ልዩ ግርማ ሞገስ አለው፤ በሚያስገርሙ፣ በሚያስደስቱና ለዘመናት በማይደበዝዙ አያሌ ክስተቶች የተሞላ ነው። ከተፈጥሮ ቅኝት ጋር ያለው ውህደትና መስተጋብር አጃኢብ የሚያሰኙ ሁነቶችን አስከትሎ የመጣው የመስቀል በዓል ዛሬም ዓለምን ብቻ ሳይሆን እኛን የባህሉን ባለቤቶች ሳይቀር በዓመት አንድ ጊዜ ብቅ እያለ ያስደምመናል። ተፈጥሮ በአደይ አበባ የምታጅበው፣ የምታሳምረው የመስቀል በዓል የሚናፈቀው ገና የዘመን መለወጡን ተከትሎ ነው።
ይሄንኑ ድንቅ ባህል የሚናፍቀው ደግሞ ሀገሬው ብቻ ሳይሆን ዝናውን የሰሙ፣ መጥተው ያጣጣሙ ቱሪስቶች ጭምር ናቸው። ይህ የአደባባይ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶችን አጣምሮ የያዘው የመስቀል በዓል የማይዳሰሱ የዓለም ቅርስ በመሆን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የባህልና የትምህርት ድርጅት ተመዝግቧል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም የደመራና መስቀል በዓል ዛሬ ላይ እንዴት እንደደረሰ ካጠኑት ጥናት በመነሳት የቅርሶች መመዝገብ ውጤቱ ቀደም ሲል የነበረው የአከባበር ሥርዓት ውጤት መሆኑን ይጠቅሳሉ። ስለሆነም መስቀል ሲታሰብ ደመራን ለቆ አይሆንም። ምክንያቱም በደመራ ዕለት ከልጃገረዶች እኩል ሰፈር መንደሩ ይደምቃል። የደመራ ችቦም ተለኩሶም አገሪቱ በብርሃን ትንቦገቦጋለች፤ ቋንቋ ሳይለይ ‹‹ድገምና ለዓመቱ›› ይባላል። ለመልካም ምኞት ምላሽ ሰጥቶ መለያየትም በዚያ ጊዜ የሚከወን ነው።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የማይመረመር ቢመረመርም ከጥልቀቱ የተነሳ የማይደረስበትና ወጥ ቀመር የማይበጅለት ነው የሚሉት መምህር መክብብ፤ ታላቁ ባለቅኔ መንግስቱ ለማ ስለመስቀል በቋጠረው ስንኝ እንዳለው ተፈጥሮ ቀጠሮ ይዛ የምትመጣበት ብቸኛ አገርና በዓል መስቀል መሆኑን ያነሳሉ። እንዲህ ሲሉ
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፣
ማንያውቃል?
ብሎ ይጠይቃልና ነው። ይህንን ለምን አለ ከተባለ መልሱ እንዲህ ነው። ግጥሙ ውስጥ ትልቅ ሀሳቡን ያሸከማት “ማን ያውቃል?” የምትለው መዝጊያ ስትሆን፤ የተገለፀውን የሀገረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ባህሪ የምትገልጥ ሆና እናገኛታለን ይላሉ።
የመስቀል ወፍም ሆነ አደይ አበባ ከማን ጋር ቃልኪዳን ተጋብተው? የማን ወይም የምን ፍቅር አስገድዷቸው? የማን ስብዕና ማርኳቸው በየዓመቱ ከተፍ እንደሚሉ የጠየቃቸው የለም። ማንም አነጋግሯቸው መልስ አላገኘም። የተፈጥሮ ሂደት ብቻ ስለሆነ በአምላክ ፈቃድ ተግባሩን ይከውናሉ። እናም መስቀልም በየዓመቱ ሲከበር ለአገር ብልጽግና ይዞት የሚመጣው ነገር እንዳለ ታሳቢ እያደረጉ ማክበር እንደሚገባ ከዚህ መገንዘብ ይቻላል ባይ ናቸው።
