ኑዛዜ ምንድን ነው?
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
መቼም ኑዛዜ የሚለው ቃል ለብዙዎቻችን እንግዳ እንዳልሆነ እርግጥ ነው።ቃሉን በየቤታችንና በምንውልባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ደጋግመን ሳናደምጠው አንቀርም።ሙግት ላይ አረፋፍደው በፍርድ ቤቶች አካባቢ ሰብሰብ ብለው የሚጓዙ ባለጉዳዮችና ጠበቆቻቸው ሲነጋገሩ ከምታደምጧቸው ቃላት ውስጥ ጎልቶ የሚሰማው ኑዛዜ ወይም ውርስ ሊሆን ይችላል።የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችን አጨናንቀው ከሚገኙት የክርክር ዶሴዎች ውስጥ የውል፣ የመሬት፣ የአሰሪና ሠራተኛ እንዲሁም የውርስ ጉዳዮች ይገኙበታል።
በአገራችን የውርስ ሕግ መሠረት ውርስ በሁለት ዓይነት ሥርዓቶች ይፈጸማል – በኑዛዜ እና ያለኑዛዜ።ከስያሜያቸው መረዳት እንደሚቻለው በኑዛዜ የተደረገ ውርስ የሚፈጸመው በኑዛዜው መሠረት ነው።ያለኑዛዜ ውርስ የሚባለው ደግሞ ሟች ከመሞቱ በፊት ንብረቱን በተመለከተ ምንም ዓይነት ኑዛዜ ሳያደርግ የቀረ እንደሆነ ውርሱ በሕጉ በተቀመጠው መሠረት ያለኑዛዜ (ለሕጋዊ) ወራሾቹ የሚተላለፍበት ሂደት ነው።
በአግባቡ የተጠናቀረ መረጃ ማቅረብ ባይቻልም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአብዛኛው ውርስን በኑዛዜ የማስተላለፍ ልማድ እንደሌለው በተለያዩ ጽሑፎች ላይ ሰፍሮ እናነባለን።በዚሁ መነሻ ውርስ የሚከናወነው ሕጉ ባስቀመጠው የወራሽነት ደረጃ አማካኝነት በተወላጆችና በወላጆች እንዲሁም ወደጎን ባለ ዝምድና (እህትና ወንድም) መካከል ነው፡፡
ያም ሆኖ በፍርድ ቤቶች ከውርስ ጋር ተያይዘው ከሚደረጉት ክርክሮች ውስጥ አያሌዎቹ ኑዛዜን የተመለከቱ ናቸው።ከኑዛዜ ለሚመነጭ ክርክር ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ተናዛዦች ሕግን ተከትለው ኑዛዜ አለማድረጋቸው ነው።የኑዛዜ ተጠቃሚዎችም ሆኑ ያለኑዛዜ (የሕግ) ወራሾች ከኑዛዜው ጋር በተያያዘ ሕጋዊ መብትና ግዴታቸውን ጠንቅቀው አለማወቃቸውም ለሙግቶች መብዛት ዓይነተኛ መነሾ መሆኑም አልቀረም።ለኑዛዜ አድራጊውም ሆነ ለወራሾች እንዲህ ወደ ክርክር መግባት መሠረታዊው አመክንዮ ታዲያ የንቃተ ሕግ አለመዳበር ስለመሆኑ መናገር ጉንጭ ማልፋት ይሆናል።
የኑዛዜ ዓይነቶች
በሕጋችን ኑዛዜ ሦስት ዓይነት ነው።አንደኛው በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ ሲሆን ይኸውም ተናዛዡ እየተናገረ ማናቸውም ሌላ ሰው ወይም ራሱ ተናዛዡ በምስክሮች ፊት የሚጽፈው ነው።ሁለተኛው ተናዛዡ ራሱ ኑዛዜ መሆኑን በግልጽ በማስፈር ሙሉ በሙሉ ብቻውን የሚጽፈው የኑዛዜ ዓይነት ነው።ሦስተኛው የቃል ኑዛዜ ሲሆን አንድ ሰው የሞቱ መቃረብ ተሰምቶት የመጨረሻ የፈቃድ ቃሎቹን ለሁለት ምስክሮች የሚሰጥበት ነው።በኢትዮጵያ ሕግ በውስን ሁኔታዎች ማለትም ተናዛዡ የቀብሩን ሥነ ሥርዓት አፈጻጸምን በተመለከተ፣ እያንዳንዳቸው ከ500 ብር የማይበልጡ ግምት ያላቸው ኑዛዜዎችን ለመስጠት እና አካለ መጠን ላላደረሱ ልጆች አሳዳሪ ወይም ሞግዚትን የሚመለከቱ ትዕዛዞችን ለመስጠት ብቻ የቃል ኑዛዜ ይፈቀዳል።
በየትኛውም የኑዛዜ ዓይነት ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ የሚያሰፍራቸው ቃሎች በጣም ወሳኝና ሕግን የተከተሉ መሆን አለባቸው።ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ አንድ ወይም ብዙ የጠቅላላ ሐብቱን ወራሾቹን መግለጽ፤ ልዩ የኑዛዜ ስጦታ ማድረግ፤ የቀብሩን ሥነ ሥርዓት የሚመለከቱ ትዕዛዞችን መናገር ወይም መጻፍ እንዲሁም አንድ የበጎ
አድራት ድርጅት ወይም የንብረት አደራ ጠባቂ ማድረግ ወይም አንድ ወይም ብዙ ወራሾቹን ከወራሽነት መንቀልን የተመለከቱ ቃሎችን ሊያስቀምጥ ይችላል።
ከሕግ የግንዛቤ ማነስ የተነሳ በአብዛኛው ተናዛዦች የውርስ ሕጉን ተከትለው ኑዛዜ አያደርጉም።ኑዛያቸውም በሕግ ተቀባይነትን ያጣል።በዚህም ምክንያት ከሞታቸው በኋላ የንብረታቸውን ድልድል በተመለከተ እንዲህ መሆን አለበት ብለው ያስቀመጡት የመጨረሻ ፈቃዳቸው ተግባራዊ ሳይሆን ይቀራል።ለቋሚ ወዳጅ ዘመድም ቢሆን የክርክርና የግጭት መነሻ ሆኖ ሲያፋጅ መኖሩ አይቀርም።
ለዚህም ነው በዚህ ጽሑፋችን ስለ ኑዛዜ በተለይም ደግሞ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ኑዛዜ ምን መምሰል አለበት በሚለው ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የወደድኩት።
ኑዛዜ በሟች በራሱ የሚፈጸም ድርጊት ነው
ኑዛዜ የሟቹ ጥብቅ የሆነ ራሱ የሚፈጽመው ሕጋዊ ድርጊት ነው።ሀብቱን ማን መውረስ እንዳለበት፤ እንዴትስ ለወራሾቹ መከፋፈል እንዳለበት የመወሰን መብት ያለው ራሱ ተናዛዡ ነው።ይህ ማለት ሟቹ አንድን ሌላ ሰው በእሱ ቦታ ሆኖ ወይም በስሙ ኑዛዜ እንዲያደርግ፣ እንዲለውጥ ወይም እንዲሽር ሥልጣን (ውክልና) ሊሰጠው አይችልም ማለት ነው።ኑዛዜ ስጦታ አይደለም።ስጦታ ውል ነው።ስጦታ አንዱ ሰው ውል ሰጪ ሆኖ ሌላው ደግሞ ውል ተቀባይ ሆኖ ችሮታ በማድረግ ሃሳብ ከንብረቶቹ አንዱን የሚለቅበት ወይም ግዴታ የሚገባበት ውል ነው።ለስጦታ ውል ፍጹምነት ደግሞ የተቀባዩ ፈቃድ ያስፈልጋል፤ ማለትም ልግስናውን እቀበላለሁ ብሎ ሃሳቡን መግለጽ አለበት።
ኑዛዜ ግን ውል ሳይሆን በሟች ይሁንታ ላይ የተመሰረተ የብቻው ሕጋዊ ድርጊት ነው። እርግጥ ነው በኑዛዜ ውስጥ ስጦታ ሊደረግ ይችላል።ነገር ግን የተቀባዩ ፈቃደኛ አለመሆን ኑዛዜውን ፈራሽ አያደርገውም።የኑዛዜውን ስጦታ አልቀበልም ካለ በሕጉ መሠረት ንብረቱ ከሟች በአደራ ለተቀበለው ሰው ይተላለፍለታል።ከዚህ ሌላ የስጦታ ውል የሚፈጸመው ወይም እንደውሉ ተቀባዩ ንብረቱን የሚወስደው ሁለቱም በሕይወት ሳሉ ሲሆን ኑዛዜ የሚፈጸመው ወይም የኑዛዜው ቃል ተግባራዊ የሚደረገው ደግሞ ተናዛዡ ከሞተ በኋላ ነው፡፡
ኑዛዜ ለማድረግ ችሎታ ያስፈልጋል
የፍትሐብሔር ሕጉ “ስለ ሰዎች ችሎታ” በሚለው ርዕስ ስር ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት ችሎታ ያለው ስለመሆኑ ግምት ወስዶ በተመሳሳይ አንድ ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑ በሕግ ተወስኖ ሊቀመጥ እንደሚችልም በግልጽ አስቀምጧል።“ችሎታ” አንድ ሰው በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ተግባር ለማከናወን ያለውን ብቃት (ability to perform a juridical act) የሚያመላክት አነጋገር ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም በዚሁ የሕግ ጉዳዮች አምድ በተጻፈ ማብራሪያ መመልከታችን አይዘነጋም።
በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ተግባር (juridical act) የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ደግሞ ውል መዋዋልን ጨምሮ ጋብቻ መመስረትን፣ ኑዛዜ መስጠትን፣ መወከልን፣ ንብረት ማስተዳደርንና ሌሎችንም ሕጋዊ ክንዋኔዎችን የሚያጠቃልል ነው።ስለዚህ በሕጉ ማንኛውም ሰው ችሎታ አለው በሚል የተወሰደው ግምት ሰው ሁሉ እነዚህን ሕጋዊ ክንዋኔዎች ለመፈጸም ብቃት ያለው መሆኑን ለመደንገግ ነው ማለት ነው።
ነገር ግን ይህ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት ችሎታ አለው የሚለው ግምት ፍጹም ባለመሆኑ ሕጉ ራሱ ሰዎች ችሎታ ሊያጡ የሚችሉባቸውን ምክንያቶች አስቀምጧል።የተፈጥሮ ሰዎች የችሎታ ማጣትን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ጠቅላላ እና ልዩ በመባል ይታወቃሉ።ጠቅላላ ምክንያቶች ዕድሜ፣ የአዕምሮ ሕመም፣ ዕብደት፣ በፍርድ እና በሕግ የተጣለ ክልከላ ናቸው።
ልዩ የሚባለው ደግሞ ሕጉ በኢትዮጵያውያንና በሌሎች አገራት ዜጎች መካከል የመብት ልዩነት እንዲኖር በማሰብ የውጭ ዜጎችን ችሎታ የሚገደብበት እንዲሁም የመንግሥት ሹማምንት ከምንዝሩ ዜጋ እኩል ችሎታ ኖሯቸው በሥልጣናቸው ያለአግባብ እንዳይገለገሉበትና ሕዝባዊ ኃላፊነታቸው ከግል ጥቅማቸው ጋር እንዳይጋጭ በሚል ችሎታቸው የሚገደብበት ሁኔታ ነው።በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ሰዎችም ከባህሪያቸው፣ ከምዝገባና ፈቃድ አሰጣጣቸው፣ ከተቋቋሙበት ዓላማ እንዲሁም በሕግ በሚደረግ ክልከላ አማካኝነት ችሎታቸው ሊገደብ ይችላል።
ከፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 860 እና ከተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 225 ጣምራ ንባብ እንደምንረዳው 16 ዓመት ያልሞላው ልጅ ኑዛዜ ማድረግ አይችልም።16 ዓመት ያልሞላው ልጅ ኑዛዜ ቢያደርግ እንኳ 16 ዓመት ከሞላው በኋላ ኑዛዜውን ባይሰርዘውም ኑዛዜው በሕግ ፊት ውጤት አይኖረውም።ይህ ብቻ ሳይሆን ሞግዚቱም ቢሆን በዚህ ልጅ ስም ኑዛዜ ሊያደርግ አይችልም፡፡
የአእምሮ ሕመም የሰዎችን ችሎታ የሚያሳጣ ሌላው ምክንያት ነው። በፍትሐብሔር ሕጉ መሠረት አንድ ሰው የአዕምሮ ሕመምተኛ (አዕምሮው የጎደለ ሰው) ነው የሚባለው በተፈጥሮ ዕውቀቱ ያልተስተካከለ (ዘገምተኛ) በመሆኑ፤ በአዕምሮ ሕመም ወይም በመጃጀት ምክንያት የሚሰራው ሥራ የሚያስከትለውን ውጤት በቅጡ መገንዘብ የተሳነው ሲሆን ነው።ከዚህም በተጨማሪ የአዕምሮ ደካሞች፣ ሰካራሞች፣ በመጠጥና አፍዛዥ አደንዛዥ በሆኑ ነገሮች ሱስ የተዘፈቁና ገንዘብን ያለአግባብ የሚያባክኑ ሰዎችም እንዲሁ አዕምሯቸው የጎደለ ሰዎች ናቸው በሕግ አንድምታ።
ሕጉ በአእምሮ ዝግመት፣ በአዕምሮ ሕመም ወይም በእርጅና ምክንያት አዕምሯቸው የጎደሉ ናቸው ከሚላቸው ሰዎች በተጨማሪ በተለመደው አጠራር ዕብዶች የሚባሉትን ሰዎች “በግልጽ የታወቀ የአዕምሮ ጉድለት ያለባቸው” የሚል ስያሜ በመስጠት ሕጋዊ ሥራ ለመፈጸም ችሎታ የሌላቸው ናቸው ይላቸዋል።እነዚህ የታወቀ የአዕምሮ ጉድለት ያለባቸው ሰዎች በሆስፒታል ወይም በአዕምሮ ሕሙማን መኖሪያ ቦታ እንዲሁም ከሁለት ሺ የማያንሱ ነዋሪዎች በሚገኙበት አካባቢ የሚኖሩና በቤተ ዘመድ ወይም አብረዋቸው በሚኖሩ ሰዎች በአዕምሯቸው ምክንያት ጥበቃ የሚደረግላቸውና ለእንቅስቃሴያቸውም ወሰን የተበጀላቸው ሰዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ የውርስ ሕግ ታዲያ በመርህ ደረጃ ተናዛዡ ኑዛዜ በሚፈጽምበት ወቅት አዕምሮው የጎደለ ነበር በማለት ምክንያት ኑዛዜ ሊሻር አይችልም።ይህ ማለት ተናዛዡ የአእምሮ ዝግመት ነበረበት ወይም በአዕምሮ ሕመም አልያም በእርጅና ምክንያት አዕምሮው የጎደለ ነበር በማለት ያደረገውን ኑዛዜ መቃወም አይቻልም።ይሁን እንጂ ተናዛዡ ኑዛዜውን ባደረገበት ወቅት የታወቀ ዕብድ (በግልጽ የታወቀ የአዕምሮ ጉድለት ያለበት) የነበረ እንደሆነ በአዕምሮው ጎደሎነት ምክንያት ኑዛዜው እንዲሻር ወራሽ የሆነ አልያም ሌላ ጥቅም ያለው ሰው ክስ ለመመስረት መብት አለው።
ከዚህ የምንረዳው የአገራችን ሕግ በአዕምሮ መጉደል ምክንያት ኑዛዜን ለመቃወም ጠባብ መንገድ (ተናዛዡ የታወቀ ዕብድ ከሆነ) ብቻ ማስቀመጡን ነው።ነገር ግን የታወቀው ዕብድም ሆነ በአእምሮ ዝግመት፣ በአዕምሮ ሕመም ወይም በእርጅና ምክንያት አዕምሯቸው የጎደሉ ሰዎች የሚሰሩትን ድርጊትም ሆነ የሚያስከትለውን ውጤት በቅጡ መገንዘብ የሚሳናቸው ሰዎች ስለሆኑ ልክ እንደ እብድ ሁሉ በተመሳሳይ ኑዛዜን ፈራሽ ለማድረግ ምክንያት ሊሆኑ ይገባ ነበር።
