የታሪክ ድርሳናት ቢጠቀሱ፤ ታሪክ አዋቂዎች ቢጠየቁ፤ የሕግ አንቀጾች እማኝ ቢሆኑ፤ ሕዝባዊ እና ማኅበራዊ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ሁነትና ክስተቶች ቢፈተሹ፤ ኢትዮጵያ እና የባሕር በር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ስለመሆናቸው በድፍረት ይገልጣሉ፡፡ ይሄው የታሪክም፣ የማኅበራዊ ስሪትም፣ የመልክዓ ምድርና ኢኮኖሚያዊ ሁነትም፣ የሕግ ማዕቀፍም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች እማኝ የሚቆሙለት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ታዲያ፤ ዛሬ ላይ ከእውነቱ በራቀ፣ ከታሪኩ ባፈነገጠ፣ ከሕግ አንቀጾች እማኝነትም በተዛነቀ መልኩ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነት ከፊት ቀድሞ ይገለጣል፡፡
ይሄ ሁነት ደግሞ በቀጣናው ከፍ ያለ ተፅዕኖም፣ የዲፕሎማሲ የስበት ማዕከል፣ የአዳጊ ኢኮኖሚ ባለቤት፣ ከፍ ያለ የሕዝብ ቁጥር እና ሌሎች ጎልተው ቀጣናዊውን ብቻ ሳይሆን አሕጉራዊ ከፍታዋን የሚመሰክሩ ጉዳዮች ላሏት ኢትዮጵያ ትልቅ ራስ ምታትም፤ የሕልውና አደጋም ጭምር ሆኖ የተከሰተ ሐቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ አዳጊ ኢኮኖሚ ባልተቆራረጠ የዕድገት መስመር ለመራመድ፣ ከውጪም መግቢያ፣ ከውስጥም መውጫ በር ይፈልጋል፡፡
ይሄ መውጫ በር ደግሞ አንድም በአየር፣ ሁለትም በምድር፣ ሦስተኛም በባሕር ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ በተለይ ዓለምአቀፍ የንግድና ኢኮኖሚ ክዋኔዎችን ከማሳለጥ አኳያ የባሕር በር ጉዳይ በምንም ሊተካ የማይችል ዐቢይ የሀገራት ኢኮኖሚ ሳንባ ነው፡፡ ይሄ ሳንባነቱ ታዲያ ለኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የሠላምና ፀጥታ ጉዳይን በእጅጉ የሚፈትን፤ በተለይም የአንድን ሀገር ሕዝብ ክብር፣ የሀገርንም ሉዓላዊነት፤ በጥቅሉም የሀገርና ሕዝብን ሕልውና የሚወስን እስትንፋስን መውሰጃ ጭምር እንጂ፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ፣ አንድም የሕዝብ ቁጥሯ በእጅጉ እያደገ ከመሆኑ አኳያ፤ ይሄንን የሕዝብ ጥያቄ የሚመልስ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ስላለባት፤ ለኢኮኖሚዋ የአየር ዝውውር አቅም የሚሆን የባሕር በር ያስፈልጋታል፡፡ ሁለትም እያደገ የመጣው ኢኮኖሚዋ የሚፈጥረው ተደማሪ የውጭ ተፅዕኖም ሆነ የሉዓላዊነት ስጋት በመኖሩ፤ ይሄንን የሉዓላዊነት ስጋት መመከት የሚያስችል አቅም መገንባት ስላለባት፤ ለዚህ የሚሆን የባሕር መዳረሻና በራሷ ሊከፈትና ሊዘጋ የሚችል ቁልፍ የጨበጠችበት የባሕር በር የግድ ይላታል፡፡
እነዚህ እና ሌሎች ዐበይት የሀገርን ሕልውና ጉዳይ የሚፈታተኑ ጥያቄዎቿን የምትመልስበት፤ ለዚህ የሚሆን አቅምና ቁመና የምትፈጥርበት ይሄ የባሕር በር ጉዳይ ታዲያ፤ ዝም ብሎ በምኞት የሚገኝ አይደለም፡፡ ይልቁንም የታሪክም፣ የማኅበራዊ ክስተትም፣ የሕግ አንቀጾችም፣… የሚሰጧትን መብት ተጠቅማ፤ የጎረቤት ሀገራትን ብሎም የቀጣናውን አብሮና ተባብሮ የመልማትና የማደግ አጀንዳ አስቀድማ፤ ከምንም ይልቅ ሠላማዊ ውይይትና የሰጥቶ መቀበል የድርድር መርሕን ተከትላ በመስራት ስለመሆኑ ታምናለች፡፡
ማመን ብቻም አይደል፣ የሕልውናዋ አደጋን በማጤንና የቀጣናውን ወንድማማችነትና አቅምን አሰብስቦ አብሮ የመልማት ፍላጎት ማዕከል በማድረግ፤ ለሁሉም የጎረቤት ሀገራት የተባብረን እንበልፅግ ጥሪን አቀረበች፡፡ ይሄ ጥሪ ደግሞ ያለ ልዩነት ለሁሉም የቀረበ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥሪ በልኩ ተገንዝባ ምላሽ የሰጠችው ግን ሶማሊላንድ ብቻ ነበረች፡፡
ይሄ ለኢትዮጵያም፣ ለሶማሊላንድም መልካም ዕድል፤ ለቀጣናውም ትልቅ አቅም የሚሆን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከፍ ስትል፤ ኢትዮጵያ ስትበለፅግ፤ ኢትዮጵያ አቅም ስትፈጥር ማየትም መስማትም የማይፈልጉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፤ ይሄንን የሁለቱን አካላት የባህር በር ተጠቃሚነት ስምምነት እንደ ትልቅ ስጋት በመቁጠር ከፍ ያለ የውንጀላ ተግባር ውስጥ ሲገቡ ታየ፡፡ ብሂሉ ግመሉም ይሄዳል፤ ውሾቹም ይጮኃሉ ነውና፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የሁለትዮሽም፤ ለቀጣናውም አቅም የሚሆነውን ስምምነት ከዳር ለማድረስ፤ በሌሎች ላይ የተፈጠረውን ብዥታም የማጥራት ሥራቸውን አቀናጅተው በመጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይ ደግሞ በሶማሊያ እና በግብጽ በኩል የተያዘው እና ኢትዮጵያን በማዳከም ውስጥ ቀጣናውን የሁከትና ብጥብጥ ማዕከል፤ በኢኮኖሚም የተዳከመ ቀጣና ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ከውንጀላ እስከ የወታደራዊ ኃይል ትብብር የደረሰው ምኞት በዚህ ረገድ ከፍ ያለ ድርሻ አለው፡፡ በዚህ ረገድ፣ ግብጽ ቀድሞም ቢሆን የኢትዮጵያ አቅም ማደግ በእጅጉ የማይዋጥላት፤ ይሄን መንገዷን ለማደናቀፍም ከጥንት ጀምሮ በቀጥታ ጦር አዝምታ ጭምር ለመውጋት ሞክራ ያልተሳካላት ናት፡፡
የሶማሊያ ጉዳይ ግን፣ ትናትን እንደ ሀገር የመዝለቅ ሕልውናዋ በተፈተነ ጊዜ፤ መንግስት አልባ ሁና በሽብር ቡድኖች በምትተራመስበት ወቅት፤ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍላ እንደ ሀገር እንድትቀጥል፣ ባለ መንግስትም እንድትሆን፣ ዛሬም ድረስ በዚሁ አግባብ ዋጋ እየከፈለችላት ላለችው ኢትዮጵያ በዚህ ልክ ከታሪካዊ ጠላት ጋር አብሮ የችግር ምንጭ ለመሆን እየተጓዘች ያለችበት አካሄድ በእጅጉ ሊጤን የሚገባው ነው፡፡
ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ ማንንም ለመጉዳት ወይም ለመውረር አይደለም፡፡ ይልቁንም በወንድማማችነት መንፈስ፤ አቅምን እና ሀብትን በጋራ አሰባስቦ መሥራት እና በጋራ አብሮ ማደግና መበልጸግ የሚቻልበትን መርህ የተከተለ ነው፡፡ ይሄን የምታደርገውም በሰላማዊ መንገድ፣ በጎረቤት ሀገራት መልካም ፈቃድ እንጂ ጦር በማዝመት አይደለም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከመልካም መርህ ያልወጣ፤ ፍጹም ሰላማዊ እና በቀጣናው ሀገራት መካከል ወንድማማችነትና አብሮ የመበልጸግ እድልን የሚሰጥ የሕልውናዋ ጥያቄ መሆኑን መገንዘብ ይገባል!
አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም