የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ የያዘ ወቅት ነው። ዘመናዊውን ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመቋደስ እድል ያገኙት ኢትዮጵያውያን ምሁራን ያገራቸው ኋላቀርነት እያብከነከናቸው ለውጥ ለማምጣት በጽሑፋቸውም በተግባራቸውም ታግለዋል። በብዙ ተመራማሪዎች ዕይታ የነዚህ ምሁራን ቁንጮ ተብለው የሚጠቀሱት ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ናቸው።
ገብረሕይወት ባይከዳኝ በ1878 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ፣ ዓድዋ አካባቢ ማይ መሻም በተባለ ስፍራ ተወለደ። አባቱ ሻለቃ ባይከዳኝ ገብረዝጊ የንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ባለሟል ስለነበሩ በንጉሰ ነገሥቱ የመጨረሻ ዘመቻ (የመተማ ዘመቻ) ተሳትፈው በጦርነቱ ላይ ስለሞቱ ሕፃኑ ገብረሕይወት ከእናቱ ጋር መኖር ጀመረ። ከንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ሞት በኋላ ትግራይ ውስጥ በሰፈነው አለመረጋጋትና በወቅቱ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ረሀብ አካባቢውን አስጨንቆት ስለነበር ገብረሕይወት ገና በሰባት ዓመቱ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ወደ ኤርትራ ተሰደዱ። ኤርትራ ውስጥ ምፅዋ አካባቢ ይገኝ ወደነበረ በአንድ የስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብተው መማር እንደጀመሩ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ምፅዋ ወደብ ሄዱ። በወቅቱም በወደቡ ላይ መልህቋን ጥላ ወደነበረች መርከብ ውስጥ ገብተው መርከቧን ማየት ይጀምራሉ። የመርከቧ መነሻ ሰዓት ሲደርስ ገብረሕይወት ከጓደኞቹ ተነጥሎ ቀረ። የመርከቧ ካፒቴን የገብረሕይወትን ተደብቆ መቅረት ያወቀው ብዙ ከተጓዙ በኋላ ስለነበር ምንም ማድረግ ሳይችል ቀረ። መርከቧ ከማረፊያ ቦታዋ ስትደርስ ካፒቴኑ ገብረሕይወትን ለአንድ ኦስትሪያዊ ሀብታም ቤተሰብ በጉዲፈቻ እንዲያሳድገው ሰጠው።
ኦስትሪያዊው ቤተሰብም ገብረሕይወትን ተቀብሎት በዚያው መኖር ጀመረ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ትምህርት ቤት ገባ። በትምህርት አቀባበሉ ቀልጣፋና ጎበዝ የነበረው ታዳጊው ገብረሕይወት ብዙ ጊዜ ሳይፈጅበት ጀርመንኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ቻለ። ከዚያም ወደ ጀርመን ሄዶ እንዲማር ስለተወሰነ ወደ በርሊን ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የሕክምና ትምህርት አጥንቶ ተመረቀ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት የነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በመታመማቸው ንጉሰ ነገሥቱ ከጀርመን መንግሥት ሦስት ሃኪሞች እንዲመጡላቸው ጠይቀው ነበር። የጀርመን መንግሥትም ጥያቄውን ተቀብሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩ ሐኪሞችን ሲመርጥ ሐኪም ገብረሕይወት ባይከዳኝ አንዱ መሆን ቻለ። ይህን እድል በማግኘቱም አሳዳጊዎቹን አመስግኖ ተሰናበተ። ገብረሕይወት ከሌሎች ሁለት ሐኪሞች ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መጣ።
እነ ገብረሕይወት ኢትዮጵያ ሲደርሱ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ታመው ስለነበር የተቀበሏቸው እቴጌ ጣይቱ ነበሩ። እቴጌዋም ከገብረሕይወት ጋር የመጡትን ጀርመናውያን ሐኪሞች ተቀብለው ገብረሕይወት ‹‹ችሎታ አይኖረውም›› በሚል ጥርጣሬ የሕክምና ስራ እንዳይሰሩ ከልክለዋቸው ነበር ይባላል። ገብረሕይወት ኢትዮጵያን የለቀቀው ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ ስለነበር የኢትዮጵያን ባሕልና ቋንቋ ረስቶት ነበር። ደጃዝማች ይገዙ በሃብቴ ለገብረሕይወት አማርኛ የሚያስተምረው ሰው መደቡለት። በሰባት ወራት ውስጥም አማርኛን በሚገባ አቀላጥፎ መናገር ቻለ። አቀላጥፎ መናገር ብቻም ሳይሆን ከጥሩ ዝርው ስነ-ጽሑፍ ፀሐፊዎች መካከል አንዱ እስከመሆን ያደረሰውን ችሎታ አሳይቶበታል። ከገብረሕይወት መጻሕፍት መረዳት እንደሚቻለው ገብረሕይወት የአማርኛ ቋንቋን እጅግ ተራቅቆ ጽፎበታል።
ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከሕመማቸው ካገገሙ በኋላ ደጃዝማች ይገዙ በሃብቴ እና ነጋድራስ ኃይለጊዮርጊሥ ወልደሚካኤል (በኋላ ቢትወደድ) ለንጉሰ ነገሥቱ ስለገብረሕይወት ነገሯቸው። ንጉሰ ነገሥቱም ስለገብረሕይወት በሰሙት ነገር ተደስተው ገብረሕይወትን አስጠሯቸው። ስለትምህርታቸው ከጠየቋቸውና ካነጋ ገሯቸው በኋላም የራሳቸው የግል ፀሐፊና አስተርጓሚ አድርገው ሾሟቸው። ገብረሕይወት ገና በሕፃንነታቸው የትውልድ ቀያቸውን ለቀው በመሄዳቸው ከወላጆቻቸው ጋር ተረሳስተው ይኖሩ ነበር። ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ይህንን ችግር ተመልክተው አዋጅ አስነግረው ከወላጆቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲገናኙ አድርገዋል።
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከሕመማቸው ጨርሰው ሊድኑ ባለመቻላቸው ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ሚካኤል የዙፋናቸው ወራሽ መሆኑን በአዋጅ አሳወቁ። ይህንን ሐሳባቸውን ለውጭ መንግሥታት ለማሳወቅ በፈለጉ ጊዜም ወደ ውጭ መንግሥታት በተላከውና በደጃዝማች መሸሻ ወርቄ በተመራው የልዑክ ቡድን ውስጥ ገብረሕይወት አባል ነበር። የልዑክ ቡድኑም የተላከበትን ተግባር አከናውኖ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል።
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሕመም ላይ በነበሩበት ወቅት እቴጌ ጣይቱ ከጀርመን ሐኪሞች ጋር አለመግባባት ፈጥረው ነበር። ገብረሕይወት በጀርመን ተማሪነታቸውና ከጀርመኖች ጋር በነበራቸው መቀራረብ ምክንያት ከጀርመን ዲፕሎማሲ ስለሚገኘው ጠቀሜታ ደጋግመው በመናገራቸው የእቴጌ ጣይቱን አመኔታ ማግኘት ሳይችል ቀረ።
ሐኪሞቹ ‹‹የንጉሰ ነገሥቱ ሕመም ‹ፓራላይዝድ› (Paralyzed) መሆን ነው። ጳጳሱና እቴጌዋ ግን ሐኪም እንዳይነካቸውና ‹በፀበል ብቻ ይድናሉ› እያሉ በቀዝቃዛ ውሃ ስለሚነክሯቸው ሕመማቸው ባሰባቸው›› በማለት ገለፁ። ከንጉሰ ነገሥቱ ሕመም ጋር በተያያዘ የሚወራው ወሬ ከእቴጌዋና ከሐኪሞቹ አልፎ በመኳንንቱ መካከልም ውዝግብ አስነሳ። ሁኔታው ከኢትዮጵያ አልፎ በጀርመን፣ በፈረንሳይና በኢጣሊያ ጋዜጦች መካከልም የከረሩ የሃሳብ ልውውጦችን ቀሰቀሰ። የዚህ ውጥረትና ብጥብጥ ጦስ በተለይ በወቅቱ በአስተርጓሚነት ያገለግሉ የነበሩ ምሁራንን አጣብቂኝ ውስጥ ከተታቸው። ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሸሽተው ጀርመን ኤምባሲ ውስጥ ተጠለሉ። ገብረሕይወት ደግሞ ወደሱዳን ለመሰደድ ተገደደ። ብላቴንጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴም ‹‹የሕይወት ታሪክ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ‹‹…እቴጌ ጣይቱ ስለተጣሏቸው ወደ ካርቱም ተሰደዱ …›› ብለው ጽፈዋል።
ገብረሕይወት ሱዳን ውስጥ በስደት ላይ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ጀምረውት የነበረውን ‹‹አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› የተሰኘውን መጽሐፍ ጽፈው ጨረሱ። ከሱዳን ሲመለሱም በፅኑ ታመው ስለነበር ምፅዋ ሆስፒታል ገብተው ተረፉ። በዚህ ጊዜ በገንዘብ የረዷቸው ወዳጃቸው አቶ ጳውሎስ መናመኖ ነበሩ። በወቅቱ ገብረሕይወት ለአቶ ፓውሎስ መናመኖ የጻፈው የምስጋና ቃል ‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› የተሰኘው መጽሐፍ ሲታተም በመጽሐፉ መግቢያ ላይ አብሮ ታትሟል።
ገብረሕይወት ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ የእቴጌ ጣይቱን ከቤተ መንግሥት ስራ መወገድና የልጅ ኢያሱን ስልጣን መያዝ አውቀው ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው መጡ። ልጅ ኢያሱም ተቀብለዋቸው በቤተ መንግሥት ውስጥ የግምጃ ቤት ሹም አደረጓቸው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሁኔታ መሻሻል ሊያሳይ አለመቻሉ፣ ልጅ ኢያሱም ለማሻሻል ይህ ነው የሚባል እርምጃ አለመውሰዳቸውና አንዳንድ ጊዜም የአልጋ ወራሹ የልጅነት ባህርያት ያስከፏቸው ነበር። ገብረሕይወት የሚያስቡትን በድፍረት የመናገር ልማድ ስለነበራቸው ከልጅ ኢያሱ ጋር የነበራቸው ግንኙነትም እየተበላሸ ሄደ። መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ተሽረው ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት፤ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) ደግሞ አልጋ ወራሽ ሆነው ሲሾሙ፣ ገብረሕይወት የፍራንኮ-ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኩባንያ ተቆጣጣሪ ሆነው ተሾሙ። ለአንድ ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ በ1910 ዓ.ም የድሬዳዋ ነጋድራስ ተባሉ። በስራቸው ላይ ከነበራቸው ጥንቃቄና ጉብዝና ባሻገር ለአገራቸው መሻሻል ያስቡ ስለነበር ሃሳቦቻቸውም ጠንካራ ነበሩ።
ነጋድራስ ገብረሕይወት ከጀርመን ተመልሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር በማወዳዳር ይበሳጩና ይፀፀቱ ነበር። ‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› እና ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› የተባሉት ዘመን ተሻጋሪ መጽሐፎቻቸውም የዚህ ፀፀት ውጤቶች ናቸው። በነዚህ መጻሕፍት የኢትዮጵያ ወደኋላ መቅረት በእጅጉ እንዳሳሰባቸውና እንዳሳዘናቸው በጠራ ቋንቋና በሚገርም አገላለፅ አስረድተዋል። የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ጨምሮ የወቅቱን ሹማምንት ድክመቶችም ገልጸዋል።
‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለታሪክ ምንነትና አፃፃፍ፣ ስለኢትዮጵያውያን የታሪክ ፀሐፍት ድክመቶች እንዲሁም የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ጨምሮ የአፄ ዮሐንስ ፬ኛንና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥታትን በአጭር በአጭሩ ቃኝተውበታል። ስለታሪክ ጥቅምና አፃፃፍ እንዲሁም ስለኢትዮጵያውያን የታሪክ ፀሐፍት ድክመቶች ሲያስረዱ …
‹‹ታሪክን መማር ለሁሉ ሰው ይበጃል፤ ለቤተ-መንግሥት መኮንን ግን የግድ ያስፈልጋል፤ የዱሮ ሰዎችን ስህተትንና በጎነትን አይቶ ለመንግሥቱና ላገሩ የሚበጀውን ነገር ያውቅ ዘንድ። የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅም የእውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው። እውነተኛንም ታሪክ ለመፃፍ ቀላል ነገር አይደለም። የሚከተሉት ሦስት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ያስፈልጋሉና። መጀመሪያ ተመልካች ልቦና የተደረገውን ለማስተዋል። ሁለተኛ የማያደላ አዕምሮ በተደረገው ለመፍረድ። ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ የተመለከቱንና የፈረዱትን ለማስታወቅ። ያገራችን የታሪክ ፀሐፊዎች ግን በነዚህ ነገሮች ላይ ኃጢአት ይሰራሉ። በትልቁ ነገር ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ። ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጥባሉ። አፃፃፋቸውም ድብልቅልቅ እየሆነ ላንባቢው አይገባም … ›› አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ፣ ገፅ 1
በተለይ በዚህ መጽሐፍ የመጨረሻ ክፍል ላይ ‹‹ … መንግሥታችን እንድትቀና የሚከተሉት 10 ነገሮች በቶሎ ቢፈፀሙ ማለፊያ ነበር … ›› ብለው የጠቀሷቸው ምክረ ሃሳቦች የነጋድራስ ገብረሕይወትን የአዕምሮ ምጥቀትና የአገር ፍቅር በግልፅ አሳይተዋል። ትምህርትና ስርዓት የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፎች እንደሆኑ በፅኑ ያምኑ ነበር።
ነጋድራስ ገብረሕይወት በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ምን ያህል እንዳስጨነቃቸውና እንዳበሳጫቸው ለመገንዘብ በዚሁ መጽሐፋቸው ላይ ከተጠቀሱት ሃሳቦች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት …
‹‹ … ትምህርት በሌለው ሕዝብ ዘንድ ንጉሥ ማለትና መንግሥት ማለት ትርጉሙ አንድ ነው። ንጉሳቸውም የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል። በመላው ሕዝቡ ባሮቹ ናቸው … አዕምሮ ባላቸው ሕዝቦች ዘንድ ግን መንግሥት ማለት ማኅበር ማለት ነው። ንጉሣቸውም የማኅበራቸው አለቃ ነው። ስለዚህ ንጉሱ የፈቀደውን ያደርግ ዘንድ አይችልም። ስልጣኑ የሕዝቡ ማኅበር በደነገገው ሕግና ወግ የተወሰነ ነው … አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ስርዓት የለውም። ስርዓት የሌለው ሕዝብም የደለደለ ኃይል የለውም። የኃይል ምንጭ ስርዓት ነው እንጂ የሰራዊት ብዛት አይደለም። ስርዓት ከሌለው ሰፊ መንግሥት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች … ›› አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ፣ ገፅ 9-10
‹‹ … ንጉሱ ቢታመሙ ሃሳባቸው ስለምን በውጥን ቀረ? የሚፈፅመው ሰው ታጣ? አዎን። የሚበዙ ሹማምንቶቻቸው እንኳን የታሰበውን ነገር ሊፈፅሙ የተፈጸመውም ቢፈርስ ግድ የላቸውም። የሹሞቹ ስንፍና አያስደንቅም፤ ካለመማራቸው የተነሳ ነው። ያልተማረ ሰው ሁሉ የራሱን እንጂ ያገሩንና የመንግሥቱን ጥቅም ሊያስብ አይችልም። ስለዚህ በገንዘብ ይታለላል፤ ቢያኮርፍም ይሸፍታል፤ ስለመንግሥቱም ልማት መከራን ችሎ ተዋርዶ ከሚኖር ብዙ ሰው ፈጅቶ አገርንም አጥፍቶ ቢሞት ወይም ቢታሰር ስም ይመስለዋል›› አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ፣ ገፅ 17
‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የተካተቱት ሃሳቦች ነጋድራስ ገብረሕይወት ‹‹ልማታዊ ምጣኔ ሀብት (Development Economics)›› ከሚባለው የምጣኔ ሀብት ዘርፍ አንዱን ክፍል ገና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከማንም ቀድመው እንደተራቀቁበት ማሳያዎች ስለመሆናቸው ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች ገልፀዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ስራዎች በአንድ ጥራዝ በታተሙበት ‹‹ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ – ስራዎች›› በተሰኘው መጽሐፍ መቅድም ላይ እንዲህ ብለዋል …
‹‹ … ነጋድራስ በ1950ዎቹ በደቡብ አሜሪካ ተፈጠረ የተባለውን በመዋቅራዊ ችግሮች ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ አተናተን (Structural Economics)፣ በተለይ ደግሞ የፕሬብሽንና የፕሮፌሰር ሲንገርን ስራዎች፣ የታዋቂዎቹን የእንግሊዛውያን ኢኮኖሚስቶች የፕሮፌሰር ፒጉና ኬንስን እንዲሁም የፖላንዱን ስመ ጥር ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ሚካኤል ካልስኪን ስራዎች እርሳቸው ቀድመው አውቀውት በዚህ መጽሐፍ (‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር››) ጽፈውት ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም እ.አ.አ በ1970ዎቹ በፈረንሳዊው ፖለቲካል ኢኮኖሚስት አርጌ ኢማኑኤልና እና በግብፁ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ ሳሚር አሚን እንደተተወረ የሚነገርለት ‹‹ያደጉና ያላደጉ አገራት ያልተመጣጠነ የንግድ ሁኔታ ትንተና›› በዚህ መጽሐፋቸው ቀድመው ትወራውን አድርገውት ነበር። ሆኖም በአማርኛ ስለፃፉት ይሁን ከአፍሪካ ስለሆኑ እርሳቸው ቀድመው የፈለሰፉትን አስተሳሰብ ሌሎች 40ና 50 ዓመታት ዘግይተው ሲያውቁት በኢኮኖሚክሱ ዓለም ገናና እና ታዋቂ ሆኑበት … ይሁን እንጂ ልማታዊ ምጣኔ ሀብት (Development Economics) ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓና በአሜሪካ ኢኮኖሚስቶች እንደተፈጠረ ነው ዛሬ ብዙ ተመራማሪዎች የሚያውቁት …
እንግዲህ ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ነው የልማት ምጣኔ-ሐብታዊ ትንተና የሚባለው ትምህርት መሰረቱ አፍሪካ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ መሆኑን መጠቆም የምፈልገው። በተጨማሪም የነጋድራስ ስራዎች ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔ የሚጠቁሙ ቁልፍ ስራዎች መሆናቸውን አስረግጬ እገልፃለሁ … ››
ይህ መጽሐፋቸው ሕክምና ተምረው ሳለ ፖለቲካል ኢኮኖሚን አበጥረው ያብራሩበት ስራቸው መሆኑ የገብረሕይወትን ችሎታ አስደናቂ ያደርገዋል። እስቲ ከመጽሐፉ ሃሳባቦች ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት ፡- ‹‹ … ማናቸውም ሕዝብ ከፍ ወዳለው የእውቀት ደረጃ እንዲደርስና ሀብት እንዲያገኝ በውስጡ ያሉት የያይነቱ እቃ ሰራተኞች በቶሎ እየተገናኙ የተለዋወጡ እንደሆነ ነው … ›› መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፣ ገፅ 131
‹‹ … የመንግሥት መሰረት ትምህርት ቤት ነው። ትምህርት በሌለበት አገር አዲስ ደንብ ቢወጣ ከሚጠቅመው የሚጎዳው ይበልጣል …›› መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፣ ገፅ 148
‹‹ … የማናቸውም መንግሥት ሀብትና ኃይል የሚያድገው ሕዝቡ በስራ የሰለጠነ እንደሆነ ነው … በስራ በሰለጠኑ ሕዝቦች አገር ጥቂቱ ብር እንኳ ስለብዙ ሆኖ በሁለትና በሦስት ወገን ሊሰራ ይችላል። ሕዝቡ በስራ ባልሰለጠነ አገር ግን እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን ነገር በፍጥነት አያገኝምና አንዳች ነገር ሸጦ የተቀበለው ብር ወደ ሌላ እጅ እስኪያልፍ ደረስ ብዙ ጊዜያት ይሄድበታል … ›› መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፣ ገፅ 151-158
በርካታ አንጋፋ የኢትዮጵያ ሹማምንትና ምሁራን ስለነጋድራስ ገብረሕይወት ታታሪነት፣ አገር ወዳድነትና የአዕምሮ ንቃት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከነዚህም መካከል …
‹‹ነጋድራስ ገብረሕይወት በጣም እውነተኛ፣ ቅን፣ ለስራ ትጉህና ወስላታነትን የሚጠላ ሰው ነበር። ከጉብዝናውና አርቆ አሳቢነቱ የተነሳ የሁላችንንም ሃሳብ መለወጥ ችሏል›› ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ::
‹‹ነጋድረስ ገብረሕይወት በስራው ጥንቁቅ፤ በአነጋገሩ ደፋር ነበርና በጊዜው ከነበሩ ሰዎች ጋር አልተስማማም ነበር›› ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ።
‹‹ገብረሕይወት ከትምህርቱ ተግባሩ፤ ከተግባሩ ትምህርቱ የተዛመደ ተደናቂ ሰው ነው›› አለቃ ታዬ ገብረማርያም ::
‹‹ገብረሕይወት ባይከዳኝ ብልህና አዋቂ በመሆናቸው በዘመናቸው የነበረውን ሕዝብ ለማስተማር አንድ ጠቃሚ የሆነ የአስተዳደር መጽሐፍ ጽፈዋል›› ብላቴንጌታ ማኅተመሥላሴ ወልደመስቀል ::
‹‹ከዘመኑ ምሁራን ሁሉ ልቆ የሚታየው ገብረሕይወት ባይከዳኝ ውጭ አገር ሄዶ ዘመናዊ ትምህርት ሊቀስም የቻለው በግል ጥረቱ ነው። ወደ አገሩ ተመልሶ ዓለምን ያስደነቀው በሕክምና ጥበቡ ሰይሆን የፖለቲካ ኢኮኖሚን አበጥሮ በማወቁና በተለይም ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ለማዛመድ በመቻሉ ነው …›› ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ።
ለአገራቸው ቅን አሳቢና ታታሪ የነበሩት ባለብሩህ አዕምሮው ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ በ33 ዓመታቸው ሰኔ 24 ቀን 1911 ዓ.ም ሐረር ከተማ ውስጥ አረፉ።
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
አንተነህ ቸሬ