ከአንድ አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎችን በአንድ «ዶርም» አይመድብም
የተማሪ ማደሪያ ሕንፃዎችን የትምህርት ክፍሎች እንዲቆጣጠሩ ያደርጋል
አዲስ አበባ፡- የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች ቅበላ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ:: በተቋሙ ከአንድ አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች በአንድ ዶርም እንደማይመደቡ ተጠቁሟል፡፡ የተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃም ቁጥጥር የሚደረገው በትምህርት ክፍሎች አማካኝነት መሆኑ ታውቋል፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ አንዳርጌ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ለ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የማደሪያ ሕንፃዎችን ለአገልግሎት ዝግጁ የሚሆኑበት ደረጃ ላይ የማድረስ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፤ በዚህም ባለፈው ዓመት ከነበረው ችግር የተነሳ የተጎዱ ማደሪያ ክፍሎችን የመጠገን ሥራው በመጠናቅ ላይ ይገኛል:: ከዚህም ባለፈ ምድረ ግቢውን ጽዱ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ጤፍና አትክልትን ጨምሮ ለተማሪዎች የምግብ ፍጆታ የሚውሉ ግብዓቶችን በማሟላት ላይም ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲው መሠረታዊ ችግር ሊሆን የሚችለው የውሃ አቅርቦት መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የውሃ እጥረትን ሊፈታ በሚችል መልኩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን፤ መምህራንን ከማሟላት አኳያም ቅጥር እየተካሄደ መሆኑንና በሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች ድልድል እየተካሄደ መሆኑን፤ የማስተማሪያ ግብዓቶችም በመሟላት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
እንደምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይስተጓጎልና ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ ከተቋሙ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋራ በቀጣይ መሰራት ያለባቸውን ጉዳዮች ያካተተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም ተካሂዷል፡፡ በውይይቱም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከዞኑ አመራሮች ጋር የሚካሄደው መሰል የውይይት መድረክ ነባርና አዳዲስ ተማሪዎች ሲገቡም የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ባለፈው ዓመት በተማሪ ዎች የማደሪያ ክፍል “የዶርም” ምደባ አሰራር ላይ ችግሮች እንደነበሩና ይህም ተማሪዎች እርስ በእርስ ተደራጅተው መጥፎ ተግባራትን መፈጸም እንዳስቻላቸው ጠቁመው፤ በዘንድሮ ዓመት ግን ለየት ባለ መልኩ ከአንድ አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች በአንድ ዶርም ውስጥ እንደማይመደቡ ጠቅሰዋል:: ይህም በቡድን ግጭት ለመፍጠር የሚነሳሱ ተማሪዎች እንዳይኖሩ ከማድረግ ባሻገር፤ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂዱቱን ምቹ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የምደባው ስብጥር በትምህርት ክፍል የሚሆን ሲሆን፤ በዋናነትም የተማሪ ማደሪያ ሕንፃዎችን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኙ ኮሌጆች የሚቆጣጠሩ ይሆናል፡፡ በአንድ ኮሌጅ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችም በማደሪያ ሕንፃም አንድ ላይ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ኮሌጆቹም ተማሪዎቹን በቅርበት በመከታተል የሚያስፈልገውን ድጋፍ በመስጠት የዩኒቨርሲቲው ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ በአሠራሩ ኮሌጆች ኃላፊነት ወስደው ችግሮች ሲከሰቱ አፋጣኝ መልስ ለመስጠት አመቺ ይሆናል፡፡ ውስጣዊ ችግሮችንም በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች መካከል የሚፈጠር ግጭት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው ገልጸው፤ ድርጊቱ አገርን ለሌላ ቀውስ ስለሚዳርግ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ አመራሮችና የተቋሙ ማህበረሰብ በሙሉ እኩይ ተግባራት እንዳይፈጸሙ መከላከል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው