የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች መካከል ይጠቀሳል፤ የቻን ዋንጫ። የስፖርቱን ተስፈኞች ለዓለም የሚያሳየው ይህ ውድድር፤ በሀገር ውስጥ ሊጎች ተደብቆ የቀረ አቅማቸው ለዓለም እንዲታይና ከዕውቅና የሚገናኙበትን እድልም የሚፈ ጥርላቸው ነው። ለዚህ ውድድር መጀመር መንስኤ የሆነው በአህጉሪቷ የእግር ኳስ ስፖርት ትልቁ ውድድር፤ የአፍሪካ ዋንጫ ብሄራዊ ቡድኖች የሚያካትቷቸው አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በዓለም ዙሪያ ስመጥርና በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱትን መሆኑ ነው። በመሆኑም በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች የብሄራዊ ቡድን ተሳታፊነት እድል ለመስጠት ሲባል ውድድሩ ተዘጋጅቷል።
በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድርም ማረፊያው የምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኑን አረጋግጧል። ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽም የወቅቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነዲ ባሻ፤ የአዘጋጅነት መለያ አርማውን በሞሮኮ ከካፍ ፕሬዚዳንት መረከባቸው የሚታወስ ነው። በወቅቱም ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት ፍላጎትና ዝግጁነት እንዳላትም ገልጸው ነበር። አሁን በሀገሪቷ እየተገነቡ ያሉት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ደግሞ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ያሉ ውድድሮችን የማሰናዳት አቅም እንደምታ ጎለብትም ጠቁመዋል። እአአ በ2020 የሚካሄደው የቻን ውድድርም እአአ የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጅነት ብቃቷን የምታሳይበት እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው።
አዲሱ ስራ አስፈጻሚ ወደ ስራ ከገባ በኋላም ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት የተረከቡት አቶ ኢሳያስ ጂራ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ዝግጅቱ ገለጻ አድርገዋል። በገለጻቸውም ላይ፤ «ቀድሞ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አዘጋጅነቱን በይሁንታ ተቀብለውት ነበር። ከዚያ በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመምጣታቸው የእርሳቸውም ፈቃድ የሚያስ ፈልገን በመሆኑ እርሳቸውን ለማግኘትም ጥቂት ጊዜ ወስዷል። አሁን ግን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ቀጥሉበት’ ተብሎ በኢፌዴሪ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በኩል ትዕዛዝ ተሰጥቶናል። ቻን የሀገር ጉዳይ ነው፤ ስለዚህም ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ መስራት የሚገባው ከመንግስት ጋር በመሆኑ እጅና ጓንት ሆኖ ይሰራል። ከወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነሩ ርስቱ ይርዳው ጋርም ተቀራርበን እየሰራን እንገኛለን» ብለው ነበር።
በቻን የሚሳተፉት ሀገራት 16 ሲሆኑ፤ አራት ቡድኖች በአንድ ስታዲየም ውድድራቸውን ያደርጋሉ። አራት ስታዲየሞች ለውድድሩ አስፈላጊ በመሆናቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው ብሄራዊ ስታዲየም፣ የባህርዳር፣ የመቀሌ እና የድሬዳዋ ስታዲየሞች ተመርጠዋል። ፌዴሬሽኑም አዘጋጅነቱን በይፋ ከተረከበ ስምንት ወራት ተቆጥረዋል፤ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥስ ምን ያህል ስራዎች ተከናውነዋል? ውድድሩ በፌዴሬሽኑ አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር እየተከናወነ ያለው ነገር ምን ይመስላል? ለውድድሩ በአጠቃላይ ምን ያህል ወጪ ያስፈልጋል እንዲሁም የካፍ የቅኝት ቡድኖች በየጊዜው በመምጣት ዝግጅቱን ይከታተላሉ? በሚለው ላይ የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ምላሹን ሰጥቷል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ፤ የውድድር አዘጋጅነቱ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ፌዴሬሽኑ ከመንግስት ጋር እየተነጋገረ በመስራት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። በምን ዓይነት ሁኔታና መልክ ውድድሩ እንደሚካሄድም አቅጣጫ ተቀምጧል። በአቅጣጫው መሰረትም አዘጋጅነቱ ከፍተኛ ገንዘብና የመንግስትን ይሁንታ የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንኑ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ከዚህ በኋላ የአንድ ዓመት ጊዜ የሚቀር በመሆኑም እየተኬደበት ነው ያለው። በቅርቡም የመንግስትን አቅጣጫና አጠቃላይ የስራ መመሪያ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ይጠቁማሉ።
