አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ለጤና አደገኛ የሆኑ ህገ ወጥ ምርቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ቢወስድም ድርጅቶቹ የምርቶቻቸውን ስም በመቀየር ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገለጸ። የድርጅቶቹን ህገ ወጥ አካሄድ ለመግታት በ47 ከተሞች በየወሩ አሰሳ በማድረግ እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የምግብ አምራቾች ዳይሬክተር አቶ በትረ ጌታሁን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2011 ዓ.ም የነበረውን የቁጥጥር አካሄድ በመቀየር የገበያ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በማሸጊያቸው ላይ ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸው፣ የተመረቱበትና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የማይታወቅ፣ በአመራረታቸው ችግር ያለባቸው፣ በጤና ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትሉና የሚመረቱበት ሥፍራ የማይታወቅ ህገ ወጥ ምርቶች ተገኝተዋል። አምራቾቹ እንዲያስተካክሉ በምርቶቹ ላይ በተገለጸው አድራሻቸው ለማግኘት ቢሞከርም ህጋዊ ስላልሆኑ አብዛኞቹን ማግኘት አልተቻለም።
ዳይሬክተሩ ባለፈው በጀት ዓመት የ103፣ በዘንድሮው ዓመት ደግሞ የ17 ድርጅቶች ምርቶችን ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም ባለስልጣኑ በመገናኛ ብዙሃን ማሳወቁን ጠቅሰው፤ የሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተቆጣጣሪዎች እስከ ወረዳ ድረስ ህገወጥ ምርቶችን ሰብስበው እንዲያስወግዱ መደረጉንም ተናግረዋል።
‹‹እርምጃውን ተከትሎ ድርጅቶቹ ወደ ህጋዊ መስመር ይገባሉ ብለን ብንጠብቅም ከ120 ድርጅቶች ውስጥ ችግራቸውን በማስተካከል ወደ ህጋዊ መስመር የመጡት 12 ድርጅቶች ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ድርጅቶች ስያሜያቸውን በመቀየር ህገ ወጥ ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ ቀጥለዋል። እያደረግን ባለው ቁጥጥር አብዛኞቹ ምርቶች አዲስ ናቸው። ይህም ቀደም ብለን ይዘን ያስቆምናቸው አምራቾች ስያሜያቸውን ቀይረው በህገ ወጥነታቸው ለመቀጠላቸው ማረጋገጫ ነው›› ሲሉ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የህገወጦቹ ድርጊት ከጤና ጉዳት ባለፈ በህጋዊ አምራቾች ላይ ጫና እያደረሰ ነው። በምን አይነት ሁኔታ እንደተመረተ የማይታወቅ ምርት የኑግ ዘይት እየተባለ ገበያ እየተሸጠ ነው። ይህ በዜጎች ጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አደገኛ ነው። ህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ከማስወጣቱም በላይ የዜጎችን ጤና ያቃውሳል። በመሆኑም ህገ ወጥ ምርት የሚያሰራጩ አምራቾች ህጋዊ መስመሩን መከተል አለባቸው። ወደ ህጋዊ መስመር ከገቡ ለመደገፍ ዝግጁ ነን፤ በህገወጥነታቸው ከቀጠሉ ግን እርምጃው የከፋ ይሆናል።
ዳይሬክተሩ ‹‹የንግድ ፍቃድ መውሰድ ያለባቸው ከባለስልጣኑ በመሆኑ ፍቃድ ሳያገኙ የምግብ ምርቶችን አምርተው የሚያሰራጩ ህገወጥ ናቸው ። ለባልትና ዝግጅት ፍቃድ ወስደው የህፃናት ምግብ የሚያመርቱ አሉ። ያለፈቃድ ዘይት አምርተው መርካቶ በመውሰድ በመላው አገሪቱ ያስራጫሉ። የኢትዮጵያን የአስገዳጅ ደረጃ አሟልተው ማቅረብ አለባቸው። የሚመረትበት አካባቢና አድራሻም በግልጽ መታወቅ አለበት። ይህን ካላሟሉ ህጋዊ አይደሉም። በህገ ወጦች ላይ በስድስት ቅርንጫፎችና ከክልሎች ተቆጣጣሪ ተቋማት ጋር በመሆን ዜጎች ምርቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ለህዝብ እናሳውቃለን፣ ምርቶቹን እናስወግዳለን፣ ህጋዊ እርምጃም እንወስዳለን›› በማለት አስጠንቅቀዋል።
ባለስልጣኑ በ2012 ዓ.ም ቁጥጥሩን እንደሚያጠናክርና በየወሩ በአገሪቱ በሚገኙ 47 ከተሞች አሰሳ እንደሚያካሂድ፣ ህገወጥ ምርቶችን ህዝቡ እንዳይጠቀም የማሳወቅ ስራ እንደሚሰራ፣ ምርቶችንም ሰብስቦ እንደሚያቃጥል፣ ስያሜያቸውን በመቀያየር ምርቶቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶችንም ለህግ እንደሚያቀርብ፣ ወደ ህጋዊ መስመር የሚመጡትን እንደሚደግፍ፣ በአዋጅ የተሰጠውን ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል የሚሻገሩ ምርቶች ከመመረታቸው በፊት ከባለስልጣኑ ፍቃድ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚሰጡትን ፍቃድ ህጋዊነት የመቆጣጠርና ለምርቶቹ የሚሰጡትን ፍቃድ የተመለከተ ክትትል እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኸኝ