አዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢህአዴግና የኦዲፒ ሊቀ መንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበርና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፥ አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ባህል እና ሀሳብ እንደሌለው መገዳደል እና መሰዳደብ ትክክል አይደለም፤ ፖለቲካችንን ማዘመን ይጠበቅብናል ብለዋል።
ባሉን ሀሳቦች ላይ በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ህጋዊ በሆነ መንገድ ፍላጎታችንን ከግብ ማድረስ እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ሀሳቦቻችንን ለህዝብ ለመግለፅ እና ለመታገል የሰው ልጅ መታሰር፣ መንገላታት እና መጎዳት የለበትም፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተወያየን መስራት እንችላለን የሚለው ትልቅ ሀሳብ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ይህ ሀሳብ እዚህ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም የሚሰራ ይመስለኛል ብለዋል በንግግራቸው።
“በውስጡ ሰላም የሌለው ሰው ለሌላው ሰላም መስጠት አይችልም፤ ለራሳችን የተሻለ ሀሳብ ከሌለን ለሌሎች ማካፈል እንችልም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስለዚህ እየተወያየን እና እርስ በእርስ እየተማማርን የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን መወያየትና በጋራ መስራት በጣም ወሳኝ ነው ብለዋል።
በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች አሁን ላይ እንደ አዲስ ጥያቄ ሆነው መቅረብ አይችሉም ያሉት ዶክተር አብይ፥ አሁን እያደገ ያለውን እና እንደ ሀገር ትልቅ ኃላፊነት የወሰደውን ህዝብ በምን መልኩ አዳዲስ ሀሳብ አምጥተን ሀገሪቱን ማሸጋገር እና በአፍሪካ ቀንድ የራሳችንን ሚና መጫወት አለብን የሚለው ላይ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል የተካሄደውን ምክክር ያዘጋጁትን አካላት ያመሰገኑት ዶክተር አብይ “የኦሮሞ ህዝብን ከኛ የሚጠብቀው ይህንን ነው፤ የኦሮሞ ሽማግሌዎች የትገቡ ለሚለውም ምላሽ የሚሰጥ እና ለወጣቶችም ትምህርት የሚሰጥ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አክለውም ቀጣዩ ምርጫ ያለምንም ጥርጥር ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ይሆናል፤ ህዝቡም ከዚህ በኋላ በሃሳብ የፈለገውን አካል የመምረጥ እድል አለው ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን በኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የጀመረው በጋራ የመስራት የምክክር መድረክ እንደ ሀገር በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ማደግ እንዳለበት እና ፖለቲካ ፓርቲዎች በምን መልኩ አብረን ብንሰራ ሀገሪቱን ማሸጋገር እንችላለን የሚለው ላይ ቁጭ ብለው መምከር እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁለት ቀናት ሲያደርጉት የነበረውን የምክክር መድረክ በትላትናው እለት ከስምምነት ላይ በመድረስ አጠናቀዋል።
በስምምነቱ መሰረትም በኦሮሞ ህዝብ ተጠቃሚነት ላይ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው በጋራ ባወጡት መግለጫ ያስታወቁት።
በዚሁ መሰረት የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የኦሮሞ አመራሮችን በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብ (ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ) እንዲመሰረት ተስማምተዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና ግጭቶችንም በዚሁ የኦሮሞ አመራር ጥላ ስር ቀርቦ እልባት እንደሚያገኝም አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሰላምን አስመልክቶም በክልሉ የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፥ በክልሉ ግጭቶችን ለማስቆም እና ሰላምን ለማስፈን በጋራ ለማስራት ተስማምተዋል።
ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃ እና ግልፅ እንዲሆን በቅንጅት ለመስራት እና ምርጫው በክልሉ በምን መልኩ መካሄድ አለበት የሚለው ላይም ተመካክሮ ውሳኔ ለማሳለፍ ከስምምነት ደርሰዋል።
በመጨረሻም በስብሰባው ላይ የተካፈሉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በስምምነት
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012