አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት በተከሰተው ድርቅ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ህዝብ የዕለት ምግብ ተረጂ መሆኑን ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን_ አስታወቀ፡፡ ችግሩን ለመቋቋም 21 ቢሊዮን 37 ሚሊዮን 822 ሺ 234 ብር ወጪ ማድረጉንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከነሐሴ 2007 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በአገሪቱ ድርቅ አለ፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ ከ2007 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2010 ዓ.ም ድረስ በሁለቱ ምክንያቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የተደረገ፣ የምግብ ግዥ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ግዥዎች፣ የቁሳቁስ ማጓጓዣ የትራንስፖርት ወጪ፣ ለክልሎች ለሚደረግ ድጋፍ፣ ለእንስሳት መኖ እና ለሌሎች ድጋፎች 21 ቢሊዮን 37 ሚሊዮን 822 ሺ 234 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ለምግብ ግዥ ወጪ የሆነው 13 ቢሊዮን 740 ሚሊዮን 197 ሺ 120 ብር፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ግዥዎች የመጠለያ፣ የአልባሳትና የቤት ዕቃዎች ግዥ ደግሞ 212 ሚሊዮን 454 ሺ 142 ብር፣ ለተረጂዎች የሚሆን ቁሳቁስ ለማጓጓዝ የትራንስፖርት፣ ማራገፊያና ማስጫኛ ወጪ፣ ሦስት ቢሊዮን 195 ሚሊዮን 83 ሺ 555 ብር፣ ለክልሎች የሚደረግ ድጋፍ ሦስት ቢሊዮን 490 ሚሊዮን 674 ሺ 174 ብር እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዮች የሚደረግ ድጋፍ በተለይ የእንስሳት መኖ መግዣ 399 ሚሊዮን 413 ሺ 241 ብር ወጪ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በዕርዳታ አሰጣጡ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች አሉ የሚሉት አቶ ደበበ፤ ከእነዚህም ውስጥ ምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ እንዲሁም ቤንሻንጉል ክልል ካማሼ ዞኖችና በከተሞች አካባቢ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ባልታወቁ ሰዎች መታገት፣ የመኪናዎቹን ቁልፍ አስገድዶ መውሰድ፣ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑት ድጋፎች ሲላኩ በትክክል ቦታው ላይ እንዳይደርስ የማድረግ፣ በተፈጠሩ ግጭቶች፣ የመንገድ መዘጋቶች፣ መሳሪያ ይዞ ማስፈራራት ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
በበልግና በመኸር ወቅት በብሄራዊ ሰጋት አመራር ኮሚሽን የዕርዳታና ድጋፍ አሰጣጥን በተመለከተ ጥናት እንደሚካሄድ የጠቀሱት አቶ ደበበ፤ የሚደረገው የጥናት ሥራ በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ክልሎችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጥናቱ ሲደረግ በየስድስት ወሩ በአገሪቱ የሚገኙ የተረጂዎችን ቁጥር ለመለየት እገዛ የሚያደርግ ሲሆን፤ አሁን የተደረገው በበልግ ወቅት የተካሄደ ጥናት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም አሁን እየተከሰተ ያለውን ግጭት መሰረት አድርገው የሚመጡ አደጋዎች ከክልሎች አቅም በላይ ሲሆኑ ብሄራዊ አደጋ ሰጋት አመራር ኮሚሽን ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
በመርድ ክፍሉ