እግር ኳስ በአፍሪካ ከተወዳጅ ስፖርትነቱም በላይ አንድ የገቢ ማስገኛ መንገድ ነው። ለስፖርት አመቺ የሆነ መሰረታዊ ስልጠና እና መሰረተ ልማት ባይሟላም በርካቶች በራሳቸው ጥረት ባህር ተሻግረው በአውሮፓ ክለቦች እስከ መንገስ ደርሰዋል። በአንጻሩ ሀገራት የስፖርቱን ጥቅም ይመልከቱ እንጂ የሚሰጡት ትኩረት ግን እዚህ ግባ የማይባል ነው። በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመትም ከፌዴሬሽን አመራሮች ጋር በተያያዘ በርካታ የሙስና ቅሌቶች መጋለጣቸው የሚታወስ ነው።
ከዚህ ባሻገር በዓመቱ ጎልቶ የታየው ሌላኛው ችግር ከውድድር አዘጋጅነት ጋር የተያያዘ ነው። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በበላይነት ከሚመራቸው አህጉር አቀፍ ውድድሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ከዝግጅት ማነስ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። ባሳለፍነው የጥር ወር ለተካሄደው የቻን ውድድር በአዘጋጅነት የተመረጠችው ኬንያ ከዝግጅት ማነስ ጋር በተያያዘ እድሉን መነጠቋ የሚታወስ ነው። ሀገሪቷ ዛንዚባርን በመርታት አዘጋጅነቱን ከእጇ ያስገባች ይሁን እንጂ ጊዜው ሲደርስ ግን «እጅ አጠረኝ» ማለቷ አልቀረም።
ኬንያ ለውድድሩ ከሚያስፈልጉት አራት ስታዲየሞች መካከል ዝግጁ ያደረገችው አንዱን ብቻ እንደነበረም የካፍ የቅኝት ቡድን ነው ያረጋገጠው። በህዝቡ በኩል በርካታ ቅሬታ ቢቀርብም ስፖርቱን የሚመሩት አካላት ግን ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ባለባቸው ችግር ውድድሩን ለማሰናዳት እንደማይችሉ ለካፍ አስታውቀዋል። በመሆኑም ሞሮኮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅታ ውድድሩን ለማካሄድ ችላለች።
በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው የአፍሪካ ታላቁ የእግር ኳስ ውድድር መድረክ የአፍሪካ ዋንጫም ለካሜሩን የተሰጠ ነበር።
የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ለአዘጋጅነቱ ከአራት ዓመት በላይ የጊዜ ገደብ ቢሰጣትም ውድድሩ ወራት ብቻ ቀርተውትም መሰናዶዋን ባለማጠናቀቋ አዘጋጅነቷን ልትነጠቅ ችላለች። ካፍ መዘግየቱን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ከመስጠቱም ባሻገር በተደጋጋሚ የቅኝት ቡድኑን ወደ ሀገሪቷ ቢልክም ግን ለውጥ ማየት አለመቻሉ ወደ እርምጃው እንደወሰደውም የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ማስታወቃቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ይህንን ተከትሎም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውድድሩን የማስተናገድ አቅምና ፍላጎት ያላቸው ሀገራት እንዲያመለክቱ ካፍ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ እና ግብጽ ብቻ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። ይሁንና የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር በድጋሚ ወጪው ምን ያህል ይሆናል የሚለው በመንታ መንገድ ላይ እንዲገኝ እንዳስገደደው የቢቢሲ አፍሪካ ድረ ገጽ አስነብቧል። የማህበሩ ቃል አቀባይ፤ ሀገሪቷ ፍላጎቷን በወቅቱ ብታሳውቅም ግን በወራት እድሜ ውስጥ 24 ሀገራት የሚሳተፉበትን ውድድር ለማሰናዳት የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታ በግልጽ እንዳልተ ቀመጠ ገልጸዋል። በካፍ በኩል ለውድድሩ ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልጋል፣ የካፍ እገዛ ምን ያህል ይሆናል እንዲሁም የስፖንሰር አድራጊዎች ጉዳይ ግልጽ መሆን ስለሚገባው ይህንን በማጤን ላይ እንደሚገኙም ነው ቃል አቀባዩ ያብራሩት።
በአህጉሪቷ የተሻለ ኢኮኖሚ ካሏቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ፤ ውድድሩን እአአ በ1996 እንዲሁም ሊቢያን በመተካት እአአ 2013 አዘጋጅታለች። ከዚህም ባለፈ በአፍሪካ ምድር የዓለም ዋንጫን እአአ በ2010 ያዘጋጀች ብቸኛዋ ሀገር እንደ መሆኗ ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ችግር ያጋጥማታል የሚል ስጋት የለም። ሆኖም ማህበሩ በራሱ አቅም ውድድሩን ለማዘጋጀት የማይችል በመሆኑ የመንግስትን ካዝና ማስከፈት የግድ ይለዋል። ነገር ግን ሀገሪቷ ከገንዘብ ቀውስ ጋር በተያያዘ ትንቅንቅ ላይ መሆኗን ተከትሎ የባለሀብቶች ድጋፍ የግድ አስፈላጊ ሆኖባቸዋል።
