ካለፈው ዓርብ ሴፕቴምበር 20 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ታሪካዊ ተግባር እየተፈፀመ ሲሆን፣ ድርጊቱም ዓለምን እያሳተፈ ይገኛል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያመፁ ወጣቶች ያደራጁት እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴያቸውንም ተከትሎ ዓለም አቀፍ ጥሪ ማስተላለፋቸው፤ ጥሪውንም በመቀበል እንቅስቃሴ መጀመሩና በዓለም ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በደኖች ላይ እየደረሰ ያለው የመጨፍጨፍ አደጋ እንዲቆም ጥያቄ ማንሳታቸው ነው።
“የአየር ንብረት መዛባት ጊዜ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም፤ በመሆኑም እኛም ጊዜ ልንሰጠው አይገባም።” በሚል አቋም በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት እነዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች እርምጃቸውን በማድነቅ ሁሉም ሰው ሊተባበራቸው እንደሚገባ እያሳሰቡ ይገኛሉ።
በዚህ “GLOBAL CLIMATE STRIKE – SEP. 20–27” በተሰኘውና ለሳምንት በሚዘልቀው ፕሮግራም በመጀመሪያው እለት ብቻ ከ150 አገራት በላይ የሚገኙ ወጣቶች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ክንዳቸውን ያነሱ ወጣቶችን መቀላቀልና አብሮ መስራት የፈለጉበት ዋና ምክንያት በደኖች ላይ እየደረሰ ያለው ቃጠሎና ጭፍጨፋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱና የሙቀት መጠን መጨመር መሆኑን በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡት መቆየታቸውን ጠቅሶ (edition.cnn. com) እንዳስነበበው፤ ባለፈው ዓርብ ሴፕቴምበር 20 ብቻ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ደጋፊዎች ከቤታቸው፣ ከሥራ ቦታቸውና ከትምህርት ቤታቸው በመውጣት ይህን የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ተግባር እንዲያከናውኑ በቀረበው ጥሪ መሰረት እርብርብ ሲደረግ ነው የዋለው።
እንቅስቃሴውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ተቀላቅለውት የነበረ መሆኑን የዘገበው ግሎባል ክላይሜት ሪስክ የተሰኘው ድረ ገጽ፣ እንደሚለው፤ ይህ “Fridays For Future” የሚል ስያሜ ያለው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ አደጋ ላይ የሚገኘውን የደኖች መጨፍጨፍ ሁኔታን ከመታደግ ባሻገር የተስተካከለ አየርን ለዓለም ከማበርከት አኳያ የራሱን ጉልህ ድርሻ ይጫወታል።
እየወደመ ያለው የአካባቢ ደንና እየደረሰ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጣዳፊ በመሆኑ ከእስከ ዛሬው የተለየና አዲስ አይነት አቀራረብን ይፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ከእንቅስቃሴው ጋር በተያያዘም ችግሩ ፈጣን ምላሽ ያስፈልገዋል ሲል “THE GLOBAL CLIMATE STRIKE IS HAPPENING NOW” በሚል ርእስ ነው ድረገጹ ያስነበበው፡፡
በተሳታፊዎቹ የሚወሰደው እርምጃም የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምን ብቻ መሰረት ያደረገ ሳይሆን የዓለም ህዝቦችን ሰብዓዊ መብቶች፣ ፍትህ እና እኩልነትን ጭምር ከግንዛቤ ያስገባና እነሱንም መሰረት ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ የ“Fridays For Future” እንቅስቃሴ አባላት ጠንካራ አቋም ስለነበር ነው።
ይህ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ባለፈው ዓርብ በተከናወኑ ተግባራት ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። የሲኤንኤን ዘገባ እንዳመለከተው እንቅስቃሴው የበለጠ ተጠናክሮ እስከ ሴፕቴምበር 27 ድረስ ይቀጥላል። አዘጋጅ ወጣቶቹ ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት ከአሜሪካና ሌሎች አገራት በርካታ፤ በተለያዩ የእድሜና የሙያ ዘርፎች የሚገኙ ሁሉ ከያሉበት በመውጣት ዝግጅቱን ታድመዋል።
እነዚሁ ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የዓለምን ህዝብ ወንድማማችነትና አንድነት የተመለከቱ መልእክቶች ያስተላለፉ ሲሆን፤ ሁሉም ሰው ከተለመደው አደገኛና ምን ቸገረኝ የተዛባ አሰራር በመውጣት በጋራ ለጋራ እንዲሰራ በሚያሳስብ ድምፀት ጥሪ ማስተላለፋቸው ታውቋል።
የ16 ዓመቷ የስዊድን አየር ንብረት ለውጥ አቀንቃኝ ግሬታ ተንበርግ፣ ከቡድኑ ጎልተው ከወጡት መካከል አንዷ ስትሆን፤ የመገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ ርእሰ ጉዳይ ሆና ሰንብታለች። በስልጣን ዘመናቸው በሰሯቸው፤ በተለይም ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ በወሰዱት ጠንካራ አቋም ምክንያት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን የሃሳቧ ተካፋይ እና ተሳታፊ ማድረጓ የበለጠ የመገናኛ ብዙኃንንና ህዝቡን ቀልብ እንድትስብ የራሱን ድርሻ ተጫውቷል።
ይህ ከዓርብ እስከ ዓርብ የሚከናወነው የዓለም አየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ እንቅስቃሴ ከአነሳሱ ጀምሮ አንድን አገር እንዲያሳትፍ ሆኖ የተቀረፀ ፕሮግራም ባለመሆኑ አሳታፊነቱ ዓለም አቀፍ ነው። በዚህም ከፍተኛ ትኩረትንና በርካታ ቁጥር ያለው ተሳታፊን ማግኘት ችሏል። እንቅስቃሴው በአሳታፊነቱና ድንበር ተሻጋሪነቱ ምክንያት እስካሁን በዓለማችን ወደር የሌለው መሆኑም እየተነገረለት ይገኛል።
የት ምን ተካሄደ የሚለውንም በተመለከተ ባለፈው ሐሙስ ብቻ በትዊተር ገጽዋ “በሁሉም አህጉራት በሚገኙ 139 አገራት 4ሺህ 638 ሁነቶች መከናወናቸውን ገልጻለች፡፡ በዚህም በኒው ዮርክ ብቻ 1ነጥብ1 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተነስተው በፕሮግራሙ ላይ መሳተፋቸውን ጠቁማለች፡፡ “እናዝናለን፤ በርግጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስተዋለ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣነው እኛ ወጣቶች አይደለንም። ግን ደግሞ ዝም እንዳንል በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂዎቹ እኛ ነን” የምትለው ተንበርግ፤ ሁሉም በዚህ ቁልፍ ተግባር ላይ እንዲሰማራና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪም አቅርባለች።
በአላስካ የተፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስና ሙቀት መጨመር ከአሜሪካ አልፎ በአጠቃላይ በዓለማችን ላይ እያሳደረ ያለው ተፅእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህም የዚህ የዓለምን አየር ለውጥ ለመታደግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ወጣቶችን ትኩረት ከሳበው መካከል አንዱ ሲሆን፤ ወደ አካባቢው በመሄድም የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየሰሩ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ሁሉም በየአካባቢው ተመሳሳይ ድርጊትን እንደሚያከናውን ይጠበቃል የሚል እምነት በእንቅስቃሴው አባላት ዘንድ አለ።
ፕሮግራሙ በዛሬው እለት ኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ፅህፈት ቤት አካባቢ የሚካሄድ ሲሆን፤ ዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬስም ለዓለም መሪዎች የዚህ ተጨባጭና የወቅቱን እውነታ ያገናዘበ ፕሮግራም አካል እንዲሆኑ፤ በፅህፈት ቤቱም እንዲገኙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
መስራችና ተሳታፊ ወጣቶቹ እንደሚሉትና ግሎባል ክላይሜት ሪስክ ድረገጽ እንደዘገበው፤ የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ የዓለምን የፖለቲካ አመራር የጨበጡ አካላት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም። ወጣቶቹን ለዚህ እንቅስቃሴ የገፋፋቸው ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት ካላቸው ተነሳሽነትና ቁጭት የመነጨ ነው።
የፊውቸር ኮአሊሽን (Future Coalition) መስራችና ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር የሆነችው ካቲ ኤደር እንደምትለው፤ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ ዓለማችን እንደዚህ አይነት የአየር ንብረት ለውጥ አጋጥሟት አያውቅም። የሙቀት መጨመር ዓለምን ከማትወጣው መከራ ውስጥ እየከተታት ይገኛል። የሚገርመው ነገር ይህ ሁሉ ችግር እየታየ ችግሩን ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ነው። “ይህ ደግሞ ለዓለማችን ጥሩ አይደለም። ተስፋ አስቆራጭ ነው። ያ ከመሆኑ በፊት ደግሞ እኛ ወጣቶች ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን።” ስትልም ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
“እኛ ወጣቶች የወደፊት እጣ ፋንታችን አደጋ ላይ እንደሆነ እናውቃለን። ከሁሉም በላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሊውጠን እንደደረሰ ተረድተናል። በመሆኑም ነው የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት አብዮት የጀመርነው። በአሁኑ ሰዓት እኛ ወጣቶች በየክፍላችን፣ ካፌ፣ ቤተ መፃህፍት፣ በጉዞም ላይ፤ ባገኘንና በተገናኘንበት ስፍራ ሁሉ እምንነጋገረው ስለዚሁ ስለ አየር ንብረት ለውጥና ሙቀት መጨመር ጉዳይ ነው።
ከሚገባው በላይ አሳስቦናል። እየተስተዋለ ያለው የአየር ንብረት መዛባት አካሄዱ አደገኛ ነው። ጊዜ እየሰጠን አይደለም። መፍጠን አለብን።” የምትለው ዳይሬክተር ካቲ ኤደር፤ ዓለም ይህን የእነሱን እንቅስቃሴም ሙሉ ለሙሉ እንዲደግፍ ጥሪዋን ደግማ ታቀርባለች። “መፍጠን አለብን” የሚለው ቃሏም ያለ ማቋረጥ በየመገናኛ አውታሮች እየተላለፈላት ይገኛል።
ገና በዋዜማው በአሜሪካ ብቻ ከ500 በላይ ሁነቶች እንዲስተናገዱ ምክንያት የሆነው ይህ የወጣቶቹ እንቅስቃሴ ከሴፕቴምበር 20 እስከ 27 የሚቆይ፤ በተለይም መክፈቻና መዝጊያው በደመቀ ሁኔታ ዓለም የሚሳተፍበት ሲሆን፤ በየቀኑ የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ፤ የሚከናወኑ ሁነቶችም እየበዙ በመሄድ ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው።
“ይህን እንቅስቃሴ ለየት የሚያደርገው አይቻሉም የተባሉ ነገሮች ሁሉ ተችለው መገኘታቸው ነው።” የሚለው የሲኤንኤን ዘገባ፤ እንቅስቃሴውንም “ለወደፊቱ ብሩህ ዓለም፣ ለወደፊቱ ትውልድ፣ ለወጣቶች፣ ለህፃናት፤ ባጠቃላይም ለዓለማችን ሲባል መሆን ያለበት ሰብዓዊ ተግባር ነው።” ሲልም በድረ ገፁ አስነብቧል።
ይህ አይነቱ በትምህርት ቤት ወጣት ተማሪዎች አማካኝነት የሚዘጋጅ እንቅስቃሴ ሲደረግ ይህ አዲስ አለመሆኑን በመግለጽም፤ አሜሪካ ውስጥ ሰብዓዊ ቀውስም ሆነ ሌላ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ሲኖር የሚደረግ መሆኑንና ለዚህም ባለፈው ዓመት በትምህርት ቤቶች የሚደረግን ጅምላ ግድያ በመቃወም ተመሳሳይ አደረጃጀትን በመፍጠር “National School Walkouts” መደረጉንና የተወሰነ ተፅእኖ መፍጠር መቻሉንም አስታውሷል።
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2012
ግርማ መንግሥቴ