አባቴ ከሄደበት እስኪመለስ በቅናት ዓይን በሚመለከቱኝ የሰፈር ጓደኞቼ ተከብቤያለሁ። ልደቴ መሆኑን ያውቃሉ፤ አባቴ አንበሳ ግቢ እንደሚወስደኝም። የልደት ቀኔን የምወደው አንበሳ ግቢ ሄጄ አንበሳ ከማየት እና ፎቶ ከመነሳት በላይ አንበሳ ግቢ ሄደው የማያውቁትን ጓደኞቼን ስለ አንበሳ ግዙፍነት እያወራሁ ማስቀናት ስለምችል ነው። ልብሴን ቀይሬ ደጃፋችን ላይ በሰፈር ጓደኞቼ ታጅቤ የባጥ የቆጡን እየቀበጣጠርኩ በሚያስቀውም በማያስቀውም እናውካካለን።
ሰዓቱ ደረሰና ለአንድ ሰሞን በሰፈራችን የሚያነግሠኝንና ተደማጭም ወደሚያደርገኝ አንበሳ ግቢ ከአባቴ ጋር አቀናን። ከሰፈራችን ተነስተን አንበሳ ግቢ እስክንደርስ ጋሽ አባተ የግቢው ጥበቃ መሆናቸውን ረስቼዋለው። እኚህ አጭርና ኮስታራ ሰውዬ ከአንበሳ ግቢ በተጨማሪ የትምህርት ቤታችን ጥበቃም ናቸው። ተማሪው ሁሉ ከርዕሰ መምህራችን እና ከተጋራፊዋ ሂሳብ መምህራችንም ይልቅ ይፈሯቸዋል። እርሳቸው ተረኛ ሲሆኑም አርፍዶ የሚገባም ሆነ ያለ ሰዓት የሚወጣ ተማሪ አይኖርም።
የአንበሳ ግቢው በር ላይ እንደደረስንም አባቴ 50 ሳንቲም አውጥቶ ለመክፈል ወደ ጠባቧ መስኮት ሲያቀና እኔና ጋሽ አባተ ፊት ለፊት ተፋጠጥን፤ በጎርናናው ድምፃቸው «አንተ» ሲሉኝማ መንቀሳቀስ ተስኖኝ በቆምኩበት ደርቄ ቀረሁ። በዚያ ሁኔታ አንበሳው ወጥቶ ከፊት ለፊቴ ቢቆም እንደዚህ የምደነግጥ አይመስለኝም። ከልደቴ ሦስት ቀን በፊት የእንግሊዘኛ መምህራችን ቀርቶ ክፍል ውስጥ ስረብሽ መያዜ ነበር ከእኚህ አስፈሪ ጥበቃ ጋር ያገናኘን። ከአንዱ ወንበር ወደ አንዱ ወንበር እየዘለልኩ ስረብሽ፤ ከውጭ የተመለከቱኝ ርዕሰ መምህራችን በንዴት እንደጦፉ ማጅራቴን ይዘው አስወጡኝ። የክፍላችን በር ላይ አንበርክከው ከገረፉኝ በኋላም አትክልት እንድኮተኩት ወደ ጋሽ አባተ ወሰዱኝ።
ጋሽ አባተ የሚያስፈራ ዓይንና ስቆ የማያውቅ ፊት አላቸው፣ እንደቁመታቸው ያጠረችውን አለንጋም ከእጃቸው አይለዩም፤ የአንበሳ ግቢው በር ላይ ግን አልያዙትም። ታዲያ በእሳቸው መሪነት በግቢ ውስጥ የሚገኙ አትክልቶችን መኮትኮት ጀመርኩ። ዙሪያውን ካዳረስኩ በኋላ አንድ ማደግ ላይ ከሚገኝ አበባ ስር ስደርስ ግን የመሃረብ ቋጠሮ ተመለከትኩ፤ ምንም ሳላቅማም አንስቼው በሩጫ ተሰወርኩ።
በንጋታው ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር ከጓሯችን ከሚገኘው ግራር ስር ተሰበሰብን። ያለወትሯችን ጨዋታ ትተን የመስብሰባችን ምስጢር ደግሞ ከትምህርት ቤት ያገኘሁት መሐረብ ነው፤ ነገር ግን መሃላችን አስቀምጠን ከመመልከት ውጭ ደፍረን ቋጠሮውን ለመፍታት አልቻልንም። ገንዘብ፣ ወርቅ ወይም ሌላ ነገር ይኖረዋል ብለን ጓጉተናል፤ እንዳንከፍተውም ድፍረት አላገኘንም ምክንያቱም «ፈንጂ ሊሆን ይችላል» እያለ ከእኛ በዕድሜ የሚበልጠው ቶማስ አስፈራርቶናል። የሆነው ይሁን ብዬ መሃረቡን ፈታሁት፤ ሁላችንም ደነገጥን። በዚያ ዕድሜ ሊገኝ ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል 150 ብር፤ ድፍን100 ብር እና አምስት ባለ አስር ብሮች።
የዚያን ዕለት ከመተኛት ይልቅ በፍርሃትና በደስታ መካከል ስዋልል ሌሊቱን ገፋሁት። ይህን የሚያክል ብር ቆጥሬም ኖሮኝም አያውቅ፤ ከየት አመጣሁት እላለው? አገኘሁት ብል፤ የት? ሰው ሰጠኝ ብል፤ ማን? ልባል ነው። በህይወቴ የመጀመሪያዋን ጭንቀት የቀመስኩት የዛን ዕለት ሳይሆን አይቀርም፤ ቆይቼ ደግሞ ፈጣሪ ለልደቴ አስቦ ነው የሰጠኝ እያልኩ ፍርሃቴን ለመሸሸግ እጥራለሁ። አፍታም ሳልቆይ ደግሞ ፍርሃቴ አገርሽቶ በጨለማ የደበቅኩበትን ፍራሼን እየገለጥኩ መኖር አለመኖሩን በዳበሳ አረጋግጣለው። አይነጋ የለም፤ ሲነጋ ለጓደኞቼ እንደ ቅርበታቸው 50 ብሩን አከፋፈልኳቸው። 100 ብሩን ግን የራሴ ንብረት በመሆኑ ትራሴን ቀድጄ ሸሸግኩት።
በልደቴ ቀንም ከጋሽ አባተ ጋር ተፋጠጥኩ። «አንተ…» እያሉ ተንደርድረው ወደ እኔ ሲመጡ አባቴ ደግሞ ከፍሎ ሲመለስ ተጋጩ። በትንሽ ልጁ እና በጥበቃው መካከል ምን እንደተፈጠረ ያልገባው አባቴ «ምነው ጋሼ?» እያለ መካከላችን ገባ። እሳቸው ግን የኣባቴን ጥያቄ ችላ ብለው «150 ብሬን…150 ብሬን…» እያሉ በመጮህ እኔን ማንገላታት ጀመሩ። ንዴቱ ወደ አባቴም ተጋብቶ «የምን 150 ብር ነው የሚያመጣው?» በማለት ሊያስለቅቀኝ ሞከረ ግን አልቻለም፤ በስንት ትግልም ጋሽ አባተ ለቀቁኝ።
«ማክሰኞ ጥበቃ የምሰራበት ትምህርት ቤት ደመወዜን ሰጥቶኝ በመሐረቤ ጠቅልዬ ከኪሴ ዶልኩት» ይህንን ሲናገሩ በንዴታቸው ምትክ የሮሮ መልክ ተላበሱ። «ጉድ ፈላ፤ አባቴ ጉዴን ከሰማ ይገድለኛል» ትንሿ ልቤ በፍርሃት ራደች። እሳቸውም በደላቸውን «ታድያ ይህ ያንተ ልጅ ጥፋት አጥፍቶ እንዲቀጣ እኔ ዘንድ አመጡት…» ንግግራቸውን ሳይጨርሱ ጣልቃ ገብቼ «ብሩን ወድቆ ነው ያገኘሁት…እመልስልዎታለሁ» አልኩኝ።
ጋሽ አባተ ንዴታቸውን ወደ አባቴ ያጋቡት መሰለኝ፤ እንዲህ ሲቆጣ አይቼው አላውቅም «አንተ ዝም በል» ብሎ አጮለኝ። ጋሽ አባተ ካቆሙበት ቀጥለዋል «አትክልት እንዲኮተኩት ብዬ መኮትኮቻ ሰጥቼው ወደ ክፍሌ ገባሁ»፤ ከዚህ በኋላ ያለውን ታሪክ ለመቀጠል አቅም አጡ መሰለኝ አንገታቸውን አቀርቅረው ብዙ ቆዩ። የአዛውንት በማይመስል ቅልጥፍናም «ብቻ የሰረቀኝን 150 ብር ይመልስልኝ» ብለው የአባቴ እግር ስር ወደቁ።
የጓጓሁለት የልደት ቀን የአንበሳ ግቢ ጉብኝቴም ከበር ሳያልፍ ወደ ቤት ተመለስን። አባቴ ቃል ሳያወጣ ሲራመድ በፍርሃት ነበር የምከተለው፤ ሰፈር ስንደርስ ጓደኞቼ ያየሁትን ሊሰሙ ቢጠጉኝም አንገቴን እንዳቀረቀርኩ አለፍኳቸው። አመሻሹ ላይም እናቴ እሳት እንድታቀጣጥል በአባቴ ታዘዘች። እኔ ደግሞ ሱሪዬን ዝቅ አድርጌ ሳጥኑ ላይ እንድተኛ ተደረገ።
ከዚያማ በቀበቶ እየገረፈ «ሰርቀሀል ወይስ አልሰረክም?» የሚል ምርመራውን ጀመረ። «ሌባ» ተብዬ የባሰ ቅጣት እንዳይደርስብኝም «አልሰረኩም» እያልኩ በለቅሶ ድምፅ እመልሳለሁ። እንዳሰብኩት ሊያምነኝ አልቻለም፤ እንዲያውም «እሳቱን አምጪው» ብሎ በርበሬ ያጥነኝ ጀመር። በርበሬውም መስረቄን እንዳምን ብቻም ሳይሆን መወለዴንም እንድጠላ ነበር ያደረገኝ። ቅጣቴን ስጨርስም የደበቅኩትን 100 ብር እንዳመጣ አዘዘኝ። ከዚያን ቀን በኋላም በልደቴን ቀን አንበሳ ግቢ ሄጄ አላውቅም።
እስካሁን የልደቴ ቀን ሲመጣ ያንን አጋጣሚና፤ 150 ብር የነበረውን ክብር አስታውሳለሁ። በዚያ ዕድሜ አንበሳ ግቢ ሄዶ ለጓደኞች ስለ አንበሳ ባህሪና ሁኔታ እንዲሁም ስለሌሎች እንስሳቶችና አጠቃላይ ሁኔታው ማውራት፤ ክብርን፣ ዝናንና ሌሎች ብዙ የኩራት ስሜትን ያስገኝልኝ ነበር። በጥፋቴ ከመሄድ ስታገድማ ጋሽ አባተ ብሩ የጠፋቸው ዕለት የተሰማቸውን ስሜት ነበር ያስተናገድኩት።
እርሳቸው ከወር ወር ሁለት ቦታ ሰርተው እንደሚያገኟት ጥሪታቸው፤ እኔም አንበሳ ግቢ ለመሄድ በዕድሜዬ ላይ አንድ ዓመት መጨመር ይገባኝ ነበር። በብር የማይለካውንና ከጓደኞቼ የማገኘውን ስሜት መቀማቴ የእርሳቸውን ያህል መከፋት ለማስተናገድ ቅርብ ነበር። አሁን ሳስበው ከሁሉ በላይ የሚያስቀኝ የሰረቅኩት እኔ አንዲት ሳንቲም ሳልጠቀም ይህ ሁሉ ቅጣት ደረሰብኝ። 50ብሩን ያካፈልኳቸው ጓደኞቼ ግን በብሩ ብዙ ነገር ገስተው ‹‹እንቁልልጭ›› እያሉ ሳምንት አብሽቀውኛል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
መርድ ክፍሉ