ከላይ ከተብራሩት የችሎታ ማጣት ምክንያቶች (ሕፃንነት፣ የአዕምሮ ጉድለትና ዕብደት) በተጨማሪ ፍርድ ቤት በሚቀርብለት ማስረጃ በመመርኮዝ አንድን ሰው የአዕምሮ ጉድለት አለበት በማለት ፍርድ ለመስጠትና ለጤናው እንዲሁም ለራሱና ለወራሾቹ ጥቅም ሲባል ሕጋዊ ተግባራትን የመፈጸም ችሎታውን በመንፈግ ችሎታ የሌለው ሰው ሊያደርገው ይችላል።የተከለከለ ሰው ታዲያ የክልከላው ፍርድ ከተሰጠበት በኋላ ኑዛዜ ለማድረግ አይችልም።ከተከለከለበት ቀን በፊት ያደረገው የኑዛዜ ቃል ግን ይጸናል።ይሁንና በፍርድ ከመከልከሉ በፊት ያደረገው ኑዛዜ ይዘቱ ሲታይ በፍርድ ቤቱ ዕምነት ለርትዕ ተቃራኒ ከሆነ ወይም ኑዛዜው የጤንነቱ መታወክ ውጤት ነው የሚያሰኝ ከሆነ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል ሊያፈርሰው ይችላል።
ፍርድ ቤት ተናዛዡ በፍርድ ከመከልከሉ በፊት ያደረገውን ኑዛዜ በሙሉ ወይም በከፊል የማፍረስ ስልጣን እንዳለው ሁሉ ተናዛዡ በፍርድ ከተከለከለ በኋላ ያደረገውን ኑዛዜም በሙሉ ወይም በከፊል ሊያጸናው ይችላል።ፍርድ ቤት ይህንን የሚያደርገው ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ የተመለከቱትን ቃላት በጤናው መታወክ ምክንያት ያደረጋቸው አይደሉም የሚል እምነት ካደረበት ነው።ይህ ማለት ተናዛዡ በፍርድ ከተከለከለ በኋላ ባደረገው ኑዛዜ ውስጥ የሰፈሩትን ቃላት የተናገረው (የጻፈው) ጤናው ስለታወከ ሳይሆን በጤናማ አዕምሮው ያደረገው ነው ብሎ ካመነ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል ሊያጸናው ይችላል ማለት ነው።
በአንጻሩ በሕግ የተከለከሉ ሰዎች ኑዛዜ ለማድረግ ሙሉ ችሎታ ያላቸው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።በሕግ የተከለከሉ ሰዎች የሚባሉት በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ከተፈረደባቸውና ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ በተጨማሪነት ፍርድ ቤት በወንጀል ሕጉ በተደነገገው አግባብ ከመብታቸው የሻራቸው ሰዎች ናቸው።ለዚህም ነው በሕግ የተከለከሉ ሰዎች የተሰኙት።እናም በመብታቸው ሊሰሩባቸው ያልተገቡ መሆናቸው ሲታወቅ ከሕዝባዊ መብቶች በተለይም ከመምረጥ መመረጥ፣ ከማዕረግ፣ ከምስክርነትና ከዋስትና መብቶች ሊከለከሉ ይችላሉ።
