አዲስ አበባ ፦ የማህበረሰቡን ባህል፣ ሃይማኖትና ፍላጎት ያላማከሉ ኢንቨስትመንቶች ቀጣይነታቸው አስተማማኝ አለመሆኑ በተግባር በመታየቱ መንግሥት በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ሲሰጥ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ገለጹ።
የዶንኪ ሳንክቹዋሪ የኢትዮጵያ ካንትሪ ተወካይ ዶክተር ቦጃ ወንድሙ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በቢሾፍቱ እና አሰላ ከተሞች በቻይናውያን ባለሀብቶች ተከፍተው የነበሩ የአህያ ቄራዎች በህብረተሰቡ ባህልና ሃይማኖት ጋር ተቃርኖ ስላላቸው እንዲዘጉ ተደርጓል። አሁንም ቻይናውያኑ ቄራዎቹን ዳግም ለመክፈት ፍላጎት ስላላቸው በአገኙት አጋጣሚ ግፊት እያደረጉ ነው። በመሆኑም መንግሥት የማህበረሰቡን ፍላጎት የማይወክሉ ኢንቨስትመንቶችን ፈቃድ ሲሰጥ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል።
እንደ ዶክተር ቦጃ ገለጻ፤ ሰሞኑን በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት በተደረገበት ወቅት ቻይናውያኑ ፈቃድ ቢሰጣቸው በአንድ ቀን ውስጥ ሥራውን ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ታይቷል። በቻይናውያን ተፈላጊ የሆነውን የአህዮች ቆዳ ለገበያ በማቅረብ ቄራውን ሲከፍቱ በመጀመሪያ የማህበረሰቡ ቅቡልነት መጠናት ነበረበት። አሁንም ዳግም የህብረተሰቡን ተቀባይነት ያላገኙ ፋብሪካዎች እንዳይከፈቱ መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአህያ ቄራዎች እና የማህበረሰቡ ተቀባይነት ላይ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ፍጹም ዓለምአየሁ በበኩላቸው፤ የቻይናውያን የአህያ ቄራ ሲከፍቱ ማህበረሰቡ በቂ ውይይት አለማድረጉ ቅሬታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ ነበር። በመሆኑም ቀጣይነት ላለው የኢንቨስትመንት ሥራ የህብረተሰቡን ፍላጎት ያማከሉ ፋብሪካዎችን መክፈት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
በቅርብ ጊዜ ውስጥ በተሰራ ጥናት በኬንያ ሦስት የአህያ ቄራዎች በመከፈታቸው በሞያሌ አካባቢ በአንድ ገበያ ብቻ በሳምንት እስከ ስድስት ሺ አህዮች ወደ ኬንያ እንደሚጓጓዙ ለማወቅ ተችሏል። በመሆኑም መንግሥት አገር ውስጥ ያሉትን ፋብሪካዎች ቢዘጋም በተዘዋዋሪ መንገድ ከሀገር እየወጡ ያሉትን አህዮች ጉዳይ መፍትሄ ሊያበጅለት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በቢሾፍቱ እና አሰላ ከተሞች ተከፍተው የነበሩት የአህያ ቄራዎች እያንዳንዳቸው በቀን እስከ ሦስት መቶ አህዮች እያረዱ ቆዳቸውን ለቻይና ገበያ ያቀርቡ ነበር። ከህብረተሰቡ በተነሳ ቅሬታ መሰረት ከሁለት ዓመታት በፊት መዘጋታቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
ጌትነት ተስፋማርያም