በፍላጎቷ የጸናችው ሌላኛዋ ሀገር ግብጽ ደግሞ ካሜሩንን ለመተካት የምትችለው ብቸኛዋ ሀገር መሆኗን በመግለጽ ላይ ትገኛለች። የሀገሪቷ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት ሃኒ አቦ ሪዳ ከካፍ ፕሬዚዳንት ጋር አህመድ አህመድ ጋር በተገናኙበት ወቅትም ይህንኑ ፍላጎታቸውን ነው ያንጸባረቁት፤ «ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገር በተሻለ የመሰረተ ልማትና የስታዲየሞች ዝግጅት አለን። በካይሮ፣ አሌክስአንደሪያ፣ ሱኤዝ እና ፖርት ሰኢድ ስታዲየሞች አሉን» ሲሉም ነው የገለጹት።
ካፍ፤ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱን በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያው ወር በዘጠነኛው ዕለት በሴኔጋሏ ዳካር ጠቅላላ ጉባኤ መጥራቱን በይፋዊ ድረገጹ አስታውቋል። በእለቱም ከሁለቱ ሀገራት መካከል መመዘኛዎቹን የሚያሟላው ሀገርም ከወራት በኋላ የሚካሄደውን ተናፋቂውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ይሆናል። 32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከሌላው ጊዜ የተለየና ለአዘጋጅ ሃገራትም አዳጋች ያደረገው 16 የነበሩትን ተሳታፊ ሀገራት ወደ 24 በማሳደጉ ነው።
የካፍ ውዝግብ በዚህ የሚያበቃ ግን አልሆነም፤ ይልቁኑም ከሁለት ዓመታት በኋላ እአአ በ2021 በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነትም መቋጫ ያላገኘ ጉዳይ ሆኗል። ዝግጅቷን ባለማጠናቀቋ እድሏን የተነጠቀችው ካሜሩን ቀጣዩን ውድድር እንድታሰናዳ ካፍ ከውሳኔ ላይ ደርሷል፤ አዘጋጅ የነበረችው ኮትዲቯር ደግሞ ከአራት ዓመታት በኋላ ጊኒን ተክታ እንድታሰናዳ ማስታወቁ ሌላ ውዝግብ አስነስቶበታል። በዚህ ምክንያትም የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው አካል ከውሳኔ መድረስ እንዳልቻለ መረጃዎች ያሳያሉ።
የካፍ ፕሬዚዳንት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው እንዳስታወቁት ከሆነም «ካሜሩን ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልጋት በመሆኑ እአአ የ2021 አዘጋጅነት ተሰጥቷታል። ይህም የኮትዲቯር እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ያበሳጨ ሲሆን፤ ጉዳዩን በመያዝም ወደ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ምክር ቤት ወስዶታል።
ፌዴሬሽኑ በጻፈው ደብዳቤ ላይም፤ እአአ በ2014 አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ እአአ የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገር ሆና መመረጧን ጠቁሟል። ይሁን እንጂ ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከየትኛውም የሀገሪቷ ባለስልጣናት እውቅና ውጪ የካፍ ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው የሚያስደንቅ ነው። ህዝቡ እና ፌዴሬሽኑም አዘጋጅነቱን እንደሚ ፈልገውና መራዘሙ ቅሬታ እንደፈጠረ ባቸውም አስታ ውቀዋል።
የዓለም እግር ኳስ ከዓመታት በፊት የገባበት የሙስናና ብልሹ አሰራር አመራሮቹ ተነስተውም ያበቃ አይመስልም። እንደ ቀድሞው የፊፋ መሪ ሴፕ ብላተር ሁሉ የቀድሞው የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኢሳ ሀያቱ በከፍተኛ ሙስና የተዘፈቁና በህግም ተጠያቂ መሆናቸው ይታወቃል። እአአ ከ1988 እስከ 2017 ድረስ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት ሰውየው ከሚታሙባቸው የሙስና ጉዳዮች መካከል አንዱ የውድድር አዘጋጅ ሀገራት ምርጫ ነው።
እአአ በ2017 ኮንፌዴሬሽኑን አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በመሪነት የተረከቡት አህመድ አህመድ ደግሞ እርሳቸው ያበላሿቸውን ስራዎች በማስተካከል ላይ ተጠምደዋል። ይሁን እንጂ ይህ ለካሜሩን ዳግም የአዘጋጅነት እድል የመስጠት ውሳኔያቸው ግራ አጋቢ እና ጥያቄም የሚያስነሳ ሆኗል። ለቀጣይ አዘጋጅነት በተመረጡት ሀገራት ላይም ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። የአዘጋጆቹ ሽግሽግ የሚጸና ከሆነም እአአ የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት ያሳወቀችው ኢትዮጵያ፤ ሃሳቧን ለሌላ ሁለት ዓመት ማራዘም የሚጠበቅባት ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
ብርሃን ፈይሳ