እንደአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1841 የመጀመሪያው የኦፕየም ጦርነት በተባለው ውጊያ ብሪታንያ ኪዊንግ ከተባለው የቻይና ሥርወ-መንግስት አገዛዝ ትንሿን የባሕር ዳርቻ ግዛት ሆንግ ኮንግን ማረከች። እንዲሁም፤ ብሪታንያ እ.አ.አ በ1898 ተጨማሪ አካባቢዎችን ለ99ኝ ዓመት ለማስተዳደር ከቻይና ተኮናተረች።
ነገር ግን እ.አ.አ ከ1920ዎቹ ጀምሮ የግዛቲቱ ሕዝብ የብሪታንያን እና ለአጭር ጊዜ የቆየውን የጃፓንን ቅኝ አገዛዝ በመቃወም ይፋለሙ ጀመር። በተለይ እ.አ.አ በ1922፤ በ1925፣ በ1950፣ በ1967 እና እስከ 1997 ከቅኝ ገዥዎች ለመላቀቅ የተደረገውን ሰልፍና አድማ የመሩት ኮሚኒስቶች ነበሩ።
በመሆኑም የዛሬ 70 ዓመት በሊቀ መንበር ማኦ ዜዱንግ የሚመሩት የቻይና ኮሚኒስት ሸምቅ ተዋጊዎች፤ የብሔረተኛውን የሻንጋይ ሼይክ አስተዳደር መንግለው ጥለው “የቻይና ሕዝባዊ ሪፖብሊክ” የምትባለዋን አገር መሠረቱ፡፡ በኮሜንታንግ የፖለቲካ ማህበር ይመራ የነበረው ተሸናፊው የብሔረተኞች መንግስት ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ታይዋን ደሴት ተሰደደ፡፡
ከዚህ በኋላ የቻይና መንግስት ሆንግ ኮንግን ከብሪታንያ ቅኝ ገዥዎች እ.አ.አ በ1997 ተረከቡ። በወቅቱም በወጣው ሕገ-መንግስት መሠረት ግዛቲቱ የቻይና አንድ ግዛት ሆና፤ ነገር ግን በራስዋ ሕግ አውጪና ሕግ አስፈፃሚ የምትተዳደር ራስ-ገዝ አስተዳደር ሆነች።
ይሁንና፤ የግዛቲቱ ዋና አስተዳዳሪ ወይም አገረ- ገዢ ሆኖ የሚመረጠው ለቤጂንግ ይወግናል በሚል በሚታማው አንድ ሺህ 200 አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2014 ቻይና አዲስ ማሻሻያ ሕግ ማውጣቷ በወቅቱ ለተቀሰቀሰውና ለከፋው ተቃውሞ ምክንያት፤ እንዲሁም ከወራት በፊት በግዛቷ ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዋነኛው እርሾ እንደሆነ ይታመናል። እ.አ.አ በ2014 የወጣው ሕግ ለቤጂንግ አስተዳደር ቅርበት አለው የሚባለዉ ኮሚቴ ለመሪነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ዝርዝር ለሕዝብ ያሳውቃል። ሕዝቡም ከቀረቡለት ዕጩዎች መካከል ብቻ አስተዳዳሪውን ይመርጣል፤ የሚል ነበር።
ሕጉ “አሳፋሪ ዴሞክራሲ” የሚል ውግዘትና ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ የግዛቲቱ ምክር ቤት ውድቅ አድርጎታል። ምክር ቤቱ ከሚያስተናብራቸው ከ70ዎቹ የእንደራሴዎች እንኳን የተወሰኑት በቤጂንግ ትዕዛዝ ምክር ቤት የሚገቡ እንጂ በሕዝብ የተመረጡ አይደሉም።
የቤጂንግ ኮሚኒስቶች የሆንግ ኮንግ ተከታዮቻቸውን አስተዳደር በመቃወም እንደ አውሮፓውያን በ2014 በግዛቷ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶችን ፖሊስ በኃይል በበተነበት ወቅት ሰልፈኞቹ “ዳግም እንመለሳለን” ብለው ነበር።
በመሆኑም፤ ዘንድሮ ከሰኔ ወር ጀምሮ ዳግም በግዛቷ ከፍተኛ ተቋውሞ ተቀስቅሷል። የተቃውሞውም መነሻ የግዛቷ አስተዳዳሪ የኬሪ ላም አስተዳደር በወንጀል የሚጠረጠሩትን የግዛቲቱ ተወላጆች ለቤጂንግ አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያደርግ ደንብ ማርቀቁ ነበር። ከአዲሱ ህግ መርቅቅ ጋር ተያይዞ ከወራት በፊት በግዛቷ ምድር የሚያንቀጠቅጡ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፤ በሆንግ ኮንግ የአየር መንገድ አገልግሎት እስከማቋረጥ የዘለቀ ነበር። ይሁንና፤ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የወጣው ረቂቅ ደንብ የተሻረ ቢሆንም፤ የተቃውሞው መሰረታዊው ምክንያት ከ2014፤ ምናልባትም ከ1997 ጀምሮ የተጠራቀመ ብሶት በመሆኑ ረቂቁ ከተሻረ በኋላም ተቃውሞው በግዛቷ ቀጥሏል።
እ.አ.አ ከ1997 እስካሁን ድረስ በግዛቷ ለሚቀሰቀሱ የተቃውሞ ሰልፎች አስተባባሪዎች “ስልጣናቸውን የተቀሙ፤ የካፒታሊስቱን ዴሞክራሲ የሚያቀነቅኑ፤ በካፒታሊስቶች የሚደገፉ ኃይሎች ናቸው” ስትል ቻይና የምትከስስ ሲሆን፤ 150 ዓመታትን ከቅኝ ገዢዎች ለመላቀቅ ባደረገችው እልህ አስጨራሽ የትግል ስልት የበለጸገችው ግዛቲቱ፤ አዲሱ ትውልድ ደግሞ በግዛቷ የኮሚኒስቶችን መረን የወጣ ጣልቃ ገብነት እስከወዲያኛው ለመገርሰስ ትግሉን ዳግም ከሰኔ ጀምሮ አፋፍሞታል።
በዚህም የሆንግ ኮንግን አስተዳደሮችና የቻይናን ኮሚኒስታዊ አገዛዝ የሚቃወሙት የግዛቲቱ ወጣቶች የእኛን ታላቅ አብዮታዊ መሪ የማኦ ዜዶንግን አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና አስተምሕሮ ምናልባት ከተጣመመ ትርጓሜው ባለፈ አይተውት፣ ኖረውበት፣ በቅጡ አስተንትነውትም ማወቃቸው በርግጥ አጠራጣሪ ነው ይላሉ።
ማኦ እ.አ.አ በ1934 በፃፉት መጣጥፍ «አብዮታዊ ጦርነት፣ የሰፈው ሕዝብ ጦርነት ነው» ያሉ ሲሆን፤ የግዛቷን ወጣቶች የሚቃወሙት የሆንግ ኮንግ አስተዳዳሪዎች «ነውጠኛ ተቃዋሚዎች» እያሉ በማጣጠል፤ እኚህ እውቅ ኮሚንስታዊ መሪ ከዛሬ 85 ዓመት በፊት ብለውት እንደነበረው «እኛ ብዙሐን አብዮተኞች ነን» በማለት ወጣቶችን ተቃውሞ ያጣጥሉታል።
ማኦ እ.አ.አ በ1963 ለጓድ ኩኦ ሞጆ (KUO MO-JO) መልስ ባሉት ግጥማቸው “በዚች ትንሽ ዓለም፣ ጥቂት ዝንቦች ከግንብ ጋር ይላተማሉ” ብለው ነበር። ይሄንንም የእርሳቸውን ንግግር የቤጂንግ ተከታዮቻቸው የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚዎችን ብዛት ለማሳነስ ዘንድሮ ተጠቅመውበታል። የሆንግ ኮንግ አስተዳደር ዋና ፀሐፊ ደግሞ ከወራት በፊት በግዛቷ ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ የታላቁን አብዮታዊ መሪ ቅኔ ተቃዋሚዎችን ለማስጠንቀቅ፤ ሕዝብን በተቃዋሚዎቹ ላይ ለማሳመፅ ሞክረዋል።
“እነዚህ ጥቂት ነውጠኛ አመፀኞች ሁከታቸውን እያባባሱት ነው። ሕግ እየጣሱ ነው። የሆንግ ኮንግን ሰላም፤ ሥርዓትና የሕዝቡን ኑሮ ክፉኛ እያወኩ ነው። ለሕዝብ ደሕንነት ደንታ የላቸውም። ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እራሱን ከሁከቱ ማራቅና የነውጠኞቹን የጭካኔ ርምጃ ማውገዝ አለበት። መንግስት ሁከቱን ለማስቆም አበክሮ ይጥራል።” ሲሉም ተድምጠዋል።
እኚህ ሰው አክለውም፤ አይደለም ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጣው ቀርቶ አጠቃላዩ ሰባት ሚሊዮን ሕዝቧ ቢያምፅ እንኳ 1.386 ቢሊዮን ከሚገመተው የቻይና ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር በርግጥም ማኦ እንደተቀኙት ከግንቡ ጋር እንደሚላተሙት “ጥቂት ዝንቦች”ናቸው፤ ሲሉ የወጣቶቹን ተቃውሞ አንኳስሰዋል።
ይሁንና ከቱኒስ እስከ ካርቱም፤ ከካይሮ እስከ ሀራሬ የማይደፈሩ የሚመስሉ ገዢዎችን ከየመንበራቸው አሽንቀንጥሮ ለመጣል የሕዝብ ዓላማና ፍላጎትን ያነገቡ ወጣቶች እንጂ፤ መላው ሕዝብ አደባባይ መሰለፍ አላስፈለገውም። የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚ ሰልፈኞችም “ጥያቄ፤ አላማችን የሕዝብ ነው” በማለት ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል። ሆንግ ኮንጎች ተቃውሟቸው “የሰፊዉ ሕዝብ” ባይባል እንኳን ሚሊዮኖችን ማሰለፋቸው እርግጥ ነው።
በመሆኑም በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ቻይና የቻይና ህዝቦች ሪፐብሊክ (ፒአርሲ) ተብሎ የሚጠራውን የኮሚኒስት ፓርቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት በደመቀ ስነስርዓት ባከበረችበት እለት አያሌ የሆንግ ኮንጎች ወጣቶች አደባባይ በመውጣት ተቋውሟቸውን ለዓለም አሰምተዋል።
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ምስረታ 70ኛ ዓመት በዓል በደማቅ ወታደራዊ ትርዒት በያዝነው ማክሰኞ እለት የተከበረ ሲሆን፤ በስነ ስርዓቱ ላይ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከበርካታ ሀገራት የተውጣጡ ወታደራዊ ልኡካን ተገኝተዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ “የአዲሲቷን ቻይና ሪፐብሊክ ቀጣይነት ማንኛውም ምድራዊ ሃይል ሊያስቆመው አይችልም” ብለዋል። ለዚህም ቻይና ዘመኑን የዋጁና በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠኑ ወታደሮች፤ እንዲሁም ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።
ለቻይና ነፃነት፤ ልማት እና ብልፅግና ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አርበኞችና ሰማዕታትም ታላቅ ክብር እንዳላቸው አውስተዋል። በተመሳሳይ፤ የውጭ አጋር ሀገራት እና ወዳጆች ቻይና እዚህ ደረጃ እንድትደርስ ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በዓሉን አስመልክቶ በቤጂንግ ቲያነንሜን አደባባይ በተከናወነው ወታደራዊ ትርዒት ሀገር በቀል የሆኑ ዘመናዊና ግዙፍ የጦር መሳሪያዎች ለዕይታ የበቁ ሲሆን፤ የቻይና ህዝብ ኮሙኒስት ሪፐብሊክ 70ኛ የምስረታ በዓል ለማክበር በተሰናዳው ዝግጅት ላይ የቻይና ጦር እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ይፋ አድርጓል።
ከዚህም ውስጥ ከድምፅ ፍጥነት አምስት እጥፍ በላይ የሚወነጨፍ ሃይፐርሶኒክ የኒዩክሌር ባሊሲቲክ ሚሳኤል ይፋ ሆኗል። ዲ ኤፍ-17 የተሰኘው ዘመናዊ የጦር መሳሪያም በተሽከርካሪ ላይ ሆኖ ለዕይታ ቀርቧል።
አዲሱ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል በአሜሪካና አጋሮቿ ለስራ ዝግጁ የሆኑ የሚሳኤል መቃወሚያዎችን ዒላማ አልፎ ጥቃት ማድረስ የሚያስችል ነው የተባለ ሲሆን፤ ቻይና በ30 ደቂቃ ውስጥ አሜሪካ መድረስ የሚችሉ ሚሳኤሎችንም አሳይታለች።
አንዳንድ ተንታኞች የቻይናን ወታደራዊ ትርዒት ለአካባቢው ስጋት ነው ያሉ ሲሆን፤ በተለይም በፍጥነታቸው ከፍተኛ የሆኑ መሳሪያዎችን ማሳየቷ ለቀጣናው ወታደራዊ ደህንነት የመከላከልና የማጥቃት ሚዛን ላይ ጫና እንደሚፈጥር ነው ያነሱት፤
ሃይፐርሶኒኩ ሚሳኤል ከመሬት በዝቅተኛ ርቀት ላይ የሚወነጨፍ መሆኑም ጥቃት ለሚከላከሉ ሀገራት የሚሳኤል መቃወሚያዎች ፈታኝ እንደሚሆን ተገምቷል። በስነስርዓቱም ዲ ኤፍ-41 ከ12 ሺህ እስከ 15 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚወነጨፈው ድንበር ተሻጋሪ ባሊሲቲክ ሚሳኤል ይፋ ሆኗል። ጄ ኤል-2 ሚሳኤል፣ የተዋጊ መርከብ መቃወሚያ የሆነው ዋይ ጄ-18 ሚሳኤልም በትርዒቱ ቀርበዋል።
እጅግ ዘመናዊ የተባለ ጄት እና ሚሳኤል አነፍናፊ መሳሪያ እና ኤች ኪው-9ቢ የተሰኘ( HQ-9B) የጥቃት ማክሸፊያ መሳሪያም ይፋ ሆኗል። በአጠቃላይ በትርዒቱ ላይ 15 ሺህ ወታደሮች፤ 170 የጦር አውሮፕላኖች፤ 580 ባለስቲክ ሚሳኤሎች፤ ዘመናዊ ድሮውንና ታንኮችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ቀርበዋል።
ነገር ግን፤ የሆንግ ኮንግ ወጣቶች ይህንን በዓል ጥላውን እንዳያጠሉበት ተብሎ ከወዲሁ ተሰግቶ የነበረ ሲሆን፤ እንደተፈራውም በሆንግ ኮንግ አደባባዮች በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አደባባይ በመውጣት “በዓሉ የገዳዮች በዓል ነው። ለኛ ደግሞ የሀዘን ቀን” ሲሉ ተቃውሟቸውን ለዓለም አሰምተዋል።
ቻይና ፈርጣማ ክንዷን ለዓለም ለማሳየት በበዓሉ ላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና ወታደራዊ ትርኢቶችን ያሳየች ቢሆንም፤ ተቃዋሚዎች የቻይናን ፈርጣማ ክንድ ከምንም ሳይቆጥሩት አደባባይ በመውጣት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተናንቀዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ አላማም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጋድሎ ለታላቅ ዲሞክራሲ ትግል እንዲበቃና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቃውሞው እንዲስፋፋ እንዲሁም የከተማዋን የፖለቲካ መሪዎች አንገት ለማስደፋት የታለመ ሲሆን፤ ማክሰኞ ዕለትም ፖሊሶች ሰልፈኞቹን በኃይል ለመበተን በመሞከራቸው ከሰልፈኞቹ ጋር በተደረገ ግብግብ ከመቶ በላይ ሰልፈኞች ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል። በወቅቱም አንድ የአስራ ስምንት ዓመት ተማሪ በጥይት ደረቱ ላይ መመታቱን ተከትሎ በሆንግ ሆንግ ውጥረቱ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2012
ሶሎሞን በየነ