በወጣትነቱ ራሱን መቆጣጠር የሚችል፣ ማህበረሰባዊ የሞራል ግዴታዎችን የሚያከብርና የሚወጣ፣ በአስቸጋሪና በከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ የብርሃን ጭላንጭል የሚታየውና የመፍትሄ አካል ለመሆን የሚጥር ትውልድ ራሱንና አገርን የማሻገር አቅም ባለቤት እንደሆነ ይነገራል።
የዚህ አይነት ሥነምግባርን የተላበሰ ወጣት በኢትዮጵያ ከመንግስትም ባለፈ በየትኛውም የእምነት አስተምህሮት የሚፈለግና የተወደደ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ከስሜታዊነት በመውጣት አገራዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ምን ይጠበቅባቸዋል? ስንል የተለያዩ ክልሎች ወጣት ማህበራት አመራሮችና አባላትን አነጋግረናል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት ተክሌ ቱኬ እንደሚለው፤ በኢትዮጵያ ያልተለመዱና አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች እየተስተናገዱ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ሁለንተናዊ፣ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ጥቅማቸውን ማስከበር እንዲችሉ፣ አገራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር አልመው መስራት አለባቸው ይላል። የሚያነሷቸው ሃሳቦችና ተግባሮቻቸው በሰከነ አዕምሮ የተመረመሩና ምክንያታዊ መሆን ይኖርባቸዋልም ብሏል።
ወጣቱ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው ምህዳሮች ሰፊ ናቸው። ስለዚህ መብቱን ብቻ የሚጠብቅ ሳይሆን ግዴታውንም እየተወጣ ሁለንተናው ለውጥ መፍጠር የሚችል፤ ስሜቱን ተቆጣጥሮ ቆም ብሎ ማሰብ የሚችል እና ከራሱ፣ከወገኑና ከአገሩ ዘላቂ ጥቅም አንጻር ሰጥቶ በመቀበል አስተሳሰብ የሚመራ በሳል ሊሆን ይገባል ሲል ወጣት ተክሌ ይናገራል።
ወጣቱ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ተላብሶ በመወያየትና በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም የሚል እምነት ያለው መሆን አለበት። በአመክንዮ ላይ መሰረት ያደረጉ ሃሳቦችን በማመንጨት እና በማንሳት መፍትሄ ማግኘት ይቻላል። በተለያየ መንገድ የሚፈጠሩ የልዩነቶች አስተሳሰብና ድርጊቶችን መፍትሄ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች እርምጃዎችን ለመውሰድ፣ መፍትሄዎች ለማስቀመጥ፣ ‹‹አንተ አጥፍተሃልና ታረም›› ለማለት በተጨባጭ መረጃዎች ላይ መመስረት አስፈላጊ ነው። እውነታው ላይ መሰረቱን ያላስቀመጠ መፍትሄ ዘላቂ አይሆንም። ተዓማኒነትም አይኖረውም ይላል። ሰላም ማስፈን ይሳነዋል። ስለዚህ ወጣቶች ስሜታዊነትና ያልተጨበጠ ወሬ የሚመራቸው በፍጹም መሆን የለባቸውም።ያገኙትን መቀበል ተገቢ አይሆንም።
ወጣቱ የሚፈልገውና የጠይቀው ነገር ምላሽ ላያገኝ ይችላል።ያገኘው ምላሽ አጥጋቢ ላይሆንም ይችላል። በሂደት ምላሾች የሚገኙ እንደሆኑና ነገሮች እንደሚለወጡ ምክንያታዊ ሆኖ ማሰብ አለበት፤ መሞገት ይኖርበታል። ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ የወጣቱን ሃሳብ የሚደግፉ በመምሰል የራሳቸውን ሥውር አጀንዳ አስታጥቀውና ጭነው የወጣቱን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት አይጠፉም። ስለዚህ ወጣቱ ሰከን ብሎ ማሰብ፣ቁጭ ብሎ መመርመር ይኖርበታል።ሰላም ሲኖር ሁሉም ነገር ሊኖር እንደሚችል መረዳት አስፈላጊ ነው።
ወጣቱ አገሩ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገወዲያም የሱ ናት። በአገሩ ላይ የሚያመጣው ለውጥም ሆነ ጥፋት የሚጠቅመውም ሆነ የሚለበልበው ከማንም በፊት እሱን ነው። ስለዚህ ሰላምን የአይን ብሌኑ አድርጎ መንቀሳቀስና መስራት አለበት።
በአገሪቱ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ለውጦች እየመጡ ነው የሚለው ወጣት ተክሌ ፤ እነዚህ ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉትና ፍሬ ሊያስገኙ የሚችሉት ሰላም ሲኖርና አገር ሰላም ስትሆን ብቻ ነው። ወጣቱም ጤናማ አስተሳሰብ ሊኖረው ያስፈልጋል። የአስተሳሰብ ጤንነት ሲባል ያልተገቡ አድሎዎች፣ ያልተገቡ ጥቅሞች፣ያልተገቡ ውዴታዎችና ጥላቻዎች፣ያልተገቡ ማግለልና መነጠሎች፣ያልተገቡ አካታች ያልሆኑ እይታዎች እና ሌሎችንም ለአንድ አገር በጋራ ማሰብና በጋራ ክንድ ለመስራት እንቅፋትና መሰናክል የሚፈጥሩና የሚሆኑ የአስተሳሰብ ዝንፈቶች ለማለት ነው። የዚህ አይነት እሳቤዎች ወጣቱን አያሳድጉም፤ አይለውጡም።
አለም የደረሰበትን የሥልጣኔ እና የለውጥ ደረጃ አሻግሮ ማንበብ፣መረዳት፣መገንዘብ እና ወደዚያ በሚደረገው ጉዞም የወጣትነት ሚናውን ተንትኖ ተረድቶ መወጣት አለበት። አሁን በአገሪቱ የሚስተዋሉት አብዛኞቹ ፓርቲዎች ብሔርን መሰረት አድርገው የሚያቀነቅኑ በመሆናቸው ምክንያታዊ የሆነ እና ሚዛናዊነት ያለው አስተሳሰብ ለማራመድ ሲቸገሩ ይስተዋላል።
ስለዚህ በተለይ ወጣቶች በፖለቲካ ሂደቶች ውስጥ በሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ አገርንና ሕዝብን በሚለውጥና በሚጠቅም ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ቅኝት መሆን አለበት። ይች አገር የሁላችንም ናት። ስለዚህ ወጣቱ በቅድሚያ ከራሱ ጋር መስማማት አለበት፤ከዚያም ከማህበረሰቡ ጋር ይስማማል ብሎም አገርን ያስማማል፤ አንድ ያደርጋል። ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ያመጣል የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል።
የበታችነትም ሆነ የበላይነት አስተሳሰብን ተጭኖ የተለቀቀ ወጣት የሀገር ሸክም ነው። አልፎ አልፎ የዚህ አይነት ጭነት ተሸክመው በዚህ ሥልጡን ዘመን የሚወላገዱ እና የረከሰ አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ ጥቂት ወጣቶች የአገርን ሀብት፣ የራሳቸውን ሀብት፣ የወገኖቻቸውን ሕይወት ሲያጠፉና ሲያበላሹ ታዝበናል። በእርግጥ የዚህ አይነት በምክንያት የማያምንና በደመነፍስ የሚመራ አስተሳሰብ ሰለባ የሆነን አካል የአገሪቱ ወጣት ከሚመለከተው የጸጥታ አካል ጋር በቅንጅት መክቶ መስመር እንዲይዝ ሕግና ሥርዓት እንዲይዝ በሚያደርገው ትንቅንቅ እስከ ሕይወቱ ድረስ መስዋዕት እየከፈለ ይገኛል።
በዚህ በኩል መመስገን የሚገባቸው በርካታ ወጣቶች አሉ። ‹‹የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው እንደሚባለው ሁሉ የአገርም ሆድ እንደዚያው ነው›› በመሆኑም የአገር መከታ የሆኑ ወጣቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ማሳሰብ እወዳለሁ ሲል ወጣት ተክሌ ገልጿል።
በሀገር ደረጃ ሲካሄዱ በነበሩ የወጣት ለወጣት ግንኙነቶች የልምድ ለውውጥ ፕሮግራሞች አስተባባሪ እና የአማራ ወጣቶች ማህበር አባል የሆነው ወጣት ቴዎድሮስ ወርቁ እንደገለጸው፤ ወጣቶች አሁን ላይ መስራት ያለባቸው ጊዜያዊ ከሆኑ ስሜቶች ጸድተውና እርቀው ዘላቂ በሆነ መንገድ አገርን ማየትና መታደግ የሚችል ተግበር መስራት አለባቸው።
የሚስተዋሉ የተለያዩ የአሰራር ግድፈቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመታገል ያለመሰልቸት ራሳቸውን ማዘጋጀትና መፈጸም ይኖርባቸዋል። በዚህች አገር በሚከሰቱ የሰላም ችግሮች ዋና ተጎጂው ይሄ ኑሮውን ለማሸነፍና ተስፋውን ለመጨበጥ ደፋ ቀና የሚለው ወጣት ነው። የአማራ ወጣቶች በሥራ እድል ፈጠራ እምብዛም ተጠቃሚ ሆነዋል ማለት አይቻልም ብሏል። የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል ማለትም አይደለም።
ወጣቱ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረቡ ይቀጥላል። በተረጋጋና በሰከነ መንገድ ሊከራከርና ሊጠይቅ እንዲሁም ግዴታውን ሊወጣ ይገባል። ወጣቶች በዋናነት አስተዋይ መሆን እንዲችሉ ከማህበራዊ ሚዲያ ውዥንብሮች ራሳቸውን መገደብና መቆጠብ አለባቸው ሲል መክሯል።
በወጣቶች ፣በመንግስት በኩል እና አልፎ አልፎ በሕዝብም በአዎንታና በአሉታ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተገቢው ቁጭ ብሎ በመመርመር እንዲታረሙና አገርን ከሚያፈርስ አስተሳሰብና ድርጊት እንዲቆጠቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይሄን ለማድረግ ሚዛናዊ መሆን ፣በምክንያት የሚያምን፣በደመነፍስ የማይመራ፣አገርንና ወገንን ከራሱ ጥቅም ማስቀደም የሚችል እና ጠንካራ ሥነልቦና ያለው ወጣት በተግባር ሆኖ መገኘት ወይም መፍጠር አስፈላጊ ነው። ወጣቱ ይህን በማድረግ ራሱንና አገሩን ለመለወጥ መጣር አለበት።
የአገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ብሔር ተኮር የሚመስል መልክ ቢኖረውም ወጣቱ በዚች አገር ሰፊ ባለድርሻና ባለቤት እንደመሆኑ ቀድሞ ተጠቃሚም ቀድሞ ተጎጂም እሱ ነው። ስለዚህ ይሄን ተረድቶ የአገሩን ሰላም በማስጠበቅ አንድነትን ማጠናከር የሚችሉ፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮችን በፍትሃዊ እይታ፣በቀና አስተሳሰብ እየመዘኑ መከተል ቀዳሚ ምርጫው ሊሆኑ ይገባል ሲል መክሯል።
ለነገሮች ችኩል ሆኖ አገር ማሳደግም ማዳንም አይቻልም። በተጨማሪም የአገሪቱ ሀብት ከራሷ ዜጎችም አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ነው የሚለው ቴዎድሮስ፤ ወጣቶች ይሄን አውቀው አንድነታቸውን እና ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያዳክም ያረጀ የፖለቲካ አስተሳሰብ አውልቀው በመጣል ለሰላም ዘብ መቆም አለባቸው፤ ከወሬ ይልቅ ለተግባር መንግስትም፣ወጣቱም ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል በማለት ወጣቱ መክሯል።
ወጣት አባይነህ አስማረ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩሉ፤ ለአገር እድገት ምክንያታዊ ወጣት ማፍራት አስፈላጊ ነው። ወጣቶች ራሳቸውን ለማብቃት፣ለማወቅ፣ ለመማር መጣር አለባቸው። ራሳቸውን በእውቀት ባበለጸጉ እና ባሳደጉ ቁጥር ማንም ተነስቶ እንደፈለገ ሊሾፍራቸው አይችልም።
ስለዚህ በስሜት ሳይሆን ማንኛውም ነገር በእውቀት እንደሚመራ ማሳየትና ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። በተለይም ባልተስተካከለ የአስተሳሰብ ቁመና እያሰቡና እየተመሩ የትም መድረስ እንደማይቻል ወጣቶች ተረድተው በብሔር ላይ ተንጠልጥለው ሀገራዊ አንድነትን የማያጠናክርና ዘላቂ ሰላም የማያመጣ ተግባር የሚሰሩ አካላትን ማቃናትና ማስተካከል የወጣቱ ኃላፊነት ነው።
ወጣቶች በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሯቸውም ዋናው የዴሞክራሲያዊ አደረጃጀት ጥያቄ እንደነበረ የሚናገረው ወጣት አስማረ ይሄን መነሻ በማድረግ ባልተለመደ ሁኔታ ከምክትል ከንቲባው ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጋር በሁሉም ከፍለ ከተሞች ወጣቶች ጋር በተደረጉ ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ራሱን የቻለና ለአገሪቱ ሰላም፣አንድነትና እኩልነት የሚታገል ቁመና ያለው ወጣት አደረጃጀት እንዲፈጠር ተደርጓል ይላል። ይህ መሆኑ ደግሞ ወጣቱ በሰከነ መንገድ ማሰብ እንዲችል ፣በምክንያታዊነት የሚያምን፣አገር ወዳድና በደመነፍስ የማይወስን ወጣት እንዲኖር ያደርጋል።
የሰው ልጅ አንዱን ከአንዱ የሚለየውና ውጤታማ እንዲሆን የሚረዳው ከስሜታዊነት የጸዳ መሆኑና ስሜታዊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ራሱን ተቆጣጥሮ አካባቢውን፣ ያሉ ተጨባጭ እውነታዎችን፣ አገራዊና ወገናዊ ጥቅሙን ተመልክቶና መዝኖ መወሰን መቻሉ ነው። ኢትዮጵያን በአንድ አይን እኩል አይቶ የሚለውጥና ለቀጣይ ትውልድ የሚያሸጋግር እና ሰላሟን የሚጠብቅ የዚህ አይነት ወጣት አስፈላጊ እንደሆነ አንስቷል።
በአጠቃላይ ወጣቶች ከስሜታዊነት በመላቀቅ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ከማህበረሰቡ ጋር መስራት አለባቸው። ይህ ሲሆን የአገሪቱ የእድገት ደረጃ ከሚያመነጨው ገቢ በፍትሃዊ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናሉ። የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት ስር እንዲሰድና ዋስትና እንዲኖረው በማድረግ ለትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ መደላድልን መፍጠር ከወጣቱ ብዙ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2012
ሙሐመድ ሁሴን