“የወባ በሽታ ጭንቅላት ላይ ወጥቶ እከሌን ገደለ” ሲባል እንሰማለን፤ በእውነቱ የወባ በሽታ አንጎል ውስጥ ይገባልን?የሚለውንና ከወባ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እናያለን፡፡ወደ ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት ግን በቅድሚያ እንኳን ከክረምቱ አልፋችሁ ለብሩሁ በጋ ደረሳችሁ! እላለሁ፡፡ዘመኑ ከወባና መሰል በሽታዎች የምትጠበቁበት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡
በበጋ ሰዎችን ከሚያጠቁ በሽታዎች ውስጥ አንጋፋ የሆነው እና በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ በተለይም ከሰሀራ በታች የሚገኙ አገሮችን የሚያጠቃው በሽታ ወባ (Malaria) ነው፡፡ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከ30 ሚሊዮን አመታት በፊት ጀምሮ የሰው ልጆችን እያጠቃ የሚገኝ በሽታ ነው፡፡ሆኖም የሰው ልጅ ስለ ወባ በሽታ በትክክል መመርመር የጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት አራተኛ ምዕተ አለም (4th century B.C.) በግሪኮች ስልጣኔ ግዜ ውስጥ ነው፡፡ተመራማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለወባ በሽታ መድሃኒት ያገኙት በ19ኛ ክፍለ ዘመን በ1820 ነው፡፡
የወባ በሽታ ምን ያክል ሰውን ይገድላል?
በአመት 3 ቢሊዮን ሰዎች ለወባ በሽታ ይጋለጣሉ፡፡ከነዚህም ውስጥ የወባ በሽታ ይዟቸው ምልክት የሚያሳይባቸው ሰዎች 243 ሚሊዮን ይሆናሉ፡፡የወባ በሽታ እ.ኤ.አ. በ2004 በአንድ ዓመት በቻ 1.82 ሚሊዮን ሰዎች ገሏል፡፡በ2010 ውስጥ ግን ዝቅ በማለት የ1.24 ሚሊዮን ሰዎች ህይወትን ቀጥፏል፡ ፡የአለም ጤና ድርጅት ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ከ2 አመታት በፊት ማለትም እ.ኤ.አ. 2017 ግማሽ ሚሊዮን ያክል (435,000) የሚሆኑ ሰዎችን ገድሏል፡፡የወባ በሽታ ከሚገድላቸው ሰዎች ውስጥ 80 በመቶ (80%) ከሰሀራ በታች በሚገኙ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ራሽያ ያሉት አገሮች ከ30 አመታት በፊት ጠፍቷል፡፡ወደ አገራችን ስንመጣ በአገራችን ውስጥ የሚገኙ ቦታዎች 75 በመቶ (75%) ለወባ በሽታ የተጋለጠ ነው፡፡
የወባ በሽታ ከአገራችን በብዛት የሚያጠ ቃው አካባቢ የት ነው? በአገራችን ውስጥ የወባ በሽታ ስርጭት ከቦታ ቦታ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው ከባህር ጠለል በላይ የቦታ ከፍታ (Sea level) ያለውን ልዩነት መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ከባህር ጠለል ከ2000 ሜትር ከፍታ በታች የሚገኙ ቦታዎች ከፍተኛ የሙቀት መጠን ስላላቸው ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ነው፡ ፡ስለዚህ የወባ በሽታ ይበዛበታል፡፡በዚሁ መሰረት የምዕራብ ኦሮሚያ ፣ አማራ እና ትግራይ ቆላማ ቦታዎች፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ በሙሉ የወባ በሽታ አስከፊ የሚሆንባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
የምስራቅ ኢትዮጵያ ቆላማ ቦታዎች (በይበልጥ ሱማሌ እና አፋር ክልሎች) ውስጥ ደግሞ የወባ በሽታ በብዛት የማይገኝ እና የውሃ ፍሰትን በመከተል፣ በወንዝ አካባቢ ብቻ ይገኛል፡ ፡ይህም የምስራቅ ቆላማ ቦታዎች የሙቀት መጠናቸው ከፍተኛ ቢሆንም እርጥበት ስለሌላቸው ለወባ ትንኝ እርባታ ምቹ አይደሉም፡፡የአገራችን ወይናደጋ ደግሞ ቅዝቃዜ ስላለበት ከወባ በሽታ ነፃ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የወባ በሽታ ሰውን የሚይዘው ከምን ምንድነው? በአመዛኙ የሚተላለፍባቸው ወቅቶች የትኞቹ ናቸው?
የወባ በሽታ አምጪ በአይን የማይታዩ አይነታቸው ፕሮቶዝዋ (protozoa) የሆኑ ፕላስሞዲየም (plasmodium) የሚባል ጥቃቅን ህዋስ ናቸው፡፡ፕላስሞዲየም 6 አይነት ዝርያ ያላቸው ሲሆን በአገራችን የወባ በሽታ አምጪ የሆኑት 2 አይነት ናቸው፡፡እነሱም ፕላስሞዲየም ፈልሲፓሪየም (plasmodium falciparum) እና ፕላስሞዲየም ቫይቫክስ (plasmodium vivax) ናቸው፡፡እነዚህን ጥቃቅን ህዋሳት ከሰው ወደ ሰው የምታስተላልፈው አኖፊለስ ሞስኪቶ (anopheles mosquitoes) የምትባል ሴት የወባ ትንኝ ናት፡፡ ይህች ትንኝ የምትራባው የተጠራቀመ ውሃ ውስጥ ነው፡፡የወባ ትንኝ በብዛት እና በከፍተኛ ደረጃ የሚተላለፉበት ወራት ደግሞ በመስከረም እና ሚያዝያ ወራት ነው፡፡
የወባ በሽታ ምልክቶች ምንድናቸው?
በወባ በሽታ ህመምተኛ ላይ የሚታዩ ምልክቶች ከወባ ጋር ተመሳሳይነት ባላቸው ሌሎች በሽታዎች ላይ ስለሚታዩ ለመለየት ይከብዳል፡፡ይህንን ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በጤና ባለሙያ የሚለይ ቢሆንም በምናያቸው የወባ በሽታ ምልክቶች፡ የጤንነት ስሜት አለመሰማት፣ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ድካም ስሜት፣ የሰውነት መሰባበር (የጡንቻዎች መታመም) እና አንዳንድ ጊዜ በሆድ ውስጥም ደስ የማያሰኝ ስሜት ከተሰማን በበሽታው መያዛችንን መጠርጠር ይገባል፡፡
ትኩሳት፣ መንቀጥቀጥ እና ብርድ ብርድ ማለት ለተወሰነ ጊዜ ከቆመ በኃላ በየ48 ወይም 72 ሰአታት ልዩነት ሊመላለስ ይችላል፣ እንደዚሁም አንዳንድ ጊዜ በቀጣይነት ምልክት ሊያሳይ ይችላል፡፡ብዙውን ጊዜ የወባ በሽታ በመደጋገም ሰውን ከያዘ እና የያዘው ደግሞ ከሰውነት ውስጥ ሳይጠፋ ቆይቶ ሲቀመጥ ሆድን መንፋት እና በሆድ እቃ ውስጥ የሚገኙ አካላት እንደ ጣፊያ (Spleen) የሚባለውን ሊያሳብጥ ይችላል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ምልክቶች የሚታዩት የወባ በሽታ ቀላል ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ወባ ጭንቅላት ከገባ (cerebral malaria) የተለየ ምልክት ሊያሳይ ይችላል፡ ፡ይሄ ነው “የወባ በሽታ ጭንቅላት ላይ ወጥቶ እከሌን ገደለው” ሲባል የምንሰማው፡፡ የወባ በሽታ ከባድ ከሆነ እና በተለይም አይነቱ ፕላስሞዲየም ፈልስፓሪየም (plasmodium falciparum) በሚባለው የሚመጣ ከሆነ አእምሮ ያለመስራት፣ የሌለ ነገር መናገር (መቀባዠር)፣ ራስን መሳት፣ መንቀጥቀጥ (የሚጥል በሽታ እንዳለበት ሰው የመሆን) ምልክት እና ባስ ሲልም ነፍስ እስከመቅጠፍ ሊሄድ ይችላል፡፡
የወባ በሽታ ነፍሰጡር ሴቶችን በተለየ መልኩ የሚያጠቃው እንዴት ነው? የወባ በሽታ በሌላ ሰው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ ነፍሰጡር ሴት ላይ ያይላል ፡፡ለደም ማነስ ፣ በሰውነት ውስጥ ለሚገኝ ግሉኮስ ማነስ እና ለሳምባ በሽታ ነፍሰጡር ሴቶችን የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡በህፃናት ላይ፡ እንደ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የፅንስ ሆድ ውስጥ መጨናገፍ፣ ጊዜ ሳይደርስ መወለድ እና በወባ በሽታ ተይዞ መወለድን (congenital malaria) ያስከትላል፡፡እነዚህ ችግሮች ሁሉ የህፃኑ በህይወት የመኖር እድሉን ያሳንሳሉ፡፡
የወባ በሽታ ህክምና የሚሰጠው እንዴት ነው?
