በወርሃ ጽጌ አደይን ተከትሎ በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በልዩ ልዩ ዝግጅት በድምቀት የሚከበረው የመስቀል በዓል በተለይ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ አለው።መስቀል ከሃይማኖታዊ ስርዓት ባሻገር ባህላዊ ገጽታው ብዙዎችን ይስባል፤ ይማርካል።ህብረ ብሔራዊነትም እንዲሁ።የመስቀል በዓል መከበር ከጀመረ በርካታ ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይነገርለታል።በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ደምቆና አሸብርቆ የሚከበር መሆኑም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ማዕከል(ዩኔስኮ) ከአስመዘገባቸው ቅርሶች መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል።
የመስቀል በዓል አከባበር እንደየአካባቢው ይለያያል። በጉራጌ፣ በከንባታ፣ በሌሎችም ብሔሮች ዘንድ በዓሉ የተለየ ትኩረት ስለሚሰጠው ለየት ተደርጎ ይከበራል። በእዚህ ጽሑፍም በጉራጌ የመስቀል በዓል መከበር የሚጀምረው መስከረም በገባ በ13ተኛው ቀን ጀምሮ ነው። ከአገር ውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው የብሔሩ ተወላጅ እንዲሁም ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በመግዛት ይዘጋጃሉ።
የብሔሩ ተወላጆች የመስቀል በዓልን ለማክበር ከያሉበት ወደ ትውልድ ቦታቸው የሚያቀኑት ቀደም ብለው ነው። ለመስቀል አገሩ ያልገባ የአገሩ ተወላጅ “ሞቷል”ተብሎ ስለሚታመን እንደምንም ብሎ በዓሉን ከወዳጅ ዘመድ ጋር ለማሳለፍ ጥረት ያደርጋል። ለበዓሉ ማድመቂያ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችንም አስቀድሞ ያደርጋል። አገር ቤት የገባው የተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶችን በመፈጸም እስከ መስከረም 21ቀን ድረስ ይቆያል።በየዕለቱ የሚከናወኑት እነዚህ ባህላዊ ስርዓቶች የተለያዩ ስያሜዎች አሏቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በእዣ ወረዳ አገና ከተማ በደሳለኝ ሎጅ ተገኝቶ የበዓሉን ሁነቶች እንዲህ ቃኝቶታል።
የመስቀል በዓል አጀማመር የክርስትና መሰረት የሆነው የክርስቶስ መስቀል መገኘት ጋር ተያይዞ ሲሆን የክርስቲያኖች ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ በዓሉን የሚያከብረው እንደ ህዝቡ ባህል፣ አኗኗር፣ ወግ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ገፅታ ነው። ስለበዓሉ ሊያስረዱን ገለጻቸውን የጀመሩት የጉራጌ ዞን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ አባተ ነበሩ።
አቶ ፈለቀ ይናገራሉ የጉራጌ ብሔረሰብም ከሚታወቅባቸው በዓላት መካከል መስቀል ተጠቃሽ ነው።የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓት ቢኖረውም የብሄረሰቡ አባላት ከተለያዩ ባህላዊ መገለጫዎች ጋር አዋህዶ ያከብረዋል። ይህ በዓል ከመከበሩ አንድ ወር አስቀድሞ ሴቶችና ወንዶች ስራ ተከፋፍለው ዝግጅት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።ወንዶች የማገዶ እንጨት፣ የስጋ ከብት ግዢ፣ የዳመራ ተከላ፣… መሰል ስራዎችን ሲያከናውኑ ሴቶች በበኩላቸው ቆጮ፣ቅቤ፣ ሚጥሚጣ ያዘጋጃሉ፤ ቤት ያጸዳሉ በተለያዩ ቀለማትም በእጅ የተሰሩ ምንጣፎች (ጂባ) የማንጠፍና የመሳሰሉ ተግባራትም ያከናውናሉ።
በእዚህ ታላቅ በዓል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጉራጌ ተወላጆች ከሚኖሩባቸው ከተሞች ወደ ሀገር ቤት የሚተሙበትና ከዘመድ አዝማዱ የሚገኝበት በመጨረሻም ተደስተው የሚመለሱበት በዓል መሆኑንም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
የጉራጌ ማህበረሰብ በስራ ፈጣሪነቱና ወዳድነቱ እንዲሁም ስለታታሪነቱ ብዙዎች ተቀኝተውለታል፤ ፀሐፍትም አረጋግጠውለታል። አንደበተ ርዕቱ አቶ ፈለቀ አሁንም ይገልጻሉ፤ በሀገራችን ታሪክ በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የንግድ ስራውን ከአረቦች እጅ ተረክበው አሀዱ ብለው ያስተማሩት የጉራጌ ማህበረሰብ እንደሆኑም አስታውሰው ጉራጌዎች ለመስቀል ትልቅ ክብር እንደሚሰጡ ነግረውናል። አብዛኛው ተወላጅም ቢሆን አጭቶ ወይንም ትዳር መስርቶ የሚወጣው በወርሃ መስከረም የመስቀልን በዓል ምክንያት በማድረግ ነው።
በዓሉ በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ስላለው የተጣላ ካለ መስቀል ከመድረሱ በፊት የሚታረቅበት፣ የተቸገረም የሚደገፍበት በዓል ነው። የመስቀል በዓል መግባቱ የሚበሰረው ነሐሴ 12 በእያንዳንዱ ቤት ደጃፍ የልጆችና የጋራ ዳመራ በመደመር ነው። በዋናነት የጉራጌ መስቀል መከበር የሚጀምረው መስከረም 12 ሴራ ያርጅቦ (ሌማት የሚወርድበት) ቀን በመባል ይታወቃል። በዚህም እለት የግቢ እና የቤት እቃዎች በጠቅላላ የሚፀዳበት ነው። በጉራጌ ብሔረሰብ የመስቀል በዓል አከባበር ከጅማሮ እስከ መጨረሻ ቀን ድረስ የየራሳቸው ስያሜ ያላቸው ሲሆን በእያንዳንዱም እለት የተለያዩ ስነ ስርዓቶች እንደሚከናወኑ አቶ ፈለቀ ነግረውናል።
መስከረም 13 ”ወሬት የኸና”
ይህ ቀን እንቅልፍ የነሳ ቀን ተብሎ ይታወቃል። በዕለቱ መላው ቤተሰብ ለመስቀል ምን እንደሚሰሩ ስለሚያስቡ እንቅልፍ ይነሳቸዋል።ለዚህም ነው ወሬት የኸና የተባለው ። በተለይ በሰባት ቤት ጉራጌ አካባቢ ምንም የሚሰሩት ነገር የለም።
ቀደም ባሉት ዘመናት ዶሮ እንደጮኸ ኮሶ ይጠጣ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ቀን በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ዘንድ ግን መሶብ የሚወርድበት ቀን ነው። በዚህ ዕለት በቀጣይ ቀን የሚውለውን የዴንጋ እሳት (የዴንጊያ እሳት) የልጆች ደመራ ወይም ታሳቢ በማድረግ መለስተኛ የመስቀል መባቻ ይደረጋል። ይህ ስርዓት በአብዛኛው በቤተ ጉራጌዎች የሴቶች በዓል ተብሎ ይታወቃል።
መስከረም 14 ይፍት (ደንገሳት)
በዚህ እለት አመሻሽ ነሀሴ 12 የተደመረው የልጆች ዳመራ ጎረ ጎረ ጎረ ጎረ…. እያሉ የሚለኮስበት እና እናቶች ጣፋጭ የሆነ የጎመን ክትፎ እና “ ዳቡየ” ወይንም “ዳፓ” የተሰኘ ወፍራም ቆጮ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ አዘጋጅተው ቤተሰብ በሙሉ በይወደረ(ባህላዊ ምግብ ማቅረቢያ) ዙሪያ ከቦ በደስታ የሚመገብበትና የሚደሰቱበት እለት ነው።
መስከረም 15 ወኸምያ( የጨርቆስ ማይ)
ወኸምያ ማለት ደስታ ማለት ነው። ይህም የሚውለው መስከረም 15 ሲሆን እለቱ ወኸምያ (የጨርቆስ ማይ) በመባል ይጠራል። በዚህ እለት የመላው ጉራጌ የእርድ ቀን ነው። ኬር ይሁን ኬር… ኬር…ኬር (ሰላም ይሁን፣ ሰላም…) ሀገሩ አድባሩ ተባብለው እና ተመራርቀው ነው የእርድ ስነ-ስርዓት የሚጀመረው። የጉራጌ ክትፎ መበላት ሳይሆን “መጠጣት” የሚጀመረው በዚህ እለት ነው። ሌላው በጉራጌ ብሔረሰብ የሚታወቀው ጨፉየ (ለየት ያለ ቁርጥ ስጋ በቂቤ) የሚበላውም በዚሁ እለት ነው።
ከበሬው የሚፈሰው ደም በቃንጫ ተነክሮ የቤት ደጃፍ መቃንና ምሰሶ ይቀባል። ከበሬው የተገፈፈ ሞራም እስከ መጪው ዓመት እርድ ድረስ የቤት ምሰሶ ላይ ይሰቀላል። ይህ አዲሱ ዓመት የደስታና የጥሩ መኸር ጊዜ እንዲሆንላቸወ፤ ወኸምያም በየአመቱ በሰላም እንዲያደርሳቸው፤ለመጣባቸው መጥፎ ነገር ጥላ ከለላ እንዲሆናቸው ፈጣሪን ለመማጸን ነው ። ሁሉም ቤተሰብ የክት ልብሱን ልብሶ አምሮና ደምቆ የሚውልበት እለት በመሆኑ እለቱ የደስታና የፍሰሃ ሆኖ ይከበራል።
መስከረም 17 ”ንቅ ባር (ማለቅ በዓል)”
አብይ መስቀል የሚለውን ስያሜ የያዘ ሲሆን በብሔራዊ ደረጃ የሚከበረውን የመስቀል በዓልን ተከትሎ ይከበራል። በዚህ እለት ለመስቀል የታረደ ከብት ሻኛ በመቀቀል በቀዬው በሚገኝ ታላቅ አዛውንት ቤት ሁሉም ቤተዘመድ እና ጎረቤት በጋራ ተመራርቆ የሚበላበት ነው። ለአዛውንቶች ልዩ ክብር በመስጠት ቅቤ አናታቸው ላይ ተደርጎላቸው ዘና ብለው የሚውሉበትም ቀን ነው።
ከመስከረም 17 ጀምሮ ”የጀወጀ”
ከመስከረም 17 በኋላ ባሉት ቀናት የሚካሄድና አንድ ሳምንት ያህል የሚቆይ ስነ-ስርዓት ሲሆን ባልና ሚስት ስጦታ በመያዝ ወገኖቻቸውን በተለይም እናትና አባቶቻቸውን የሚጠይቁበት ነው። ቀደም በእነዚህ ቀናት መስቀልን የተመለከቱ ዘፈኖችና ጭፈራዎች በየቦታው ይካሄዱ ነበር። የሙየቶች ጭፈራም ነበር። ሙየት ማለትም በአብዛኛው በእናቶችና በሴቶች ዘንድ የሚዘፈን ባህላዊ ጨዋታ ነው።
ከመስከረም 17 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ”አዳብና”
በአንዳንድ ቤተ ጉራጌዎች ዘንድ ከተለመደው በተለየ መልኩ አሁንም ድረስ በድምቀቱ የሚታወቅ ሲሆን ለወጣቶችና ሴቶች ልጃገረዶች የተለየ የጭፈራ አጋጣሚ ነው። ጭፈራው ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ጥቅምት ድረስ ይዘልቃል።የአዳብና ጭፈራ በገበያዎች ላይ የሚከወን ሲሆን ድንቅ ባህላዊ አልባሳት እና የጉራጌኛ ውዝዋዜ ትእይንቶች ይታይበታል። ይህን ለመመልከት ታዲያ ወርሃ መስከረም ማገባደጃን አስቦ በተለይ ወደ ሶዶ ወረዳ ማቅናት ቢችሉ እርካታን ይጎናፀፋሉ።በዚህ እለት ትዳር ጓደኛን ለመምረጥ እና ሎሚ ለመወራወር ምቹ አጋጣሚ ነው።
መስከረም 18 ”የፌቃቆ ማይ የስንደዶ ለቀማ ቀን”
በዚህ እለት በሶዶ ቤተ ጉራጌ አካባቢ ልጃገረዶች ለአመቱ መስቀል የሚያገለግሉ የስፌት ውጤቶችን ለማዘጋጀት የሚረዳቸው ስንደዶ የሚለቅሙበት እለት ነው።
ጥቅምት 5 ”መንጠየ”
የቋንጣ ክትፎ የሚበላበት የመስቀል በዓል የመጨረሻ ስነ-ስርዓትና ማሳረጊያ ነው። ይህ በዓል በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቅምት 5 ይውላል። ከሩቅም ከቅርብ የመጣው ሁሉ ተመራርቆ ይሸኛል። ሁሉም አመት አመት ያድርሰን ብሎ ወደ ስራ ይገባል።
አቶ ፈለቀ እንዳሉት መስቀልና ጉራጌ በአመት አንድ ጊዜ የሚገናኙ ልዩ አጋጣሚዎች ናቸው። የመስቀል በዓልን ተከትሎ ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የአካባቢው ህብረተሰብ በጋራ ይወያያል፤ ችግሮችን ይፈታል። መስቀልን በጉራጌ ለማክበር ከመላው አለም ወደ ዞኑ የሚተመው ትራንስፖርትና የሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚ ሲታይ በዓሉ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ መመልከት ይቻላል።
ይህም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል። እኛም ቱባውን በዓል ለማየት ታድመንም ታድለንም ነበር። ቱሪስቱ ይህንን የመስቀል በአል አከባበር በአካል ተገኝቶ ለመመልከት በወርሃ መስከረም ወደ ቤተ ጉራጌ አካባቢ እንዲያመራ የጉራጌን መስቀል በዓል አከባበር ይበልጥ እንዲጠና፣እንዲለማና በአለም ዘንድ እንዲተዋወቅ ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡ መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012
አብርሃም ተወልደ