መንግሥት በኢ-መደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማራውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራምን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በሙከራ ደረጃ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አስራ ሦስት ወረዳዎች ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል።
በሙከራ ትግበራ ወቅት የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር በ2005 ዓ.ም ፕሮግራሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰፋ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅትም በ657 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፣ በቀጣይ ፕሮግራሙ ተግባራዊ የሚሆንባቸውን ወረዳዎች ቁጥር 680 ለማድረስ ታቅዷል። እስካሁንም በፕሮግራሙ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል።
በመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ ዜጎችንም ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥት የማህበራዊ የጤና መድህን ፕሮግራም የቀረፀ ሲሆን፣ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ልዩ ልዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም፣ እስካሁን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም።
ለመሆኑ ሁለቱም የጤና መድህን ሥርዓቶች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? በመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ በሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ላይ የማህበራዊ ጤና መድህን ፕሮግራሙ እስካሁን ያልተጀመረበት ምክንያት ምንድን ነው? በሚሉና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽንና ሞቢላይዜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘመድኩን አበበ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- በመንግሥት የተቀረፀው የኢትዮጵያ ጤና መድህን ሥርዓት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- መንግሥት የጤና መድህን ሥርዓትን ለመጀመር ሲያቅድ በመጠኑም ቢሆን፣ የግንዛቤ አቅሙ የተሻለውንና የተማረውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም ነበር። ይሁንና በአንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮችና በሥርዓቱ አገላለፅና አቀራረብ ሁኔታዎች ህብረተሰቡ ባልጠበቀው ሁኔታ በመረዳቱ ለጊዜው እንዲቆይ ተደርጓል።
ይሁን እንጂ በጤና ችግር የሚጠቃው አብዛኛው የገጠሩ ህብረተሰብ ክፍል መሆኑን መንግሥት በመረዳቱና የገጠሩን ህብረተሰብ በመጥቀም ሥርዓቱ ወደ ከተማ ነዋሪው ቢመጣ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በመገንዘቡ በተለይ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሥርዓትን በአራቱ ሰፋፊ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች ላይ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። በሂደትም ፕሮግራሙ ወደ 374 ወረዳዎች ተስፋፍቶ በአሁኑ ወቅት የአርብቶ አደር ክልሎችን ለማካተት ተሞክሮ እስከ 2011 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 657 በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል። በ2012 ዓ.ም ፕሮግራሙን በ680 ወረዳዎች ላይ ለማድረስም ታቅዷል።
አዲስ ዘመን፡- በጤና መድህን ሥርዓት ተጠቃሚ ለመሆን የህብረተሰቡ ዝግጁነት እንዴት ይገለፃል?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- በጤና መድህን ሥርዓት ተጠቃሚ ለመሆን የህብረተሰቡ ዝግጁነት በሁለት መንገድ ይታያል። አንደኛው ትክክለኛ እወቀትና ግንዛቤ ኖሮት የጤና መድህን አገልገሎቱን የሚጠይቅ ማህበረሰብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እያመነታ ሳይገባው ወደ አገልግሎቱ ገብቶ ካየው በኋላ አገልግለቱ ጥሩ መሆኑን የተረዳ ነው። ሆኖም በገጠር የሚገኙ የጤና ተቋማት ለማህበረሰቡ ሽፋን የመስጠታቸው አቅም ውስን መሆን አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ ስለማያስችል ህብረተሰቡ አገልግሎቱ ምን ያደርግልኛል? ወደሚል አመለካከት ውስጥ ይገባል። ለዚህም በአገልግሎቱ ጠቀሜታ ዙሪያ ህብረተሰቡን ማሳመንና ከሀገሪቷ እድገት ጋር ተያይዞ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል ማስረዳት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ህብረተሰቡ የጤና መድህን ሥርዓት ገብቶት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በእናንተ በኩል ምን አይነት ጥረት ተደርጓል?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- ተቋሙ ገና በማደግ ላይ ያለ ከመሆኑ አኳያና በሰው ሃይል፣ በመዋቅርና በባለሞያ ስፋት ውስንነት አለበት። ይሁን እንጂ ባለው የሰው ሃይል የወረዳ አመራሮች፣ የክልል መስተዳደሮች እና ሌሎችም በየዘርፉ ያሉትን እንዲያግዙና እንዲተባበሩ ህብረተሰቡንም እንዲያነቃንቁ ግንዛቤ የመፍጠርና የማስተማር ጥረት ባሉት ወረዳዎች እያደረገ ይገኛል።
የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን በተለይ የየወረዳው የጤና ባለሞያዎች እንዲያስተምሯቸውና ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በየደረጃው ጥረት እየተደረገ ነው። የመገናኛ ብዙሃንም በዚህ ጥረት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል። በተለይም በማህበረሰብ ሬዲዮኖች፣ በራሪ ፅሁፎች፣ ስብሰባዎችና የሃይማኖት ቦታዎች አማካኝነት ህብረተሰቡ በሚገባው ቋንቋ መረጃዎች እንዲተላለፉ ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮግራሙ በተጀመረባቸው ወረዳዎች ውስጥ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ምን ይመስላል?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በየወረዳዎቹ ላይ አቅም አላቸው ተብሎ በመመሪያው መሰረት ከተቋሙ ጋር ውል ገብተዋል። ይሁንና የጤና ተቋማቱ ደረጃቸውን ያልጠበቁና አቅማቸው ዝቀተኛ ከሆነ ተቋሙ ውል አይገባም። በተለይም ከግል ጤና ተቋማት ጋር ተቋሙ እስካሁን ውል አልፈፀመም።
ከዚህ በኋላ አገልግሎቱን ከሚፈልገው ህዝብ ቁጥር አንፃር የግል ጤና ተቋማትም በአገልግሎቱ እንዲሳተፉ እቅድ ተይዟል። ሪፈራል ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ውስን በመሆናቸው በአቅራቢያው የተሻለ ተብለው ወደሚታሰቡና ተቋሙ ውል ወዳሰረባቸው ጤና ጣቢያዎች በመሄድ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን እንዲጠቀም እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣ ይስ በየትኞቹ ክልሎች ላይ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ታስቧል?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- እስካሁን ድረስ ፕሮግራሙን በመተግበር ረገድ አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ አራቱ ትላልቅ ክልሎች በስፋት ሄደውበታል። ፕሮግራሙን እንደ አዲስ የጀመሩ የአፋርና ሶማሌ አርብቶ አደር ክልሎችና የጋምቤላ ክልል ይገኙበታል። በዚሁ መሰረት ፕሮግራሙ በክልሎቹ እንዲጀመር ተወስኖ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ። በተመሳሳይ አገልግሎቱን ከጀመሩ ነባር ክልሎች መካከልም እንደ ኦሮሚያ ያሉት ፕሮግራሙን በአዳዲስ ወረዳዎች ላይ ለማስፋት እቅድ ይዘዋል። ተጨማሪ ስራዎች ከተሰሩም ፕሮግራሙን በ680 ወረዳዎች ለማስፋት ከተያዘው እቅድ በላይ ማከናወን ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ጤና መድህን ሥርዓት እስካሁን ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለው በምን ምክንያት ነው?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- ለዚህ በዋናነት የሚቀርበው ምክንያት በማህበራዊ ጤና መድህን ጠቀሜታ ዙሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በሚፈለጉ ቦታዎች ላይ ተገቢውን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟሉ የጤና ተቋማት በብዛት አለመኖርም ሥርዓቱ ተግባራዊ ላለመደረጉ እንደ ተጨማሪ ምክንያት ይጠቀሳል። የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ መሆንም በህብረተሰቡ ፍላጎት ልክ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትንና ቁሳቁስን ለማቅረብ አላስቻለም።
አዲስ ዘመን፡-አገልግሎቱ መቼ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- በመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለውን የማህበራዊ ጤና መድህን ሥርዓት ለማስጀመር የመጀመሪያው አዋጅ ተዘጋጅቷል። በዚህ አዋጅ መሰረት ሥርዓቱን ማስኬድ የሚቻል ቢሆንም ለተግባራዊነቱ በመንግሥት በኩል ውሳኔና መመሪያ ይፈልጋል። በመሆኑም መንግሥት ቅድመሁኔታዎችን ካሰተካከለና ያሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ፈትቶ አዋጁን ማስኬድ ይቻላል ብሎ ውሳኔ ሲሰጥ ሥርዓቱ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል። ህበረተሰቡም የጤና መድህን ሥርዓቱን እየተረዳ በሄደ ቁጥር ሥርዓቱ ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ጤና መድህን ሥርዓቱ ተግባራዊ እንዲሆንና ህብረተሰቡ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ከተቋሙስ ምን ይጠበቃል?
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- በየደረጃው ያለው የመስተዳደር አካል ለተቋሙ ግንዛቤ ኖሮት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ጤና መድህን መልዕክት በማስተላለፍ ህብረተሰቡን ማንቃትና ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረግ አለበት። የመገናኛ ብዙሃንም እንደህዝብ አገልጋይነታቸው መደበኛ ፕሮግራም ቀርፀውና አቅደው በጤና መድህን ጠቀሜታ ዙሪያ መሥራትና በየጊዜውም በህዝቡ ዘንድ ግንዛቤ ማስረፅ ይጠበቅባቸዋል።
የተቋሙ መዋቅርም በአግባቡ የተደራጀ፣ ብቃት ባለው የሰው ሃይል የተሟላና ውጤታማ ሥራዎችን ሊያሠራ የሚችል መሆን ይኖርበታል። በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለሞያዎችና ለህዝቡ ተደራሽ የሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በተሟላ መልኩ ማህበረሰቡ በሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ልክ እያሟሉ መሄድም ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ ከልብ እናመሰግናለን!!
አቶ ዘመድኩን አበበ፡- እኔም አመሰግናለሁ!!
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2012
አስናቀ ፀጋዬ