ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተከስተው ለነበሩ የህዝብ ቅሬታዎችና ግጭቶች አንዱ መንስኤ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም መንግስት እያካሄደው ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ለአገልግሎት አሰጣጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት በተለያዩ ተቋማት ሪፎርሞች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም መነሻነት ሰሞኑን ምሁራን፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት “በሁለንተናዊ ተሳትፎና አገልግሎት የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ በቅንነት የሚያገለግል የሲቪል ሰርቪስ እንፍጠር” የሚል መድረክ ለ5ኛ ጊዜ አካሂዶ ነበር፡፡ እኛም በመድረኩ ላይ በመገኘት የተለያዩ አካላትን አነጋግረን የሚከተለውን አዘጋጅተናል፡፡
የምሁራን አስተያየት
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዳንኤል ሊሬቦ፤ የከተማ ዲዛይንና ፕላኒንግ ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የማንኛውም መንግስታዊ ተቋም ግብ የተገልጋይን እርካታ ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህም ምን ይደረግ? በሚል በመንግስት የሚከናወኑ ተግባራት በመልካም የሚታዩ ናቸው ይላሉ፡፡ ግን ደግሞ ከመንግስት ውጪ በግለሰብ፣ በአካባቢ እንዲሁም በተቋም ደረጃ የሚደረግ ለውጥ አስፈላጊና መሠረታዊ መሆኑንም ከግንዛቤ መክተት ይገባል፡፡ ለውጤቱ የድንጋይ መሠረት የሚሆነውም በዋናነት የግለሰብ ለውጥ ነውና፡፡
እያንዳንዱ ግለሰብ በዕውቀትና በክህሎት የታነፀ ሲሆንና ሲለወጥ ተቋሙ እንደሚለወጥ ዲኑ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አዳዲስ ፅንሰ ሃሳቦችንና ቴክኖሎጂዎችን ፈጣሪ፣ የሚያሰባስብና የሚፈላሰፍ ሠራተኛ መፍጠር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ዕቅድ የሌለው ባለሙያ ሊኖር የማይገባውም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ዕቅዱን አውቆ እየሰራ ነው ወይ? ሥራውን የሚለይና ምን ውጤት እንደሚያመጣ መተንበይ የሚችል ባለሙያስ አለ ወይ? በተገቢውና በሚመጥነው ቦታ ላይ ተቀምጦስ ነው ወይ እየሰራ ያለው? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙና ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የተለየ ነው የሚሉት ዶክተር ዳንኤል በተቋም ውስጥ ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ለቦታው የሚመጥኑ ኣካላትን ወደ ጎን በማለት ከሌላ ቦታ ኃላፊ ይሾማል፡፡ ይህም ሥራው ላይ ተፈላጊው ውጤት እንዳይመጣ ማነቆ ከሚሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡
ችግሮችን ለማቃለል እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሚና ያለው በመሆኑ ወደ ራሱ ሊመለከት ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ‹‹እኛ የቱ ጋር ነው ያለነው? በአገሪቱ በርካታ ችግሮች ለምንድነው በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ ሊመጣባቸው ያልቻለው?›› በሚል መፈተሽ ይገባል፡፡ ዶክተር ዳንኤል፤ ለዚህ ችግር አንዱ የጊዜ አጠቃቀም እደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ሠራተኛው ተሰብስቦ በሃሜት የሚያሳልፈው ጊዜ ለሥራ ከሚሰጠው ሰዓት የበለጠውን ይይዛል፡፡ ይህም ለመመራመርና ለፈጠራ ጊዜ እንዳይኖር ሸብቦ የሚይዝ አደናቃፊ መጥፎ ባህል ነው ሲሉም ይተቻሉ፡፡
ሥራን መሠረት ያላደረጉ ወሬዎች ከጥበቃና መዝገብ ቤት ጀምሮ የተሰጠውን ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ መወጣቱንም አጠራጣሪ ያደርገዋል የሚሉት ዶክተር ዳንኤል ችግሩን ለማቃለል ለውጡን እንዴት አድርገን በተሳለጠ መልኩ መውሰድ ይቻላል? በሚል ስትራቴጂ መቅረጽ ለዛም የሚረዳ ማስፈፀሚያ መዋቅርና የሰው ኃይል ማስቀመጥ ይገባል ይላሉ፡፡ አክለውም በከተማ መሬት አስተዳደር በማስተርስ ደረጃ የተማሩ ዜጎች መዝገብ ቤት ሲመደቡም ይስተዋላል፡፡ ይህም ትልቅ ብክነት ነው፡፡ ምን ያክል ብር ወጥቶ ይህ ሰው እንደተማረ ማሰብ እንዲሁም ይህን የኖረ ድርጊትም የሚቀይር አመራር ያስፈልጋል፡፡ ከችግር ተላቆም ያደጉ አገራት ተርታ ለመሰለፍ ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ሥራ መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ይሆናል፡፡ በተያያዘ መደጋገፍን ባህል በማድረግ ትስስሩን ማሻሻል ይቻላል፡፡ ተከታታይ አቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው ወይ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ መስራትም እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለፃ በአገሪቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ከተያዘ አበቃ፡፡ ተከታታይ የሠራተኛውን አቅም ሊያጎለብቱና ተቋሙን ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ስልጠናዎች አይሰጡም፡፡ ዓለም ተቀያያሪና በቴክኖሎጂም ከቀን ወደ ቀን ተለዋዋጭ ነው፡፡ ስለሆነም ሰው ተምሮ አበቃ ብሎ ማሰብ አይገባም፡፡ ዘወትርም አቅምን ለማጎልበት በልዩ ትኩረት መስራትን ይጠይቃል፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮም ከተለያዩ አካላት ጋር ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል፡፡ ይህም የሰላ አቅም በመፍጠር ዕመርታዊ ለውጥን ለማስመዝገብ ይረዳል፡፡
መንግስት ተዓማኒነትን ማግኘት የሚችለው ጥራት ያለው አገልግሎትን ለህዝቡ ማድረስ ሲችል ነው የሚሉት ዶክተር ዳንኤል ጥራቱ የሚመጣውም በክህሎትና ዕውቀት የበለፀገ ባለሙያ ሲፈጠርና ይህንን ሊያግዝ የሚችል አሰራር ሲዘረጋ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በከተማዋ የመሬት አስተዳደር፣ የገቢዎችና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ታይቷል፡፡ በመሆኑም መንግስት ከህብረተሰቡ ተዓማኒነት እንዲያገኝ ምን ይደረግ? ምን ይሰራ? የሚለው መታየት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ የተለያዩ ተቋማት ሰነዶችን ማህደሮችን የሚሰርቁ ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት በመኖራቸውም የመረጃ አያያዝ ስርዓቱም ሊፈተሽ ይገባል፡፡
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ዮሴፍ ቤኮ በአገሪቱ ትልቅ ሃብት ፈሰስ ከሚደረግባቸው ዘርፎች መካከል አንዱና ዋነኛው ትምህርት መሆኑን ነው የሚልጹት፡፡ ዘርፉ በአገሪቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍቻ ቁልፍና ለውጥ አምጪ መሣሪያም ነው፡፡ ምሁሩ ሆኖ ተመራምሮ ለአገር ለውጥ ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ተማሪውም ተምሮ አገሩን የሚያገለግል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው፡፡
በጀቱ መልካም ዘርን ለማብቀል ሳይሆን ለጥፋት እየሆነ እንዳለ የተለያዩ ማሳያዎች እንዳሉም ነው አቶ ዮሴፍ የሚያመላክቱት፡፡ ተማሪው እየተለመነ የሚማርበት አገር እየሆነ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡ ትልቅ የአገር ሃብት ፈሰስ ተደርጎበት ከሚጠበቅበት በተቃራኒ ጎዳና ሲገኝ ከዚህ በላይ ልብ ሰባሪ ሁነትም አይኖርም፡፡ ተማሪ ከክፍል ወደ ክፍል ሲሄድ ሀሞቱ የፈሰሰ የደብተር አያያዙ የወደቀ አካሄዱ ዘገምተኛ የመሆኑ ምስጢር ለችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነውና መፈተሽ ይገባል፡፡ ምሁሩስ የሚጠበቀውን ለውጥ ያላመጣው ለምን ይሆን? ብሎ መጠየቅም ይገባል፡፡ ምሁሩ ተመራምሮ ለውጥን ካላመጣ፣ ተማሪው ካልተማረ እንዲሁም ፐብሊክ ሰርቪሱ ከአገልጋይነት ይልቅ ተገልጋይ መሆን ካማረው አገሪቱ በሚጠበቀው የለውጥ ጎዳና በተቃራኒው እየተጓዘች መሆኗን መገንዘብ የግድ ይሆናል፡፡
ጀግንነት ማለት ለሌሎች መኖርና አለፍ ሲልም መሞት በመሆኑ አገርን ለመለወጥ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ተገቢ አይሆንም፡፡ ደመወዝ አልበቃኝም፤ ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረልኝም፤ ወዘተ የሚሉ አስተሳሰቦችን ገለል በማድረግም መሥራት መፍትሔ እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡ ከፍተኛ የሕዝብ ተወካይ ሆነው የተቀመጡ የሥራ ኃላፊዎች ዜጎች በተሰማሩበት ቦታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ነው ወይ? በሚል ታች ወርደው መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ በማለት በዋናነት ግን አገልጋይ የሚፈጠርባቸው የትምህርት ተቋማት ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚኖርበት አቶ ዮሴፍ ያሳስባሉ፡፡
የነዋሪዎች እይታ
ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወይዘሮ ሣራ ሽፈራው ሌሎች አገራት ላይ እንኳን አይደለም የህዝብ አገልጋይ የቤት ውስጥ ለግል ፍጆታ የሚውል ምግብ እንኳ ሲሰራ ታቅዶ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ ግን ነገሮች በተቃራኒው ሆነው ይስተዋላሉ፡፡ ይህም የሚያመላክተው የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ነው፡፡ መፍታት እየተቻለ ዙሪያ ጥምጥም አሰራር በመዘርጋት ባለጉዳይ እንዲያለቅስ የሚደረግበት ሁኔታም ተገቢነት የጎደለው ነው ሲሉ ይኮንኑታል፡፡ በአመራር ደረጃም ሆነ ታች ያለው ባለሙያ ቀና አመለካከት ቢላበስ መልካም ይሆናል ባይ ናቸው፡፡ ጦርነትንም ሆነ ለሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መነሻ የአስተሳሰብ ችግር ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ ቆም ብሎ ማገናዘብ ይገባል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቀና ሲሆን ነውና አገሩን መለወጥ የሚችለው ችግር እንኳ ባይፈታ ጊዜ ሰጥቶ ማዳመጥም ትልቅ ነገር ነው ሲሉ ያሳስባሉ፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪው ወጣት ማቲዎስ ብርሃኑ በበኩሉ፤ በከተማዋ ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ በርካታ ማህበራት በዘመቻ ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን በማንሳት ሃሳቡን ይጀምራል፡፡ በለውጡም አዲስ በሥራው ላይ የተመደቡ ሥራ አመራሮች ቤቶች ልማት የሚያስተዳድራቸው 18 ያክል የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳሉ በማንሳት ከወጣቱ ተነጥቀው ሙሉ በሙሉ ለባለሃብት መሠጠታቸውን ይገልፃል፡፡ ለውጥ እየተደረገ ነው በሚል ምላሽም 19 የሚደርሱ ማህበራት እንዲፈርሱና ባለሃብቶች እንዲሰሩ መደረጉን ይናገራል፡፡
