አርበኛ፣ ደራሲ፣ የሴቶች መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ የክብር ዶክተር ስንዱ ገብሩ በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር፣ በመናገሻ አውራጃ፣ አዲስ ዓለም ከተማ ውስጥ ጥር 6 ቀን 1908 ዓ.ም. ተወለደች። ዕድሜዋ ለትምህርት በደረሰበት ወቅት ቤት ውስጥ አስተማሪ ተቀጥሮላት የአማርኛን ትምህርት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም ድረስ ተማረች። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሄዳ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተምራለች።
አባታቸው በኢትዮጵያ አስተዳደር እና ፖለቲካ ውስጥ ብዙ ሚና የተጫወቱት ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ አርበኛ እንዲሁም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሹመትም የመጀመሪያው የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሲሆኑ እናታቸው ወይዘሮ ካሣዬ ኤሌምቱ ይባላሉ፡፡ ታናሽ እህታቸው ደግሞ የውብዳር ገብሩ (እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ) ናቸው።
ከንቲባ ገብሩ ወጣቷን ስንዱ ገብሩን እያስከተሉ ወደ ቤተ መንግሥትም ሆነ ሌላ ሥፍራዎች ይወስዷት እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (የኋላው ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) ጋር እንዳስተዋወቋት በወይዘሮ ስንዱ ታሪክ ላይ ሰፍሯል።
ከዕለታት አንድ ቀን ታዳጊዋ ስንዱ አንዲት የድብ አሻንጉሊት ይዛ እጅ ለመንሳት ወደ ቤተ-መንግሥት ሄደች፡፡ ወደ አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ፊት ቀርባም ‹‹ይቺ አሻንጉሊት ከተሰራችበት አገር ለትምህርት ይላኩኝ›› ብላ ጠየቀቻቸው፡፡ አልጋ ወራሹም ፈገግ ብለው አሻንጉሊቷን ተቀብለው አገላብጠው ተመለከቷት፡፡ አሻንጉሊቷ የስዊዝ ስሪት ነበረች፡፡ አልጋ ወራሹ ‹‹እሺ እልክሻለሁ›› ብለው መለሱላት፡፡ ስንዱም ‹‹አማርኛ እንዳልረሳ አንዷ እህቴ አብራኝ ትሂድ›› ብላ ፈቃድ ጠየቀች፡፡
አልጋ ወራሹም የወጣቷን ብልሀትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ስንዱ እና ታናሽ እህቷ የውዳብር ገብሩ በ1920 ዓ.ም ውጭ ሄዱ፡፡ ከንቲባ ገብሩ ደስታ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ለኖረው ማርቲን ፍላድ ለተባለው ጀርመናዊ ‹‹ልጆቼን ተከታተልልኝ፤ወኪል አባት ሁንልኝ፤ እንደእኔ ሆነህ ወደ ትምህርት ገበታቸው ስደድልኝ›› ብለው መልዕክት ላኩበት፡፡ ማርቲን ፍላድም እነስንዱን ተቀብሎ የቤተሰቡ አባል እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡ አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ለሥራ ጉዳይ ወደ አውሮፓ ባመሩበት ወቅትም ልጆቻቸውን ይጠይቋቸው ነበር፡፡
ስንዱ በውጭ አገር የትምህርት ቆይታዋም በአገር በቀል ሳይንስ ጥናት በዲፕሎማ ለመመረቅ በቃች፡፡ ቀጥሎም ሕግ ማጥናት ጀምራ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፍላጎቷ ወደ ሥነ-ጽሑፍ በማዘንበሉ ምክንያት ሌላ ትምህርት ቤት በመግባት የሥርዓተ ትምህርት ጥናት፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ታሪክ፣ ፈረንሣይኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን በማጥናት ተመረቀች፡፡ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡
(ከዚህ በኋላ ስንዱ በዕድሜም እየበሰለች አበርክቶዋም እየጨመረ ስለመጣ ‹‹አንቺ›› ማለትን በ‹‹አንቱ›› ተክተን ታሪካቸውን መዘርዘር እንቀጥላለን)
ወደአገራቸው እንደተመለሱም አዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የፈረንሳይኛ ቋንቋን፣ የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍንና ሌሎች ትምህርቶችን ማስተማር ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ አንድ ዓመት እንደቆዩ ለብላታ ሎሬንዞ ትዕዛዝ ተዳሩና ባለቤታቸው የሐረርጌ ክፍለሀገር አስተዳዳሪ ሆነው በመሾማቸው ከባለቤታቸው ጋር ወደዚያው አቀኑ። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላም ብላታ ሎሬንዞ የፍርድ ቤት ሹምና የዜና ስርጭት ኃላፊ ሆነው በመሾማቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ወይዘሮ ስንዱም ከባለቤታቸው ጋር አብረው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ እንግሊዝ ሀገር ሲሰደዱ የወይዘሮ ስንዱ ባለቤት ብላታ ሎሬንዞም አብረው ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ወደ ለንደን ሄዱ። ወይዘሮ ስንዱ ብቻቸውን ቀሩ፡፡ ልጅ የላቸውም፤ የሚያስተዳድሩት ቤተሰብም አልመሰረቱም፡፡
ስለሆነም ወደ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ተመልሰው ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲሁም ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ ወደ መቶ የሚጠጉ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ዝግጅት ጀመሩ፡፡ አባታቸው ከንቲባ ገብሩ እየገሰገሰ በመምጣት ላይ የነበረውን የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር ለመመከት እየተሰናዱ ስለነበር ጊዜው ወይዘሮ ስንዱ ለአገራቸው ነፃነት ከመፋለም ውጪ አመራጭ የለም ብለው ቆራጥ አቋም እንዲይዙ አደረጋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ስለመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት የተማሩት።
ወደ ነቀምቴ በመሄድም ሕዝቡን እየሰበሰቡ ስለ ነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። የፋሺስት ጦር በአገሬው ላይ ምን ዓይነት ደባ እየፈፀመ እንደሆነ ሕዝቡ እንዲገነዘብ አደረጉ፡፡ በዚህ ወቅት ለፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር አሽከርነት ባደሩ ባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሺስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ።
‹‹እናት ኢትዮጵያ ውዲቱ ውዲቱ፣
ላንቺ የማይረዳ ሳለ በሕይወቱ፣
በረከትሽን ይንሳው እስከዕለተ ሞቱ፡፡›› የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ፡፡
በዚያም ሳሉ በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ ሲያማክሯቸው 500 ብር ስለሰጧቸው ቀይ መስቀል አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የ‹‹ጥቁር አንበሳ›› ጦር በፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ሲመታ በፋሺስት ጦር ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ መጡ። ለጥቂት ቀናት ያህል ከታሰሩ በኋላም የቁም እስር ተበይኖባቸው ከአዲስ አበባ እንዳይወጡ ተደረገ፡፡
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒን ለመግደል በነአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም አቀናባሪነት በተሞከረው የግድያ ሙከራ የወይዘሮ ስንዱ ወንድም መርሻ ገብሩ አሉበት ተብለው ይፈለጉ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት በነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከአስመራ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ብዙ ወንዶችና ወይዘሮ ስንዱንና እህታቸውን የውብዳርን ጨምሮ ጥቂት ሴቶች ሆነው በመርከብ ‹‹አዚናራ›› ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ለዘጠኝ ወራት ታሰሩ።
እስረኞቹ ከምፅዋ ወደ አዚናራ ደሴት ሲወሰዱ ስለነበረው ሁኔታና ስለግዞት ቆይታቸው በየውብዳር (እማሆይ ጽጌማርያም) ገብሩ የሕይወት ጉዞ ላይ አተኩሮ በተፃፈ መጽሐፍ ላይ ባለታሪኳ እንዲህ ብለዋል …
‹‹ … ከአዲስ አበባ በካሚዮን ምፅዋ ድረስ ከሄድን በኋላ በመርከብ ወደ ሳርዲና ወሰዱን፡፡ እዚያም ስንደርስ እኛን አዚናራ ወደምትባል ትንሽ ደሴት ወሰዱን፤ ሌሎቹን ደግሞ በዚያው አካባቢ አስቀመጧቸው፡፡ ከጫካና ከውሃ እንዲሁም ከጠባቂዎቻችን በስተቀር ምንም የምናየው ነገር የለም ነበር፡፡ የምንሰራው ነገር አልነበረም፡፡ በኑሮ በኩል በደንብ ነበር የተያዝነው … የግዞት ቦታ ውስጥ እያለን ሁሉንም ነገር የሚሰሩልን ጣሊያኖች ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ አብረው በግዞት ያሉት የቤት ሠራተኞች የእኩልነት መብት ስለተሰማቸው እመቤቶቻቸውን በመናቅ ምንም ነገር መታዘዝ አይፈልጉም ነበር፡፡ ማመፅ ብቻ ሳይሆን የቀደመ ቂማቸውን መወጣት በመፈለግ ለመማታት የሚቃጣቸውም ነበሩ፡፡ ታዲያ ጣሊያኖቹ ይህን ሁኔታ በመረዳት የሥራ ድርሻ ሰጧቸው፤ ቤትና መፀዳጃ ቤቶችን እንዲያፀዱ ከታዘዙ በኋላ ቀዝቀዝ አሉ …››
እነወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ጣሊያን በቆዩባቸው ጊዜያት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ይህ ነው ተብሎ በቀላሉ ሊገለፅ የማይችል የመከራ ዶፍ ዘነበባቸው፡፡ በተለይ በከንቲባ ገብሩ ቤት በየዕለቱ ይስተናገድ የነበረው ኀዘን የመረረ ነበር፡፡ ከወይዘሮ ስንዱና ከእህታቸው የስደት እስራት በተጨማሪ ወንድማቸው መቶ አለቃ መርሻ ገብሩ ከየካቲት 12 ሰማዕታት መካከል አንዱ ሆነ፡፡
ከዘጠኝ ወራት እስራት በኋላ ፋሺስቶች ወደነወይዘሮ ስንዱ ቀርበው ‹‹ነፃ ናችሁ፤ምኅረት አድርገንላችኋል፤ወደ አገራችሁ እንመልሳችኋለን፤ወደ አገራችሁ ከተመለሳችሁ በኋላ አመፅ ከቀሰቀሳችሁ ግን ቅጣታችን የበረታ ይሆናል፡፡ ንብረታችሁ ወድሞ ከተገኘ የኢጣሊያ መንግሥት ያቋቁመዋል›› ብለው ነግረዋቸው ወደ ኢትዮጵያ መለሷቸው፡፡
ይሁን እንጂ ፋሺስቶቹ እነወይዘሮ ስንዱን አርበኞችን በመርዳትና ሕዝቡን በማነሳሳት ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጧቸውም ወይዘሮ ስንዱ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው ቀስቃሽ ጽሑፎች በማዘጋጀት አርበኞችን በግጥምና በወኔ በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበልና መሣሪያ በማዳረስ ታላቅ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል። አዚናራ ደሴት ታስረው የነበሩት የንጉሥ ሚካኤል የልጅ ልጅ የሆኑት ደጃዝማች አመዴ አሊ ሚካኤል ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ሁለተኛ ባል ነበሩ፡፡
ወይዘሮ ስንዱ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅትና ከድል በኋላ በሀገር ፍቅር ስሜት በመነሣሣት በርካታ ስሜት ቀስቃሽ ግጥሞችን፣ ተውኔቶችንና ሌሎች ጽሑፎችን ጽፈዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ትግል››፣ ‹‹ዓድዋ››፣ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ››፣ ‹‹የታጋዮች ስሜት ከግራዚያኒ ንግግር በኋላ››፣ ‹‹ኮከብህ ያው’ና ያበራል ገና››፣ ‹‹በግራዚያኒ ጊዜ የየካቲት ቀኖች››፣ ‹‹ከማይጨው መልስ››፣ ‹‹የኔሮ ስህተት››፣ ‹‹የልቤ መጽሐፍ››፣ ‹‹የታደለች ሕልም››፣ ‹‹ርዕስ የሌለው ትዳር››፣ እንዲሁም ‹‹ፊታውራሪ ረታ አዳሙ›› የሚሉት ሥራዎቻቸው የወይዘሮ ስንዱን የሀገር ፍቅር ስሜትና የሥነ ጽሑፍ ችሎታ ያሳዩ ናቸው፡፡
ወይዘሮ ስንዱ እነቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ትያትሮችን በደረሱ ጊዜ አባታቸውን ከንቲባ ገብሩን ተከትለው ወደ ተውኔት አዳራሾች ይሄዱ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚም በኋላ ለተጠመዱበት የትያትር ፍቅር እንደአንድ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ወይዘሮ ስንዱ ‹‹በግራዚያኒ ጊዜ የየካቲት ቀኖች›› የተባለውን የተውኔት ድርሰታቸውን የካቲት 12 ቀን 1942 ዓ.ም. ባቀረቡ ጊዜ የታዳሚው ሕዝብ ስሜት በከፍተኛ ደረጃ በመነካቱ ቁጭት አድሮበት እንባውን ያላፈሰሰ አልነበረም፡፡
በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ. ም.ጭፍጨፋ ወይዘሮ ስንዱ በግላቸው ብዙ ዘመዶቻቸውን አጥተዋል፡፡ ንጉሰ ነገሥቱም በገፀ-ባህርያቱ አቀራረፅና በተዋንያኑ አመራረጥ ተመስጠው፣ የዚያን ዘመን የአገሪቱን ገፅታ የሚያሳይ መሆኑን መስክረው ወይዘሮ ስንዱን አመስግነዋቸዋል፡፡ በእርግጥ ይህ የወይዘሮ ስንዱ የተውኔት ድርሰት መልዕክቱ በቅጡ እንዲተላለፍና በዘመኑ አርብቦ የነበረው ገፅታ በተመልካቹ ልቦና እንዲቀረፅ በእህታቸው የውብዳር (እማሆይ ጽጌማርያም) ገብሩ ያማረ የፒያኖ ድምፅ ታጅቧል፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም በርዕሰ መምህርነት (የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ሆነው) ሰርተዋል። ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ካደላደሉ በኋላ ሦስተኛውንና የልጆቻቸውን አባት የሆኑትን ሻለቃ አሰፋ ለማን አገቡ፡፡
ከዚህ በኋላ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተሣትፎአቸው እየሰፋና በቁጥርም እየተበራከተ መጣ፡፡ በ1948 ዓ.ም. በተደረገው የፓርላማ ምርጫ የእንጦጦና የጉለሌን ወረዳ ወክለው ተወዳደሩ፡፡ ምርጫውን በማሸነፍም የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባል ሆኑ፡፡ ይህም የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ አስቻላቸው፡፡ በሕግ መምሪያ ምክር ቤትም እንደገና ተወዳድረው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ በፓርላማ የነበራቸው ተሳትፎ አብረዋቸው ለነበሩት እና በኋላም ለተመረጡት ሴት የፓርላማ አባላት ትልቅ ብርታት ነበሩ። በዚህ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እና ‹‹የወንድ ዓለም›› በገነነበት የታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን በብዙ የታገሉ ሴት ነበሩ።
በአንድ ወቅት በተደረገ የምክር ቤት ውይይት ላይ የፍትሐብሄር ህግ ረቂቅ ቀርቦ በሚመክሩበት ወቅት በትዳር የመኖሪያ ስፍራን ባል እንዲመርጥ የሚደነግገውን አንቀፅ በመቃወም በባልና ሚስት (በሁለቱም) ምርጫ መሆን እንዳለበት ቢተቹም የእርሳቸው ንግግር ሊደመጥ ባለመቻሉ ‹‹እናንተ ዛሬ ሃሳቤን ውድቅ ብታደርጉትም ወደፊት በዚህ ምክር ቤት ሴት ተወካዮች ቁጥራቸው ሲጨምር ይህን እኩል ውክልና የማግኘት ጥያቄ ያነሱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ብለው ተናግረው ነበር።
ወይዘሮ ስንዱ በፖለቲካና በአስተዳደር መስኮች ካበረከቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ ማህበራዊ ተሣትፏቸውም እጅግ ሰፊ ነበር፡፡ በሴቶች የበጐ አድራጐት ድርጅቶች፣ በቀይ መስቀል ማኅበር፣ በአካል ጉዳተኞች አገልግሎት እና በሌሎችም ማህበራት ያለመታከት ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ዋና ፀሐፊና አስተዳዳሪ፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ ሆነው ሰርተዋል።
ከ1966 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ሙሉ ጊዜያቸውን ያዋሉት ለሥነ-ጽሑፍ ሥራ ላይ ነበር፡፡ ብዙ የተውኔት እና የታሪክ መጽሐፍትን ፅፈው በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መጽሐፍት እንዲቀመጡ አድርገዋል፡፡ ከ1966 ዓ.ም. በኋላ ከፃፏቸው መካከል ‹‹ራስ መኰንን ከአረጋዊ መካር ጋር›› ፣ ‹‹ጥቁር አንበሳ››፣ ‹‹ሰገሌ የመንግሥት ለውጥ››፣ ‹‹የጥቁር አንበሳ ትግል በምዕራብ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ጃንሆይ በእንግሊዝ አገር››፣ ‹‹ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ እንዲነግሱ ሲጠየቁ›› የሚሉት ሥራዎቻቸው ይጠቀሳሉ።
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ በመምህርነት፣ በአርበኝነት፣ በፖለቲካና በአስተዳደር፣ በሥነ-ጽሑፍ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ተግባራት ላበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች ሥራ የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥተ ሣባ የወርቅ ኒሻንና የቀይ መስቀል ማኅበር የወርቅ ሜዳልያ ተሸልመዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።
ክብርት ዶክተር ስንዱ ገብሩ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 14 / 2012
አንተነህ ቸሬ