ዘወትር በምሥጋና…

የአዲስ ዓመት ዋዜማ …

የአዲስ ዓመት ድባብ አካባቢውን ማወድ ይዟል። በርካቶች ለአውደ ዓመቱ ዝግጅት ሸብረብ እያሉ ነው። አንዳንዶች የመጪውን ዘመን ዕቅዳቸውን ያልማሉ። ሌሎች ደግሞ ባጠናቀቁት ዓመት የከወኑትን ስኬት እያስታወሱ፣ ዳግም ስለነገው እቅድ ይዘዋል።

ከዚህኛው መንደር ከአንደኛው ግቢ ደግሞ ውሎ በተለየ መልኩ ቀጥሏል። እንደ አበባ የፈኩ ሕጻናት ቀኑን በተለየ ሥሜት ተቀብለው እየፈነጠዙ ነው። የአብዛኞቹ ገጽታ በፈገግታ በርቷል። እርስ በርስ ፍቅርና ጨዋታን መጋራት ይዘዋል። ዛሬ በዚህ አጸድ ደስታ እየተመነዘረ ሳቅ ጨዋታ እየደራ ነው። ሁሉም ይህን ስሜት በእኩል መጋራት ይዘዋል።

ከዚህ እውነት ባሻገር ሌላው አይደበቄ ሀቅ በግልጽ እየታየ ነው። የነዚህ ዕንቦቃቅላ ወላጆች ደስታ ከፊታቸው ይነበባል። ሁሉም ስሜታቸው በአንድ መጋመዱ ግልጽ ነው። ዛሬም ሀሳባቸው በእኩል ተጣምሯል። ጨዋታ ወጋቸውን አመሳሳሎ፣ ችግር ሀዘናቸውን ያመሳሰለው ሚስጥር ደግሞ የጋራ አጀንዳቸው ከሆነ ቆይቷል። የልጆቻቸው ጤና፣ የፍሬዎቻቸው ሕልውና ጉዳይ።

በእነሱ ዘንድ ትውውቅና መግባባት ይሉት ጉዳይ መስፈርት ሆኖ አያውቅም። ስሜታቸው በአንድ ታስሮ ጨዋታቸው የጋራ ለመሆን አይዘገይም። የሁሉም እናቶች ትከሻ ስለልጆቻቸው ሰፊ እንደሆነ ጊዚያትን ዘልቋል። ወደፊትም ለእነሱ ከሆነ ድካም ይሉትን አያውቅም። እጆቻቸው ቢዝሉም ፈጽሞ አይሸነፉም።

ልብ ለልብ …

እናቶቹ በተገናኙ ቁጥር ስለ ልጆቻቸው አበክረው ያወጋሉ። ሁሌም የዛሬው ኑሯቸው፣ ያሳሥባቸዋል። የነገ ተስፋቸው ያሰጋቸዋል። የአብዛኞቹ እናቶች ስሜት ከሌሎቹ እናቶች ማንነት የተለየ ነው። እነሱ ‹‹ከልጆቻችን በፊት እኛን ያስቀድመን›› ብለው አያውቁም። ልጆቻቸው ከእነሱ አንዲት ደቂቃ ቀድመው ቢያልፉ /ቢሞቱ/ይመርጣሉ።

ሕጻናት ሲወለዱ ከአፈጣጠር ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮች ይኖራሉ። ከነዚህ መካከል የነርቭ ዘንግ ክፍተት /ስፓይና ቢፊዳ/ እንዲሁም ሀይድሮሴፋለስ ዋንኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት እነዚህ ችግሮች በእርግዝና ክትትል ግዜ የፎሊክ አሲድ ንጥረነገር ባለመውሰዳቸው የሚከሰቱ እክሎች ናቸው።

የነርቭ ዘንግ ከጀርባ የመሀለኛው ክፍል የላይኛውንና የታችኛውን ይዞ ከሀያ አንደኛው እስከ ሀያ ስምንተኛው የእርግዝና ቀናት ድረስ መዘጋት ያለበት የራስ ቅልና የሕብለሰረሰር ዘንግ ክፍተት ነው።

ሀይድሮ ሴፋለሰስ ደግሞ በጭንቅላት ወስጥ ከመጠን ያለፈ ፈሳሽ ሲያጋጥም ሲሆን በእርግዝና ግዜና ከወሊድ በኋላ በኢንፌክሽን ምክንያት ሊከሰት የሚችል ችግር ነው። የጭንቅላት መጠን በፍጥነት ማደግና መጨመር ሕመሙ ስለመከሰቱ ያመላክታል።

ይህ አይነቱ ሕመም የተከሰተባቸው ሕጻናት በወቅቱ የቀዶ ሕክምና ማግኘት ከቻሉ በጭንቅላታቸው ላይ ከመጠን በላይ የተከሰተውን ፈሳሽ ማስወገድ ይቻላል። የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉትም በወቅቱ ሕክምና መደረጉ የነርቭ ሕዋሳቱ የከፋ ችግር ሳይደርስባቸው የሕጻናቱን ሕይወት ለመታደግ ያስችላል።

ወደመነሻችን እንመለስ። መግቢያችን ላይ ወዳነሳናቸው ወላጆችና ሕጻናት። እነዚህ ወገኖች ከእርግዝና ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ የጭንቅላትና የነርቭ ዘንግ ክፍተት ሳቢያ ዋጋ የሚከፍሉ ቤተሰቦች ናቸው። አብዛኞቹ ወላጆች እናቶች ቢሆኑም ስለልጆቻቸው የመልካም አባት ተምሳሌት የሆኑ ጥቂት አባቶችም ተቀላቅለዋቸዋል።

ከእነዚህ ወላጆች ጋር የሚታዩ ልጆች ጭንቅላታቸው ላይ በሚከሰት ችግር ለተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና የወሰዱ፣ አልያም በመውሰድ ላይ የሚገኙ ናቸው። በተመሳሳይ የጀርባ ላይ ክፍተት ያለባቸው ሕጻናት በአብዛኛው ከወገባቸው በታች መንቀሳቀስ የማይችሉ ናቸውና የዕድሜ ልክ ዳይፐር ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከነዚህ ሕጻናት መሀል ገሚሶቹ ከወላጆቻቸው ጋር በወጉ የሚግባቡ ናቸው። የተወሰኑት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የሌሎችን እገዛ የሚሹና የእይታም ሆነ የመግባባት ልማድ ታይቶባቸው የማያውቅ ሆነው ቀጥለዋል። ይህ እውነት ልጅ ወልዶ በጤና ለማሳደግ ለሚጓጓ ወላጅ ፈታኝ የሚባል ክፉ አጋጣሚ ነው።

ብዙ ግዜ በቤተሰቡ መሀል እንዲህ አይነት ልጆች በተወለዱ ግዜ የመከራ ዳፋው የሚወድቀው በእናቶች ትከሻ ብቻ ይሆናል። እንደውም አንዳንድ አባቶች የልጆቹን ችግር ባዩ ግዜ ትዳር ፈተው፣ ቤታቸውን በትነው ይርቃሉ። ብዙ ናቸው ባይባልም ጥቂት ልበ መልካም አባቶች ደግሞ የልጆቻቸውን ችግር ተቀብለው ሕመም ስቃያቸውን በእኩል ይጋራሉ።

ሆፕ. ኤስ .ፒ. ኤች/ Hope –SPH/ የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት በሀገራችን ብቸኛው በስፓይና ቢፊዳና ሀይድሮሴፋልስስ ችግር ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ነው። ድርጅቱ በዘውዲቱና በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች ወላጆችን የማማከርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራትን ይከውናል።

በችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሕጻናት ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ የሕህክምና መሳሪያዎችን ከውጭ አገራት በማስመጣት የስልጠና መርሀግብሮችን ያመቻቸል። ከየክልሉ ለልጆቻቸው የሕክምና ክትትል የሚመጡና ተቀባይ ዘመድ ለሌላቸው ወገኖችም በቂ ማረፊያ በማዘጋጀት ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛ በሻህ በዚህ ችግር ተጠቂ በሆነው ልጃቸው ምክንያት ድርጅቱን ከፍተው መሰል ወላጆችና ተጎጂ ልጆቻቸውን ለማሰባሰብ ምክንያታቸው ሆኗል።

እሳቸው አብዛኞቹ ወላጆች በተለይም እናቶች የሚደርስባቸውን ሕመምና ችግር ይጋሩታል። ልጃቸው ደግሞ ከሌሎች ሁሉ ይለያል። የመናገር፣ የመስማት፣ የማየትና የመንቀሳቀስ ችግሮች አሉበት። ሁልግዜ ግን ትንሹ ህዝቅኤል ብሩህ ፈገግታ ከፊቱ አይጠፋም።

እናት ቤዛ ሁኔታው ቢያሳዝናቸውም ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጡም። የእሱ ተፈጥሯዊ አጋጣሚዎች ለበርካታ ወላጆችና ልጆቻቸው ምክንያት ሆኖ በከፈቱት ተቋም ብዙሀንን ማሰባሰብ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ሰሞኑን አዲስ ዓመትን አስመልክቶ በድርጅቱ በነበረው መሰባሰብ የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሕጻናትና ወላጆቻው በእንግድነት ተገኝተው የአዲስ ዓመትን ዋዜማ አክብረዋል።

ከሕጻናት እንግዶቹ መካከል አብዛኞቹ፣ በዊልቸር የሚጠቀሙ፣ ጥቂት የማይባሉትም በእናቶቻቸው ትከሻ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ራሳቸውን ችለው የሚጓዙትም ቢሆኑ ከወላጆቻቸው የተለየ ትኩረትና ክትትል የሚርቁ አይደሉም። በግቢው ማረፊያ የሚስተናገዱ የሩቅ እንግዳ ወላጆችም ጨቅላ ልጆቻቸውን እንዳቀፉ በዝግጅቱ ታድመዋል።

ዕለቱን በነበረው የአዲስ ዓመት አቀባበል በርካቶቹ ከከተማው ራቅ ካለ ስፍራ የተገኙ ናቸው። ሁሉም በሚባል ግምት ግን ገጽታቸው ላይ ደስታ ይነበባል። የልጆቻቸው እርስ በርስ መገናኘትና የወላጆች ስሜትን መጋራት የተለየ ስሜት አሳድሯል።

አብዛኞች የቅርብ ዘመድ ያህል ተቀራርበው እያወጉ ነው። የውስጣቸውን ቋጠሮ ፈተው፣ ይወያያሉ፣ ልብ ለልብ. መናበባቸው ደግሞ የጋራ ሕመማቸውን አስታግሷል። ተመሳሳይ ቁስላቸውን ፈውሷል። ዝም ያሉት ያዳምጣሉ፣ የሚናገሩት ደግሞ የሌሎችን ስሜት ይጋራሉ። የግቢው ድንኳን መልከ ብዙ ፊቶች ይታዩበታል። ፈገግታ፣ ዝምታና ብሩህ ተስፋ።

በመድረኩ ላይ የወጡት ሕጻናት በተኮላተፈ አንደበት ኅብረዜማ ማሰማት ይዘዋል። ትንንሾቹ በልካቸው በተዘጋጁ ወንበሮቻቸው ይንቀሳቀሳሉ። በእህት ወንድሞቻቸው፣ በእኩያ ባልንጀሮቻቸው ታጅበዋል። ወንዶቹ ‹‹ሆያሆዬ ›› እያሉ ነው። ሴቶቹ ደግሞ አበባዬ ሆሽን ያዜማሉ። ዝብርቅርቁ ድምጻቸው አይረብሽም። የእነሱ ደስታ እጥፍ ሆኖ ስሜቱ ወደሌሎችም መጋባት ጀምሯል።

እንደ አዲስ ዓመት ልማድ የወረቀት አበባ ስለው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ታዳሚውን ዘንድ የደረሱ ወንድ ሕጻናት ምርቃትና በረከትን አላጡም። ሁሉም ስለምኞታቸው የወጉን አድርሷቸዋል። የአዲሱ ዓመት ዋዜማ ንጹህ ልቦና ባለቸው ሕጻናት መልካም ምኞት መበሰሩን ቀጥሏል።

የጥያቄው መልስ …

ከዚህ ቆይታ በኋላ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ቤዛ በሻህ በድንገት አንድ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄው በዝግጅቱ ለታደሙት ወላጆች በሙሉ የደረሰ ነበር። እንዲህ ይላል።

‹‹እኛ ሁልግዜ የምንኖረው ለልጆቻችን ነው። ሀሳባችንም ለእነሱ ብቻ ያተኩራል። በእናንተ እሳቤ ግን ምርጥና ውጤታማ ወላጅ ማለት ምን ማለት ነው?

ይህ ጥያቄ በስፍራው ለታደሙት ወላጆች በሙሉ ከጥያቄ በላይ ነበር። ምክንያቱም በዚህ ሀሳብ ውስጥ ብዙ ታሪኮች አሉ። በርካታ አይገለፄ መከራዎች፣ ያልታበሱ ዕንባዎች በግልጽ ይታያሉ። በሁሉም ልቦና ውስጥ ለመመለስ፣ ለመናገር የሚከብዱ ውጣውረዶች ሊታወሱ ግድ ነው።

ለአፍታ ያህል ከበድ ያለ ዝምታ ሰፈነ። ዳሩ ብዙ አልቆየም። ተከታታይ እጆች መታየት ጀመሩ። ዕድሉ ውቢት ለተባለች እናት ተሰጠ። የመነጋገሪያውን ማይክ በእጇ እንደ ጨበጠች የውስጧን ሀሳብ ትዘረግፈው ያዘች።

‹‹ከእግዜር ስለተሰጠን ሁሉ ምላሻችን ምስጋና ነው››

‹‹ልጄ ሰባተኛ ዓመቱን ሊይዝ ነው። በተሰራለት ተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና ግራና ቀኝ ‹‹ሼንት›› የተባለ ማገዣ ገብቶለታል። ሰሞኑንም ተጨማሪ ቀዶ ሕክምና ላይ ተሰርቶለታል። ቀደም ሲል በእግሩ አይሄድም ነበር። አሁን ግን ሕክምናው ረድቶት መራመድ ጀምሮልኛል። እሱ ገና ትንሽ ልጅ ቢሆንም ሲከፋኝ፣ ሲጨንቀኝ ፊቴን አይቶ ውስጤን ይረዳል። ‹‹አይዞሽ እናቴ ለእኔ ነው ቁጭ ያልሽው፣ በእኔ ነው የከፋሽ›› ይለኛል። ይህኔ ላለቅስ የፈለኩትን ትቼ ፈገግታ አሳየዋለሁ። ደስ ይለዋል።

እኛ በውስጣችን የበዛ ሀዘንና ትካዜ ይዘናል። ሁሌም ግን ትዕግስት ሊኖረን ግድ ነው። በእኔ ዕምነት ይህ ችግር ለእኛ ለወላጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠን ነው። ይህን ደግሞ አምነን በምስጋና ልንቀበለው ያስፈልጋል።

እንዲህ ስንሆን መልካም ወላጆች እንሆናለን፣ በልጆቻችን ተስፋ እናያለን። ጥንካሬን እንወርሳለን አሁን ላይ በየሆስፒታሉ ችግሩ በጨቅላ ሕጻናት እንደ አዲስ ሲከሰት እያየን ነው። እሱ ከፈለገ ደግሞ በአንዴ ታሪክ ሊቀይር ይችላል። ››

ቀደም ሲል የተነሳው ሀሳብ ጥያቄው ተደገመ።

‹‹ምርጥና ውጤታማ ወላጅ ማለት ምን ማለት ነው ? አሁንም አንዲት እናት እጇን አወጣች ።

‹‹ልጄ ከእግዜር የተሰጠኝ ፀጋ ነው››

‹‹ልጄ አስራ ሶስት ዓመቱ ነው። ዛሬም ድረስ ያለ አባት አሳድገዋለሁ። ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም በእናትነቴ እጅግ እኮራበታለሁ። እሱ ማለት ከእግዚአብሔር የተሰጠኝ ጸጋ ነው። ለአንድም ቀን ፈጣሪን ‹‹እንዲህ አይነት ልጅ ለምን ሰጠኸኝ ስል አማርሬው አላውቅም። ሁሌም በምስጋና ስሙን እጠራዋለሁ። ልጄን ተሸክሜው እውላለሁ፣ ተሸክሜውም እሰራለሁ። በዚህ ደግሞ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ከግዜ በኋላ ትንሽ አፉን ይይዘው ጀምሯል። እንዲያም ሆኖ ‹‹አይዞሽ እናቴ›› ሲል ያበረታኛል። ይህን ስሰማ ፈጣሪ በሰጠኝ ጸጋ አመሰግነዋለሁ።

