አዲስ አበባ፡- የቱለማ
አባገዳና የገዳ ኦሮሞ ህብረት አባ ገዳዎች ትናንት በኦሮሞ ባህል ማዕከል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ
ኅብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የህብረቱ ዋና ጸሐፊ አባ ገዳ ጎበና ኦላ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ መላው የከተማዋና አካባቢው ነዋሪዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል።
በአምስቱም የአዲስ አበባ መግቢያ በሮች የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተማ ነዋሪዎችም በተለመደው የኦሮሞ ባህል መሠረት እንግዶችን በመቀበል እንዲያስተናግዱ ያሳሰቡት አባገዳ ጎበና ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት አንዱ እንጂ ከፖለቲካ ጋር የሚገናኝ በዓል አይደለም ብለዋል። በዓሉም የኦሮሞ ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት በመሆኑ ሁሉም በጋራ ሊያከብሩት ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ከሀገር ውጪ የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎችም የሚሳተፉበት በመሆኑ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ጠቀሜታ በማሰብ ከአለባበስ ጀምሮ በዓሉን በማስተዋወቅና ሰላምን በመስበክ ማክበር እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
የአፋን ቀሎ አባ ገዳ አቶ አብዱረዛቅ አህመድ በበኩላቸው እንደገለፁት፣ ኢሬቻ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት በዓል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ሆኖ ሊያከብረው ይገባል።
ኢሬቻ በዘርና በሃይማኖት ልዩነትና መከፋፈል የማይደረግበት በመሆኑና አባ ገዳዎችም በሰላም እንዲከበር ጥሪ በማድረጋቸው የሚፈጠር ችግር አይኖርም ያሉት አቶ አብዱረዛቅ በአሁኑ ወቅትም ሃያ ሺ የሚደርሱ ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሰላም ለማስከበርና ኅብተሰቡን ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በዓሉን ለማክበር የሚሳተፉ ሁሉ የጸጥታ ችግር እንደማይኖር ተገንዝበው ያለ ስጋት እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ መስከረም 24 ቀን በአዲስ አበባ እንዲሁም መስከረም 25 ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ እንደሚከበር የተገለጸ ሲሆን ከአምስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ ይታደማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም
ራስወርቅ ሙሉጌታ