ፌዴሬሽኑ የመነሻ ፕሮፖዛል ያዘጋጀ ሲሆን፤ ካፍም የዝግጅት ስምምነት ሰነድ መላኩን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ይገልጻሉ። በሰነዱ ላይ ለዝግጅቱ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ያሳያል፤ በዚህ ላይ በመመስረትም መነሻ ሰነድ ተዘጋጅቷል። ስለዚህም በዚህ ሳምንት ውስጥ የአብይ እና ንኡሳን ኮሚቴዎችን ለማደራጀት በእንቅስቃሴ ላይ ነው። ኮሚቴዎቹ ከተደራጁ በኋላም እያንዳንዳቸው ለስራቸው የሚያስፈል ጋቸውን እቅድ ፕሮፖዛል መነሻ በማድረግ ያዘጋጃሉ።
በአጠቃላይ ውድድሩን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ወጪም ከዚህ በኋላ የሚታወቅ ይሆናል። እያንዳንዱ ንኡሳን ኮሚቴዎች የየራሳቸውን በጀት ካቀረቡ በኋላ አብይ ኮሚቴዎች በጋራ እቅዱን በማጠናቀር ወጥ የሆነ የቻን ውድድር እቅድና በጀት ይሰራል። ይህንን እና በካፍ የሚጠየቀውን በጀት በመደመርም ውድድሩ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል የሚለውን ማወቅ ይቻላል። እንደ አጠቃላይ ግን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ውድድር መሆኑም አቶ ሰለሞን ይጠቁማሉ።
ይህ ከተጠናቀቀ በኋላም ከካፍ ጋር በስምምነት ሰነዱ ላይ እንፈራረማለን። የውድድር ዝግጅቱ የራሱ ጽህፈት ቤት ተከፍቶለትና ጸሃፊ ተመድቦለትም፤ በየክልሉ ውድድር የሚካሄ ድባቸው ክልሎችም ኮሚቴዎች ተቋቁመውም ዝግጅቱ ይቀጥላል።
ባለፉት ወራት የካፍ ቅኝት ቡድን አንዴ መጥቶ ነበር፤ ከዚህ በኋላም ሁለተኛና ሶስተኛ ዙር ቅኝት ያደርጋሉ። በመጀመሪያው ቅኝት ላይም በአራቱም ስታዲየሞች፣ ከተሞች፣ ሆቴሎች፣… ተገኝተው በተመለከቷቸው ነገሮች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ፌዴሬሽኑም አስተያየቱን ለክልሎቹ በማውረድ በዚያ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። በሀገሪቷ ያሉት አብዛኛዎቹ ስታዲየሞች በግንባታ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በቶሎ መጠናቀቅ እንዳለባቸው ተጠቁመዋል። አንዳንድ ክልሎች ፈጣን ስራ በማከናወን ላይ ያሉ ሲሆን፤ ዝቅተኛ እንቅስቃሴ ያላቸው ክልሎችም መኖራቸው ታይቷል፤ በዚህም ላይ ክትትል በመደረግ ላይ ይገኛል።
ለሁለተኛው ዙር ቅኝት ደግሞ ቡድኑ በቀጣይ የሚመጣ ይሆናል፤ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ግን የውድድሩን ጊዜ መወሰን እንደሚገባ የቤት ስራ ሰጥቷል። ቀድሞ የተቀመጠው የውድድር ጊዜ ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ፤ ፌዴሬሽኑ ይህንን በማጥራት ስራ ላይ ይገኛል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ንግግር የተደረገ ሲሆን፤ የአስቸኳይ እና መደበኛ ጉባኤው መቼ ይካሄዳል የሚለውን ለማሳወቅም ለዛሬ ቀጠሮ መያዙን ኃላፊው ያመላክታሉ። ከዚህ በኋላም ውድድሩ የሚጀመርበትንና የሚጠናቀቅበትን ትክክለኛ ቀን ኮንፌዴሬሽኑ ሲያውቅ፤ የቅኝት መርሃ ግብሩን በማስተካከል ቡድኑ የሚመጣ ይሆናል።
በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያ መልካም ተሞክሮ ያላት መሆኑን የሚያነሱት ኃላፊው፤ ሴካፋን በጥሩ ሁኔታ መስተናገዱንም በማሳያነት ያነሳሉ። በመንግስት በኩልም ቁርጠኝነት አለ፤ በማዘውተሪያ ስፍራዎችም ቢሆን ውድድሩን ለማካሄድ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ያረጋግጣሉ። የሚጠበቁት ስራዎች ግን በርካታ እንደመሆናቸው፤ አቅም በፈቀደ ሌት ተቀን መስራትን ይጠይቃል። በፌዴሬሽኑም በኩል ጥሩ ስራ በማከናወን የተሳካ ውድድር ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል። ከዚህ በኋላም ዝግጅቱ የደረሰበትን ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ መስራት የሚገባውን ለማመላከት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በየጊዜው በመገናኘት እንደሚሰራም ኃላፊው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
ብርሃን ፈይሳ