አዲስ አበባ፦ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመቶ ቀናት እቅዱ ችግሮች እንዳልገጠሙትና ባቀደው ልክ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
የሚኒስቴሩ የሕዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዋና ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በመቶ ቀናት እቅድ ውስጥ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጥናትና ጥገና ይፈልጋሉ ከተባሉ 26 ቅርሶች መካከል ለሦስቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። የተመረጡት ቅረሶች በመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት ተዘንግተው በመቆየታቸው፤ ከፍተኛ በጀት የሚያስወጡና አደጋቸው የከፋ እንደሚሆን በመረጋገጡ ስራዎች ተጀምረዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኪነጥበብንና ሥነጥበብን ለአንድነትና ለሰላም ሚናቸውን እንዲወጡ በማድረግ በኩል ተግባራት መለየታቸውን የገለጹት አቶ ገዛኸኝ፤ የኪነጥበብ ዘርፍ በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋለና ያልተጠቀምንበት መሣሪያ በመሆኑ የጋራ እሴቶችን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች እንዲጎለብቱ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ የአገር ውስጥ ቱሪዝም እና የኢኮ-ቱሪዝም ስትራቴጂዎችን በመቶ ቀናት እቅድ ተካቶ እየሰራ ሲሆን፤ የሀገር ወስጥ ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የአገርህን እወቅ ክበባት፣ የሃይማኖት ተቋማት የምዕመናን ጉብኝቶች፣ የተለያዩ የስብሰባና የውይይት መድረኮች በብዛት ይካሄዳሉ ብለዋል። ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በኩል ጥናቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ካለው አቅም አንጻር የፈጠረው የሥራ ዕድል በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም ያስታወሱት አቶ ገዛኸኝ፤ የባለኮከብ ሆቴሎች ባለሙያዎችን ከባህር ማዶ እያመጡ ይቀጥራሉ። ይህ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳትና በአገር ውስጥም ክፍተት ኖሮ ከሆነ ለማስተካከል የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሚኒስቴሩ የመቶ ቀናት እቅድ መካከል አገራዊ ስፖርት ንቅናቄ መፍጠር፣ ለስፖርት አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግና ስፖርታዊ ጨዋነትን ማጎልበት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት የሚሉት ተካተዋል። በመዋቅርና አደረጃጀት ስም የስታድየም ሥራ አይጓተትም፤ሥራዎች እየተከናወኑ ይቀጥላሉ።
እቅዶቹን ተግባራዊ የማድረግ ሂደቱ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ እንዳለም ጠቅሰዋል።
የአመራር ቁርጠኝነት እስካለ ድረስ ባለው ሀብት መንቀሳቀስ እንደማያዳግትም ጠቁመዋል። ጊዜ የሚወስዱ ሥራዎች ቢኖሩም በአመራሩ በኩል ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ስላለ በመቶ ቀናት እቅድ ከተያዙት ውስጥ እስከአሁን ያልተከናወኑ ተግባር የሉም ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
በሊድያ ተስፋዬ