አባት ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ውስጣቸው ያለውን የቀለም ጥማት ለማርካት የሕይወት ሩጫ
ሳይፈቅድላቸው ትዳር መስረተው ልጆች ደጋግመው ወልደው ይስማሉ፡፡ እርሳቸው ያጡትን የቀለም ትምህርት ጥማት በልጃቸው ለማርካት በፅኑ
ተመኙ:: ቤታቸውን ለማስተዳደር ከሚታትሩበት ሥራቸው፤ ሕይወት ለመምራት ከሚባዝኑበት ሩጫቸው ቆም ብለው ዕድሜው ለትምህርት የደረሰውን
ልጃቸውን ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ ያስባሉ፡፡
የአብራካቸው ክፋይ የቀለም ቀንድ ይሆን ዘንድ ተመኝተው፤ ለልጃቸው ቦርሳ ገዝተው፣ ለትምህርት የሚሆን ቁሳቁስ አሟልተው፣ ወደ ትምህርት ቤት እጁን ይዘው ለማስመዝገብ ይወስዱታል፡፡ ሁሌም የትምህርት ፍቅር በውስጣቸው የነበረው አባት ልጃቸውን ሲያስመዘግቡ «ለምን እኔም ከልጄ ጋር አልማርም» የሚል ሀሳብ በውስጣቸው ይጫራል፡፡
ወዲያው ይወስኑና ከልጃቸው ጋር በትምህርት ገበታ ላይ አብረው ቁጭ ብለው ፊደል መቁጠር ቁጥሮችን ማስላት ይጀምራሉ፡፡ በመጀመሪያ ክፍል ሲገቡ ተማሪዎች መምህራቸው መስለዋቸው «እንዴት አደሩ መምህር?» በማለት ተነስተው እንደተቀበሏቸው ትምህርት በጀመሩበት ሰሞን የገጠማቸውን ትውስታ የሚናገሩት ሼህ ካሚል አልዬ በውስጣቸው የነበረውን የትምህርት ፍላጎት ከልጆቻቸው ጋር ጓደኛ ሆነው ለመማር ብርታት እንደሆናቸው ይገልፃሉ፡፡
በልጅና በአባት መካከል ብርቱ የሆነ ቤተሰባዊ ፍቅርና የትምህርት ፍላጎት ነበረና ከሚማሩበት ክፍል ተራ በተራ እየተቀያየሩ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ፤ ደግሞ በሚቀጥለው አንዱ አንደኛውን ጠንክሮ በመብለጥ አስገራሚ ውጤት ማስመዝገብ ይያያዙታል፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቅቀው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ከዚያም የመሰናዶ ትምህርታቸውን በሰላማዊ የቀለም ፍልሚያ በጥሩ ውጤት አጠናቅቀው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እስኪገቡ ድረስ በአባትና በልጅ መካከል በፍቅር የታጀበው ፉክክር ለትምህርት ውጤታቸው ማማር ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
የሼህ ካሚል አልዬ የመጀመሪያ ልጅና በትምህርት ዓለም የሚፎካከራቸው ልጃቸው ረመዳን ካሚል በአሁኑ ሰዓት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪውን በማጥናት ላይ ይገኛል፡፡ «ከአባቴ ጋር የምናደርገው ሰላማዊ ፉክክር በትምህርት ውጤታችን የተሻልን እንድንሆን ረድቶናል» በማለት ካባቱ ጋር የሚያደርገው ፉክክር የስኬቱ ምንጭ መሆኑን ይገልፃል፡ ፡ «በአባቴና በእኔ መካከል የጓደኝነት ስሜት መፈጠሩና በቤት ውስጥ ያለን የእርስ በእርስ ፍቅርና መረዳዳት ለመልካም ግንኙነት መሠረት ነው» ሲልም ያስረዳል፡፡
ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ፉክክሩን አጠናክረው ቀጥለው አባት አንደኛ ሲወጡ ልጅ ሁለተኛ፤ ልጅ አንደኛ ሲወጣ አባት ሁለተኛ ሆነው በስኬት ጉዞ ወደፊት ማለት ይያያዙታል፡፡የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና በጋራ ወስደው አባት 3.6 ሲያመጡ ልጅ 3.8 በማምጣት ፉክክሩ ቀጠለ፡፡ በመሰናዶ ቆይታቸው አንዱ ሌላኛውን በበጎ መልኩ ለመብለጥ ሲጥር ቆይቶ በ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ልጅ 500 አባት 490 ውጤት በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ፡፡
አባት ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት በአመርቂ ውጤት ሲመረቁ ልጅም በበኩሉ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀይድሮሊክ ኢንጅነሪንግ በከፍተኛ ውጤት ተመረቀ፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የልጃቸው ጥሩ ውጤት አምጥቶ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መቅረቱን የሰሙት አባት በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲይዙ ልጅም ሁለተኛ ዲግሪውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ አባት በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በመምርነት በማገልገል ላይ ሲሆኑ ልጅም የጀመረውን ትምህርት ለማጠናቀቅ ጠንክሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ከልጄ ጋር የምናደርገውን ሰላማዊ ፉክክር ወደፊትም በበጎ ነገሮች እንቀጥልበታለን የሚሉት ሼህ ከማል አልዬ ወላጆች ልጆቻቸውን በመልካም ጓደኝነት በመቅረብ ሊያንፁና ለስኬት ሊያበቁ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ ጤናማ የሆነው የእርስ በእርሱ ፉክክር ጠንክረው እንዲሰሩ፤ በጥረታቸውም ፍሬያማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋልና ዛሬም የእርስ በርሱን ፉክክር ቀጥለውበታል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም
ተገኝ ብሩ