«የአፋር ክልል አሁንም ከታዳጊ ክልሎች መካከል ይመደባል። የመሰረተ ልማት ግንባታ በአግባቡ አልተስፋፋም፤ የወጣቶች የስራ ፈጠራ በተገቢው መንገድ አልተሰራበትም፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ለመናገር መድረኮች አልነበሩንም ፤ እነዚህ ክፍተቶች በአዲሱ ካቢኔ እንዲስተካከሉ እንፈልጋለን» ይላል የሎጊያ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት አብደላ መሀመድ።
የአፋር ህዝብ በክልሉ መሬትና ተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ተጠቃሚ አለመሆኑን የሚያነሳው ወጣት አብደላ ዝናብ ሲጠፋና ድርቅ ሲከሰት እጅን ለልመና መዘርጋት በስፋት ሲስተዋል እንደነበር በማስታወስ ችግሩ መስተካከል እንዳለበትም ይናገራል።
አዲሱ ካቢኔ ለክልሉ የሚቆረቆርና ለለውጥ የሚተጋ ፣ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት በማድረግ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባም ይገልጻል። የክልሉን ህዝብ ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል የሚለው ወጣት አብደላ ህዝቡ በክልሉ የመሰረተ ልማትና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲስፋፋ ፍላጎት እንዳለው ይገልፃል። ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው የአሰራር ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም በመጠቆም ለአፋር ህዝብ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በስፋት መሰራት እንዳለበትም ይጠቁማል።
መምህር ሩፋኤ ሃምዛ በበኩላቸው አዲሱ ካቢኔ ሴቶችና ወጣቶችን ወደፊት ማምጣቱን በበጎነት በማንሳት ፈጣን ለውጥ ያመጣሉ የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ይገልፃሉ። በክልሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት እንዲከናወኑ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል መሰራት እንዳለበት በመግለፅ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥኖ መስተካከል አለበት የሚል አስተያየት አላቸው።
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ሁንዴ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀጣጠለውን ለውጥ የአፋርን ህዝብ ባሳተፈ መንገድ በክልሉም እንደሚካሄድ ቃል ገብተዋል። የመንደር ማሰባሰብ፣ የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራሞች የህዝቡን ተጠቃሚነት ባማከለ ሁኔታ ይተገበራሉ የሚሉት ርእሰ መስተዳድሩ በለውጥ ስራው ሁሉም የህብረተሰብ ከፍሎች እንዲሳተፉ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋም ተናግረዋል።
«ልማትን ለማስፋፋትና የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያስችል የተጠናከረ ስራ ይሰራል» የሚሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ፣ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በአፋር ክልል በመቻቻልና በመከባበር እንዲኖሩ የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደሳቸው ማብራሪያ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ስራ ይሰራል፤ ወጣቶች፣ የሴቶች፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል አደረጃጀቶችን በመፍጠርም በየደረጃው ውይይት የሚካሄድ ይሆናል። በሚያለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት በውይይት ጥረት የሚደረግ ሲሆን በሚያግባቡት ላይ የጋራ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል። ለውጡን ወደፊት ለማራመድ በጋራ ርብርብ የሚደረግ ይሆናል። ለዚህም ሁሉም በትጋት እንዲሰራ ሁኔታዎችን የማመቻቸት፣ መድረኮችንም የማዘጋጀት ስራ በቀጣይነት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ያሉት አቶ አወል የሃይማኖት አባቶች የጎሳ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በለውጡ ሂደት እንዲሳተፉ እንደሚደረግም ተናግረዋል። ወጣቶችና ሴቶችንም በየደረጃው በሚገኝ የመንግስት መዋቅር ተሳታፊ የማድረጉ ተግባር ወደታችኛው መዋቅር እንደሚወርድም ጠቅሰዋል።
የመከላከያ ሚኒስትርና የአብዴፓ ሊቀ መንበር ኢንጂነር አይሻ አህመድ በበኩላቸው የካቢኔ አባላቱ የክልሉን ህዝብ ፍላጎት መሰረት አድርጎ ለመስራት አቅምና ክህሎት ያላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። በክልሉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን፣ የትምህርት ጥራት ችግርን፣ የተደራሽነት ጥያቄን፣ የመሰረተ ልማት ማስፋፋትን፣ በተደራጀ መንገድ ለመምራት አቅምና ክህሎት ያላቸው መሆናቸውን በመጠቆምም ለውጡ እስከ ታችኛው መዋቅር እንደሚወርድም ገልጸዋል።
አዲሶቹ አመራሮች ከህዝቡ ጋር በቅርበት የሚሰሩ ይሆናል ያሉት ኢንጅነር አይሻ በክልሉ የተለያዩ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በማስታወስ ይሄ ችግር ይፈታልናል በሚል ህዝብ ብዙ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል። የአፋር ክልል ወደ ኋላ ቀርተዋል ከሚባሉት ክልሎች ግንባር ቀደም ነው ፤ በመሆኑም ከሌሎች ክልሎች በበለጠ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
በዘላለም ግዛው