ሽር ጉድ ከሚበዛባቸው የኢትዮጵያ ወራቶች አንዱ መስከረም ይመስለኛል። መስከረም የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ምድሪቱ ከቆላ እስከ ደጋ ልምላሜ የሚላበስበት ወቅት ነው። አንገቱን ደፍቶ የከረመ የቄጠማ ሣር የክረምቱን ማለፍ የሚያረጋግጠው መስከረም በምትለግሰው የማለዳ ጮራ ነው። ለወራት ከአጎነበሰበት ቀና ብሎ ‹ወፌ ቆመች› እንደሚል ህፃን ከአንገቱ ቀና ብሎ ለመቆም የሚውተረተረው በዚሁ ወቅት ነው።
የወፎች ህብረ ዝማሬ ደመቅ የሚልበት በመስከረም ነው። ሰፈራቸውን ትተው የተሰደዱ የአዕዋፋት ዝርያዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሥነምህዳሩን ውበት የሚያላብሱበት፣ በጫጫታቸው የተኛን የሚቀሰቅሱበት ወቅት ነው መስከረም። እንደ ዛሬው የእጅ ሰዓትም ሆነ ስልክ ከመኖሩ በፊት ወፎች የሰዓት ተናጋሪነት ሚና ነበራቸው። ‹‹ወፍ ሲንጫጫ›› የሚለው የአማርኛ ፈሊጣዊ ንግግርም የሚያመለክተው ንጋትን ነው።
ሲነጋ እንደማለት ነው። እነዚህ ወፎች ታዲያ ይህን ሚና የሚወጡት ከዚህ ከመስከረም ወር ጀምሮ ባለው የበጋ ወቅት ነው። ክረምት ላይ አይኖሩም። መስከረም የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የአዕዋፋትና እፅዋትም አዲስ ነገር ማስጀመሪያ ነው።
በእኔ አተያይ እንደ እንቁጣጣሽ የተጨበጨለት የተዘፈነለት እንደመስቀልም የተደመረለት በዓል አይገኝም። መስከረም ነገረ ብዙ፤ ሀሳበ ብዙ ነው። ከዚህም ባሻገር በዚህ ወር ያለፈውን ዓመት ረስቶ በአዲስ ተተክቶ ሌላ ሕይወት ለመጀመር ሰዎች ደፋ ቀና የሚሉበት ነው። በመስከረም መስኩ የለመለመ፣ ጭቃው የጠፈፈ ሁሉ ነገር ሸጋ ነው። በዚህ ወር ከሚከበሩ በዓላት ታዲያ ከእንቁጣጣሽ ተከትሎ የበርካቶች መድመቂያ በዓል መስቀል ነው።
እነሆ እኛም በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍሎች በደምቀት የሚከበረውን የመስቀል በዓልን አስመልክቶ አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት፣ ሄኖክ ስዩም (ከአገሬ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን)፣ አዲስ ዘመን እና አዲስ አድማስ ጋዜጣ ብሎም ከተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርሳናት ያገኘናቸውን መረጃዎችና ግላዊ ምልከታዎችን አሰናስለን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።
የታሪክና የሃይማኖት ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፤ የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327ዓ.ም) ጀምሮ ይከበራል። በዓሉ ሃይማኖታዊ ትውፊት የተላበሰ ሲሆን፤ በዘመኑ የነበረችው ንግሥት እሌኒ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሃይማኖታዊ ቅርስ ተላብሶ ይከበራል። ንግሥቲቱ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂራቆስ በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የክርስትና ሃይማኖት ድርሳናት ያስረዳሉ።
ንግሥት እሌኒ የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት ጠይቃ፤ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች። መስቀሉም ከወራት ቁፋሮ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ወጥቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መስከረም 16 ቀን ‹ደመራ› እና መስከረም 17 ቀን ‹የመስቀል በዓል› እየተባለ ይከበራል።
ከአራተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እንደሚከበር የሚነገርለት ይህ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት በኢትዮጵያ ስም እንዲመዘገብ ተደርጓል። የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንደጠበቀ ሆኖ በየአካባቢው እንደ ማህበረሰቡ ባህልና ወግም ይከበራል። በተለይም ደግሞ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተለየ ትርጉም ሰጥተው ያከብሩታል።
ለአብነት መስቀል ሲወሳ ጉራጌ፤ ጉራጌ ሲነሳ መስቀል የሚነጣጠሉ አይመስሉም። ጉራጌዎች የመስቀል በዓል ሌላው የባህል አምባሳደራቸው ነው። ከመስከረም 12 ቀን እስከ ጥቅምት 5 ቀን በተከታታይ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበረው የጉራጌዎች የመስቀል በዓል በዘመናት መካከል ነባር ትውፊቶቹን ጠብቆ የዘለቀ ደማቅ በዓል ነው። ከደመራና መስቀል ቀናት በፊትና በኋላ ባሉት ቀናት በተለያዩ ስነስርዓቶች የሚከበረው መስቀል፤ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች ወደ ትውልድ ቀያቸው በመሄድ በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአንድነት ያከብሩታል።
መስቀል በጉራጌ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ዝግጅቱም ያንኑ ያክል ሰፊ ነው። የመስቀል በዓል ከተከበረበት ዕለት ጀምሮ ለሚመጣው ዓመት የመስቀል በዓል ዝግጅት ይጀመራል። ጉራጌዎች ለመስቀል በዓል ዝግጅት ሲጀምሩ ስራ በእድሜና በጾታ ክፍፍል ይደረጋል። በዚህም መሰረት ልጆችና ወጣት ወንዶች ጫካ ወርደው እንጨት ፈልጠው ለደመራ ሲያደርቁ አባቶች የእርድ ከብቶችን ያደልባሉ ያዘጋጃሉ። እናቶች ለበዓሉ ቅቤ ሲንጡና እንሰት ሲፍቁ ልጃገረዶች ቤት ማዘጋጀትና ማስዋብ ድርሻቸው ይሆናል። ‹ሌማት ይወርድቦ ቀነ› በመባል በሚታወቀው መስከረም 12 ቀንም ግድግዳ ላይ የተሰቀሉ የምግብ እቃዎች ወርደው ይፀዳሉ።
የጉራጌ እናቶች የምግብ ሙያ ግሩም የሚባልለት ክትፎ መስከረም 16 ቀን በጣባ ይበላል። ከመስከረም 12 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ቀን ድረስ ጉራጌ በመስቀል ትደምቃለች። ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበረሰባዊ ወጎችና ልምዶች በየዕለቱ ይከወናሉ። መስቀል በጉራጌ ይደምቃል፤ ጉራጌም በመስቀል ሃሴትን ታደርጋለች። በመጨረሻም በመስቀል በዓል ማጠናቀቂያ ወቅት ስለግብርናና ንግድ አባቶች ይመክራሉ። ወጣቶችም ከእድሜ ባለፀጎች ኃላፊነት ተቀብለውና ተመራርቀው በዓሉ ያከትማል፤ ጉራጌዎችም ከርሞን ያልማሉ።
ሌላኛው በታላቅ ድምቀት መስቀልን የሚያከብረው የጎፋ ብሔረሰብ ነው። በዓሉ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ድሃውም ሆነ ሀብታሙ፤ ያለውም ሆነ የሌለው አንድ የሚሆንበት ነው። ለበዓሉ 15 ቀናት ሲቀረው እንኳን ሰው፣ የቤት እንስሳም እንዳይራብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት ይደረጋል። እያንዳንዱ አባወራ በቤቱ ለሳምንት የሚበቃ የእንስሳት መኖ እና ውሃ ያቀርባል።
አባ ወራው በመስቀል ሣምንት ከቤት ርቆ የትም ስለማይሄድ እቤት በዓሉ እስከሚያልፍ ድረስ በበቂ ሁኔታ የሚመገቡበትን በየድርሻቸው ያዘጋጃሉ። በተለይም ሴቶች ጤፍ፣ በቆሎ እና ሌሎች ለበዓሉ የሚሆኑ እህሎችን በመፍጨት ቦርዴ ጌሾና ጠላ በመጥመቅ እንዲሁም ወንዶቹ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጠው በማቅረብና ለደመራ ችቦ የሚሆኑ ‹‹ግንግና›› የተባለውን ጭራሮ በመልቀም፣ የእርድ ቢላዋና እርዱ የሚፈጸምበትን ቦታ በመወሰን የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በአጓጊ ሁኔታ ያጠናቅቃሉ።
አካባቢው በአደይ አበባ ሲያሸበርቅ በብሔረሰቡ አጠራር ‹‹ቤላ ጭሻ›› ጋራው ሸንተረሩ ሲያሸበርቅ አርሶአደሩ በብሔረሰቡ ዘንድ በስፋት ከሚታወቀው ምርት በዋናነት ጤፍን በጊዜው ከአረም ነፃ የሚያደርጉበት፣ ሰብሉም አብቦ የሚደምቅበት ነው። ወርሐ መስከረም ሲገባ መስቀል በዓል ሲቃረብ፣ ልጆች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ላይ ሆነው ከብት የሚጠብቀውም፣ እንጨት የሚለቅመውም፣ ውሃ የሚቀዳውም ሆነ ሣር ለማጨድ ከአንድ በላይ ሆነው በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ያለማንም ቅስቀሳ ሲያዜሙ ይደመጣሉ።
«ሎያ ባይ ሎያ ባይ ሎያ
ማስቀላ ባይ ማስቃል
ኡፋይስ ባይ ሙሰ ሀሹ ባይ»
ሲሉ ይደመጣሉ። መስቀል እንኳን መጣህልን! የእኛ ደስታ! የእኛ መዝናኛ መስቀል እንኳን መጣህልን! በማለት ያዜማሉ። በጎፋ ብሔረሰብ በተለየ ሁኔታ ለመስቀል በዓል የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች የሚዘጋጁ ሲሆን፤ በዋናነት በደመራው ዕለት የሚበላው ከበቆሎ የሚዘጋጅ ገንፎ ነው። ስያሜውም‹‹ ማስቃላ ሆቴ›› ይባላል። አዘገጃጀቱም ከሳምንት በፊት ወተት በማጠራቀም ምንም ውሃ ሳይታከልበት ከበቆሎ ዱቄት የተዘጋጀ በተነጠረ ቅቤ፣ በአይብና በቅመማ ቅመም የሚዘጋጅ ገንፎ ማለት ነው።
ይህ ገንፎ ከተዘጋጀ በኋላ ቤተሰቡ ሁሉ በአንድነት በመሰባሰብ እጃቸውን ወደ መሶቡ የሚሰዱበት ሥርዓት ከምንም በላይ ፈጣሪያቸውን የሚያስቡበትና የሚማፀኑበት ስለሆነ «ማስቃላ ዮ! ዮ!» እያሉ በጋራ የሚቀምሱበት፣ በፍቅርና በአንድነት የሚበሉበት ሲሆን፤ ከእንሰት ምርት የሚዘጋጀውን ቡላ፣ በአይብ፣ የሐረግ ቦዬ በአዋዜም በዋናነት በመስቀል በዓል ዕለት የሚመገቡ የምግብ ዓይነቶች ናቸው።
ጎፋዎች በዓመት አንዴ ለሚያከብሩት መስቀል አይሰስቱም። «ማስቃላ ዮ! ዮ!» የበረከት ቃል ነው። ጎፋዎች ደስታን የሚያበስሩበት፤ መስቀል እንኳን ደህና መጣህልን እንደማለት ነው። እሰይ ማለት የፈለገ እየደጋገመ «ዮ! ዮ! ዮ!» ይላል። የጎፋዎች የመስቀል ፍቅር ጥግ ከተፈጥሮ የተዛመደ ነው። «ዳናው ዳና አልባ ዙማዳን ዳና» ይላሉ። አልባ ዙማ በአካባቢው የሚገኝ ትልቅ ተራራ ነው። ተራራው ብዙ ዘመን መስቀልን እያየ የኖረ ነው። እናም ገና እንደእርሱ እንኖራለን ብዙ መስቀል እናያለን ይላሉ።
እንዲህ አይነት በዓላትን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘታቸው ሳይበረዝ እንዲቆዩ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። ይህ በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሆኗል። ዓለም አቀፍ ቅርሶችን መዝጋቢው ‹‹ዩኔስኮ›› ይገባዋል ብሎ መዝግቦልናል፤ እኛ ደግሞ እንዲህ አይነት ቅርሶቻችንን መጠበቅ አለብን። በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሰነዘረው ተደጋጋሚ ወቀሳ የአገር ባህልና ወግን ከማስጠበቅና ከማስተዋወቅ ይልቅ ለውጭ ባህል ወጣቱን ያጋልጣሉ የሚል ነውና ከመገናኛ ብዙኃንም ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቃል።
መልካም የመስቀል በዓል!
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር