አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድ የምታቀርባቸውን ምርቶች ለመጨመርና የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ለማሳደግ የፋይናንስ ተቋማት የወጪ ንግድ ምርት አቅራቢዎችን እንዲደግፉ ላኪዎች ጠየቁ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ዙሪያ ከላኪዎች ጋር በሂልተን ሆቴል ባደረገው ምክክር ላይ የወጪ ንግዱ እንዲጠናከር ምርት አቅራቢዎችን መደገፍ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ላኪዎቹ እንደተናገሩት፣ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት የወጪ ንግዱን ለማሳደግ በውጭ ምንዛሪ እና በብድር አቅርቦት ላኪዎች ላይ ትኩረት አድርገው መስራታቸው ጥሩ ቢሆንም በየጊዜው እየተዳከመ የመጣው የወጪ ንግዱን ለማጠናከር ግን ምርት አቅራቢዎችን በይበልጥ መደገፍ አለባቸው፡፡ አገሪቱ ለውጭ ንግድ የምታቀርባቸው ምርቶች ዓይነትና መጠን እንዲያድግ በብድር አቅርቦትና በፋይናንስ ዘርፉ እድሎች ሊደገፉ የሚገባው ምርት አቅራቢዎች መሆን አለባቸው፡
ስጋ በማቀነባበር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የተሰማራው የአላና ግሩፕ ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ግደይ ገብረመድህን እንደተናገሩት፤ በስጋ ዘርፍ ኢትዮጵያ በገበያ ተወዳዳሪ መሆን አልቻለችም፡፡ ለዚህም ምክንያት ከሆኑት መካከል በቂ የእንስሳት አቅርቦት ባለመኖሩ ነው፡፡ እንስሳቶችን ለማቀነባበሪያዎች የሚያቀርቡ ገበሬዎች እንስሳቶችን ለማደለብ የብድርም የማበረታቻም ተጠቃሚ እየሆኑ ባለመሆኑ በቋሚነት በእንስሳት እርባታ ላይ አተኩረው እንዳይሰሩ ችግር ሆኖባቸዋል፡፡ የስጋ ምርት በገበያ ተፈላጊነቱ በሚጨምርበት ወቅትም በቂ የሆነ ምርት ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ የፋይናንስ ተቋማትም ለወጪ ንግዱ መጠናከር ላኪዎች ላይ በትኩረት የሚሰሩትን ያህል ግብዓት አቅራቢዎችን ለመደገፍ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣው የአገሪቱን የወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ለወጪ ንግድ ግብዓት አምራቾች በግብርናው ለተሰማሩ የተሻለ ዘር፣ ማሽነሪ፣ ማዳበሪያ፣ ምርት ሂደት እንዲያዘምኑና የማጓጓዣ አቅም እንዲያሳድጉ ብድር አቅርቦት ለመስጠት ባንኮች መድፈር እንዳለባቸው በቅባት እህል ላኪነት ላይ የተሰማሩና ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ባለሀብት ጠቁመዋል፡፡
የወጪ ንግድ ምርቶች አምራቾች ለምርት ወጪያቸው እንኳን በአግባቡ መሸፈን የማይችሉበት ጊዜ እንዳለ የጠቆሙት ባለሀብቱ፤ የብድር አቅርቦት ቢመቻችላቸው ምርትን በበቂ ሁኔታ የሚያቀርቡበትን ዘዴ እንዲፈልጉ እንደሚረዳቸው አመልክተዋል፡፡ ለወጪ ንግዱ መጠናከር ምርታማነትን መጨመር ቀዳሚ በመሆኑ እንደ አገር የተያዘው የምርታማነት እቅድን የፋይናንስ ተቋማት በየዘርፉ በመከፋፈል አቅደው ሊደግፉ ይገባልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቱን የወጪ ንግድ ዙሪያ ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ የሆነው ይህ የምክክር መድረክ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ ማዘጋጀቱ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
በሰላማዊት ንጉሴ