አዲስ አበባ፡- በአፋን ኦሮሞ የተሠሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችንና ባለሙያዎችን የሚያበረታታ ኦዳ የኪነ ጥበብ ሽልማት ለሦስተኛ ጊዜ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
የበሻቱ ቶለማርያም መልቲ ሚዲያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ በሻቱ ቶለማርያም የመርሀ ግብሩን አዘገጃጀት አስመልክተው ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ የበሻቱ ቶለማርያም መልቲ ሚዲያ ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ኦዳ የኪነ ጥበብ ሽልማት፤ በአፋን ኦሮሞ የሚሰሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በማበረታታት ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዕድገት ቋንቋውና ማህበረሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ መርሀ ግብሩ ለሦስተኛ ጊዜ በ18 ዘርፎች ሽልማት በመስጠት ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጇ ማብራሪያ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱት አንደኛውና ሁለተኛው የኦዳ ሽልማት ዝግጅቶች በ17 ዘርፎች ከ120 በላይ ለሆኑ ባለሙያዎች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም ለበርካቶች መነቃቃትን በመፍጠር በቋንቋው በርካታ ሥራዎች በጥራት እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡የዘንድሮው ሽልማትና እውቅና ከባለፉት ሁለት ዓመታት በተለየ ሴቶችንና የቡድን ሥራን ለማበረታታት «የዓመቱ ምርጥ ሴት ድምጻዊት» እና «የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ጥምረት» የሚሉ ዘርፎች ተጨምረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአፋን ኦሮሞ ለተሰሩ ቴአትሮችና ለ«ቢፍቱ ባንድ» እውቅና ይሰጣል፡፡ እንዲሁም፤ ለአንድ ሙያተኛ የሕይወት ዘመን ሽልማት ይሰጣል:: ለሽልማት የሚበቁ ዕጩ ሥራዎች በአጠቃላይ በ2011 ዓ.ም የተሰሩት ብቻ ይሆናሉ፡፡
ሥራ አስኪያጇ፤ በሦስተኛው የኦዳ ሽልማት ከ12 በላይ ፊልሞች በአፋን ኦሮሞ ተሠርተው መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ዕድገት ውስጥ ኦዳ ሽልማት የራሱን በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ውድድሩ ደረጃውን የጠበቀ፤ አሳታፊ፤ እንዲሁም ፍትሐዊ እንዲሆን ትኩረት መደረጉን፤ የውድድሩ ዳኞችም በኪነ ጥበብ ሥራ ውስጥ የታወቁ፤ ጥናቶችን ያደረጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በውድድሩ ከዳኞች የሚሰበሰበው ውጤት 70 በመቶውን ሲሸፍን፤ 30 በመቶው ድምጽ ደግሞ በጽሑፍ መልዕክት ከሕዝብ እንደሚሰበሰብ ገልጸዋል፡፡
ሽልማቱ የኢትዮጵያን ኪነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪ በማድረግ የአገሪቷን ባህል፣ ወግና ማህበራዊ ሥሪት እንደሚያስተዋውቅ የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ፤ ከኢንዱስትሪው ኢትዮጵያ የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ ያስችላታል ብለዋል፡፡
ከአዘጋጁ አካል የተገኘው መረጃ እንደ ሚያሳየው፤ በሦስተኛው የኦዳ ሽልማት በሙዚቃ ዘርፍ፤ የዓመቱ ምርጥ አልበም፣ ነጠላ ዜማ፣ ቪዲዮ ክሊፕ፣ ሙዚቃ አቀናባሪ፣ አዲስ ድምጻዊ፣ ሴት ድምጻዊት፣ የሙዚቃ ጥምረትና ተጽእኖ ፈጣሪ ባለሙያዎች ተመርጠው ይሸለማሉ:: የዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ ወንድ ተዋናይ፣ ሴት ተዋናይት፣ ዳይሬክተር፣ ደራሲ፣ ሲኒማቶግራርና ኤዲተር በፊልም ዘርፍ የሚመረጡ ሲሆን፤ የዓመቱ ምርጥ ልብ ወለድና የግጥም መጽሐፍም የውድድሩ ዘርፍ አካል ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው