አዲስ አበባ፡- አቅማቸው በቻለው ሁሉ አገሪቷን ጠብቀው ለዚህ ትውልድ ያስተላለፉት አረጋውያንን መደገፍና መንከባከብ በመብታቸው እንጂ የችሮታ ጉዳይ እንዳልሆነ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ ትላንት የአረጋውያን ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ28ኛ ጊዜ በሚሊኒየም አዳራሽ በተከበረበት ወቅት፤ አረጋውያን በወጣትነትና በአፍላ የእድሜ ዘመናቸው ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው፤ ለአረጋውያን ክብር መስጠት፣ ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ እንደ መብት የሚነሳ እንጂ የችሮታ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ አረጋዊያን በተለያየ ጊዜ በአገር ላይ የተጋረጠውን ችግርና ፈተና የቱንም ያህል ቢበዛና ቢፈራረቅ ሳይበገሩ ኢትዮጵያን ዛሬ ላይ አድርሰዋል፡፡ ልጆቻቸውም ዛሬ በእነርሱ ቦታ ተተክተው ሊያከብሯቸው ይገባል፡፡ የአረጋውያን ጉዳይ ሥርዓት በተዘረጋለት መንገድ በጋራ ካልተያዘ በዓል በማክበርና ሰሞነኛ ትኩረት በማድረግ ብቻ ችግሩን ማቃለል እንደማይቻልና የህይወትን ቀጣይነት የሚያሳዩት አረጋውያን መብታቸው በአግባቡ ሊከበርላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ያለ አረጋውያን ልፋትና ድካም ህልውናዋ መቀጠል አይችልም ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ በርካታ አረጋውያን ሰርቶ የማደር አቅም በተሟጠጠበትና የጤና መታወክ በሚያጋጥምበት ዕድሜ ላይ ያለ ደጋፊ ቀርተው ለተጎሳቆለ ኑሮ የሚዳረጉበት አጋጣሚ በገሀድ እየታየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ስለሆነም በአገራዊ ለውጥ ጉዞ ውስጥ የአረጋውያን ችግር ተግባራዊ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ አረጋውያንን በእኩልነት ይዞ መቀጠል የእያንዳንዱ ባለ ድርሻ አካል ጥረት ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡
የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የስነ ህዝብ እድገትና ስብጥር ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት፤ ማንንም ሰው ወደ ኋላ መተው እንደማይገባ በተለይም የአረጋውያን ጉዳይ ችላ ማለት እንደማይገባ ፕሬዚዳንቷ አስታውቀዋል፡፡
የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ዛሬ በዚህ ትውልድ ይዞታ ሥር የሚገኙ ነባር ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት ሁሉ የአረጋውያን አሻራ ያረፈበት ከመሆኑም በላይ አረጋውያን የኖሩበት ዘመን የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ የተከፈለበት ስለሆነ፤ ለአረጋውያን ክብር በመስጠት ማህበራዊ ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹የአባትና የእናትን፣ የአያትና ቅድመ አያትን፣ የትላንት መልካም አገራዊውን ውሎ የመዘከር አደራን የመቀበል ማህበራዊ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ሰው የትውልድ ክብር ሊሰማው ይገባል›› ብለዋል፡፡
አረጋውያንን ለመንከባከብ የሚያስችል አገራዊ አቅም ገና በጅምር ላይ የሚገኝና ያልጎለበተ በመሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ከፍ እንደሚያደርገው፤ በተለያዩ ተቋማት ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም፤ አረጋውያንን በመንከባከብና ችግራቸውን በማቃለል ረገድ እያበረከቱ የሚገኘው ድርሻ የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
አገር አቀፍ የአረጋውያን ቀን ‹‹የለውጥ ልማታዊ ጉዞ አረጋውያንን በእኩልነት ይዞ›› በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ29ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012
አዲሱ ገረመው