ያሆዴ መስቀላ በሀዲያ ብሔር የአዲስ አመት ማብሰሪያ ነው። አዲሱ አመት የሰላም፣ የፍቅር፣የብልፅግና እንዲሆን የሚመኙበት በዓል በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይከበራል። በዓሉ የብርሃን የአዲስ ሕይወት ማብሰሪያ ያለፈው አሮጌ አመት ቂም የሚረሳበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ በተለያየ ምክንያት ከአካባቢው እርቀው የሚኖሩ ከወላጆቻቸው ጋር የሚገናኙበት ታላቅ ክብረ በዓል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ክብረ በዓል ለትዳር የደረሱ ወጣቶች የሚተጫጩበትም ነው። በዓሉን በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ከፍተኛ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በዓሉ በዋናነት አንድነትን፣ አብሮ መኖርንና መተባበርን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። ይህ በዓል መስቀል ከመግባቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ መከበር ይጀምራል። የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ ከጥንት ጀምሮ ያሆዴን ሲጠቀም ቆይቷል።
የሀዲያ ዞን የምክር ቤት አማካሪ ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ዘመድኩን ያሆዴ መስቀላን እንደሚከተለው አብራርተውታል፤ ያሆዴ መስቀላ ለሀዲያ ሕዝብ ብዙ ነገሩ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ያሆዴ ለሀዲያ ህዝብ የሁሉም ነገር መጀመሪያ ነው። በዚህም የተነሳ መስቀል ሲመጣ ያሆዴ መስቀላ በማለት ሁሉንም ነገር አንድ ብሎ ይጀምራል። አዲስ አመቱንም ይቀይራል። ማንኛውንም ክስተት የሚዘግበውና የሚያስታውሰው በዛን አመት መስቀል ፣ ያሆዴ መስቀላ ሊደርስ ይህን ያህል ቀን ሲቀረውና ያሆዴ መስቀላ ባለፈ በዚህን ያህል ቀን በማለት ነው። ያሆዴ መስቀላ ሰዎች ይቅር ለእግዚብሔር የሚባባሉበት ነው።
አስታራቂዎችም ቂም ይዞ አዲስ አመትን መቀበል አይቻልም በማለት የተጣሉ ሰዎችን ያስታርቃሉ። ሌላው ደግሞ በዚህ ዕለት ማታ ፉኒታ ( ሆያ ሆየ) የሚጨፈርበትና ጨፋሪዎች ደግሞ ከዚህ ቤት ችጋር ይውጣ፣ በሽታ ይውጣ ብለው ችቦ እያቀጣጠሉ ይጨፍራሉ። ጨፋሪዎች መርቀው ሲወጡ የቤቱ አባወራና እማወራ ደግሞ እናንተም እደጉ በማለት ይመርቁና ይሸኟቸዋል። ይህም እለት ሁሉም የሀዲያ ሕዝብ የሚመራረቅበት ነው።
ለዚህ በዓል ሴቶችም ከአለባበስ እስከ ፀጉር አሰራር ድረስ በተስተካከለ ሁኔታ ይዘጋጃሉ። የሀገር ሽማግሌዎች ተሰልፈው ስርአቱን ያስጀምራሉ ። ይከታተላሉ፤ ይመርቃሉ። የሀዲያ ብሔር እሴት የሆነው ያሆዴ ከነሀሴ ወር ጀምሮ በብሩህ ተስፋ የተሞላ ነው። በዚህ በዓል ሴቶች ቀደም ብለው ስራቸውን ይጀምራሉ። ቤታቸውን ያዘጋጃሉ። በህብረት ስራ ይሰራሉ። ወንዶች ደግሞ እንጨት ያዘጋጃሉ። ሰንጋ ይገዛሉ። ህፃናት ጦምቦራ (ችቦ) ቀድመው ይሰራሉ። በያሆዴ መስቀላ ሰው ብቻ ሳይሆን ከብቶችም አዲስ አመት የሚቀይሩበት በመሆኑ ከአምስት ወር ጀምሮ ጥብቅ ወይም ክልክል ሳር ይፈቀድላቸዋል።
በአሉ ከመከበሩ በፊት በርካታ ዝግጅቶ ይካሄዳሉ። እነዚህም ክንውኖች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ነው።
የእርቅ ሥነ ሥርዓት
በሀዲያ አዲስ አመትን ያሆዴን ለመቀበል በቅድሚያ አንድ ሰው ከተጣላው ጋር እርቀ ሰላም ማውረድ አለበት። ቂም ይዞ አዲሱን አመት መቀበልም ሆነ ማንኛውንም አይነት ዝግጅት ማድረግ አይችልም። በርካታ የሀገር ሽማግሌዎችም እየዞሩ የተጣላን ያስታርቃሉ። ታዲያ የተጣሉ ሕፃናትም ቢሆኑ ተፈላልገው ይታረቃሉ። ወይንም አስታርቁኝ ብለው እኩዮቻቸውን ይልካሉ። ይህም ሁኔታ በማህበረሰቡ ዘንድ መረጋጋት እንዲኖር ከማድረጉ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ከዚህ በዓል ማግስት ጀምሮ የሀዲያ ህዝብ የመረዳዳት ባህሉን በስፋት የሚያንፀባርቅበት፣ጥልንና ቂምን በማስወገድ በአዲስ መንፈስ በማህበረሰቡ መካከል ግንኙነትን በማጠናከር እንደ ቤተሰብና እንደ አካባቢው እቅዶች ተለይተው የሚታረቁበት፣ እንደ ማህበረሰብ እንዴት መለወጥ እንዳለባቸው የሚመካከሩበትና አቅጣጭ የሚይዙበት በመሆኑ ማህበራዊና ባህላዊ ጥቅሙ የጎላ ነው ። እንዲሁም በልማት፣ በግብርና፣ በንግድና በሌሎች ስራዎች ላይ የሚመክሩበት በዓል ነው።
ለስራው ባለው ትጋት እንደምሳሌነት የሚጠቀሰው የሀዲያ ህዝብ ለስራ ከተሰማራባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከሀገር ውጭም ሳይቀር ያሆዴ በዓልን ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከአብሮ አደግና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለማክበር ወደ ሀዲያ ይተማል። በአሉን ለማክበር በወርሀ መስከረም መግቢያ ላይ ወደ ሀዲያ ምድር የሚተመው አውቶቡስ፣ ሚኒባስ የግል መኪና ቁጥር በቀላሉ ሊጠቀስ የማይችል ነው። ይህ እውነታም በሙዚቃና በሥነ ቃል ጎልቶ ይታያል።
ያሆዴ ያሆዴ ያሆዴ…… ያሆዴ ሆ ያሆ
ዱቢንሴ ኢንጃ ጉሎ………ዴ ሆ ያሆ
ባሪንሴ ዋሳ ጉሎ………..ያሆዴ ሆ ያሆ በማለት ያዜማሉ። ትርጓሜውም ከጓሮ ቅመም ጨራሽ ከጉድጓድ ቆጮ ጨራሽ እንደማለት ነው።
የእብድ ገበያ
አንዱና ዋነኛው የያሆዴ መስቀላ በዓል ከሚከበርበት ዕለት ከአስራ አምስት ቀናት አስቀድሞ የሚጀመረው ‹‹የመቻዕል ሜራ›› የበዓል ዝግጅት የሚደረግበት ገበያ ነው። መቻዕል ሜራ የሚለውን ቃል የያዘውን ፅንሰ ሀሳብ በአቻ ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ሀሳቡ የእብድ ገበያ እንደማለት ነው። በያሆዴ መስቀላ የእብድ ገበያ አንዱ አካል ነው። ይህ ስርአት በብሔሩ ባህላዊ አንድምታ ያለውና የገበያ ተጓዦች ስርአት ሲሆን፤ ከትውልድ ቀያቸው እርቀው የሚኖሩትን የማህበረሰብ አካላት ሳይቀር የሚያገናኝ የበአል ገበያ ነው። በዚህ ገበያ ፈጣሪ ይመሰገናል።