ለእኛ ለሚወዱን ኢትዮጵያውያን ወይም ለሚወዷት ምደረ ቀደምት ሀገረ ጦቢያ ባላቸው የማይናወጥ ፍቅር ቀጠሮ ሳያዛንፉ በየዓመቱ እየመጡ እንደሆነም አስበን “እንኳን አደረሳችሁ” መባባሉም ከዚህ የመነጨ እንደሆነ የሚናገሩት መምህር መክብብ፤ አደይ አበባና የመስቀል ወፍ ለዘመናት የደመቁበት፤ የዓውዳመት ዜማና ግጥም ደራሲዎች ብቅ ማለት የሚጀምርበት ጊዜ መስቀል መሆኑን ይናገራሉ።
የዓውዳመቱ መዓዛና ሽርጉድ፣ የፍቅርና መዋደዳችን ናፍቆት፣ የሰላምና መከባበራችን ትዝታ ጠርቷቸው መካከላችን ለመገኘት ባህር ተሻግረው፣ ወንዝ አቋርጠው፣ ጥሪታቸውን ከስክሰው ከውበታችን እፍኝ ሸምተው በውበታችን ላይ ውበት ሊደርቡ፣ ከፍቅር ፅዋ ተጎንጭተው በፍቅራችን ላይ ፍቅር ሊጨምሩ፣ ከደስታ ሀሴት ባህራችን ጠልቀው በድምቀታችን ላይ እልፍ ድምቀት ሊያክሉ በየዓመቱ የሚመጡ የመስቀል ወፍና የአደይ አበቦች እንዳሉን እናውቃለን።
ይህ ደግሞ ደመራንም ይጨምራል የሚሉት መምህር መክብብ፤ እስከዛሬ እያከበርን በመጣነው ደመራችን፤ የሰላም አየር ተንፍሰናል፣ የምንጓጓለትን ፍቅርና መተሳሰብ ልማድ አድርገንም ተጉዘናል። የመከባበር ቀናዒ ማህተማችንን አጎልብተንበታል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ መልካችን መጉላት የቻለውም በዚህ እንደሆነ ያነሳሉ። ለመሆኑ ወደ መስቀል ቀን የሚወስደን ደመራ መቼ መከበር ጀመረ ከተባለ ዝርዝር ጉዳዮችን በማንሳት ያወጋሉ።
መስቀል መቼ መከበር ጀመረ
የመስቀል ደመራ ማክበር የተጀመረው በ1898 ዓ.ም በአፄ ምኒልክ ዘመን ሲሆን፤ የሚከበረውም በጃንሜዳ ነበር። ያን ጊዜ ጃንሜዳ ለሰልፍ፣ ለስብሰባ፣ ለስፖርት ተብሎ የተቋቋመ ቢሆንም ደመራም እዚያው ነበር የሚከበረው። ከዚያ በልጅ እያሱ ጊዜ ማለትም መስከረም 16 ቀን 1908 ዓ.ም በዚያው በጃንሜዳ ደመቅ ተደርጎ እንደተከበረ ይናገራሉ።
በወቅቱ በትልቅ ወታደራዊ ትርኢት የተከበረ ሲሆን፤ ሌላው ቀርቶ ደመራው ከተደመረ በኋላ የአለባበስ ሥርዓቶች ሳይቀር ደምቀው የታዩበት ነበር። ይህ ሥርዓት ደግሞ ከልጅ እያሱ የጀመረ ሲሆን፤ ቀይ ከፋይ ባለወርቅ ሰገባ ይዞ ባለወርቅ ካባ ደርቦና በወርቅ ኮርቻና መጣምር ባጌጠ፣ “ጤና” በተባለ ፈረሱ ላይ ተቀምጦ፣ በፈረስ ታጅቦ እንደገባ ባጠኑት ጥናት እንዳገኙ ይናገራሉ። አሽከሮቹ ደግሞ ከወርቅና ከብር በተሰራ ልዩ ልዩ ጌጥ አጊጤው ተቀብለውት እንደነበርም ያነሳሉ። ይሁንና በዓመቱ ግን ልጅ እያሱ ላይ ተቃውሞ መነሳት በመጀመሩ የመስቀል ደመራው እዚያ መከበሩ አልቀጠለም።
እናም ጃንሜዳ ከዚያ በኋላ አዋጅ ማወጃ ሆነ። “ልጅ እያሱ አይቀጥልም፤ ይውረድ” የሚሉ ተቃውሞዎች መግለጫ ቦታም ተደረገ። ስለዚህ ደመራው በቀጣይ ዓመትም እንዳይቋረጥ በሚል ፍልውሃ ሜዳ ተወስዶ መከበር ጀመረ። የ1918 ዓ.ም ደግሞ ኃይለሥላሴ ሲነግሱ እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ 58ኛው የተባሉ የደብረ ሊባኖስ እጨጌና ራሳቸው ጃንሆይ በተገኙበት፣ የአራዳና የክብር ዘበኞች በዘመናዊ ሥርዓት ተሰልፈው፣ ልዩ ትርኢት በደመራ ጊዜ እያሳዩ በዚሁ ስፍራ መከበሩን መርስኤሀዘን ወልደቂርቆስ ‹‹ የ20ኛው ዘመን መባቻ›› ከሚለው መጽሐፋቸው ላይ ያገኙትን አብነት በማድረግ ይናገራሉ። በዚህ ጊዜ ደመራ ሲከበር ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ መስቀል ታሪኩ ጭፍሮቻቸውንና የፖስታ ቤት ሠራተኞቻቸውን አሰልፈው አርባ ያህል የአርመን ሙዚቀኞችን በመያዝ በሙዚቃ ታጅበው ትርኢት አቅርበው እንደነበርም ያስረዳሉ።
የደመራና የመስቀል በዓል በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፊ ቦታ እየተሰጠው በመምጣቱ የሚያከብረው ሰው በዛ። ስለዚህም ቦታው በቂ ስላልነበር ወደ አራዳ ጊዮርጊስ ሜዳ እንደተሸጋገረ የሚገልጹት መምህር መክብብ፤ እስከ 1920 ዓ.ም ድረስ ከአራዳ ሳይነጠል በዓሉ ሲከበር እንደቆየ ያስታውሳሉ። አንድ ቦታ ተወስኖለት ሳይከበር የቆየው የደመራ ወይም የመስቀል በዓል አሁንም ከአራዳ ጊዮርጊስ ሜዳ ተነስቶ አፄ ምኒልክ ሐውልት የቆመበት ትልቁ ሜዳ ላይ መከበሩን ቀጠለ።
ያን ጊዜ እንደውም በበዓሉ ዕለት ሦስት አውሮፕላኖች እያንዣበቡ በመገለባበጥ ትርኢት አሳይተዋል። የወረቀት አበባና የግጥም ፅሑፎችን ይበትኑ እንደነበር ይነገራል ይላሉ መምህር መክብብ። በጣም የተለየ አከባበር እንደነበረውም ያነሳሉ። በጣም የሚገርመው ግጥሞች ሁሉ የቀረቡ መሆኑን ጠቅሰው ጥቂት ግጥሞችንም አስታውሰው እንዲህ ነግረውናል።
«የመስቀል በዓል ምንኛ ገነነ ከአምናም ዘንድሮ የበለጠ ሆነ ንግስትና ንጉስ በዙፋን ላይ ሆነው ጀግናው ተሰልፎ መኳንንቱ ከበው በግራና በቀኝ በራስጌ በግርጌ አምስት ጳጳሳት ስድስተኛ እጨጌ ደግሞም ተንዣበበ በስተላይ ባየር ከጓደኞቹ ጋር የተፈሪ ንስር» «ንስረ ተፈሪ» እንግዲህ በዚያን ወቅት የአውሮፕላኑ ስም ነበርም ይላሉ። «አበባ አበባ ሊነሳ በዓሉን ሊያከብር በዘንድሮ በዓል እስኪ ደስ ይበለን እልል እንበል ብርሀንን እንልበስ ሰላምን እንውደድ ንስረ ተፈሪ ነው በጨለማ እንሂድ በአየር ላይ ሆኖ አበባን ሲሰራ ከተከታዮቹ ከመላዕክት ጋራ እንቁጣጣሽ ይላል የተፈሪ አሞራ» ይላል
ግጥሙን በመስቀል ደመራ ክብረ በዓል ላይ አውሮፕላኖች ትርኢት እያሳዩ ይበትኑታል። ከዚያ በተጨማሪም እነዚሁ አውሮፕላኖች በስዕል የተደገፈ አደይ አበባ ሳይቀር በትነው ሕዝቡን ያስደስቱ እንደነበርም አጫውተውናል። ይህ ትርኢት ካለቀ በኋላ ደግሞ ሕዝቡ ወደመጣበት ለዓመት ያድርሰን በሚል ተመራርቆ ይመለሳል።
በዚህ ሁኔታ ሲደምቅ የሚውለው ደመራ አሁንም ማረፊያው ይህ አልሆነም የሚሉት መምህር መክብብ፤ ሲከበርበት የቆየው ቦታ በመጥበቡና በ17 እስጢፋኖስም አብሮ እንዲከበር በመታሰቡ ደመራው ወደ እስጢፋኖስ ሜዳ ወይም እስጢፋኖስ አደባባይ እንደሄደ ያብራራሉ። ይህም ቢሆን ባህልና በዓል አክባሪነቱን የሚወደው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓሉን በስፋት ማድመቁን ቦታ ቢቀየርም አልቀነሰም። እንደውም እየበዛ ሄዶ ሰፊ ቦታ ጠየቀ እንጂ። ስለዚህም ጃንሆይ የክብረበዓሉን ቦታ የዛሬው መስቀል አደባባይ ላይ እንዲሆን አደረጉ።
ደርግ ቦታውን ሲቆናጠጥ ደግሞ መስቀል አደባባይ ሌላ ተግባር መከወኛ በመደረጉና አብዮት አደባባይ በመባሉ የመስቀል ደመራ ተመልሶ ወደ ምኒልክ አደባባይ እንደተዛወረ የሚያነሱት መምህር መክብብ፤ የመስቀል ደመራ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው በየሰፈሩ ሕዝቡ ሲያከብረው ቆየ። ነገር ግን ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም አገሪቱን ሲቆጣጠር አንድ ወጥ ቦታ እንዲያገኝ ተደረገ። ሕዝቡ የለመደውና የሚወደው ቦታው በበዓሉ ስም ስያሜን ያገኘውን ስፍራ እንዲይዝም ዕድል ተቸረው ይላሉ።
መስቀል አደባባይ ለደመራ በዓል ቋሚ የመከበሪያ ስፍራ መሆኑ ብዙ ጥቅሞችን እንዳስገኘ የሚናገሩት መምህር መክብብ፤ በቀደመ ግርማ ሞገሱ ዳግም በዓሉ እንዲከበርበት፤ ማህበረሰቡም ትክክለኛውን የበዓሉን ክብር እንዲሰጥበት፤ በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ እንዲመዘገብ አስችሏል ይላሉ። በ1987 ዓ.ም የሃይማኖት ነፃነት በሕገ- መንግሥቱ ሲፀድቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመላው አደባባይ እያሸበረቀ፣ የሃይማኖት አባቶችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት እየተጋበዙ የበለጠ እንዲደምቅና የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የባህልና ኪነጥበብ መድረክም እንዲሆን ከፍተኛ ዕድል የሰጠም መሆኑን ያነሳሉ።
በዓሉ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትና ከኢትዮጵያ ሀብትነት አልፎ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብም ያደረገው ቋሚ የክብረ በዓል ቦታ በማግኘቱ መሆኑን የሚያነሱት መምህር መክብብ፤ ብዙ ሂደትና ውጣ ውረድ አልፎ ለዚህ መብቃቱ የሚደንቅ በመሆኑ አሁንም የበለጠ ልናሳድገውና ልንንከባከበው እንደሚገባ ያሳስባሉ። ባህላችንን፤ እድገታችንን፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ መልካችንን የምናሳይበት ነውና እንጠብቀው፤ ለትውልድም እናሸጋግረው፤ ከዚያም አልፈን ለአገር ብልጽግና እናውለው በማለት እንሰናበት። መልካም በዓል!
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው