በኢትዮጵያ ሚሊኒየም 71 ሺ 316 ነጥብ 07 ቶን የነበረው የአገራችን የሩዝ ምርት ከስምንት ዓመታት በኋላ በ2009 ዓ.ም ወደ 126 ሺ 806 ነጥብ 45 ቶን ማደጉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከሩዝ ምርት የተገኘውን ገቢም ስንመለከት በ2000 ዓ.ም 22 ሺ 500 ቶን ሩዝ ተሸጦ 12 ነጥብ 07 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ደግሞ 311 ሺ 827 ቶን ሩዝ ተሸጦ 170 ነጥብ 69 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህም ወደ ውጭ እየተላከ የሚገኘው ገቢ በስምንት ዓመታት ውስጥ ጭማሪ ማሳየቱን ያሳያል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሩዝ በምዕራብ አማራ ክልል ፎገራ፣ ጎንደር ዙሪያ፣ ደምብያ፣ ታኩሳና አቸፈር፤ በሰሜን አማራና በቤኒሻንጉል ክልል ጃዌ፣ ፓዊ፣ መተማና ዳንጉራ፤ በጋምቤላ ክልል በአበቦና ኢታንግ፤ በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በራሌ፣ ወይቶ፣ ኦሞራቴ፣ ጉራፈርዳና መንቲ፤ በሶማሌ ክልል ጎዴ፤ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ክልል ኢሊባቡር፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ እና ጅማ ዞን እየተመረተ ይገኛል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የሩዝ ምርት ይመረት እንጂ የተመረተውን ሩዝ ወደ ገበያ መውሰድ ላይ ችግሮች እንዳሉ ይጠቀሳል፡፡ በተለይ የገበያ ትስስሩ የላላ መሆኑ፣ ዘመናዊ የሆነ መሳሪያዎች አለመጠቀም፣ ምርት አሰባሰቡ ላይ ጉድለቶች መኖርና ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርብ ምርቱን ማስተዋወቅ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ሰሞኑን ጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ባዘጋጀው የሩዝ ምርት ማስዋወቅ መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የሩዝ ምርት እድልና ተግዳሮት የሚል ጥናት ያቀረቡት ዶክተር ዳዊት አለሙ እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ ሩዝ ለማምረት የሚያስችል ምቹ ቦታዎች ያሉ ሲሆን በፎገራ፣ ፓዌ፣ አባቦ፣ ጉራፈርዳ፣ ጎዴ፣ ማይፀብሪና ጨዋቃ ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አካባቢዎቹ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ 30 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታሩ ከፍተኛ ምርት ለማምረት ሲያስችል፣ 25 ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ መደበኛ ምርት ለማምረት ይውላል፡፡ በአጠቃላይ በመስኖ ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር የሩዝ ምርት ይመረታል፡፡
የሩዝ ምርት በአሁኑ ወቅት ለምግብነትና በባህላዊ መጠጦች ለመስራት እንደሚውል የጠቆሙ ዶክተር ዳዊት፤ ሩዝን ከጤፍ ጋር በመቀላቀል እንጀራ ሆኖ ለምግብነት የሚቀርብ ሲሆን እንጀራን ለማዘጋጀት የሚወጣ ዋጋ እንደሚቀንስ ይጠቅሳሉ፡፡ ጠላና አረቄን ለማዘጋጀት የሩዝ ምርት ተመራጭ እየሆነ መምጣቱንም ያመለክታሉ፡፡
እንደ ዶክተር ዳዊት ገለፃ፤ በሩዝ ምርት ላይ በአገር ውስጥ የሚመረተው ሩዝ ውጭ ገበያ ላይ ተወዳዳሪነቱ መቀነስ፣ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ አለመከተልና ከምርት በኋላም በቴክኖሎጂ የተደረገፈ ስራ አለመሰራቱ፣ ምርቱ ከተሰበሰበ በኋላ አቀማመጥ ላይ ችግር መኖሩ፣ የተመረተውን የሩዝ ምርት ወደ ውጭ ሲላክ ዝቅተኛ ዋጋ ማውጣታቸው እና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል አለመኖር የተጋረጡ ችግሮች ናቸው፡፡
በአገር ውስጥ የተመረተው ሩዝ ለህብረተሰቡ በብዛት አለመቅረቡን በመጥቀስ፤ የቀረቡት የሩዝ ምርቶች ወደ ዱቄትነት በመለወጥ ከጤፍ ጋር የመቀላቀል ሁኔታ እንደሚበዛ ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረተውን ሩዝ ከውጭ ተገዝተው ከሚገቡት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ የማስተዋወቅ ስራው ደካማ መሆንና በሩዝ ምርት ላይ የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ በማነሱ የአገር ውስጥ ሩዝ ምርት እንደማይታወቅ ያስረዳሉ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአገር ውስጥ ያለውን የሩዝ ፍላጎት ለመሸፈን ከውጭ የሚመጡት አገር ውስጥ ከሚመረተው መብለጡ፣ የተሟላ መሰረተ ልማቶች ባለመኖራቸው የተመረተውን ሩዝ ገበያ ላይ ለማውጣት መቸገርና ደካማ የገበያ ትስስር በመኖሩ በአገር ውስጥ የሚመረተው ሩዝ እንዳይታወቅ አድርጎታል፡፡
መንግስት የግሉ ዘርፍ በግብርና ምርቶች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ባወጣው ፖሊሲ መሰረት 58 ሺ ሄክታር የሩዝ እርሻ በግል ባለሀብቶች መልማት መጀመሩን ይገልፃሉ፡፡ በሩዝ ምርት ላይ ምርምር የሚያደርግ ተቋም በፎገራና በሌሎች ቦታዎች መገንባቱንና የሩዝ ምርት ለማሳደግ የመስኖ ልማት መጀመሩን ያመለክታሉ፡፡
በቀጣይ የሩዝ ምርትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የውጭ አገራት ተሞክሮ ለማምጣት፣ ከምርት በኋላ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ምርቱን ለመሰብሰብና ለማሸግ የሚያስችሉ መሳሪያዎች ለማቅረብ እንዲሁም ጥራት ያለው የሩዝ ምርት ለማምረት እቅድ መያዙን ይናገራሉ፡፡ በፎገራ የሩዝ ምርምር ተቋም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ይጠቁማሉ፡፡
በፎገራ ብሄራዊ የሩዝ ምርምር ተቋም ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጥላሁን ታደሰ፤ በአገር ውስጥ የሩዝ ምርት ለማሳደግ በፓዌና በአበቦ የምርምር ተቋም መከፈቱን ይገልፃሉ፡፡ የምርምር ስራውን የጃፓን መንግስት እየደገፈው የተለያዩ የሩዝ ምርት ዘር መገኘቱን ይጠቅሳሉ፡፡ በፓዌ የምርምር ተቋም በጣና በለስ ፕሮጀክት መስኖ በመጠቀም የጣሊያን ተመራማሪዎች ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውንም ይናገራሉ፡፡
በፎገራ ደግሞ በሰሜን ኮሪያ ተመራማሪዎች በተደረገ ድጋፍ በደራ ወረዳና በፎገራ ወረዳ የሩዝ ምርምር መከናወኑን ያስታውሳሉ፡፡ በተደረጉ የምርምር ስራዎች የሩዝ ምርት በየዓመቱ ከጤፍ ቀጥሎ እያደገ መምጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡ የሩዝ ምርት ከመተዋወቁ በፊት በፎገራ አካባቢ ህብረተሰቡ ከብት ማርባት ላይ የተሰማራ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
በመርድ ክፍሉ