የአቢሲንያ ሽልማት ድርጅት በሀገራችን በ641 መስኮች፤ በአፍሪካ በ69 እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በ68 ዘርፎች በጠቅላላው በ706 የሙያ ዘርፎች ሽልማት ይሰጣል። በዚህ ረገድ ድርጅቱ ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ. ም በኦሮሞ ባህል ማዕከል በ706 የሙያ ዘርፎች ከፍተኛ ጥናትና ምርምር አድርገው ዓለምንና ሕዝቦቿን የሚታደግ ሥራ ለሠሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የከፍተኛ ክብር ሽልማት ማለት የሎሪየትነት ማዕረግ ሰጥቷል። ሜዳልያና ዲፕሎማ ሸልሟል። በዕለቱ የቀድሞ የኢሕፌዴሪ መንግሥት የፍትሕ ሚኒስትር የነበሩትና የአቢሲንያ ሽልማት ድርጅት የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አሰፋ ከሲቶ መርሐ ግብሩን አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
ሰብሳቢው ባሰሙትት ንግግር «መሸለምና መሸላለም በሀገራችን የተለመደ ነው። ይኸውም በኢትዮጵያ ታሪክ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት በየሙያ ዘርፉ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች ሽልማት ይሰጥ ነበር። በዚህ ዓይነት የኢሕፌዴሪ መንግሥትም ትርፍ አምራች ለሆኑ አርሶ አደሮችና ለፈጠራ ሰዎች ከሞላ ጎደል ሽልማት ሲሰጥ ቆይቷል። የአቢሲንያ ሽልማት ድርጅትም ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በምርምራቸው ሀገርን የሚጠቅም ሥራ የሠሩ ዜጎችን ሲሸልም ቆይቷል። ይህም የፈጠራና የምርምር ሰዎች አልተረሳንም፤ አልተዘነጋንም የሚል መንፈስ እንዲያድርባቸው፤ ለወደፊቱም ለፈጠራ በበለጠ እንዲነሣሡና መድረክም እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ የሚከናወን ተግባር ነው» ብለዋል።
በዚህ ዓይነት የአቢሲንያ ሽልማት ድርጅት ይህንን የከፍተኛ ክብር ተሸላሚዎች ሽልማት በየዓመቱ የሚሰጠው ሀገራችንን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ እንዲቻልና እድገታችንም ቀጣይነትና አስተማማኝነት እንዲኖረው ለማድረግ በማሰብ ነው። የሎሪየትነት ማዕረግ የተሰጣቸውና ሜዳሊያ የተበረከተላቸው ተሸላሚዎች በእውቀታቸው፤ በአስተሳሰብ ምጥቀታቸው፤ በሥነ ምግባራቸው፤ በአኗኗር ዘይቤያቸው በአርአያነት የሚታዩ ምርጥና ዕንቁ ዜጎች ናቸው።
በዕለቱ የከፍተኛ ክብር ተሸላሚዎች መኻከል ለአብነት ያህል በሕክምና ሙያ ባሳዩት ትጋትና ምርምር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ወልደመስቀል፤ በወታደራዊ አመራር ብቃታቸው ጀኔራል ሠዓረ መኮንን፤ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነትና በረጅነት አርቲስት ታማኝ በየነ፤ በሀገራችን ፖለቲካው ዘርፍ ትልቅ ቦታ ያላቸው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ በተመሳሳይ በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ታላቅ ሚና ለተጫወቱትና በመምህርነት ብዙ ባለሙያዎችን ያፈሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በሥዕል አሣሣል ጥበብ ካፒቴን ለማ ጉያ፤ ለአየር መንገድ ዋና አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ በስፖርት (እግር ኳስ) አሠልጣኝነት አቶ ሰውነት ቢሻው፤ የመቄዶንያን ቤተ አረጋውያን በመመሥረት የሚታወቁት ዶክተር ከበደ ጽጌ፤ በባህል ሙዚቃ ረገድ ድምጻዊው ዓለማየሁ ፋንታ፤ በትርጉምና በመዝገበ ቃላት ቅንብር ደራሲ ባሕሩ ዘርጋው እና ሌሎች በግብርና አገልግሎትና በእንስሳት ሕክምና ዘርፍ የተሸለሙ ተመራማሪዎች ተጠቃሾች ናቸው። እና በዚህ ዝግጅቴ ከደራሲ ባሕሩ ዘርጋው ጋር ስለአደረግሁት ቆይታ እነሆ እላለሁ።
ትውልድና ትምህርት
ደራሲ ባሕሩ ዘርጋው ግዛው በደቡብ ወሎ በቃሉ አውራጃ በተሁም ምክትል ወረዳ ስሬ በምትባል መንደር ግንቦት 27 ቀን 1929 ዓ. ም ተወለደ። እዚያው በተወለደበት መንደር መንፈሳዊ ትምህርት ተምሮ ዳዊት ከደገመና ሌላም የቃል ትምህርት ከተማረ በኋላ በወንድሙ ቀኝአዝማች ተሰማ ዘርጋው አማካይነት ወደ ደሴ ከተማ ተጉዞ ወይዘሮ ስኂን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርቱን ተምሯል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በቀድሞ ሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፤ በሐንጋሪ ቡዳፔስት ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማሠልጠኛ ተቋም በጋዜጠኝነት ሙያ፤ እንደዚሁም በኢጣሊያ ሮም ከኢንዱስትሪያል ኮንስትራክሽን ተቋም የአስተዳደርና ደንበኞች አገልግሎት ትምህርት ተከታትሎ በሦስቱም የሙያ ዘርፎች ከፍተኛ ዲፕሎማ ተቀብሏል። በተመሳሳይ አሜሪካ ከሚገኘው ቶማስ ኤድሰን ኮሌጅ በጋዜጠኝነት የባችለር ዲግሪ አግኝቷል። ነዋሪነቱ አሜሪካ ቨርጂኒያ ሊዝበርግ ከተማ ሲሆን ልጆቹንና ባለቤቱን ይዞ ወደ አሜሪካ የሔደው ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ነው።
አገልግሎት
ከአቢሲንያ የሽልማት ድርጅት የሎሬት ማዕረግ ያገኘው ደራሲ ባሕሩ ዘርጋው በትምህርት ሚኒስቴር በመምህርነት፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሒሳብ ሠራተኛነት፤ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል በዋናው ሥራአስኪያጅ ጽሕፈት ቤት በኃላፊነት፤በደንበኞች አገልግሎት ዋና ክፍል ረዳት ሹምነት፤ በሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ሹምነትና በክፍለ ሀገር መምሪያ ከፍተኛ ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል። በጊዜው በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ይታተም በነበረው ፈለገ ብርሃን ጋዜጣ ላይ የርእሰ አንቀጽና የሌሎች መጣጥፎች ጸሐፊ ሆኖ ሠርቷል።በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ በመመደብ አገልግሎት አበርክቷል።
እዚያ እያለ የባለሥልጣኑን መሥሪያ ቤት የሥራ እንቅስቃሴ የሚያመለክቱ ሥራዎችን በቪዲዮና በካሜራም በመቅረጽ አገልግሎት ላይ አውሏል። በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ቢሮ የትርጉም ሥራዎችና መጽሔቶች ዝግጅት ውጤታማ ሥራዎችን በመስራቱም ይታወቃል። በአጠቃላይ ደራሲ ባሕሩ ዘርጋው በመንግሥት ሥራ ላይ በቆየባቸው ዐርባ ዐመታት በመምህርነት፤ በጋዜጠኝነት፤ በሕዝብ ግንኙነት ሥራና በደራሲነት ለሀገሩ የድርሻውን ያበረከተና አሁንም ሙሉ ጊዜውን ለሥነ ጽሑፍ ሰጥቶ በሚኖርበት አሜሪካ ውስጥ በትጋት የሚንቀሳቀስ ሰው ነው።
የድርሰት ሥራ
ደራሲ ባሕሩ ዘርጋው የሥነ ጽሑፍ ሥራ መሥራት የጀመረው «ስም የለሽ» የተሰኘ የትርጉም ሥራ አሳትሞ ለአንባብያን በማቅረብ ነው። ስም የለሽ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለተከታታይ ወራት በ2005 ዓ.ም በአቶ ደጀኔ ጥላሁን አንደበት ተተርኮለታል። በተጨማሪም በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤላውያን መካከል ስለተፈጠረው ከፍተኛ አለመግባባትና ስለጦርነቱ አነሣሥ የሚያትትና «በባቢሎን ወንዞች» የሚል የትርጉም ሥራ ሠርቷል። እንደዚሁም «ከርታታው» የተሰኘ የራሱን የልቦለድ ሥራ አሳትሟል።
ከርታታው በወሎ ውስጥ ክርስቲያኑና ሙስሊሙ ሕዝብ በሰላም ተባብሮና ተከባብሮ፤ ተፈቃቅሮ መኖሩ የተመሰከረለት እንደሆነ፤ ስለ ወሎ ሕዝብ ማኅበራዊና ባህላዊ ሕይወት ማለት ስለመሬት ሥሪቱ፤ ስለወጉና ባህሉ፤ ያገባች ሴት ለምን በአንገቷላይ ቀለበት እንደምታደርግና ያላገባች ልጃገረድ ደግሞ በአንገቷ በማተብ ድንብል እንደምታደርግ፤ ስለከንፈር ወጃጅ…ያትታል። በጋራ ደግሞ ከሩሲያዊው ፕሮፌሰር ሞሪ ጋር «ማክሰኞዎች» የተባለ ሥራ ሠርቶ ለኅትመት አብቅቷል። እንደዚሁም በቅኝ አገዛዝ ዘመን አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀረማመት እንዴት እንደዶለቱና ተግባራዊ እንዳደረጉ የሚገልጽና የምሥጢሩ ቁልፍ የተሰኘ የትርጉም ሥራ ሠርቶ በማሳተም ለንባብ አብቅቷል።
ደራሲ ባሕሩ ዘርጋው ጥንታውያን የሆኑት ነባር ቃላት ከነዘያቸው እንዳይጠፉ በማሰብ የአማርኛ ቃላትን አሰባስቦና «ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት» በሚል ሰይሞ በተከታታይ ያሳተመ ሲሆን ይህንኑ ሥራውን በበለጠ አሻሽሎና በርካታ ቃላትን ጨምሮ፤ ላልተውና ጠብቀው በሚነበቡ ቃላት አናት ላይ የማጥበቅና የማላላት ምልክቶችን ጨምሮ በ2010 ዓ. ም ያሳተመው ሦስተኛው «ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት» እትም ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ. ም በኦሮሞ ባህል ማእከል በተከናወነ የአቢሲንያ የከፍተኛ ክብር ሽልማት ለመቀበል አስችሎታል። በነካ እጁም በራሱ ጥረት ኦሮሚፋ ተምሮና ለቱሪስቶች እንደመመሪያ ሊያገለግል በሚችል መልኩ «እንግሊሽ -አምሐሪክ- ኦሮሚፋ መዝገበ ቃላት» ( English-Amharic-Oromo Phrase Book and Dictionary for Travelers 1999 ) አሳትሞ በማሰራጨት ውጤታማ መሆኑን አጫውቶኛል።
ይህ መዝገበ ቃላት ለሀገር ጎብኚዎች እንዲጠቅም ታስቦ የተሠራ ቢሆንም በሦስቱም ቋንቋዎች እውቀት ለመገብየት የፈለገ ሁሉ ቢያነብበው ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። በዚህ እንግሊዝኛ -አማርኛ- ኦሮሚፋ መዝገበ ቃላት መጨረሻ ገጾች ላይ እንደ አፋር፤ አክሱም፤የሓ፤ነጋሽ፤ደብረ ዳሞ፤ጎንደር፤ ላሊበላ፤ ሐረር፤ደብረ ሊባኖስ፤ዳሎል ደናክል፤ጢያ፤ስሜን ተራራዎች፤ ጢስ አባይ፤ዐባያና አቢያታ ሐይቆችና እንደ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የመሳሰሉ የሀገራችን ታሪካዊ ቦታዎችና የቱሪስት መስህቦች መጠቀሳቸው ታሪክን ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ጠቃሚዎች ናቸውና መጽሐፉን ማንበብ ሁለት ዓይነት ተቀሜታ ይሰጣል።
ደራሲ ባሕሩ ዘርጋው፤
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012
ታደለ ገድሌ ዶ/ር