እውነት፣ ፍትህ፣ መሰረታዊ ነጥቦች ውጪ በአሉታዊ የሚመጣው የማይቆምበት፣ የማይደርቅበት፣ የማይረግፍበት መሆን የለበትም። ስለዚህ ይህንን መንግሥት ተረድቶ ፍትህን ማስጠበቅ መቻል አለበት። መንግሥት በቀጥታ ወደ ድርጊት፣ወደ ተለያዩ ውሳኔዎች ለመግባት ወደኋላ ያለበት ምክንያት ብዙዎች ይረዱታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ህልሙ ብቻ ሳይሆን ጥያቄው ራሱ የጠፋበት ስለሚመስል የለውጡ እንቅስቃሴ እየፈለገ ያለው መልሱን ብቻ ሳይሆን ጥያቄውን ጭምር እንደሆነ አንስተዋል።
ለዚህም ይመስላል አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያስቆጠረው የአገራችን ለውጥ እንቅፋቶች የበዙበት። ለውጥ ያለእንቅስቃሴ አይመጣም። እንቅስቃሴ ካለ ሰበቃ አለ። ይሄ ሰበቃ የሚያመጣው ህመም አለ። ሴት ልጅ ስትፀንስ የሆርሞን መበጥበጥ ይከሰትባታል። ፅንሱ እስከሚረጋጋ የመወለጃ ወሯ እስከሚደርስ ድረስ እግሯ፣እጇ ያብጣል፣ያቅለሸልሻታል፣ወደ ላይ ወደላይ ይላታል። ነገር ግን የሆርሞን መበጥበጥ፣ወደላይ ወደላይ የሚለው ምልክት ተጠልቶ ፅንስ መጨናገፍ አለበት አይባልም። ማህበረሰቡ መረዳት መቻል አለበት።
ማህበረሰቡ የመጣው አዲሱ ለውጥ እግር አውጥቶ እጅ አውጥቶ ወደተሸላ የኢትዮጵያ ምእራፍ እንዲወስድ እንዲሸጋገር ትእግስትን ማሳየት መቻል አለበት። ትዕግስቱ በሚለዋወጥ ሁኔታ ውስጥ የማይለዋወጥ ትርጉም መያዝ መቻል አለበት። አሁን ወርቅ ነው ያልነውን በኋላ ጨርቅ፣አንበሳ ብለን ያሞገስነውን ሬሳ ነው ሳንል ተመሳሳይ የሆነ ነገር ይዘን መቀጠል መቻል አለብን።
ሁኔታዎችን በብዙ አቅጣጫ መመልከትና መረዳት ያስፈልጋል። አንድ ሰው ለሚስቱ ባል፣ ለልጁ አባት፣ ለእናቱ ልጅ በመሆኑ አንዱን ሰው በብዙ ሁኔታ መግለፅ ይቻላል። ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያውያን ይህን ሁኔታ እየተረዱበት ያለው መነፅር ትክክል አይመስልም። ሰሜን ያቅለሸልሸዋል፣ ደቡብ ወደላይ ወደላይ ይለዋል፣ ማዕከል ላይ ደግሞ ይቆርጠዋል ምክንያቱም የመጣው ለውጥ ለአዲስ ነገር ለአዲስ ህይወት ምልክት ነው። ይህንን መረዳት መቻል የኢትዮጵያውያን ኃላፊነት እንደሆነ አገልጋይ ዮናታን ያብራራሉ።
ልጅ ሲወለድ ከደም ከቆሻሻ ጋር ነው። አቅፈን የሳምናቸው ልጆች ነርሷ የጠረገቻቸውንና ያጠበቻቸውን ልጆች ናቸው። አንድ አዲስ ነገር ሲመጣ ከሌላ ባእድ ነገር ጋር የሚመጣ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይህንን ስንረዳ አዲስ መጪውን ነገር የወደደው ያጥበዋል፣ ያቅፈዋል፣የጠላው ያንቀዋል። በአገራችን የመጣውን አዲስ ለውጥ፣ አዲስ አመለካከትና ፍልስፍና ጥቂቶች ለማነቅ ሲሯሯጡ ታይተዋል። አዋጪው አካሄድ ግን ለውጡን ከማነቅ ይልቅ በማጠብ ተቀፅላ ጎጂ ነገሮቹን በማስወገድ ይህን የሽግግር ጊዜ በውይይትና በመነጋገር ማለፍ እንዳለብን አገልጋይ ዮናታን ይመክራሉ።
ነገር ግን አሁን ላይ ከመወያየት ይልቅ መወዛገብን፣ ከመዋደድ ይልቅ መጠላላትን፣ከሃሳብ የበላይነት ይልቅ መሳሪያ መማዘዝን ቅድሚያ የመስጠት ዋንኛ ችግር ሆኖ የተጋረጠብን ትላንትን እየኖርን ዛሬን እየረሳን በመሄዳችን መሆኑን ደግሞ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ያወሳል። ስለትላንት ብቻ እያሰብን፣ያን የጠፋውን ጨለማውን፣ ጥቁሩን፣መጥፎውን ብቻ እያሰብን ዛሬን እረስተናል። ወይም ያልመጣውን ነገን እየሰጋን ዛሬን እያሳለፍን ነው ያለነው። ዛሬአችን እየተበላሸ በመሆኑ ቆም ብለን ማየት አለብን። ያልመጣውን ነገ ያለፈውን ትላንት እያሰብን ዛሬን እያበላሸን ከሄድን ታሪካችንም ነጋችንም ሁሉም የተበላሸ ይሆናል። የጠፋ ታሪክ አለ ከተባለ ምናልባት ሌሎች የሰሩት ጥፋት ካለ እንኳ እኛ የዛ ታሪክ አካል አይደለንም።
በጠፋው ጥፋት ይታዘናል፤አሁንያለው ትውልድ የሚወቃቀስበት፣የሚጠፋፋበት ድርጊት ግን አይደለም። ዛሬ መስራት ያለብን ታሪክ እንዳይደገም ነው ። እንዲህ ስናደርግ ነገን የተሻለ ማድረግ እንችላለን። ዛሬ ያልሰራነው መልካም ነገር ነገ አይጠብቀንም። ዛሬ ያልተከልነው መልካም ዘር ነገ አይበቅልም።
መልካም ዘር ለመዝራት ብሎም ለነገው ትውልድ የተሻለች ዴሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት መሰረት የሚሆነውን አዲሱ ለውጥ የማገዝ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆን አለበት ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም ለሁሉም እኩል የሆነች ዴሞክራሲያዊ አገር እንዳትኖረው የሚፈልግ /ከአገር የተለየ ችግር የገጠመው ወይም ጤነኛ አስተሳሰብ ከሌለው ግለሰብ ውጪ/ ሌላ ዜጋ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ከዚህ አንፃር ኡስታዝ አቡበከር እንደሚሉት ለውጥ የሚጀምረው ከሁሉም ሰው ዛሬ ነው። የተሻለ መሪ ስንፈልግ የተሻለ ተመሪዎች መሆን አለብን። ችግሮቻችን ቆም ብለን ራሳችንን ባለማየታችን የመጡ ናቸው።
አሁን ያለነው ዜጎች መልካም ነገር እንዲመጣ ምን እያበረከትን እንደሆነ ማሰላሰል አለብን። ነገአችንን እያበላሸን ለትውልዱ ነገ እንዳይኖረው እያጠፋን ያለነው እኛ በመሆናችን መነጋገር መቻል አለብን። የሀሳብ ልዩነቶቻችን፣ የሀሳብ አሸናፊነት ዛሬ ተፈራርተናል። ሰው ሀሳብን፣ ዘርን፣ ሁሉን ነገር ፈርቷል። ፍርሀታችንን ደግሞ የምንገልፀው በሌላ መገለጫ ነው። ፍርሀታችንን ለመደበቅ ጀግና ለመሆን እንሞክራለን። ይህ ጀግንነት አይደለም። እራሳችንን መመልከት ባለመቻላችን ማሸነፍ በሚገባን ነገር እየወደቅን ነው። ክፍተታችንን እየተመለከትን መጓዝ አለብን።
አሁን የተፈጠረው ነገር ትላንት የቆምንበትን ማሳያ ነው። አሁንም እንዳይደገም ማሰብ አለብን። ትላንትናውና ዛሬው አንድ የሆነበት ሰው እንደ እሱ መጥፎ ሰው የለም ይባላል። ነገው ከዛሬው የተበላሸበት ሰው ደግሞ እንደእሱ የተረገመ ሰው የለም። ቢያንስ ነገ ከዛሬ የተሻለ፣ ዛሬ ደግሞ ከትላንት የተሻለ መሆን አለበት። ለዚህም የውይይት፣የመነጋገር ባህላችንን ማሳደግ ግድ እንደሚለን ኡስታዙ ይመክራሉ።
በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ የመወያየትና ለችግሮች መፍትሄ የማፈላለግ ባህል አለመኖር አሊያም አለማደግ የለውጡ ዋነኛ ተግዳሮት እንደሆነ የሚሞግቱ እንዳሉ ሁሉ የአገሪቱን የፀጥታና ደህንነት መዋቅር መላላት ወይም ጠንካራ አለመሆንን በአገሪቱ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መንስኤ አድርገው የሚያነሱም አሉ። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪው ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም በ1970ዎቹ በተፈሪ በንቲና በጄነራል አማን አብዶ ላይ በተመሳሳይ በመኖሪያ ቤታቸውና በቢሯቸው የተፈፀመባቸውን ግድያ አንስተው በአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዐረ መኮንን የተደረገው ግድያ ከዘመኑ ጋር የማይመጥን አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን ይገልፃሉ።
የታሪክ ምሁሩ በ1970ዎቹ የተፈጠረው ድርጊት ሥርዓቱ አምባገነን በመሆኑ የተፈጠረ ሲሆን በዚህ አመት የተፈፀመው ደግሞ በመንግስት የደህንነትና የፀጥታ መዋቅር ክፍተት የተከሰተ ነው ይሉታል። ለዚህ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ ‹‹ የሀገሪቱን ጦር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም እና የአንድ ክልል ፕረዚዳንት መግደል ትልቅ የደህንነት ችግር እንዳለ ያሳያል ›› ሲሉ ያስረዳሉ። በመሆኑም መንግሥት የፀጥታና የደህንነት መዋቅሩን ሊፈትሽ እንዲያም ሲል ሊያጠናከር ይገባል ይላሉ።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰሩ በፍቃዱ ቦጋለ ከዶክተር ቴዎድሮስ የተለየ ሀሳብ አላቸው። ፕሮፌሰር በፍቃዱ እንደሚያስረዱት የአዲሱ መንግሥት ሥርዓት ደህንነትንና ፀጥታን በማስከበር ያለው ምልከታ ለየት ያለ ነው። ሰላምንና ፀጥታን ማስከበር ማለት እንደከዚህ ቀደሙ በህዝብ ላይ ወታደር እና ፖሊስ እየተላከ ህብረተሰቡ ፀጥ እንዲል ማድረግ አይደለም። መከላከያን፣ፌዴራልን፣ ፖሊስን ወይም ደህንነትን አሰማርቶ ህዝብን ፀጥ ረጭ ማድረግ አለብን ብለን ካሰብን ትክክል አይደለም የሚሉት ፕሮፌሰሩ ሰዎችን በመግደል፣ በማሰር ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ደህንነት ማምጣት አይቻልም ይላሉ።
ከዚህ ይልቅ ግን መዋቅራዊ በሆነ መንገድ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የመንግሥትና የህብረተሰቡ ቅንጅት ዋንኛ ሚና ይኖረዋል። ከዚህ በተሻገረ ግን የተፈጠረው የግድያ ክስተት በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደተፈጠረ የፖለቲካ ምሁሩ እምነት አላቸው። አንደኛው ኢህአዴግ ውስጥ የውስጠ ፓርቲ ትግል አለመጠናከርና ሁሉም ፓርቲዎች ሃሳብን ወይም ልዩነትን ይዘው ወደ ሚመሩት ወደ ሚያስተዳድሩት ህዝብ የሚሄዱበትና በዛም ጥሩ ወዳልሆነ ሁኔታ የሚመሩበት አካሄድ መታየቱ፣ሁለተኛ ፅንፍ የወጡ አስተሳሰቦች እየተቀነቀኑ መምጣታቸው ሲሆን ሶስተኛ የክልል ፖሊስ አደረጃጀትና የፀጥታ አመራር ረገድ ያሉ ክፍተቶች መሰረታዊ ክፍተቶች ናቸው።
ለውጡን ተከትሎ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ባደረገበት ወቅት የህግ መከበር ላይ ክፍተት መፈጠሩን የሚናገሩ ምሁራን ደግሞ ለደረሰው ጥፋት ህግ በማስከበር ረገድ አለ የሚሉትን ያነሳሉ። ዛሬ በአገሪቱ ዜጎች ላይ እየተፈጠሩ ላሉ ጉዳቶች የህግ መከበርና ሰላም መረጋገጥ መፍትሄዎች እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ። የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ ያየናቸውን ክፍተቶች ተከትሎ መንግሥት ህግን በማስከበር ላይ መበርታት ቀጣይ የቤት ሥራው ነው ይላሉ። ‹‹ መንግሥት ህግን ማስከበር አለበት።
ህግ ካልተከበረ ሥርዓት አልበኝነት ይሰፋል። ይህ ከሰፋ ደግሞ አገር ይጠፋል ማለት ነው። ስለዚህ መንግሥት ኃላፊነት አለበት። ይህንን መንግሥት እንዲያደርግ ደግሞ ህዝብ መደገፍ አለበት። አሁን በሆነው ነገር የተገዳደሉት ወንድማማቾች ናቸው። እንዲህ መሆኑ ለማንም የሚጠቅም ወይም ምንም የሚያመጣ ካለመሆኑ ባሻገር አጥፊና አፍራሽ የሆነ ሥራ ነው።
ጥቃት የተፈፀመው በግለሰቦች ላይ ሳይሆን በአጠቃላይ በአገር ላይ በመሆኑ ድርጊቱ እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም ተምረንበት የምናልፍበት ነጥብን በውስጡ እንደያዘ የጅማ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ከተማው ይናገራሉ። ወንድም ወንድሙን መግደል አገርን መጉዳት ነው። እንዲህ መደረጉ ጊዜ ያለፈበት አካሄድ ነው። አሁን የለውጥ ጊዜ ላይ ስለሆንን አገራችንን በዴሞክራሲ፣በኢኮኖሚ መገንባት ነው ያለብን። በግጭቱ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ተመልሰው ባይመጡም የተፈጠረው ድርጊት የሚያስተምረን ነገር አለ። በዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ብዙ መሰራት አለበት።
ረዳት ፕሮፌሰሩ በፍቃዱ ቦጋለ መንግሥት እርምጃ የመውሰድ አቅሙን የሚያሳይበት ጊዜው አሁን እንደሆነ ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ ችግር መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት፣የክልል ፖሊስ መዋቅርን መፈተሽና ፅንፈኝነትን በጋራ መመከት ግድ እንደሚል ተናግረዋል።
ወደ ከፋ ችግር የሚከቱን ጥቃቅን ብለን የምናስባቸው ነገሮች እንደሆኑ በተግባር እያየናቸው ነው። የአእዋፋት ንጉሱ፣ በደመና፣ በማእበል የሚዝናናው፣ ከርቀት ሆኖ ጤፍ መመልከት የሚያስችል ዓይን ያለው፣ተወዳጁን ንስር የምትገለው ድንቢጥ ነች። ድንቢጥ በንስር ክንፉ ውስጥ ትገባና ደጋግማ ስትመታው ይወድቃል፣ይሞታል። ነገር ግን ንስር ድንቢጥ ውስጡ እንደገባች ካወቀ በጣም ወደላይ ይነሳል፤ድንቢጥ ከሆነ ከፍታ በላይ ንፁህ አየር /ኦክስጂን/ መሳብ ስለማትችል ከክንፉ ውስጥ ትወድቃለች፤ እሱም ያመልጣታል። መምህር መስፍን አሁን እዚህ አገር ውስጥ ክንፋችንን እየበሉ ያሉ ብዙ ድንቢጦች በመብዛታቸው ቶሎ ነቅተን ከእነሱ ሃሳብ በላይ መብረር አለብን የሚል እምነት አላቸው።
ከእነሱ ሃሳብ በላይ ካልበረርን በድንቢጦቹ ተመትተን ላንመለስ እንወድቃለን። መለያየትን፣ ጠላትነትን መስበክ ድንቢጥነት ነው።ሀገራዊ ሃሳብ መኖር አለበት። ሀገር ስትኖር ብሄር ይኖራል ብሄር ሲኖር ቤተሰብ ይኖራል። ሀገር ሳይኖር ምንም ነገር ሊኖር አይችልም። በአገራችን ዋልታ ረገጥ ሃሳቦች በዝተዋል የሚሉት መምህር መስፍን አገር የምትድነው በማእከላዊ ሃሳብ መሆኑን ያምናሉ።
እንደ እሳቸው ሀሳብ ምሁራኑ፣ሃይማኖተኛው፣ሀገር በቀል እውቀት ላይ ያለው በሙሉ ተሰብስቦ አንድ ማእከላዊ ሃሳብ ማምጣት አለበት። በሃይማኖት ረገድም የሚሰባሰበው ህዝብ በርካታ በመሆኑ ለክፉ ለድንቢጥ ሀሳብ የማይተባበር ዜጋ ለመፍጠር የሃይማኖት ኃላፊዎች መስራት አለባቸው። ቅኖች ሲበዙ ከተማ ይገነባል። ክፉዎች ሲበዙ ከተማ ይፈርሳል።
ቅኖች እንዲበዙ፣ክፉዎች እንዲጠፉ ህዝብ መተባበር እና በጋራ መስራት እንዳለበት አገልጋይ ዮናታን ያስረዳሉ። እብድ በባህሪው አይተባበርም፤ ያበደውም ስለማይተባበር ነው። ይህን ያለመተባበር እብደት መተው አለብን። ማህበረሰቡ ቆም ብሎ ያለፈውን ነገር በማስታወስና በማመዛዘን ትምህርቱ መለወጥ አለበት። በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በትምህርት ቤት፣ በጋዜጣ፣ በመጽሄት፣ በሰፈር፣ በጎጥ…የነበሩ ትምህርቶች መለወጥ አለባቸው። ይህ ሳይለወጥ ከላይከላይ መነካካት ለውጥ አያመጣም።
ወባ ለያዘው ሰው ፓራሲታሞል መስጠት ራስምታቱን ያበርድለታል እንጂ በሽታውን አያድንም። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እያደረጉት ያሉት ያመመን ወባ ቢሆንም የሚሰጡን ግን ፓራሲታሞል ነው። በሽታችንን የሚነቅልልን ነገር ያስፈልጋል። ፀሐፊዎቻችን የሚፅፉልን የተደረገልንን ጥሩ ነገር ሳይሆን የተደረገብንን ክፋት ነው። ፀሐፊዎቻችን ፅሁፋቸውን መለወጥ አለባቸው። ከትላንት ስህተታችን ቀለም ተውሰው ዛሬና ነጋችንን ለመፃፍ የሚሮጡ ሰዎች መስተካከል አለባቸው።
አገልጋይ ዮናታን በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን የሳኦልንና የዳዊትን ታሪክ በማጣቀሻነት አንስተዋል። ሳኦል በግሉ ዳዊትን የልመና እንጀራ እንዲበላ፣ ጫካለጫካ እንዲሄድ አድርጎታል፣በድሎታል። እንደሀገር ሳኦል የእስራኤል መንግሥት መጀመሪያ በመሆኑ ቢበድለውም ለቅሶ ተቀመጠ ‹የእስራኤል ክብር በተራሮች ላይ ተወግቶ ሞተ አለ› ። የግል ጉዳያችንና ምክንያታችንን የሀገር ማድረግ የለብንም። ዳዊት ሳኦል ቆነጃጅቶችን የወርቅ ዘቦ ያለብሳቸው ነበር፣እንደንስር ፈጣን፣ እንደአንበሳ ብርቱ ነበር ብሎ ለአቅሙ እውቅና ሰጥቶት ክብርነቱን ውለታውን አፅፎለታል። ምክንያቱም ትውልድ ሊቀጥል የሚችለው ሳኦል ንጉስ በነበረበት ሰዓት ያጠፋውን እየተማረ ሳይሆን ለእስራኤል የዋለውን ውለታ እየተማረ ነው።
ዳዊት ለህዝቦቹ ያስተማረውን መልካም ነገር ኢትዮጵያውያን ጸሀፊያን ሊማሩበት እንደሚገባ እሙን ነው። ነገር ግን ፀሀፊዎቻችን ቢፅፉልን የሚያቀያይመን፣ ፖለቲከኞቻችን ሀውልት ቢተክሉልን ሁሌ ከንፈር እየመጠጥን የምንጠላላበትን በመሆኑ ይሄ ነገር መቅረት እንዳለበት አገልጋይ ዮናታን እምነት አላቸው። ፖለቲከኞቻችን ትምህርት መቀየር አለባቸው። ለውጡ እስከመጣበት ድረስ እንደ ትልቅ እውቀት አድርገው የያዙት የስታሊንን ፅንሰ ሀሳብ ነው።
የስታሊን የብሄር ፅንሰ ሀሳብ አውሮፓዎች መርምረው መዝነውት ሚዛናዊ እንዳልሆነ ተረድተውት የጣሉት ሀሳብ ነው። አሁንም ፖለቲከኞቻችን የስታሊንን ሀሳብ ከመፅሀፍ ማስቀመጫቸው ካላወረዱ፣ ከፖሊሲዎቻቸው ውስጥ ካላወጡ፣መሰረታዊ የድፍየና ለውጥ ካላመጡ አገሪቱ ወደ ተቃና እድገት ትመጣለች ብለው አያምኑም። ፖለቲከኞቻችን የሚያወዳድሩት ከብዙ ዓመታት በፊት ከነበሩ አፄ ሀይለስላሴ እና ከዛሬ ሃያ ሰባት ዓመታት በፊት ከቆመው ከደርግ መንግሥት ጋር ነው። ዛሬ ከኬኒያ መንግሥት፣ከሩዋንዳ መንግሥት እና ከመሰል መንግሥታት ጋር አያወዳድሩም። ይህን የከሸፈና የቆየ የፖለቲካ አካሄድ ማቆም አለባቸው። መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎች ራሳቸው ብዙዎች የሚያራምዱት ነገር በዚህ ዘመን ተፈትሾ የተጣለ መሆኑን አገልጋዩ ያስረዳሉ።
በአጠቃላይ መውጫ መንገዳችንና ሩቅ የሚያስኬደን ካሰብንበትም ሊያደርሰን የሚችለው እኩይ የሆኑ ተግባራትን በግልፅ ማውገዝ ስንችል ነው። እኩይ ተግባራትን የሚከውኑ አካላት ጥቂቶች በመሆናቸው ብዙኃኑን አይወክሉም። ቢሆንም እኩይ ተግባሩን ብዙኃኑ እንዳይስብ መደረግ አለበት። መኖር የምንችለው ወንድማማችነታችንን ማገናዘብ ስንችል፣ ልዩነቶችን በሀሳብ የበላይነት መፍታት የመጨረሻው አማራጭ መሆኑን እምነት አድርገን ስንወስድ ነው። ከቀበሌ ጀምሮ ያለው የፀጥታ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል። ህብረተሰቡ ህግን የማክበር፣መንግሥትም ህግን የማስከበር ተግባር የሁልጊዜ ተግባር ብቻ ሳይሆን ህግ ለሁሉም እኩል የሚሰራ ሁሉንም በእኩል የሚዳኝ፣የሁሉም ጠበቃ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
መንግሥት የለም የሚል እሳቤ ሰዎች ውስጥ መፈጠር የለበትም። እንዲህ ባደርግ መንግሥት ተከታትሎ አሳዶ ይይዘኛል ሊል የሚችል፣ሊያስብ የሚገባ ህብረተሰብ መፍጠር ያስፈልጋል። መንግሥት ሚዛናዊ እና ግልፅ መሆን አለበት። ህዝቡም ከጥላቻ ወንድማማችነትን፣ከመለያየት አንድነትን፣ከክፉ ሀሳብ የተቀደሰ ሀሳብን በጋራ እየሸመተ ከመጣ የለውጡ ስኬት ቅርብ ይሆናል። በዚህም ከመገዳደል ይልቅ በሃሳብ የበላይነት በማመን የውይይት ባህላችን አድጎ ዴሞክራሲያዊ አገር የመፍጠር አላማችን ይሳካል።
ዘመን መፂሄት መስከረም 2012
ሳሙኤል ይትባረክ