ከካበተ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው በመነሳት «ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ» የሚል አጎላማሽ መጠሪያን ተጎናፅፏል። ዘርፉ በኢኮኖሚ ጠቀሜታው ብቻ የሚፈረጅ ሳይሆን ፋይዳው ሁለንተናዊ ነው። በውስጡ ባህል አለ፤ ተፈጥሮ አለ፤ ትውፊት አለ፤ እምነትና አስተሳሰብ አለ፤ ታሪክ አለ፤ ውበት አለ፤ ፅዳት አለ። የአየር ንብረት ጉዳይም እዚሁ ውስጥ ነው። ባጠቃላይ ሕይወት አለ፤ አገራዊ፣ ማህበራዊና ግላዊ ማንነት ሁሉ አሉ።
ከባህልና ቱሪዝም የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቱሪዝም በዓለማችን ትኩረት ከተሰጣቸውና በየጊዜው እድገትና ውጤት በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙት የልማት ዘርፎች አንደኛው ሲሆን ሴክተሩ ለታዳጊም ሆነ ለበለፀጉ አገራት ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከማሳደጉ፣ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የንግድና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከማስፋፋቱ፤ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን ከማስገኘቱ ባሻገር በሕዝቦች መካከል መግባባት እንዲፈጠርና ጤናማ ግንኙነት እንዲመሰርት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ የሚገኝ፤ ከዘመኑ ግንባር ቀደም ክፍለ ኢኮኖሚዎች መካከል አንዱ እየሆነ መጥቷል።
እንደምናውቀውም ሆነ ሲባል እንደሚሰማው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብቷ ብቻ ከራሷም አልፋ አፍሪካን መቀለብ የሚያስችል አቅም አላት። ይህ አባባል፤ ወይም ደረቅ እውነት የትም እንሂድ፣ ምንም እናንብብ፣ ማንም ይናገር ማን ሳይዛነፍ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ በጥናትና ምርምር ሥራዎች፣ መድረኮች፣ መገናኛ ብዙኃን ሁሉ አብዝቶ የተነገረለትና እየተነገረለት ያለ ጉዳይ ነው።
«ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለተሻለ ሕይወት» በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም ቱሪዝም ቀን በአገራችን በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር አማካኝነት በድሬዳዋ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወይዘሮ ቡዜና አልከድር እንደገለፁት፣ ባህላዊ ሁነቶቹ የአገራችንን ባህላዊ እሴቶች በሚያስተዋውቅና በሚያበለፅግ መልኩ ለእይታ ቀርበዋል። ባህል ተኮር ሲምፖዚየም፣ ኤግዚቢሽን፣ ፋሽን ትርኢት፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችና በእነሱ ላይ የተመሰረቱ ውይይቶች፣ የድሬዳዋን ልዩ ባህሪ የሚያንፀባርቁ፣ አብሮ መኖርና መቻቻልን የሚያስተጋቡ፤ የቱሪዝም ሀብቷን የሚያስተዋውቁ፤ ምሥራቅ ኢትዮጵያን የሚገልፁ፤ በርካታ ዝግጅቶች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ጉብኝት፣ የግመል ውድድር፣ ባህላዊ ምግቦች አሠራርና አመጋገብ እና ሌሎች ዝግጅቶችም የበዓሉ ድምቀቶች ናቸው፡፡ የሌሎች፣ በተለይም የድሬዳዋ አጎራባች ክልሎች ባህላዊ እሴቶችና ሌሎች ተግባራትም በበዓሉ ላይ ሰፊ ቦታን የሸፈኑ ናቸው።
የበዓሉ አከባበር በ2012 የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚለው ጎልቶ የሚወጣበት ነው የሚሉት ክብርት ሚኒስትሯ በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለወጣቱ የሚፈጠርበትና ዜጎች፤ በተለይም ወጣቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት የሥራ ዘመን እንደሚሆን፤ ይህም መንግሥት በቅርቡ ያስተላለፈውን መልእክትና ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ የተያዘ እቅድ መሆኑንም ተናግረዋል።
አገራችን ቱሪዝምን በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት መሆናን የሚገልፁት ወይዘሮ ቡዜና ከሀገሪቱ የቱሪዝም እምቅና ያልተነካ ሀብት አንፃር ሲታይ ተጠቅመንበታል ማለት እንደማይቻል፤ ያም ሆኖ ግን በየጊዜው ከፍተኛ መሻሻል፣ ለውጥና እድገት እየታየ መሆኑን፤ ይህንንም ከቱሪዝም ልማት ሕዝቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይናገራሉ።
የመንግሥት አቅጣጫ የቱሪዝሙን ሴክተር ቀዳሚው አድርጎ ያስቀመጠው ከመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላትም በስፋት ተሳትፈው የሚሠሩ ከሆነ፣ የአገራችን ቱሪዝም ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ የተናገሩት ክብርት ቡዜና «ለዚህም አቅም በፈቀደ መጠን፣ ሁሉንም ባሳተፈና በተለይም ክልሎችን በዋና የዘርፉ ተዋናይነት ባስቀመጠ ሁኔታ ሥራዎች በመሰራት ላይ» መሆናቸውን ይናገራሉ።
«በተለይ በሴክተሩ በርካታ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ በትኩረት የሚሰራበት፣ ሁሉም ክልሎች በዘርፉ የሚያቅዱትም ሆነ የሚያከናውኑት በዚሁ አላማና ግብ የተቃኘ መሆን እንዳለበት፤ በ2012 በጀት ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ 75 ሺ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን» የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ቡዜና አስረድተዋል።
የቱሪዝም ዘርፉን በተፈለገው መንገድ ለመምራት፣ ለማልማትና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ሕዝቡን ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ፤ ጥረትና ተቀናጅቶ መስራትን የግድ እንደሚል የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታ ቡዜና «እስከ ዛሬ በስትራቴጂክ እቅድ የተደገፈ ተቀናጅቶ የመስራት ሁኔታ አልነበረም። ችግርም ሆኖ የቆየው ይሄው ነበር። ሁሉም በተናጠል ቢሰራም ሥራው መሆን ያለበት ግን አገራችንን ከማሳደግና ሕዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ነው። በመሆኑም ይህንን ችግር በሚገባ በመለየት፣ ከባለ ድርሻ አካላት ጋርም የጋራ ስምምነት ላይ በመድረስ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራም» ተገብቷል።
በሴክተሩ ያለውን ችግር ከመፍታትና በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን አስተባብሮ የማስፈጸም አቅምን ከማጠናከር፣ መሠረተ ልማቱን ከማሻሻል የአገልግሎት አሰጣጡን ከማዘመን፣ ተወዳዳሪነትን ከማጎልበት እና ከመሳሰሉት አኳያ ስትራቴጂክ እቅዱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ሚኒስትር ዴኤታ ቡዜና አልከድር ተናግረዋል።
ሌላው የራሱ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞለትና ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ያለው ተግባር ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ዘርፉን በሚገባ ማስተዋወቅና የጎብኚዎችን ቁጥር ማሳደግ መሆኑን የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ «ዝግጅቱ የቱሪዝምን ምንነት የምንገልፅበት፣ አገራችን በዘርፉ ያላትን አቅም የምንለይበትና ለዓለም የምናስተዋውቅበት ከመሆኑም ባሻገር የጎብኚዎችን ቁጥር፤ በተለይም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ከማበረታታትና ቁጥራቸውን ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በመሆኑም እዚህ ላይ መስራት ስለሚያስፈልግና ለዚህም በዓሉ ከፍተኛ ዕድልን» እንደሚፈጥርም ይገልፃሉ።
«በ2012 ዓ.ም በአጠቃላይ አገሪቱ 200 የአገርህን እወቅ ክበቦችን ለማቋቋም በእቅድ የተያዘ ሲሆን ይህ ቁጥርም ለየክልሎቹ ተደልድሏል።» ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ተናግረዋል።
በአብዛኛው ክልሎች ትልቁን ኃላፊነትና ድርሻ የሚይዙበትና የሚሳተፉበት ይህ በዓል ሁሉም ክልል እራሱን የሚያስተዋውቅበት፣ ያለውን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቱን ለይቶ የሚያውቅበት፣ አውቆም ለሌላው የሚያሳውቅበት፣ የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ከማሳደግ አኳያ ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ የሚያደርግበት፣ በየአካባቢው የአገር ውስጥ ቱሪስት ቁጥርን ለማሳደግ ዕድል የሚሰጥበት፣ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ለመሳብ አመቺ ሁኔታ የሚፈጠርበት ወዘተ መሆኑንም ከሚኒስትር ዴኤታዋ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ40ኛ፤ ኢትዮጵያ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት አባል መሆኗን ተከትሎ በአገራችን ለ32ኛ ጊዜ (ከበዓሉ መስከረም 17 ቀን ዋዜማ መስከረም 16 ጀምሮ እስከ መስከረም 19) የሚከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን «በአጠቃላይ የምሥራቅ ኮከቦች የታዩበት፤ የአገራችን ቱሪዝም በስፋት የተዋወቁበት፤ ዘርፉን ለማበልፀግ ሰፊ ሥራ የተሰራበት፣ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች የሚበረታቱበት፤ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር ቃል የተገባበት፣ የአገራችን ሕዝቦች ከተለያዩ የአገራችን ባህላዊ እሴቶች ልምድ የተካፈሉበት» እንደነበርም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
«እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዓሉ መስቀል ላይ ስለዋለ የቱሪዝም በዓሉን ለማክበር ከፌዴራል የሚሄዱ እንግዶች በዋዜማው ተገኝተው ከድሬዳዋ ነዋሪ ጋር የደመራ ሥነ-ሥርዓትን ማክበራቸውንም ወይዘሮቡዜና ተናረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት፤ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ዘርፉ እየተነቃቃ፤ አልሚዎችም እየተነሳሱ መሆኑ ይነገራል። የክልል መስተዳድሮች በሽሚያ እኔጋ ኢንቨስት ብታደርጉ የተሻለ አደርጋለሁ ማለታቸው በራሱ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው የሚሉ በርካቶች እየሆኑ መጥተዋል። ክልሎች ወደ እኛ ብትመጡ የተሻለ እናደርጋለን በማለት የመወዳደርና ባለሀብቱ በዘርፉ እንዲሠራ ያሳዩት ስሜት በባለ ሀብቱ ልብ ውስጥ ተስፋን እንዲፈነጥቅ አድርጓል።
የባንክ ኃላፊዎችም ብድር ሲሰጥ ከሚታሰበው ወለድ በአራት በመቶ የቀነሰ ወለድ የሚታሰብበት ብድር እናመቻቻለን ማለታቸው፤ የብድር መክፈያ ጊዜ የአራትና የአምስት ዓመት መሆኑ ቀርቶ 15 እና 20 ዓመታት ማስረዘም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑ፤ እንዲሁም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ነሐሴ 28 ቀን 2011 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው አንደኛው አገር አቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንፍረንስ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትሯ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ያደረጉት ንግግርና የገቡት ቃል ባለሀብቱም ሆነ አጠቃላይ ዜጎች ስለዘርፉ ተስፋ እንዲኖረን የሚያደርግ ስለመሆኑ ኮንፈረንሱን ተከትሎ በርካቶች አስተያየታቸውን ሲሰጡበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡
ሴክተሩ የቅንጅት ችግር ነበረበት። ፖሊሲውን በጋራ ፖሊሲነት አይቶ የማስፈፀምና መፈፀም ችግር አለ። «በተለይ ከዚህ በፊት የነበረው ኃላፊነት የግል፣ እንቅስቃሴው የግል፣ ፍላጎትም የግል ነበር። አሁን ከባለ ድርሻዎች ጋር ቁጭ ብለን ተነጋግረን፤ ተስማምተን፤ ማን ምን ይሰራል የሚለውን ለይተን፤ ወደ አንድ በማምጣት በአንድ ፓኬጅ ውስጥ በማስገባት የጋራ መግባቢያ ሰነድ አዘጋጅተናል። በሚቀጥለው ሳምንት ተፈራርመን ወደ ሥራ ይገባል» የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ለውጥ እንደሚመጣ፤ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2012
ግርማ መንግሥቴ