በተጨማሪም ከሞግዚትነት፣ በቤተ ዘመድ ላይ ካለ መብት፣ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የንግድ፣ የሙያ ወይም የኢንዱስትሪ ሥራ ከመስራት መብታቸውም ይሻራሉ።ሕጉ የሕፃናትን፣ የአዕምሮ ጎደሎዎችንና በፍርድም ጭምር የሰዎችን ችሎታ የሚገድብበት ዓይነተኛ ምክንያት እነሱንና ጥቅማቸውን ለመጠበቅ በሚል ነው።በሕግ የተከለከሉ ሰዎች ችሎታ የሚሻርበት አመክንዮ ደግሞ በመብቶቻቸው ሊሰሩባቸው የማይገባቸው ሰዎች በመሆናቸው ማህበረሰቡን ከእነሱ ሥራ ለመጠበቅ ነው።
ከኑዛዜ ጋር በተያያዘ ታዲያ በሕግ የተከለከሉ ሰዎች በወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ተብለው ቢቀጡም እንኳ ንብረታቸውን በኑዛዜ እንዳያስተላልፉ የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ አይከለክላቸውም።የብዙ አገራት ሕጎች በወንጀል የተቀጡ ሰዎችን ኑዛዜ እንዳያደርጉ የሚከለክሉ በመሆናቸው በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሕግ የሚወደስ ሆኖ እናገኘዋለን ማለት ነው።
ኑዛዜ ሊፈጸም የሚችል መሆን አለበት
የኑዛዜ ቃል ሊፈጸም የሚችል መሆን አለበት።የኑዛዜው ቃል ሊፈጸም የማይችል ከሆነ ደግሞ ኑዛዜ ማድረጉ በራሱ ትርጉም የለውም።ኑዛዜ ተፈጻሚ ሊሆን ከማይችልባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ተጠቃሚውን ወይም ጉዳዩን በግልጽ ካላመለከተ ነው።ለማሳያነት ሦስት አራት መኪናና ቤቶች ያሉት አባት በኑዛዜው ውስጥ ቤቴን ለአንዱ ልጄ፣ መኪናዬን ደግሞ ለአንደኛው ልጄ አውርሻለሁ የሚል ቃል ቢያስቀምጥ ይህ የኑዛዜ ቃል ተጠቃሚውንና ጉዳዩን በግልጽ ስለማያመለክት ለአፈጻጸም ያስቸግራል።ስለዚህ በወራሾች መካከል ክርክር ማስነሳቱ አይቀሬ ነው።
ኑዛዜ ተፈጻሚ ሊሆን ከማይችልባቸው ምክንያቶች ውስጥ ሁለተኛው አፈጻጸሙ የማይቻል ከሆነ ነው።“የማይቻል አፈጻጸም” በሚል በሕጉ የተጻፈው አነጋገር በሕጉ ትርጉም ያልተሰጠው በመሆኑ በፍርድ ቤቶችም ሆነ በተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች ዘንድ አከራካሪ ነው።በላቸው አንቷን የተባሉ የሕግ ባለሙያ “ከኢትዮጵያ የኑዛዜ ሕግ አንዳንድ ነጥቦች” በሚል ርዕስ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕጋዊነት መጽሄት ላይ ባሰፈሩት ቆየት ያለ ጽሑፍ ውስጥ ያቀረቡት የፍርድ ቤት ክርክር መዝገብ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
ኑዛዜ አድራጊው መኖሪያ ቤታቸውን ውጭ አገር ለሚኖር ልጃቸው ይሰጣሉ።በዚሁ ኑዛዜያቸው ታዲያ ለወንድማቸው ልጅ ከቤቱ ውስጥ አንዱን ክፍል ቤት አግኝታ ራሷን ችላ እስክትወጣ ድረስ እንድትኖርበት፤ ሠራተኛቸው የነበረችው ሴት እንዲሁ ልጃቸው ከውጭ እስከሚመጣ ወይም ቤት አግኝታ ራሷን ችላ እስክትወጣ ድረስ አንዱ ክፍል ውስጥ እንድትኖርበት ይናዘዛሉ።
ይህ ጉዳይ እስከ ሰበር ችሎት ድረስ አከራክሯል።እርግጥ ነው የጽሑፉ አቅራቢ ኑዛዜ አድራጊው ቤቱን በሙሉ ለልጃቸው ብቻ የሰጡ በመሆኑና ለሁለቱ ሴቶች ግን ለተወሰነ ጊዜ በቤቱ የመጠቀም ያውም በተወሰኑ ክፍሎች ብቻ በመሆኑ የማይቻል ኑዛዜ ነው ሊባል እንደማይቻል ይሞግታሉ።ኑዛዜው አፈጻጸሙ የማይቻል ነው ሊባል ይችል የነበረው ቤቱን ለልጃቸው ከሰጡ በኋላ በተመሳሳይ ለሁለቱም ሴቶች ቢሰጡ ነበር ሲሉም ያብራራሉ።
ይሁንና ሴቶቹ ቤት አግኝተው የሚወጡት መቼ ነው? በፈቃዳቸውስ ቤቱን ለቀው ይሄዳሉን? የሚሉት ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም።ይህ ከሆነ ደግሞ የኑዛዜው ተፈጻሚነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል ማለት ነው።የቤት ባለቤትነት ለአንዱ ተሰጥቶ ለሌላ ተጠቃሚ ደግሞ እስከመቼ እንደሆነ በግልጽ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ያውም በራሱ ፈቃድ ለቅቆ እስከሚወጣ ድረስ ይኑርበት ማለት ቤቱ የተሰጠው ሰው መቼ ነው ባለቤት የሚሆነው? በእርግጥስ ባለቤት ሊሆን ይችላልን? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሳል።እናም የኑዛዜው አፈጻጸም ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው።
ኑዛዜ ለሕግ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ መሆን የለበትም
አንድን የኑዛዜ ቃል ለሕግ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ነው የሚያሰኘው የኑዛዜው ጉዳይ ነው።አንዱ የኑዛዜ ጉዳይ ንብረት ነው።ነገር ግን ተናዛዡ የራሱ ባልሆነ ንብረት ላይ ኑዛዜ ቢያደርግ አይጸናም።በሌላ በኩል ልጄን እከሌ ያግባት፣ ሚስቴ ከሞትኩ በኋላ ለእከሌ ትሁን ወዘተ የሚል የኑዛዜ ቃል ሕገ ወጥና ለመልካም ጠባይም ተቃራኒ ነውና ፈራሽ ነው።
ኑዛዜ በማስገደድ፣ በተንኮልና በማሳሳት ሊሰጥ አይገባም
ኑዛዜ ሟቹ ከተጽዕኖ በጸዳ መልኩ በገዛ ፍላጎቱ ተነሳስቶ የሚያደርገው ሕጋዊ ተግባር ነው።ኑዛዜ በነፃ ፈቃድ እንዳይሰጥ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ የኃይል ሥራ ወይም ማስገደድ ይጠቀሳል።የኃይል ወይም የማስገደድ ተግባሩ በተናዛዡ ወይም በተወላጆቹ ወይም በትዳር አጋሩ ወይም በቅርብ ዘመዶቹ ላይ የማይቀርና ከባድ አደጋ የሚያደርስ ሊሆን ይችላል።በሌላ በኩል የተንኮል ሥራና መሳሳትም የተናዛዡን ፈቃድ የሚያጎድል ሁኔታ ነው።ይሁን እንጂ የኑዛዜን መፍረስ የሚያስከትለው ማናቸውም ስህተት ወይም ተንኮል አይደለም።ይልቁንም መሠረታዊ መሆን አለበት።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 14/2012
(ከገብረክርስቶስ)