የወባ በሽታ በቀላል ሁኔታ መከላከል የሚቻልና ታክሞ የሚድን ነው፡፡የሚሰጠው መድሃኒትም እንደ ወባ በሽታው አይነት ልዩነት ያለው እና በወባ በሽታው አስከፊነት ላይ ተመርኩዞ በቤት እና ሆስፒታል ተኝተው መታከምን የሚጨምር ነው፡፡ እስከአሁን ድረስ የወባ በሽታ አምጪ ህዋስ inde leloch infection ከመድሃኒት ጋር መላመድ አለመቻላቸው ማንኛውም የወባ በሽታ ታክሞ መዳን እንደሚቻል ያሳየናል፡፡
የወባ በሽታ መከላከል ይቻላልን?
ከላይ እንደተቀመጠው የወባ በሽታ መከላከል ይቻላል፡፡የወባ በሽታ መከላከያ የወባ ትንኝ ላይ ያተኩራል፡፡ይህንንም ከዚህ በታች ባለው መሰረት ከፋፍለን ማየት እንችላለን፡-
* ከሁሉም በፊት አካባቢያችን ለወባ በሽታ የሚያጋልጥ ነው አይደለም ብለን ከላይ እንደተገለፀው ሁኔታ ለይተን ማወቅ ግድ ይላል፡፡አካባቢያችን ለወባ በሽታ የሚያጋልጥ ከሆነ ከዚህ በታች የተጠቀሱ ምልክቶችን ለይተን መከላከል አለብን፤-
• በአካባቢያችን የወባ ትንኝ እንዳይራቡ ማድረግ፡ የወባ ትንኝ ለመራባት የተጠራቀመ (የማይፈስ) ውሃን ትፈልጋለች፤ ስለዚህ ነው በመስከረም እና ሚያዝያ ወራት ውስጥ በብዛት የሚተላለፈው፤ ስለዚህ በአካባቢያችን ውስጥ ተጠራቅሞ የሚገኝ ውሃን ማጥፈፍ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ በግልፅ መገንዘብ ያለበት የወባ ትንኝ ለመራባት ትልቅ ውሃ አያስፈልግም፤ በተጣለ ጫማ ወይም ተሰብሮ በተጣለ እቃ ውስጥ የተጠራቀመ ውሃ ለወባ ትንኝ መራባት በቂ ነው፤ ስለዚህ እንደዚህ ያሉ የተጠራቀሙ ጥቃቅን ውሃዎችን ማስወገድ ይገባል፡፡
• የወባ ትንኝ እንዳትነክሰን መከልከል፡ ይህም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የወባ ትንኝ በቀላሉ ቤት እንዳትገባ መስኮት እና በር በአግባቡ መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ደግሞ በመኝታ ቦታ የወባ ትንኞችን የሚከላከሉ እንደ አንጎበር ያሉ ነገሮችን መጠቀም ተገቢ ነው፡፡፤ስንተኛም ፊታችንን እጆቻችን እግሮቻችን በደምብ መሸፈን አለብን
• እነዚህም ሁሉ ማድረግ ካልቻልን ደግሞ የበሽታውን ምልክቶችን እንዳየን ወዲያውኑ ወደ ሀኪም ቤት በመሄድ በቂ ህክምና ማግኘት አለብን፡፡
ምንጭ፡- ጤና ድረ ገጽ
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012