ወጣት ማቲዎስ፤ ድርጊቱ ለውጥ ማለት ምንድን ነው የሚል ጥያቄንም ያጭራል ይላል፡፡ ለውጥ ማለት አመራር መቀየር፤ የነበረውን አፍርሶ አዲስ መገንባት ሳይሆን ቀደም ሲል ከነበረው አሰራር መልካም ጎኖቹን በመያዝ ህዝብ ቅሬታ ሲያነሳባቸው የነበሩ ድክመቶችን አንስቶ ወደ ተሻለ መንገድ መሄድ ነውና ሊታይ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው አገራዊ ለውጥ ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው ከመቀበል አኳያ ምን ይመስላል? የሚለው መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ብዙ ጊዜ መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ትኩረታቸው ከላይ ያለው ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በታችኛው መዋቅር ያሉ የመንግስት አስተዳደሮች ህብረተሰቡ በቀጥታ የሚያገኛቸው ወረዳና ክፍለ ከተሞች ላይ ሰፊ ችግሮች ይስተዋላሉና ለውጡ ሊጎበኛቸው ይገባል ይላል፡፡ ታች ያለው የቀድሞው አመራርና ባለሙያ ነው፡፡ በከፍተኛ የአመራር እርከን ላይ ያሉትን መቀየር ማለትም ለውጥ መጥቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በተለይ ሠራተኛው ሠዓት ከማክበር እንዲሁም ባለጉዳይን በአግባቡ ከማስተናገድ ጋር ተያይዞ የነበሩበት ችግሮች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
ወጣት ማቲዎስ ቢፈተሹ ብሎ ካነሳቸው ተቋማትም ውስጥ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አንዱ ነው፡፡ “ተቋሙ የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል መብት ገለልተኛ ሆኖ ሲያገለግልና ምን ሲሰራ እንደነበር አይታወቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት ካለው ለውጥም ተነስቶ ራሱን አይቶ ከተለጣፊነት ነፃ ሆኖ ሊሰራ ይገባዋል” ይላል፡፡ በተመሳሳይ የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሊፈተሽ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ኮሚሽኑ በተቋቋመበት ጥቂት ጊዜ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሰራቸው ሥራዎች እንዳሉ ባይካድም ማሻሻያ ተደረገ በሚል ስልጣኑ ወደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሄዱን ይገልፃል፡፡ ከዛም ከሀብት መዝጋቢና አስተማሪነት ያልዘለለ ሚና እንዳይኖረው ሆኗል፡፡ ይህም ተቋም በተመሳሳይ በለውጥ ውስጥ በመግባት ጥርስ ያለው ተቋም እንዲሆን ቢደረግ ከሥራዎች ጎን ለጎን ተጠያቂነትን ለማስፈን ይረዳል ይላል፡፡
የከተማዋ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ታላቅነት ካለመገንዘብና ታሪክን ባለማወቅ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈጠሩ ሆነዋል ሲሉ ሃሳባቸውን ይጀምራሉ፡፡ አገር ምንድነው? ብሎ ከማሰብ ይልቅ ግለኝነት ገንግኗል፡፡ በየቤተ ዕምነቱም ስለ ሃይማኖቱ ስለ አንድነትና መልካምነት እንዲሁም ቅንነት ሳይሆን እንዴት ተደርጎ የግል ሃብት እንደሚያካብትና እንደሚሰረቅ ነው የሚሰማው፡፡ ስብሰባም ላይ ቁጭ ሲባል ስለ አንድ ወገን ሃጥያትና ጥፋት ነው የሚወራው፡፡
ከቤት ጀምሮ እስከ አገር መልካምነትንና ፍቅርን ማስተማር ላይ ትኩረት ስለማይደረግ ቅንነት እንደጠፋም ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ ቅንነት ከሌለ ደግሞ ለውጥ ይኖራል ብሎ ማሰብ አዳጋች ይሆናል፡፡ መጀመሪያ ለውጥን ለመቀበል ቅንነትና መልካምነት ለነገሮች ያለ አተያይም ወሳኝ ነው፡፡ ባገኘው እርካታ የሌለውና ቀድሞ በዚህ ገንዘብ እንዴት እሰራለሁ? የሚል አመለካከት የተጠናወተው ዜጋም ይታያል፡፡ ይህም አገልግሎት ሰጪው የሚጠበቅበትን ሥራ በሚፈለገው ልክ እንዳያከናውን ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹የማገኘው ይበቃኛል›› የሚል አመለካከት ሊጎለብት ይገባል፡፡ አልያ ግን የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየጎመሩ በሄዱ ቁጥር ለሰላምም አስተማማኝ አይሆንምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
የሥራ ባህሉም ሊስተካል ከሚገቡ ጉዳዮች ውስጥ መሆኑን ነው ኮማንደር ፋሲካው የሚገልጹት፡፡ በዚህ ላይ ማስተማርና አስተሳሰቡን መቀየር ቀዳሚ ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡ በተቋማት ውስጥ ሥራን ከመስራት ይልቅ በየኮምፒውተሩና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠምዶ የሚውለው ሠራተኛ አብላጫውን ቦታ የሚይዝ በመሆኑ መታየት አለበት፡፡ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣትም የሚስተዋሉ መጥፎ ድርጊቶችን ወደ ጎን በማለት መልካም ባህሎችን በማዳበር እያጠናከሩ መሄድ የተሻለ ነው፡፡
ከልደታ ክፍለ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ተፈራ በበኩላቸው ሲቪል ሰርቪሱ ከከተማው ህዝብ አንድ በመቶ ያልበለጠ ቢሆንም የማይደርሰው የህብረተሰብ ክፍል ግን የለም ይላሉ፡፡ ይህ ውስን አገልግሎት ሰጪ ጋር የነበሩ ክፍተቶችም ለህዝቡ ብሶትና አሁን ለሚታየው ለውጥም መነሻ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ መሻሻሎች ቢኖሩም በዘላቂነት ችግሮቹን ለማቃለል ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለይቶ በማወቅ መፍታት ይገባል፡፡
ዘርፉ መለወጥ ካልቻለ ለውጥን በተሳለጠ ሁኔታ ማስቀጠል አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ከዚህ አንፃርም አመራሩ ምን መደረግ አለበት? ችግሩስ ምንድነው? የሚለውን ነቅሶ በመያዝ ማስተካከል አለበት፡፡ ውጤታማ ሲቪል ሰርቪስ ከመፍጠር አንፃር ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተመዘገቡ ውጤቶች በማየት የነበሩ ሰፋ ያሉ ክፍተቶች እንደነበሩበትም ኃላፊዋ ያምናሉ፡፡ የችግሮቹ ምንጮችም መንግስት የአሰራር ስርዓቱን በጥልቀት ተመልክቶ ከመፈተሽ አንፃር እንዲሁም ግልጽ የሆነ አሰራር በመፍጠርና ከማዘመን አንፃር የነበሩ ችግሮች ናቸው፡፡
ኢፍትሃዊ የሆኑ አሰራሮችም ይታዩ እንደነበር ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ያስታውሳሉ፡፡ ከተማው ብቻ ለመፍታት ስለተነሳ ሊፈታቸው የማይችላቸው ችግሮችም አሉ፡፡ ያልተጠኑና ረጅም ጊዜ የፈጁ ለዚህ በጣም ቁጥሩ አነስተኛ ለሆነ ሠራተኛ ፍትሃዊነትን ከማስፈን አንፃር ሊታዩ የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸው ይስተዋላል፡፡ የደመወዝ አከፋፈል ጋር በተያያዘም አገሪቱ ታዳጊ ናት፡፡ ሆኖም ሊከፈል የሚገባው ግን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ስለሆነ ሥራና ሥራን መሠረት አድርጎ የሚከናወነው የሥራ ደረጃ አወሳሰን በአገር አቀፍ ደረጃ መተግበር በከተማዋም መፍጠን እንደሚኖርበት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ይናገራሉ፡፡
ከፌዴራል ሥነ-ምግባና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ከፍያለ፤ ተቋሙ ላይ የተነሱ ችግሮች ትክክል እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ተቋሙ ተጨባጭ ጥናቶችን ማካሄዱንና ለሚመለከታቸው አካላት መስጠቱንም ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም የአቅሙን ቢፍጨረጨርም የኋላ ኋላ ግን አቅም እያነሰው እንደሄደ ነው የገለፁት፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ አከርካሪው እየተመታ ደካማ እንዲሆን መደረጉን በገሃድ ሲታይ እንደነበርም ያነሳሉ፡፡
ዘርፉ እንዲወቀስ በማድረግ በዚህ ድክመትም መንግስትና ህዝብ እንዲራራቅ ሲቪል ሰርቪሱ ላይ የተወሰኑ የተዘበራረቁ አሰራሮች እንዲኖሩ የተደረገው ሆን ተብሎም ነው ሲሉ አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡ ይህን ተከትሎም የታከቱ ችግሮች መኖራውን በማንሳት የሥራ ኃላፊዎች ምደባ አንዱ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ አሰራሩ ኃላፊዎች የራሳቸውን ሰው ከሲቪል ሰርቪስ ስርዓት ውጪ ለመሰብሰብ ያስችላቸዋል፡፡ ባልተገባ ትስስር የመጣ ሠራተኛ ለአምጪው ታማኝ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ምዝበራ ሲፈፀምም ሆነ ሌሎች ችግሮች ሲከሰቱም ከማጋለጥ ይልቅ ባለመነካካት ዝምታን መርጦ እንዲቀመጥ ያደርገዋል፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ የተጠያቂነት ስርዓቱ መዳከምም ሌላው ችግር ነው፡፡ በተቋሙ በስምንት ወራት ውስጥ 15 የሚደርስ የአሰራር ስርዓት ጥናት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ያጠፉ ተጠያቂ የተደረገበት ሂደት የላላ ነው፡፡ በዚህም ጥፋተኛ የሚመሰገንበትና የውሸት ሪፖርት የሚያሸልምበት ተገላቢጦሽ ሁኔታ ይታያል፡፡ በሥራቸው የተመለከቷቸውን ችግሮችን ሲያነሱም በከተማዋ ግዙፍ ግዢዎች ተፈፅመው ሲፈተሽ ግን መረጃዎች የሉም፡፡ የችግሮቹ ግዝፈትም ከተማዋም ሆነች አገሪቱ መኖሯ እስኪያጠራጥር ድረስ ጎልቶ ይታያል፡፡ በመሆኑም የነበረው ሂደት ተቀይሮ ይህች ለመላ አገሪቱ ምሳሌ የሆነችው ከተማ የተሻለች እንድትሆን የሚመለከታቸው አካላት በሚገባ ሊመለከቱት ይገባል፡፡ ከውይይት ባሻገር ጥልቀት ያለው ጥናት በማድረግ በቁርጠኝነት ችግሮችን ለማቃለል መነሳትንም እንደሚጠይቅ አቶ ተስፋዬ ይገልፃሉ፡፡
ማጠቃለያ
የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የግል፣ አካባቢያዊና ተቋማዊ ለውጦች ወሳኝ እንደሆኑ የሚያነሱት ዶክተር ኤርሴዶ ለንዴቦ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቫንት ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃፀር እንኳ መወዳደር የማይችል በእጅጉ አነስተኛ የወር ገቢ እንደሚያገኝ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም እንኳ ከሚጠበቅባቸው በላይም የሚሠሩ ባለሙያዎች ይገኛሉ ሲሉ የሥራ ሁኔታን ምቹ ማድረግ ለአገልግሎት አሰጣጡ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
የተለያዩ አካላት ሲቪል ሰርቪሱ እንደበዛ ሲያነሱ ይደመጣል፡፡ መቆረጥ እንዳለበት ሃሳብ ከሚያነሱት ውስጥ ዓለም ባንክ አንዱ ነው፡፡ ይህም ትክክል አይደለም ተብሎ መውሰድ አይገባም፡፡ በትክክልም መቀነስ ያለባቸውና ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ መመልከት ይገባል፡፡ በመሆኑም የማያስፈልጉ ሥራዎች ካሉ መቀነስ ሊሰሩ የሚችሉትን ማከፋፈል ሊተኮርበት ይገባል በማለት ዶክተር ኤርሴዶ ያመላክታሉ፡፡ በተመሳሳይ ስድስት ወር ሆኖ ወደ ዓመት ሊቀየር የሚችል እንዲሁም መቀነስ ያለባቸው የሥራ መዘርዝሮች ሊለዩ ይገባል፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይም በአገሪቱ በወረቀት የሚሰራ ሥራ በብዛት ይታያል፡፡ ይህን ለማሻሻልም ተቋማት ሊሰሩ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ መረጃዎችን በተቀናጀ ሁኔታ ወደ አንድ ቋት በማድረግ ስርቆትን ብልሹ አሰራሮችንና የመረጃ መሰወር እኩይ ተግባራትንም መከላከልና መቆጣጠር እንደሚቻል በመጠቆም ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ላይ ትኩረት ቢሰጥ የተሻለ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ በየተቋሙ ከሚሰራው መዋቅርና አቅም ግንባታ ስራ ጎን ለጎንም ተጠያቂነቱ ቸል ሊባል የማይገባ አንኳር ጉዳይ ነው፡፡ ከመንግስት ውጪም እያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ዕቅድ እያዘጋጀና እየፈፀመ ለአገሩ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ከቻለ ለውጡን በተሟላ ቁመና እንዲራመድ ያስችላል፡፡ ማህበራትና የግል ዘርፉም ከመንግስት ላይ ተቀንሶ የተለያዩ ሥራዎች ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ነፃነት ዳባ በበኩላቸው፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች አንጥሮ መለየት እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡ በዚህም ዋና ዋና ክፍሎች ላይ ሪፎርም ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ረጅም ጊዜ የቆዩ አሰራሮች እየተፈተሹ ሲሆን፤ እነዚህን ማስተካከልም ለለውጡ አንድ እርምጃ ሊሆን ይችላልና ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን አሁንም ፐብሊክ ሰርቪሱ ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት ይነሳል፡፡
ወይዘሮ ነፃነት፤ ከክፍያ ፍትሃዊነት፣ ደመወዝ ማነስ እንዲሁም መሰል ችግሮች ጋር በተያያዘ የሚነሱት ችግሮች ተገቢ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ችግሮቹን ለማስተካከልም በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ ይህ ብቻ እንዳልሆነም ያነሳሉ፡፡ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ መሬት ልማት ማጅመንትና መሰል ተቋማት የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ተደርጎ አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም ዳሩ ግን አሁንም በዛ ያለው ሠራተኛ እየረካ አይደለም፡፡ አሁንም በተለያየ መንገድ የህዝብ ቅሬታና ሮሮ በተቋማቱ ይሰማል፡፡ ይህም የችግሮቹ ምንጭ ክፍያ ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡
በቅንነት ማገልገል ራስን ከማሻሻል ይጀምራል የሚሉት ወይዘሮ ነፃነት፤ ለውጡ መሬት እንዲረግጥ ከግለሰብ ጀምሮ የተለያዩ አካላት ድርሻ እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ትምህርት ቤቶችና ማህበረሰብ የዜጎችን ሥነ-ምግባር መቅረጽ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ የሥራ ቦታዎችን ምቹ ማድረግ ደግሞ ሌላው ሥራ ይሆናል፡፡ ለዚህም ወረዳ መዋቅር ጀምሮ ሰፊ ሃብት በመኖሩ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን በማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ማድረግ ከተቻለ ችግሮቹን በአጭር ጊዜ በማቃለል ለውጡን ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ይህም ለእያንዳንዱ ችግር መንግስትን ከመጠበቅ ባለፈ መፍትሔ አካል እየሆኑ መሄድንም ያካትታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
ፍዮሪ ተወልደ