‹‹እናቴ ሆያ ሆዬ ብጨፍር ኖሮ ብሩ ይጠቅምሽ ነበር››

ማህሌት ሽቶ የሕጻን ያሬድ ብርሀኑ እናት ነች። እሷም ምርጥና ውጤታማ ወላጅ ማነው የሚለው ጥያቄ ይመለከታታልና የውስጧን ተንፍሳለች። ‹‹ልጄ ያሬድ የሀይድሮ ሴፋለስ ሕመም ተጠቂ ነው። ችግሩ የታወቀው ከተወለደ ከአንድ ዓመቱ በኋላ ነበር። መራመድ ሲያቅተው፣ ሲንቀጠቀጥ ሰዎች አግዘውኝ በሀኪሞች ችግሩ ተለየ።

አባቱ ትቶኝ የሄደው የስድስት ወር እርጉዝ እያለሁ ነው። የዛኔ ከጓደኞቼ ጋር በደባልነት ተከራይቼ እኖር ነበር። ልጄም የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ነው። ልጄን ለማሳደግ ብዙ ፈተናዎችን አልፌያለሁ። ለአስራ አንድ ግዚያት ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል።

ዘንድሮ እኩዮቹ ‹‹ሆያሆዬ›› ሲሉ አብሮ መጨፈር ፈልጎ ነበር። እኔ በየቀን ስራው ይዤው ስለምዞር የልቡ መሙላት አልቻለም። እሱ ግን ሀሳቡ ጨዋታ አልነበረም። ‹‹እማዬ እኔ ብጨፍር እኮ የማመጣው ብር አንድ ነገር ይገዛልሽ ነበር አለኝ።›› በጣም ተሰማኝ። ስለእኔ ብዙ የሚያስብ ልጄ ነው። ችግሬ ተዘርዝሮ አያልቅም። ልጄ መማር ይፈልጋል። ይህን ለማድረግ ብዙ ይጎድለኛል። እኔ በእግዚአብሔር ተስፋ አልቆርጥም ሁሌም በምስጋና አስበዋለሁ።

‹‹ፈጣሪን አላማርረውም››

ከማህሌት በኋላ የመናገር ዕድል ያገኘችው እናት ንግግሯን የጀመረችው ፈጣሪን በማመስገን ነበር። ‹‹ልጄ በጣም ደስተኛ ነች። እኔም ደግሞ ፈጣሪ ትችያለሽ ብሎ ስለሰጠኝ አላማርረውም። እሷ በተወለደች ግዜ እኔም ታምሜ ነበር። በግዜው የነበሩ ሀኪሞች ግን ከእኔ ልጅ የባሰ ችግር ያለባቸው ልጆች ስለመኖራቸውን አሳዩኝ። ፈጥኜ ተጽናናሁ። ለእኔ መልካም ወላጅነት ማለት እንዲህ ነው።

መልካም ወላጅ ሁሌም የተሰጠውን አምኖ ይቀበላል፤ በሆነበት ሁሉ ፈጣሪውን ያመሰግናል››። ልጄን ለማስተማር በሞከርኩ ግዜ እንዲህች አይነት ልጅ አንቀበልም ብለው ያባረሩኝ መምህራን ነበሩ። ‹‹ከፈለግሽ ቤትሽ አድርጊያት፣ ከፈለግሽ ደግሞ ጣያት ያሉኝም አልጠፉም። ያንን ሁሉ አልፌ ግን በትግሌ ማስተማር ችያለሁ። ስለሁሉም ነገር ምስጋና እንጂ እግዜርን አላማርርም። ››

የአዲስ ዓመት መግባትን ምክንያት በማድረግ በድርጅቱ አጸድ በነበረው ዝግጅት በርካታ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ታድመዋል። ሁሉም ሕይወታችው ብዙ የሚናገር ማንነታቸው አስደናቂ ታሪኮችን የሚመሰክር ነው። ያሉበትና ያለፉበት የሕይወት ጎዳና ብዙ አሳይቷቸዋል፣ .ፈትኗቸዋል።

እነዚህ ድንቅ ወላጆች አሁንም በምሬት አይራመዱም። እንደ ዓምና ካቻምናው ዛሬን ኖረው ነገን ተስፋ ያደርጋሉ። በሆነባቸው ሁሉ ከምስጋና ፊት ምሬትን አያስቀድሙም። ዘወትር ፈጣሪያቸወን እያሠቡ ‹‹ተመስገን›› ይሉታል። አዎ! ሁሌም ‹‹ተመስገን። ››

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You