ሁሉም ሰው ገበያውን ይጎበኛል። ታዲያ በዚህ የዕብድ ገበያ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም። ገበያ ገብቶ የለም የሚባል ቃል አይሰማም። ስያሜውም የእብድ ገበያ እንደመሆኑ ከሌሎች የገበያ ቀናት የሚለየው የራሱ የሆኑ በርካታ መገለጫዎችና ክንዋኔዎች አሉት። የእብድ ገበያም የሚል ስያሜ ያሰጠው ገበያው የሚደራበት ሰዓት ከወትሮው የተለየ በመሆኑ ነው። በዚህ ወቅት ጊዜ ውድ በመሆኑ ከጠዋቱ በአስራ ሁለት ሰዓት ገበያው በመድራቱ ነው። በዚህ ሰዓትም መገበያየት ይጀመራል። ሌላው ደግሞ እንደመደበኛ እስከ ማታ አለመቆየቱ ነው። ከቀኑ በስድስትና በሰባት ሰዓት ሰው ተገበያይቶ ገበያው ይበተናል።
ይህም ገበያ የሀዲያ አባቶች ጊዜውን እንዴት እንጠቀም በሚል በባህላዊ ጥበብ የተቀነባበረ የጊዜ አጠቃቀምን የሚያሳይ ነው። በዚህ ገበያ አባወራ በዕብድ ገበያ ከቀረቡ ሰንጋዎች መካከል መርጦ ቀልቡ ያረፈበትን ሰንጋ ሙሉ ብር እንኳን ባይኖረው ገዝቶ የሚወስድበት ባህላዊ የግብይት ሥርዓት ነው። ምንም ብር ከሌለው ደግሞ ከመጣበት አካባቢ የአንዱን ታዋቂ ሰው ስም በመጥራት ቀልቡ ያረፈበትን ሰንጋ ያለ ምንም ተያዥ ይዞ ይሄዳል። ቀሪውን ብር ደግሞ በአዝመራ ወቅት ይከፍላል።
በዚህም መሰረት ለያሆዴ መስቀላ የወሰዱትን ሰንጋ ከህዳር እስከ ጥር ባለው ወራት ውስጥ በታማኝነት ተከፍሎ ያልቃል። በዕብድ ገበያ እናቶች ለያሆዴ በዓል አተካና ለማዘጋጀት የሚጠቅሙ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን የእንሰት ተዋፅኦ ማለትም እንደ ቡላ፣ ቆጮ እንዲሁም ቅቤና አይብ ያዘጋጀሉ። እንዲሁም ናቆሮ (ዳጣ) ለማዘጋጀት ደግሞ ነጭ ሽንኩርት፣ዝንጅብል፣ ዛላ በርበሬ፣ ቀይና አረንጓዴ ሚጥሚጣ በበቂ ሁኔታ ያዘጋጀሉ። በአሉ ካለፈ እስከ መስከረም ሰላሳ ገበያ ስለማይቆም የግብይቱ ሂደት ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው።
አተካና
በዓሉን አስመልክቶ የሚኖረው ቅድመ ዝግጅት ለያሆዴ ክብረ በዓል አንዱ የሆነው የአተካና ወይም የአተካኒሞ ምሽት ተጠቃሽ ነው። ያሆዴ መስቀላ አንድ ተብሎ መከበር የሚጀምረው አተካኒሞ ከበዓሉ አንድ ቀን በፊት አዛውንቶች ችቦ በማቃጠልና አተካናን በመቅመስ ነው። አተካና የሀዲያ ባህላዊ ምግብ ነው። በብዛት የሚዘጋጀው ለያሆዴ መስቀላ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ለእንግዳ የሚቀርብ ነው። አሰራሩም በጥንቃቄና በስርአት ሲሆነ ከተሰራ በኋላ ከአንድ ወር በላይ መቆየት ይችላል። በያሆዴ አተካናን አለማዘጋጀት አይቻልም። የሚሰራው ከቆጮ፣ ቡላ፣ ከቅቤ፣ አይብ፣ ወተትና ከተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ነው። ስራውም አድካሚና ጥራትን ስለሚፈልግ ቀደም ብሎና በሕብረት መሰራት ይጀምራል።
በዚህ ሥራ ላይ እንሰት ፍቆ ቡላ ከማዘጋጀት አንፃር በተለየ ሁኔታ ልጃገረዶች ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። አተካና የዘመን መለወጫ ቀንን አመላካች ነው። በበዓሉ እለት ለሚመጣ እንግዳና ማታ ለጭፈራ ለሚመጡ ህፃናት አተካና የግድ ይሰጣል። በአቅም ምክንያት አተካናን እንኳን ማዘጋጀት የማትችል ሴት ካለች የአካባቢው ነዋሪዎች ለአተካና መስሪያ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማጠራቀም ይሰጣሉ። በአሉም የሁሉም ሰው ደስታ ሆኖ ያልፋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012
ሞገስ ፀጋዬ