ሰዎች ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻው ለሚያዘጋጁት ምግብ ጥራት ሲጨነቁ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ለምግብ ሰንሰለት የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ሆኖ ይታያል፡፡ በተለይ የእንስሳት መኖ ወደ ምግብ እንደሚሄድ ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንደሌለ ያመላክታል፡፡ በዚህ የተነሳም ከእንስሳት ተዋፅኦ ጥራትና ደህንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ እኛም ለዛሬ በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችና እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ምን ይመስላሉ የሚለውን ልናስዳስሳችሁ ወደድን፡፡
ባለስልጣኑ
የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ጠርዙ ደጋጋ እንደሚሉት፤ ማንኛውም መኖ ለእንስሳት ፍጆታ ከመቅረቡ አስቀድሞ በአምራቹ ተቋም ደህንነትና ጥራቱ ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ የመኖ ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው ለረጅም ጊዜ መቆየቱንም ይናገራሉ፡፡ አዋጅ ቁጥር 728/2004 የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ግን የመኖ ደህንነትና ጥራትን በኃላፊነት የሚከታተል፣ የሚቆጣጠርና የሚያስተዳድር ተቋም ሆኗል፡፡ ተቋሙ አዲስ በመሆኑም ሥራውን ደጋፊ አዋጁ ላይ የተመሠረተ መመሪያ የማውጣት እንዲሁም አሰራርን ስርዓት የማስያዝና ተቋማዊ አደረጃጀት ማስፈን ላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለእንስሳት የሚቀርበው መኖ ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው አምራቾች እንዲካሄድ እንዲሁም ሕጋዊ የሥራ አካሄድና የአሰራር ብቃት ባላቸው አካላትና ተቋማት ንግድ ሥራውም እንዲከናወን የራሱ መመሪያ ተዘጋጅቶለት ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡
ምርትና ምርታማነቱ ከፍ ያለ እንዲሁም በጥራትም የተሻለ የእንስሳት ተዋፅኦ ማግኘት የሚቻለው እንስሳት መኖ አቅርቦቱ ጥሩ ሲሆን ነው፡፡ መኖ የጥራት ደረጃውና ደህንነቱ ሲጠበቅ እንዲሁም በሚያስፈልገው መጠን ሲቀርብ የእንስሳት ምርትና ምርታማት ይጨምራል፣ የተጠቃሚው ጤናም ይጠበቃል፤ ብሎም የወጪ ንግድ ይበረታታል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ውጤቱን ተቃራኒ ያደርገዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ባለስልጣኑ ከተቋቋመ በኋላ የመኖ ጥራትና ቁጥጥር ላይ ገብቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ከወተት ደህንነት ጋር ተያይዞ ይታዩ የነበሩ ችግሮች እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡ ይህም ትልቅ ትምህርት ሆኖ ጥራትና ደህንነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመሪያም እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ አልፏል፡፡
በተለይ አገሪቱ ምድር ወገብ አካባቢ የምትገኝ በመሆኗ ከፍተኛ ሙቀት፣ እርጥበትና ዝናባማ አካባቢም ነው፡፡ ይህ ሙቀትና እርጥበት መኖሩም የበሽታ አምጪ ተህዋስያንን በመፍጠር የመኖ ጥሬ ዕቃዎችን የሚያበላሽ የህብረተሰቡንም ጤና የሚጎዳ ችግር ይፈጥራል፡፡ ይህንን ተቆጣጣሪ አካል ከሌለም ችግሩን ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ሳያሳስበው ለትርፍ ብሎ የሚያመርት አይጠፋምና ተቆጣጣሪ መኖሩ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም በተቋማት እንዲሁም በአምራችና በተጠቃሚ መካከል ያለውን ሰንሰለት ለማጣጣም የመመሪያ ክፍተት መኖሩ ይታያል፡፡ ይህንንም በመፈተሸ ችግሩን ሊደፍን በሚችል መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ ርብርብ ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም የመኖ አደጋ ዳሰሳና አስተዳደር አያያዝ አልፎም ደግሞ አደጋ ሲከሰት የአደጋ ምንጮች ምንድን ናቸው? እንዴት መከታተልና መቆጣጠርስ ይቻላል? በሚል የተግባቦት ስራን ያካተተ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀርቧል፡፡
ውይይቱም በእንስሳት ተዋፅኦ ላይ በሚፈጠሩ ችግሮች በህብረተሰቡና በተለይም በዕድሜ ለጋ የሆኑ ህፃናትን ከጉዳት ለመከላከልና ስርዓት ለማስያዝ ታልሞ የተዘጋጀም እንደሆነ ዳይሬክተር ጀነራሉ ያስረዳሉ፡፡ የመኖ ደህንነት ጤንነትና ጥራትን መቆጣጠሪያና መከታተያ መመሪያዎች ከዚህ ቀደምም እንደነበሩ በማስታወስም፤ ከአንድ መኖ ጥሬ ዕቃ ማምረቻ ማጓጓዣና ፋብሪካ ጀምሮ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከፋብሪካው ጥሩ መኖ ከወጣ በኋላ በማጓጓዝና በአያያዝ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች በመኖራቸው የመኖ ጥሬ ዕቃ አያያዝ ክምችት አስተዳደር እንዲሁም ወደ ገበያ ከወጣ በኋላ እንዴት ገበያ ላይ ውሎ ተጠቃሚዎች መያዝ እንዳለባቸው ከግንዛቤ በመክተት ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የሚመለከተው አካልም እንዴት አደጋውን መቀነስ ይቻላል? በሚል ይሰራል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና የበርካታ ጎብኚዎች እንዲሁም ዲፕሎማቶች መቀመጫና መመላለሻ በመሆኗ በዛ ልክ በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡ ጎብኚውም የዛሬው የእንስሳት መኖ የነገ የሰው ልጆች ምግብ ነውና ይህን የሚቆጣጠር አካል አለ ወይ? የሚለውን ሲመለከት በደስታ እንዲመጡ ያደርጋልና ሥራውን ማስተካከሉ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህም አስመጪዎች፣ ጅምላ አከፋፋዮች እንዲሁም ችርቻሮ አከፋፋዮች ጋር መኖ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ባለስልጣኑ በመመሪያ መሠረት ቁጥጥሩን ያከናውናል፡፡
ከመኖ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሁለት አመታት በወተት ላይ አፍላቶክሲን ተከስቶ ሰውንም ሆነ እንስሳትን ለጉዳት ማጋለጡን ዶክተር ጠርዙ ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ወተት የተከሰተው ችግር መነሻ በሙሉ ከመኖ የሚያልፍ ነውና ችግሩ መመሪያው በፍጥነት ለመውጣቱም ምክንያት ሆኗል፡፡
ከምሁራን
ሲዲአይኤስ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ማኔጀር ዶክተር አማኑኤል አሰፋ፤ በአሁኑ ወቅት ባለው ሁኔታ ግብርናው እያደገና ውስብስብ እየሆነም እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም እንደ ቀድሞ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ብቻ ከዩኒቨርሲቲ የሚወሰዱ ምርምሮችን አርሶ አደሩ ጋር በመውሰድ ብቻ ምርታማነትን መጨመር በቂ አይደለም፡፡ ከጎኑ የእሴት ሰንሰለቱ ተዋናዮች የሆኑ ብዙዎቹ መኖራቸውንም መዘንጋት ተገቢ አይሆንም፡፡ አምራቾችና ሻጮች ሁሉ አነስተኛ ገበሬውን የሚጠቅሙ በመሆናቸው እነርሱን ሁሉ በማግለል ከአርሶ አደሩ ጋር ብቻ መስራት የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም፡፡በመሆኑም አካታች መሆን ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የመኖ ሥራም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሚገልጹት ዶክተር አማኑኤል፤ አፍላቶክሲን በመሳሰሰሉ መርዛማ ባህርይ ባላቸው ችግሮች ወተት ከጠቃሚነቱ ወደ ጠንቅነት ሊቀየር እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ይህ ችግር የከፋ ጉዳት እንዳያደርስም መንግስት በየጊዜው ስጋቶችን መዳሰስ ይገባዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ ማዕከላዊ በሆነ መንገድ ግንኙነትን መፍጠር ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት ትልቁ ክፍተት ተብሎ የተለየው የግብርና ውስብስብ በመሆኑ የመንግስት ተቋም ለአብነት ግብርና ሚኒስቴር፣ የምርምር ተቋሞችና ዩኒቨርሲቲዎች ለብቻቸው በራቸውን ዝግ አድርገው ከመስራት ወጥተው በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል፡፡ መንግስት የጀመረው ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርም ተጠናክሮ መሄድ ይኖርበታል፡፡
አገሪቱ በዘርፉ ከፍተኛ ዕምቅ ሀብት እንዳላት ሲገለጽ ቢሰማም አሁንም ያላትን ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀሟ ወተት ከባህር ማዶ እያስገባች ትገኛለች፡፡ ከዩኒቨርሲቲው የሚወጡ ምሁራን ቢኖሩም በጋራ መስራት ላይ ባለው ችግር ግን አገሪቱ በየዓመቱ ጠቀም ያለ ገቢ ማግኘት ሲቻላት እንደውም ለጉዳት ተዳርጋለች፡፡ ለዚህም ችግር ተጠቃሹ ምክንያት ቴክኖሎጂ እንደሆነ ብዙ ዘመናት ሲነገር ከርሟል፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ ማነቆ አለመሆኑ ደግሞ ይታያል ሲሉ ዶክተር አማኑኤል ይናገራሉ፡፡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የአደረጃጀትና መዋቅር እንዲሁም የፖሊሲ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመሆኑም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለውጦች ያስፈልጋሉ ሲሉም መፍትሔ ያሉትን ሃሳብ ያመላክታሉ፡፡ የግብርና ጉዳይ ለአንድ ዘርፍ የሚተው ባለመሆኑ የሁሉም ጉዳይ ተደርጎ በመውሰድ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ልማት ሠራተኞችና ሌሎች አመቻቾችም ይህን አውቀው አሳታፊ በሆነ መልኩ ሊሰሩ ይገባል፡፡
ሚኒስቴሩ
በአገሪቱ 150 ሚሊዮን የሚገመት የእንስሳ ሀብት እንዳለ የሚናሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሐንስ፤ ይህን የሚመጥን መኖ በጥራትም ሆነ በመጠንም ተደራሽ ማድረግ ግን አልተቻለም ይላሉ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን መኖ ላይ ጥራት መጠበቅ ካልተቻለ ዞሮ ዞሮ የምርት ጥራቱ ላይ የሚያሳድረው የራሱ አሉታዊ አስተዋፅኦ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ መኖን በመጠን ለመጨመርም ያሉትን የግጦሽ መሬቶች ማሻሻል አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ በመሆኑም በቆላማው አካባቢ የሚገኙ ሰፋፊ መሬቶች ለእንስሳት ግጦሽ መዋል የሚችሉ ነገር ግን ብዙም የማሻሻል ሥራ ያልተሰራባቸው በጎርፍና ነፋስ ለአደጋ የተጋለጡ መሬቶች በመኖራቸው በትኩረት ይሰራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ በቆላማው የአገሪቱ ክፍል የእንስሳቱ ቁጥር ከፍተኛ ነው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የአርሶ አደሩ የመሬት ሁኔታ ደግሞ በተቃራኒው አነስተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ለእንስሳት ተብሎ የሚተው መሬትም የለም፡፡ ስለሆነም በዚህ ላይ በትኩረት የሚሰራው የሰብል ተረፈ ምርቶች በየዓመቱ እየጨመረ በመሆኑ ይህን በአግባቡ አስቀምጦ የመኖ ይዘት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንስሳቱን መመገብ እንዲችል የማድረግ ሥራ ነው፡፡ በቆላውም ሆነ በደጋው የሚስተዋሉ ክፍተቶች ቢኖሩም እንደ አገር እስካሁን ያለው የመኖ ፍላጎትና አቅርቦቱ ክፍተት ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በቀጣይ በሚሰሩ ሥራዎች ይሸፈናል፡፡
የግል ባለሀብቱም ሆነ አርሶ አደሩም መኖን እንደማንኛውም ምርት ለማምረት አስቦ መሬት አዘጋጅቶ ዘርቶ ማምረት ይኖርበታል፡፡ በአገሪቱ ሁኔታ እንደሚታየው አርብቶና አርሶ አደሩ እንስሳትን ይይዛል፡፡ ይሁን እንጂ ለእንስሳቱ ተመጣጣኝ መኖ አያዘጋጅም፡፡ ስለሆነም በቀጣይ ለመስራት በተያዙት ዕቅዶች አርሶ አደሩ ቢያንስ ላሉት እንስሳት መኖ ማምረት እንዲችልና በተለይ ደግሞ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከአንድ ዓመት የዘለለ መኖ በሚመረትበትና በሚያዝበት ሁኔታ ላይ ድጋፍ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ ክፍተቱ የመጣው በዋናነት በርከት ያለ የእንስሳት ቁጥር በአገሪቱ በመኖሩ ነው፡፡ አገራዊ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት 14 ሚሊዮን የእርሻ በሬ ያለ በመሆኑ ዓመቱን ሙሉ መኖ ያስፈልገዋል፡፡ አብዛኛው መኖ የሚቀመጠውም ለዚሁ ነው፡፡ የእንስሳት እርባታ ስርዓቱ ገበያ ተኮር አለመሆንም ሌላው ችግር ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ለገበያ መመረት ያለበትንና ለሽያጭ የሚቀርበውንና የሚገኘውን ትርፍ ታሳቢ ያደረገ ባለመሆኑ ምርታማ ሆነም አልሆነ አርሶ አደሩ በርካታ ቁጥር ያለው እንስሳ ይይዛል፡፡
በቀጣይ በዘር ያሉትን ችግሮች መነሻ በማድረግ ገበያ ተኮር የሆነ የእንስሳት ሀብት ልማት ለማስፋፋት እየተሰራ ነው፡፡ አርሶ አደሩም ከቁጥር ይልቅ ጥራታቸው ምርታማ የሆኑ ጥቂት እንስሳትን ይዞ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችል ከማድረግ አንፃር የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ በተለይ በቆላማው አካባቢ አርብቶ አደሩ ተጋላጭነትን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ፕሮጀክቶች ይካሄዳሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ በአጠቃላይ ዋና ማጠንጠኛቸው የመኖ ልማት ሲሆን፤ ይህም ታሳቢ የሚያደርገው አርሶ ወይም አርብቶ አደሩ የእንስሳት መኖ እንዲያገኝ፣ የእንስሳት ጤና አቅርቦት እንዲሻሻልለት በተጨማሪ ደግሞ የገበያ መሠረተ ልማት ተዘርግቶለት ተጠቃሚነቱ የሚረጋገጥበት ሁኔታ ያመቻቻል፡፡ የልማት አጋር ድርጅቶች የመንግስት እንዲሁም የሌሎችም የተቀናጀ ድጋፍ ወይም ሥራ ውጤታማ የሆነ የእንስሳት ሀብት ልማት እንዲኖር ያደርጋል ተብሎም ይታሰባል፡፡
በአሁኑ ወቅት ባለው ሁኔታ ከአርሶ አደሩ የሚገኝ እንስሳት ላይ ያተኮረ ሥራ የሚሰራ በመሆኑም ዘመናዊ የሆኑ ሰፋፊ እርሻ እንዲኖር የግል ባለሀብት ተሳትፎን ያሻል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግስት የፋይናንስ፣ የመሬት አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ቁጥራቸው በርካታ ናቸው ማለት ባያስደፍርም የተወሰኑ የግል ባለሀብቶች በሥራው ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን ይሄ መስፋትና መቀጠል ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
ፍዮሪ ተወልደ