አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል አርሶአደሩ ምርቱን በተገቢው ዋጋ ሸጦ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ፡፡
በቢሮው የሰብል ልማትና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ሂርጳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አርሶደሩ በተለያዩ ህገወጥ ደላሎችና ሌሎች ምክንያቶች ምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዳያገኝ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ቢሮውም እነዚህን ችግሮች ለማቃለል እና የአርሶደሩ ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ደጀኔ ገለጻ፤ አርሶአደሮች በተለያየ ምክንያት ተገድደው ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ የሚያውጡበት ሁኔታ ከተፈጠረ በቀጥታ በደላሎች እጅ ከሚሸጡ ይልቅ የራሳቸው ንብረት በሆነው በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል እንዲሸጡ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነዚህ ማህበራት እህሉን ከአርሶአደሮች ላይ ገዝተውና ገበያው ጥሩ ዋጋ በሚኖርበት ወቅት ሸጠው ትርፉን ለአርሶአደሩ ስለሚያከፋፍሉ፤ አርሶአደሩ ለደላሎች ሸጦ የሚያጣውን ዋጋ በትርፍ ክፍፍል እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን አርሶአደሩ አንድ ዓይነት እህል ላይ ሊያተኩር አይገባም የሚሉት አቶ ደጀኔ፤ አርሶአደሩ የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን እንዲያከናውንና ችግር ቢገጥመው እንኳን ገበያን ያማከለ አማራጭ ምርት እንዲኖረው የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ይህ ተግባርም የምርት ወቅትን ተከትሎ የሚታይ የዋጋ መቀነስ እንኳን ቢኖር አርሶአደሩ ገበያ ይዞት የሚወጣው አማራጭ ምርት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አቶ ደጀኔ እንዳሉት፤ አርሶአደሩ ዶሮ ወይም ፍየል ሊያረባ፣ ንብ ሊያንብ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን እህሉን በቅናሽ ዋጋ ከመሸጥ ይልቅ እነዚህን በመሸጥ ችግሩን ማቃለል ያስችለዋል፡፡ እናም አርሶአደሩ አማራጭ ምርት እንዲኖረው እንጂ አንድ ዓይነት የግብርና ሥራ ብቻ እንዲሠራ አይመከርም፡፡ ትልቁም ሥራ ይሄው ነው፡፡ ምክንያቱም እህል ችግር ላይ በወደቀ ዘመን አንድ አርሶደር ከብቶችን፣ ፍየሎችን፣ ዶሮዎችን ወይም ሌላ የሚያረባቸውን እንስሳት በቀላሉ የገቢ ማግኛው አማራጭ ማድረግ ይችላል፡፡
በመሆኑም አማራጭ መፍጠር ያልቻለ አርሶአደር ለፍቶ ካገኘው ምርት ተገቢውን ዋጋ ማኘት ስለማይችል ይሄን ችግር ለማስቀረት አርሶአደሩ አማራጮች እንዲኖሩት እና ተጠቃሚ እንዲሆን ቢሮው እየሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ አማራጮች በሌሉበት በአስገዳጅ ሁኔታ ሰብሉን የሚሸጥ ከሆነ በማህበራት በኩል የሚሸጥበት እድል ተፈጥሮለታል፤ በቀጣይነትም እየተመቻቸለት ይገኛል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን አርሶአደሮችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራዎችም መጀመራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በአርሲና ባሌ አካባቢ ከብቅል ፋብሪካዎች ጋር ተሳስረው እንዲያመርቱ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየሰፉ ሲሄዱም አርሶአደሩን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራው እንደሚቀጥልና እነዚህ ዕርምጃዎችም ደላሎች እንዲቀንሱና አርሶአደሩ ምርቱን ለደላሎች ሲሳይ የሚያደርግባቸው ዕድሎች እንዲከስሙ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም አርሰአደሩ ተገቢውን ገበያ አግኝቶ ከምርቱ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው ሥራዎች በስፋት የሚከናወኑ መሆኑን አቶ ደጀኔ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
በወንድወሰን ሽመልስ