የገጠር መንገድ ግንባታና ጥገና መርሀ ግብሩን ለማሳካት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ የመንገድ መሠረተ ልማት ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ያለውን ሚና በሚገባ በመገንዘብ ከሌሎች የልማት እቅዶቿ እኩል ለዋና ዋና እና ለገጠር መንገዶች ልማት ትኩረት ሰጥታ ትሠራለች፡፡ በዚህም በተለይ በዋና ዋና መንገድ ተደራሽነት ላይ ጉልህ የሚባል ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡

ሀገሪቱ ይህን የመንገድ ልማት በማስፋት በገጠር መንገድ ልማት ላይም እንዲሁ ትኩረት ሰጥታ ለመሥራት ተንቀሳቅሳለች፡፡ በዚህም እንዲሁ ወረዳን ከቀበሌ ፣ ወረዳን ከዋና ዋና መንገዶች ለማገናኘት ጥረት ተደርጓል፡፡

በመንገድ ልማቶቹ የአርሶ አደሩን ምርት ወደ ገበያ ፣ የግብርና ግብዓቶችን ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ ከፍተኛ ሚና መጫወት ያስቻሉ የአስፋልትና የጠጠር መንገዶችን መገንባት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መንገዶቹ በሀገሪቱ ለተመዘገበው የምጣኔ ሀብት እድገትም የራሳቸውን ዐሻራ ማኖር የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በተለይ በገጠር የሚታየውን የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ውስንነት ለመፍታት የራሱ የሆነ የገጠር መንገድ ልማት መርሀ ግብር በመቅረጽ፣ በዘርፉ ልማት ያለውን የተቋራጮች ቁጥር ውስንነት በማስፋት፣ በማሽነሪዎችና በሠለጠነ የሰው ሃይል በኩል ያለውን አቅምም በማጎልበት በኩል በስፋት ተሠርቷል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በቅርቡ እንዳስታወቀውም፤ ባለፉት ዓመታት በገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም የሀገሪቱን የመንገድ አውታር መጠን እና ተደራሽነት ትርጉም ባለው መልኩ ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል። ፕሮግራሙ በሀገሪቱ የገጠር ቀበሌዎችን በሙሉ በአቅራቢያቸው ከሚገኝ ደረጃውን ከጠበቀ ዋና መንገድ ለማገናኘት ታሰቦ የተዘጋጀ ነው። በዚህ ፕሮግራም ብቻ 50 ሺህ ኪሎ ሜትር የተለያየ ደረጃ ያላቸው መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ ይህ ግን መንገዶችን ለመገንባት የተቀመጠው ግብ የተመታበት እንዳልሆነም ተጠቁሟል፡፡

መንግሥት ይህን የገጠር መንገድ ልማት ለማስቀጠል የሚያስችል ተግባር ሲያከናውን ቆይቶ በቅርቡ ደግሞ አዲስ የገጠር መንገድ መርሀ ግብር ይፋ አድርጓል፡፡ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ‹‹የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና›› በሚል በሚካሄደው የመንገድ ልማት ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ እንዳመለከተው፤ በፕሮግራሙ በዋናነትም የሰባት ሺህ 554 ኪ.ሜ የወረዳ መንገድ ግንባታ፣ የአስር ሺህ 71 ኪ.ሎ ሜትር የወረዳ መንገዶች ጥገና፣ የ373 ተንጠልጣይ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች እንዲሁም የ715 የቆላማ አካባቢ መሻገሪያ ድልድዮች ግንባታዎች ይካሄዱበታል።

በፕሮግራሙ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ለ200 ሺህ ዜጎች በቀጥታ እንዲሁም ለ360 ሺህ ዜጎች ደግሞ በተዘዋዋሪ የሥራ እድል ይፈጥራል። ወደ ግንባታ ለመግባትም ከሚመለከታቸው የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት አካላት አስፈላጊው ውይይት ተደርጓል፡፡

ግንባታው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሁሉም ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 112 ወረዳዎች የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ከዓለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲሁም ከክልል መንግሥታት በሚመደብ 107 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ለእዚህም አስፈላጊዎቹ የዝግጀት ሥራዎች ተጠናቀዋል።

የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማም የገጠሩን ማህበረሰብ እርስ በርስ እና ከማአከላት ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም ተነጥለው ያሉ አካባቢዎችን በማገናኘት እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የገጠሩን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እና ለገበያ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ያለውን ተደራሽነት ማሳደግ ነው።

የፕሮግራሙ ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ትርጉም ያላቸውን ለውጦች ለማምጣት እየሠራች መሆኗ ይታወቃል፤ ይህን ተከትሎም በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አድናቆት የተቸራቸው ለውጦችንም ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡ በቀጣይም በዘርፉ ሰፋፊ ለውጦችን ለማስመዝገብ እየተሠራም ነው፡፡

ይህ ፕሮግራምም የሀገሪቱ አቅዶች፣ ራእዮችና ግቦች እንዲሳኩ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በተለይ ሀገሪቱ በመንገድ ልማት ዘርፍ ስታካሂድ ለቆየችው ተግባር መጎልበት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት በኩልም የራሱ ሚና ይኖረዋል፡፡

የልማቱ ቱሩፋት ከሆነው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በመነሳት አርሶ አደሩ የሚያደርገው ምጣኔ ሀብታዊም ሆነ ማህበራዊ አንቅስቃሴ እንዲጎልበትም ይጠቅማል፡፡ ገበያ ፣ ትምህርት ቤት ጤና ተቋምና የመሳሰሉት በቀላሉ ደርሶ መመልስ ይችላል፡፡

የግብርና ልማቱን በሜካናይዜሽን ለማከናወን በሚደረገው ጥረት ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ እንዲሁም የግብርና ምርቶችን ደግሞ ወደ ገበያ ማእከላት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ወይም ወደ ሽግግር ማእከላቸው ለማድረስ የእነዚህ መንገዶች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ ፕሮግራም እንዲመጣ ለማድረግ ብዙ እንደተሠራ መገመት ይቻላል፡፡ ፕሮግራሙ በሚገባ ተካሂዶ የተፈለገውን ግብ እንዲመታ ማድረግ ላይም እንዲሁ በትኩረት መሥራት ቀጣዩ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡

ለእዚህም ከሁሉም የክልልና የፌዴራል መንግሥት የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም ከመላው ሕዝብ ብዙ ይጠበቃል፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት እንዲገነቡ በማድረግ በኩል የእነዚህ አካላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ይሆናል፤ ሀገሪቱ በፕሮጀክት ግንባታዎች እያሳየች ያለችውን ለውጥ በእነዚህ ግንባታዎች ለመድገም መሥራትም ያስፈልጋል፡፡

የፕሮግራሙ መሳካት በተለይ በግብርናው ዘርፍ እንደ አጠቃላይም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ ለስኬቱም የሚደረገው ርብርብ የተጠናከረ ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You