ሀገራችን በለውጥ ጎዳና እየተራመደች ትገኛለች። በለውጡ የህዝቡ የዘመናት ጥማት የሆኑትን ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማምጣት፣ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ወዘተ የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው። ባለፈው አንድ ከዓመት በላይ ጊዜም ብዙ ስኬቶችን ማጣጣም ተችሏል።
ለውጡን ተቋማዊ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችም እየተከናወኑ ናቸው። ህጎች ለውጡን እንዲሸከሙ ተደርገው እየተሻሻሉ ሲሆን፣ ለውጡን ማስቀጠል የሚችሉ አመራሮች በመሰየምም ነው ስራዎች እየተከናወኑ የሚገኙት።
ገና ከጅምሩ ከዚህ በተቃራኒው የቆሙ ኃይሎች ለውጡን ከማጣጣል በተጨማሪ ለማሰናከል ያልሽረቡት ሴራ፣ ያልጫሩት እሳት የለም። በየአካባቢው በቀሰቀሱት ግጭት የዜጎች ሕይወት አልፏል፤ በሚሊዮኖች የሚቀጠሩም መፈናቀላቸው ይታወሳል። እነዚህ ዜጎች እድሜያቸውን ሙሉ ያፈሩት ጥሪት የማንም መጫወቻ ተደርጓል።
ይህ ሁሉ ሆኖም ለውጡ ከጉዞው አልተገታም። ግጭት በመቀስቀስ የተጠመዱ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለሕግ ሲያቀርብ ቆይቷል። እሳት ከማጥፋት አልፎ ሴራዎችን በአጭሩ ወደ ማክሸፍም ተሸጋግሯል።
በቅርቡ ደግሞ ለሀገሮች ሁሉ አስቸጋሪ የሆነውን የአሸባሪዎች ድርጊት በእንጪጩ ማስቀረት ያስቻለ ታላቅ ተግባር ማከናወን ተችሏል። በእዚህም ሀገር ውስጥ በመግባት የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲዘጋጁ የነበሩ የአልሸባብና የአይኤስኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። እነዚህ አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር ባይውሉ ሀገሪቱ ምን ያህል ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ እንደሚደርስባት መገመት አይከብድም።
አልሸባብ በሶማሊያ ላይ በየእለቱ የቦንብ ጥቃት በማድረስ ሶማሌያውያን በደም አበላ ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ ይታወቃል። ኬንያንም በተደጋጋሚ አጥቅቷታል። የባህር ላይ ውንብድና በመፈጸምም አለምን ጭምር አውኳል።
አይኤስ ኤስም በአለም በሰፊ አካባቢ ላይ የሽብር ተግባር የሚፈጽም ቡድን ነው። ኢትዮጵያን ቀደም ሲል ረግጧት ባያውቅም የክፋቱን ልክ በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸመው እኩይ ተግባር መረዳት ይቻላል።
ኢትዮጵያ ፊቱንም ቢሆን ለአልሸባብ ተበግራ አታውቅም። በሶማሊያ ከአፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከሶማሊያ መንግስት ጋር በመሆን አልሸባብን ስታዳክም ቆይታለች። ይህ ብቻም አይደለም ሶማሊያን ለመቆጣጠር ያለመውን ሁሉ ስታከሽፍበት ቆይታለች።
አሸባሪዎችን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻል ከፍተኛ ስራን ይጠይቃል። አልሸባብ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ክፍተቶችን በመጠቀም አላማውን የሚያሳካ መስሎት ሀገራችንን በፍንዳታ ሊያምስ ተዘጋጅቶ እንደነበር ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ሀገሪቱ የእነዚህን አሸባሪ ቡድኖች ሴራ ነው እንግዲህ ማክሸፍ የቻለችው።
የቡድኖቹ ሴራ መክሸፍ ከዚህም በላይ ትርጉም ይኖረዋል። የሀገሪቱ የደህንነት እና የፀጥታ ዘርፍ በጠንካራ መሰረት ላይ እየተገነባ ስለመሆኑም አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። የደህንነት መስሪያ ቤቱም ሆነ የጸጥታ ሀይሉ በሪፎርም ውስጥ የቆዩ መሆናቸው ይታወቃል። ይህ ስኬትም የሪፎርሙን ስኬት ጭምር ያመለክታል።
ሀገራችን በዚህ በተያዘው ወር ብሔራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በአላትን ያለምንም የፀጥታ ችግር ማክበር ችላለች። ይህ ደግሞ ትልቅ ስኬት ነው። በተለይ አብዛኞቹ በአላት በአደባባይ የሚከበሩ እንደመሆናቸው የጸጥታ ሀይሉን ስራ ከባድ እንደሚያደርጉት ይታመናል። በዚህ ላይ ደግሞ ባለፉት ዓመታት እንደተስተዋለው ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች በህብረተሰቡ ውስጥ ሽብር በመንዛት ብቻ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉባቸው እድሎች እንዲህ አይነቶቹን በአላት መጠቀም ነው። ይህ ሁሉ አለመሆኑ የእነዚህ ኃይሎች እጅ እንዲሰበሰብ ማድረግ ያስቻለ ተግባር መከናወኑን ያመለክታል።
የሀገሪቱን ሰላም በማረጋገጥ በኩል የተከናወኑ ተግባሮች እነዚህን ስኬቶች ቢያጎናጽፉንም፣ አሁንም ሰላሙን ዘላቂ በማድረግ በኩል ሊሰራባቸው የሚገቡ ተግባሮች እንዳሉም ሰሞኑን በምእራብ ወለጋ፣ በጎንደር እና በሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ግጭቶች አመላካች ናቸው።
ግጭት በተቀሰቀሰ ቁጥር የአካባቢው ህዝብ ይጎዳል። የሌሎች አካባቢዎች ህዝብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። የሰላምና መረጋጋት ችግር የሚታይባቸውን አካባቢዎች ለመታደግ አሁንም የተጠናከረ ተግባር ማከናወን ይገባል። ህዝቡን ይዞ የማይወጣ ዳገት የማይወረድ ቁልቁለት የለምና እንደ አስከ አሁኑ ሁሉ ህዝቡን በማሳተፍ ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሴራ ማምከን ብቻም ሳይሆን ሴረኞቹን በቁጥጥር ስር ማዋልም ይገባል።
መሳሪያ አንስቶ ጫካ የገባ አካል ካለም ለሰላም ሲባል የተወሰኑ እርምጃዎችን በመሄድ ቀርቦ መነጋገር ያስፈልጋል። ጸረ ሰላም ኃይሎች ራሳቸው አይመጡም፤ እጃቸው ግን ረጅም ነው። እጃቸውን መቁረጥ የሚቻለው ቀለቡን ለእነሱ የማይሰጥ ህብረተሰብ በመፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ጸረ ሰላም ኃይሎች ተላላኪ እንዳይኖራቸው ለማድረግ አሁንም በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2012